ኢትዮጵያ በቻይና ብድር እየተንበሸበሸች ነው
በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ታላላቅ ስምምነቶች ይጠበቃሉ
ከአፍሪካ ጋር መሳ ለመሳ የገባችው ቻይና በሳምንት ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ 4.5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ለማበደር ወስናለች። ከአባይን ግድብ የሚመነጨውን ሃይል የማስተላለፍና የማከፋፈል ጣቢያ ለመገንባት ከሚፈለገው 1.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 85 በመቶውን ለመስጠት መዋሰኗን የመንግስት ሚዲያዎች ዘገበዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዘወትር እንደሚደረገው የቻይና የኤሌክትሪክ ፓወር ኢኪውፕመንት ቴክኖሎጂ ኩባንያ ግንባታውን በሰላሳ ቀን ውስጥ ለመጀመርና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማስረከብ ተስማምቷል። ስለዚህ ብድሩ ከቻይና ኪስ ወጪ ተደርጎ ወደ ቻይና ኪስ ይዛወራል።
በሌላ ተመሳሳይ ወሬ ለአትዮጵያና ለጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ የሚውል 3.3 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት የቻይና መንግስት መወሰኑን ሪፖርተር አስነብቧል። ስምምነቱ ከወር በኋላ ለሚደረገው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ከሚመጡ ከፍተኛ ቻይና ባለስልጣናት ጋር የቻይና ኤግዚም ባንክ ባለስልጣኖች አዲስ አበባ ተገኝተው የስምምነቱን ፊርማ እንደሚያኖሩ ጋዜጣው ገልጿል።
ከብድር ስምምነቱ በፊት በተጠናቀቀው የግንባታ ስራ ተቋራጭ ውል መሰረት ከሰበታ ተነስቶ ጅቡቲ የሚደርሰውን የባቡር መስመር ሁለት የቻይና ኩባንያዎች እንደሚያከናውኑት ሪፖርተር በስም ጠቅሶ አመልክቷል። አንደኛው ኩባንያ የአዲስ አበባን ቀላል የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።”
የመከላለያ ጄኔራሎች በታንታለም ንግድ ዝርፊያ ተሰማርተዋል”
የመከላከያ ጀነራሎች በታንታለም ማዕድን ዝርፊያ ላይ መሰማራታቸውን ኢሳት አስታወቀ። ኢሳት ሰራተኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው የመከላከያ ሰራዊት ኩባንያ በአካባቢው የመንገድ ስራ ተቋራጭ በመሆን መንገድ እየሰራ ሲሆን፣ ለመንገድ ስራ ተብለው የተመደቡት ተሽከርካሪዎች ከመንገድ ስራ ይልቅ የታንታለም ማእድንን እየዘረፉ በሶማሊላንድ በኩል ያሻግራሉ። ማዕድኑንን የማውጣቱን ስራ ከሚሰራው የቻይና ኩባንያ ጋር ሽርክና በመፍጠር ዝርፊያውን እንደሚያካሂዱም ኢሳት አመልከቷል።
ይህ ውድና ስትራቴጂክ ማእድን በርካሽ ዋጋ መሸጡ አገሪቱን እንደሚጎዳ የዘርፉ ባለሙያዎች ለሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደጋግመው አቤቱታቸውን በማቅረብ፣ ጥሬ እቃውን ወደ ውጭ መላኩ እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ያስታወሰው ኢሳት፣ በቅርቡ መንግስት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ያጋጠመው መሆኑን ተከትሎ፣ የማእድን ማውጣቱን እና መላኩን እንደገና ለመጀመር በመወሰኑ እነዚህ የህወሀት ጄኔራሎች ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር አክሲዎን በመመስረት ታንታለም በጅቡቲ በኩል መላክ መጀመራቸውን ሰራተኞቹ አስረድተዋል።
አገር ወዳድ የሆኑ ሰራተኞች “ይህ ማእድን እያለቀ ነው፣ ታንታለም ስትራቴጂክ ማእድን ነው፣ ማእድኑ አሁን ካለቀ አገሪቱ ለወደፊቱ ከፍተኛ የሆነ ገቢ ታጣለች” በማለት መናገራቸውን ኢሳት አመልክቷል። የህወሀት ጄኔራሎች ዝርፊያውን የሚፈጽሙት ከዞን ባለስልጣናት ጋር በመዛመድ መሆኑን ምንጮች እንደነገሩት ኢሳት ጠቁሟል።
ምንም እንኳ በአካባቢው ካሉ ተወካዮች ለማረጋገጥ ባይችልም፣ በህገወጥ መንገድ ከሚወጣው ማእድን ጨረር ጋር በተያያዘ በርካታ የአካባቢው ሰዎች መሞታቸውን ኢሳት ሰራተኞቹን በመጥቀስ ይፋ አደርጓል።
መንግስት እገዳው ከመጣሉ በፊት 80 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ታንታለም የሚሸጠው ቻይና ውስጥ እንደነበር ያመለከተው ኢሳት በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ወገንን ሪፖርት ለማካተት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ ተናግሯል።
ታንታለም ሊተካ የማይችል እጅግ ውድ የሆነ ማእድን ሲሆን፣ የሞባይል ስልኮችን፣ ኮምፒዩተሮችን እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ፣ ለተለያዩ የኬሚካልና የፋርማሲዩቲካል ውጤቶች መስሪያ፣ ለኤሮስፔስ፣ ለኢነርጂና ባልስቲክ ምርቶች በግባትነት ያገለግላል። ቀንጢቻ ቦረና የኢትዮጵያ ማእድን ልማት አክሲዮን ማህበር የተባለ መንግስታዊ ድርጅት ከአመታት በፊት በጉጂ ዞን በሻኪሶና አናሶራ ወረዳዎች 2ሺ 500 ቶን የሚጠጋ ንጹህ የታንታለም ማእድን ማግኘቱ የመገናኛ ብዙህንን ትኩረት ስቦ እንደነበር ኢሳት በዘገባው አስታውሷል።
የሳዑዲ የመከላከያ ሚኒስትር በኢትዮጵያ አቤቱታ ተነሱ?
የሪፖርተር አስቂኝ ዜና የሳምንቱ መዝናኛ ተደርጎ ተወስዷል። ዜናው የሚጀምረው “የህዳሴውን ግድብ የተቃወሙት የሳውዲ ልዑል ከሃላፊነታቸው ተነሱ” የሚል ነው። የሳዑዲ አረቢያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር በቅርቡ በግብጽ ተደርጎ በነበረ የዓረብ አገሮች የውሃ ምክር ቤት ኮንፍረንስ በመገንባት ላይ ያለውን “የህዳሴ ግድብ” መቃወማቸውን በማስረጃነት ያሳየው ሪፖርተር ከዜናው ግርጌ ሚኒስትሩ ስለተነሱበት ምክንያት የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ያለው ነገር እንደሌለ አመልክቷል።
ሚኒስትሩ በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ ጉዳይ ማንሳታቸውን ፣ በዚህም ምክንያት ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሚገልጹ ጠንካራ አስተያየቶች ከሳዑዲ እየወጡ ነው። ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች የሚኒስትሩ መነሳት አገራቸው ውስጥ እያራመዱ ካለው ያልተለመደ እንቅስቃሴ ጋር ከመያያዙ ውጪ አባይ ግድብን አስመልክቶ ከተናገሩት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ለጎልጉል ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብ በማንኛውም ምክንያት የመፍረስ አደጋ ቢገጥመው ሊያጠራቅም የሚችለው 70 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ሱዳንን ሙሉ ለሙሉ ያጠፋል፡፡ ከዚህ አልፎም በግብፅ የአስዋን ግድብ ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ነበር ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ በዚህ የኢትዮጵያ ግድብ በዋናነት ተጎጂ የምትሆነው ግብፅ መሆኗን፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግብፅ ከዓባይ ውኃ ውጭ ሌላ አማራጭ የሌላት በመሆኑ ነው ብለው ነበር፡፡ በማከልም ኢትዮጵያ በዚህ ግድብ አማካይነት እያደረገችው ያለ እንቅስቃሴ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይልቅ ፖለቲካዊ ትንኮሳው ያመዝናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዓላማ ፍፁም ፖለቲካዊ ሴራ መሆኑን በመግለጽ መናገራቸውን ሪፖርተር በዜናው መጨረሻ አስታውሷል። ኢትዮጵያም ባለስልጣኑ ለተናገሩት የሳዑዲ መንግስት ማብራሪያ እንዲሰጥበት መጠየቋ አይዘነጋም።
ኬኒያና ኢትዮጵያ ለወደብ ግንባታ በጋራ ብር ሊያፈላልጉ ነው
በኬኒያ ተፈጽሞ በነበረ የጅምላ ግድያ ተከስሰው ጥፋተኛ የተባሉት አዲሱ የኬኒያ ፕሬዚዳንት አሁሩ ኬንያታና በጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ ልዑክ ኬንያ ተገኝቶ በልማትና በግልጽ ባልተነገረ ጉዳይ መወያየታቸው ተሰምቷል።
የኢህአዴግ ልሳናትና የተለያዩ መገናኛዎች ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ደቡብ ሱዳን በጋራ ለሚጠቀሙበት ግድብ ማስገንቢያ ገንዘብ በጋራ ለማፈላለግ መስማማታቸው ተመልክቷል። በሶማሊያና በቀጠናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።
አቶ ሃይለማርያም አወሮፓ ያደረጉትን “የቃል ማደስ” ጉዞ እንዳከናወኑ ወደ ኬኒያ ማምራታቸው ሶማሌ ውስጥ ከኬኒያ ጋር መስራት ስለሚገባቸው ጉዳይ የተቀበሉትን የቤት ስራ ለመተግበር ያስችላቸው ዘንድ እንደሆነ ግምት አለ።
አቶ ሃይለማርያም ናይሮቢ በነበራቸው የአንድ ቀን ቆይታ አብረዋቸው ከተጓዙት መካከል ወታደራዊ ባለሙያዎችም እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።
በአዲስ አበባ አፍሪካ ፍልስጤምን ነጻ ስለመውጣት ልምድ ልታካፍል ነው
በፍልስጤም ጉዳይ በሚቀጥለው ሳምንት የሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ እንደሚስተናገድ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል አስታወቀ። የኢህአዴግ አንዱ የንግድ ተቋም የሆነውና ዜና ከመንግስት እየወሰደ ለመንግስት የሚሸጠው ዋልታ ጉባኤው አዲስ አበባ ስለሚካሄድበት ምክንያት አላስታወቀም።
“ጉባዔው የፍልስጤማውያን የማይገሰሱ መብቶችና ለፍልስጤም ሉአላዊና ነጻ አገር የአፍሪካውያን አጋርነት” በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 21 እና 22 ቀን 2005 ዓ ም እንደሚካሄድ ዋልታ አመልክቷል። ጉባኤው አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ በመውጣት ሉአላዊነቷንና ነጻነቷን ለመጎናጸፍ ያደረገችውን ተጋድሎ እንደ ልምድ ተወስዶ ውይይት ይደረግበታል። ፍልስጤም ባለችበት አስተዳደር የገጠሟት ችግሮችና አስተዳደሩ በዓለም አቀፍ ሕጎች ያለበትን ኃላፊነትና ተጠያቂነትም ይገመግማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋልታ በዘገባው አስፍሯል።
በጉባዔው ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሐፊና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሚስተር ካርሎስ ሎፔዝ፣ የፍልስጤማውያን የማይገሰሱ መብቶች ኮሚቴ ሊቀመንበር አብዱ ሰላም ዲያሎ፣ የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጣሂር ካሊድ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
ለእሥራኤልና ፍልስጤም ሰላም ሂደት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰቡ እያበረከቱት ያለውን ድርሻም ጉባዔው እንደሚያጤን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የላከው መግለጫ ጠቅሶ ዋልታ ዘግቧል። እስራኤልን በጉባኤው ላይ ስላላት ሚናና ስሜት በዘገባው ላይ የተባለ ነገር የለም።
አንደበት
. . . እነዚህ “ሕገ ወጦች” ከሰሜንም ይምጡ ከምስራቅ፣ ከምዕራብ ይፍለሱ ከመሀል አገር ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡ የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ደግሞ ዜጎች በፈለጉት አካባቢ ሄደው ለመስራት፣ ሀብት ለማፍራትና ለመኖር እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡ እናም እነዚህ “ሕገ ወጥ” የተባሉት ሰዎች ከተወለዱበት ክልል ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሌላ ክልል ሄደው ኑሮአቸውን መመስረታቸው ከቶም ወንጀል ሊሆንና ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ሊባሉ አይችሉም፡፡ ደን መጨፍጨፍና ሕገ ወጥ ሰፈራ ማካሄድ ግን ወንጀል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ዜጎች (ሰሜንም ይወለዱ ደቡብ) ሕግ ጥሰው፣ ስርዓት አፋልሰው፣ ጥርስ ሰብረው፣ ቋንጃ ቆርጠው፣ ንብረት ዘርፈው፣ ቤት አቃጥለው፣ እንስሳ ነድተው፣ ወይም ሌላ ወንጀል ሰርተው ቢገኙ በአገሪቱ ሕግ መሰረት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲቀጡ ይደረጋል እንጂ “ወደተወለዳችሁበት ቀዬ ተመለሱ” ማለት ተገቢም ሕጋዊም አይመስለኝም … እኔ አቶ አያሌው ጎበዜን ብሆን ኖሮ ሁልጊዜ አማራ ተፈናቀለ፣ አማራ ተፈናቀለ የሚለውን መስማት ስለማልፈልግ ይህንን እርምጃ እወስድ ነበር፡፡ አማራ ክልል እንደ ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ ለተወላጆቹ በቂ የሆነ መሬትም ሀብትም እንዳለው አምናለሁ፡፡ የክልሉን ተወላጆች ይሄ “የነፍጠኛነት” ውርዴ አለቅ ብሏቸው ካልሆነ በስተቀር ጉራ ፈርዳ ድረስ የሚያስወርድ ሁኔታ ያለ አይመስለኝም …” አቶ አብዱራህማን አህመዲን የቀድሞው የፓርላማ አባል ለሰንደቅ ጋዜጣ በዘር ላይ የተመረኮዘ መፈናቀልን አስመልክቶ ካቀረቡት ጽሁፍ የተወሰደ
ታዳጊዋን የደፈሩ አዛውንት 11 ዓመት እስር ተፈረደባቸው
አዛውንቱ የፈጸሙት ተግባር የአውሬ ነው። የልጅ ልጃቸው የምትሆን ታዳጊ አስገድደው በመድፈር ላልተፈለገ እርግዝና ዳርገዋታል። አዲስ አድማስ የፍርድ ሂደቱን አስመልክቶ እንደሚከተለው ዘግቧል። በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ ግራባ ፊላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር፣ የ14 ዓመቷን ታዳጊ አስገድደው የደፈሩ የ60 ዓመት አዛውንት፣ የአስራ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸው፡፡ የታዳጊዋ ወላጆች በእርሻ ሥራ ላይ የቀጠሯቸው እኚሁ አዛውንት፣ ወሲባዊ ጥቃቱን የፈፀሙት ቤተሰቧ‹‹ቤት ጠብቂ›› ብለው ወደ ገበያ መሄዳቸውን አረጋግጠው እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል። ታዳጊዋ የደረሰባትን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ወዲያው ለቤተሰቦቿ አልተናገረችም፡፡
ወራት እየተቆጠሩ ሲሄዱ ግን ሰውነትዋ እየወፋፈረ፤ ሆድዋ እየገፋ መሄዱን የተረዱ ቤተሰቦችዋ ጥርጣሬ አድሮባቸው ጠየቋት፡፡ ታዳጊዋ የደረሰባትን ተናገረች፡፡ ያኔ የአምስት ወር እርጉዝ ነበረች። ቤተሰቦችዋ ጉዳዩን ለፖሊስ አመለከቱና ክስ ተመሠረተ፡፡ ከትናንት በስቲያ በዱግዳ ወረዳ የዋለው ችሎት፤ ተከሳሹ ድርጊቱን መፈፀማቸውን በማረጋገጡ የ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንደፈረደባቸው፤ የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር አስቻለው አለሙ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ዘወትር እንደሚባለው ሁሉ ፍርዱ አነስተኛና ከበደሉ ጋር የሚጣጣም እንዳልሆነ ግን አልተዘገበም።
የሱዳን ታጣቂዎች በመተማ አርሶ አደሮችን ገደሉ
በሰሜን ጎንደር በመተማ ዞን ደለሎ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ለረዥም ዓመታት ግብር እየከፈሉ የሚኖሩበትን ህጋዊ መሬት ለቀው እንዲወጡ በወረዳው እንደተወሰነባቸው ሪፖርተር ምንጮች ጠቅሶ ዘገበ። የሱዳን ታጣቂዎች ሶስት አርሶ አደሮችን መግደላቸውም ተገልጿል።
አርሶ አደሮቹ ለዓመታት ከኖሩበት ርስታቸው እንዲፈናቀሉ መታዘዙን የወረዳው አስተዳደርና የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን ሃላፊ አስተባብለዋል። ይሁን እንጂ ሶስቱ አርሶ አደሮች መገደላቸውን ሳያስተባብሉ አምነዋል።
የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ መኮንን አርሶ አደሮቹ በሱዳን ታጣቂዎች ተገድለዋል መባሉ እውነት መሆኑን ቢያረጋግጡም፣ ምክንያቱ ግን ከድንበር ልኬትና ከእርሻ ጋር የተገናኘ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የመተማ አርሶ አደሮች ድንበር ተሻግረው የመስፈር ሁኔታ መኖሩንና ከሱዳኖቹም በኩል ተመሳሳይ ባህሪ እንደሚታይ የገለጹት አቶ ተስፋ፣ ከሱዳኖች በኩል አንድ ታጣቂ ተገድሎ እንደነበርና በዚያ ድርጊት ቂም ይዘው ግድያውን ሳይፈጽሙ እንዳልቀሩ ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡ የድንበሩን ጉዳይ በፀባይ መያዛቸውን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆነውንና የማይሆነውን መሬት ለመለየት በጂፒኤስ ለክተው መጨረሳቸውንም አሳውቀዋል፡፡ ዝቅተኛ የመሬት መጠን ያላቸው አርሶ አደሮች በገመድ ተለክቶ እንደሚከፋፈሉም አክለዋል፡፡
አቶ ተስፋ የአርሶ አደሩን መፈናቀል በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹አርሶ አደሩ መሬቱን አልተነጠቀም፡፡ ቦታው ተለክቷል፡፡ መሬቱ ሲለካ አርሶ አደሩ መረጃ ስላልደረሰውና ወጥቶ ስላላየ የሚደረገውና የሚወራው አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ አግባብ ባልሆነ መንገድ አግበስብሶ የያዘው መሬት አለ፡፡ የሚመለከተውን ያህል ይሰጠዋል፡፡ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እየተሠራ በመሆኑ ማንም አይፈናቀልም፡፡ ሲለካ ለምን ይለካል ብሎ የሚያኮርፍ አለ፡፡ ይኼ ደግሞ ሥርዓትና አሠራር በመሆኑ ሕጉን ጠብቆ ይሠራል፤›› ማለታቸውን ሪፖርተር አመልክቷል።
በአዲስ አበባ የትራፊክ መብራቶች ከጥቅም ውጪ ናቸው
በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መብራቶች ቆመው ቢታዩም አገልግሎት እንደማይሰጡ አዲስ አድማስ ዘገበ። ጋዜጣው ተገልጋዮችን በማናገርና ተዘዋውሮ በመመለክት እንደዘገበው በከተማዋ ካሉት 26 የትራፊክ ማስተናበሪያ መብራቶች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጠው አንዱ ብቻ ነው። አዲስ አድማስ ባይገልጸውም የትራፊክ መብራቶቹ ምሶሶዎች ቀለማቸው የወየበ። የተገነጣጠሉና የከተማውን ውበት እንዲያበላሹ ታስበው የተቀመጡ መስለዋል።
በየደረጃው ያሉ ሃላፊዎችንና የአዲስ አበባ የትራፊክ ጽ/ቤት ችግሩን እንዳመኑ ያመለከተው አዲስ አድማስ ዜናውን አስገራሚ አድርጎ ያቀረበው የማይሰሩትን የትራፊክ መብራቶች ለመጠገን የመለዋወጫ ችግር መከሰቱን በመግለጽ ነው። ጥገና ለማካሄድ ተፈልጎ የመለዋወጫ እቃ ሲጠየቅ “እንዲህ ያለ እቃ አለ እንዴ” የሚል መልስ እንደሚሰጥ የተቀሰው ጋዜጣው የአዲስ አበባ የትራፊክ መብራት ዘመን ያለፈበትና ሊጠገን አይችልም ብሏል። ከባቡር ግንባታው ጋር በተያያዘ አዲስ የመብራት ተከላ ለማካሄድ ጨረታ መውጣቱንም አመልክቷል።
Gud says
በደፋሪው ሽማግሌ ላይ የተጣለው ፍርድ አሳዛኝ አሳፋሪና ተስፋ አስቆራጭ ነው። በነርዕዮት እና ውብሸት ላይ 14 ዐመት በሚፈረድበት አገር ህፃን ልጅ የሚደፍሩ ሽማግሌ ላይ 11 ዐመት መፍረድ አበጀህ እንደመለት ነው።