“የሙስሊሙ እንቅስቃሴ ከመንግስት እጅ እየወጣ ነው …”
የሙስሊሙ ጥያቄ ከመንግስት እጅ እየወጣ ስለመሆኑ የሚያመላክት ሁኔታ መታየቱን ኢሳት የካቲት 22 ቀን 2005 ዓ ም ዘገበ። ኢሳት እንዳለው የድምጻችን ይሰማ አስተባባሪዎች በነደፉት መርሐግብር መሰረት በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ተቃውሞዎች ተደርገዋል።
በመቀሌ፣ በመቱ፣ በጅጅጋ፣ በአፋር፣ በጅማ፣ ወልቂጤ፣ ጎንደር፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ተቃውሞዎች ተነስተዋል። በአዲስ አበባ ሙስሊሙ ማህበረሰብ “መሪዎቻችን ይፈቱ ድምጻችን ይሰማ በቤታችን ሰላም ስጡን” የሚሉ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ያስታወቀው ኢሳት አሁን ባለው ሁኔታ የሙስሊሙ ጥያቄ ከመንግስት እጅ እየወጣ ለመሆኑ አመላካች እንደሆነ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ለመከፋፈል መንግስት በእየለቱ የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ሙስሊሙን በቁጭት እንዲነሳ እያደረገው መሆኑን ታዛቢዎች እንደሚናገሩ ያመለከተው ኢሳት፤ “በመላው አገሪቱ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚያሰሙት ተቃውሞ ብዙዎችን እንዳስደመመ ቀጥሎአል” በማለት ዘገባውን ቋጭቷል።
“የሸሪያ ፍርድ ቤት” በጅጅጋ የአማራ ተወላጆችን ሰለባ አደረገ
ካለፉት አርባ ዓመታት ጀምሮ በሶማሊ ክልል በጅጅጋ ከተማ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ቤቶቻቸውን እያስረከቡ ለጎዳና ህይወት እየተዳረጉ መሆናቸውን ኢሳት አስታወቀ።
እስካሁን ድረስ በከተማዋ ውስጥ ዋና ዋና የንግድ ቦታዎች የነበሩዋቸው የአማራ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ ንብረታቸውን ለክልሉ ተወላጆች እንዲያስረክቡ በመዳረጋቸው ብዙዎች ድርጅቶቻቸውን አስረክበው ወደ መሀል አገር ሄደዋል በማለት ኢሳት የዘገበው የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ ም ነው። ተወልደው ያደጉበትን ቦታ አንለቅም በማለት እስካሁን የቆዩትም በተለያዩ አስተዳዳራዊ ጫናዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ በደብዳቤ እና በቃል ተነግሯቸዋል።
በጅጅጋ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ለኢሳት በጻፉት ደብዳቤ “የአንድ ብሄር የበላይነት በሰፈነበት መልኩ አማራ ወይም ሀበሻ የሚል መጠሪያ ተደርጎልን እነሆ ከህጻናት እስከ ትልቅ በመንገድም በቢሮም እየተሰደብንና እየተተፋብን መኖራችን ሳያንስ፣ አሁን ደግሞ ያለምንም ልዋጭ ቤታችን ተቀምቶ ጎዳና ላይ ተጥለን እንገኛለን” ብለዋል። ነዋሪዎቹ አክለውም “የእኛ ልጆች እንደልብ በመንገድ ላይ መሄድ አይችሉም፣ ሱሪ የለበሰች ሴት በፖሊስ ዱላ ትደበደባለች፣ ማን ፖሊስ ማን ሀላፊ እንደሆነ በማናውቀው ሁኔታ፣ የሸሪያ ፍርድ ቤት የሚል ተቋቁሞ ቤታችንን እንድንለቅ እያስገደደን ነው። ተወልደን ባደግንበት አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንደቆሻሻ እየታየን ነው” ብለዋል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የከተማው ነዋሪ በክልሉ የመኖር ተስፋቸው መሟጠጡን ተናግረዋል። ኢሳት በጅጅጋ ከተማ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን በደል በተደጋጋሚ መዘገቡንና መንግስትም ዝምታ መምረጡን አስታውቃል።
በጉምዝ የብሄር ግጭት ተነሳ
በቤኒሻንጉል ክልል የጉምዝና የወለጋ ኦሮሞዎች መካከል በብረት የተደገፈ ግጭት መፈጠሩን ዲብርሃን የተባለ ድረገጽ ገለጸ። ድረገጹ እንዳለው ግጭቱ የተነሳው ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ነው።
የህዳሴው ግድብ የሚከናወንበት የቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀስ የቤኒሻንጉል ነጻ አውጪ የሚባል ድርጅት መኖሩን በመጥቀስ የዘገበው ዲብርሃን የነጻ አውጪው ሃይል ከግጭቱ ጋር ስላለው ግንኙነት አልገለጸም። በቤኒሻንጉል ክልል ቀደም ሲል እጅግ የከፋ የጎሳ ግጭት ተካሂዶ እንደነበርና በወቅቱ ዘግናኛ የተባለ አደጋ ቢደርስም መንግስት እንደሸፋፈነው ይታወቃል።
በወቅቱ በተካሄደው ጭፍጨፋ ከሌላ ክልል በሰፈራና በተለያዩ ምክንያቶች ቤኒሻንጉል የገቡ የሌላ ብሄር አባላት ጉዳት ሲደርስባቸው መንግስት አስፈላጊውን ርዳታ ባፋጣኝ አለማድረጉ በወቅቱ ሲያስተቸው ነበር።
“የአባይ ግድብ ግንባታ አይቆምም ”
አምና በግንቦት ወር በህዳሴው ግድብ ላይ ጥናት እንዲያደርጉ ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅና ከሱዳን እንዲሁም ከዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡ የተውጣጡ አሥር ባለሙያዎች ግድቡ ሊያስከትል ስለሚችለው ተፅዕኖ የጀመሩት ጥናት፣ በመጪው ግንቦት ወር ይፋ የሚደረግ ቢሆንም ሪፖርቱ ምንም ሆነ ምን ግንባታው እንደማይቋረጥ ሪፖርተር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖምን ጠቅሶ ዘገበ።
ሚኒስትሩ በጽሕፈት ቤታቸው ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መልዕክት ይዘው የመጡ ልዑካንን ካነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳ ከልዑካኑ ጋር ስለባለሙያዎቹ ጥናት ባይነጋገሩም፣ በመጪው ግንቦት ይፋ የሚሆነው ሪፖርት ምንም ይሁን ምን የግድቡ ግንባታ እንደሚቀጥል በማስታወቅ፣ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ካሉና ከተገኙ ግን ሊስተካከሉ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ ጥናቱ እንዲካሄድ ያስፈለገው በዓባይ ወንዝና በወንዙ ተፋሰስ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎችን ያፈናቅላል የሚሉ ትችቶች በመሰንዘራቸው ምክንያት፣ ከሦስቱም አገሮች የተውጣጡ ባለሙያዎችና ገለልተኛ ግለሰቦች ጥናት እንዲያካሂዱ መመደባቸው ይታወሳል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ማብራሪያ ተጠየቀች
ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አድርገው የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ስለሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ አምባሳደር ማብራሪያ መጠየቋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቋል።
የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልጣን ሰሞኑን የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሳዑዲ ዓረቢያን አምባሳደር በማስጠራት አነጋግሯል። ስለጉዳዩም ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለይ ለጋዜጣው (አዲስ ዘመን) ዝግጅት ክፍል በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የሳዑዲ አምባሳደር ስለጉዳዩ ማብራሪያ በተጠየቁበት ወቅት «የእኔም የአገሬም አቋም አይደለም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሆኖም ኢትዮጵያ በባለሥልጣኑ አስተያየት ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጥበት መፈለጓን አስታውቃለች።
የሳዑዲ ዓረቢያው ባለሥልጣን ንግግር አስገራሚና አሳዛኝ እንደሆነ ያመለከቱት አምባሳደር ዲና፤ የግለሰቡ አስተያየት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና በናይል ተፋሰስ ሀገሮች መካከል ጣልቃ መግባትን እንደሚያሳይ፣ በዓረቡ ዓለምና በአፍሪካ መካከል ውሃን አስመልክቶ ጠብ እንዲጫር የመፈለግ አዝማሚያ ያለ እንዲሚመስልም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላት የጠቀሱት አምባሳደር ዲና፤ ባለሥልጣኑ በሰጡት አስተያየት የተጋጩት ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን በናይል ተፋሰስ ካሉ አገሮች ጋር መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከማንም ሀገር ጋር አብሮ የመሥራትና የመተባበር ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመው፤ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋርም ትብብርና ስምምነት እንደተገባና ይህም ጠንካራ እንደሆነም አመልክተዋል። ስለሆነም ዲፕሎማሲ የሚቸኩሉበት ጉዳይ ባለመሆኑ የሳዑዲ ዓረቢያ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን አብራርተዋል።
ሰሞኑን በግብፅ መዲና ካይሮ የተካሄደው የዓረብ ሀገራት የውሃ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ካሊድ ቢን ሱልጣን የተናገሩትን በመጥቀስ ሱዳን ትሪቡን በድረገጽ እንደዘገበው፤ ባለሥልጣኑ የሕዳሴው ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ፖለቲካዊ ገፅታው/ተንኮል ጎልቶ የሚታይበት ፕሮጀክት ነው በማለት ተናግረዋል። (ዘገባው የአዲስ ዘመን ነው)
መንግስት ነዳጅ አልተገኘም አለ
ሰሞኑን የተለያዩ ጋዜጦችና ድረገፆች «በኦሞ አካባቢ ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይት ክምችት ተገኝቷል» በሚል እየዘገቡ ቢሆንም፤ የማዕድን ሚኒስቴር ግን ነዳጅ ዘይትን በተመለከተ ያለው ተጨባጭ እውነታ በአሁኑ ወቅት ጋዜጦች በሚገልፁት መልኩ የሚነገርበት ደረጃ ላይ አይደለም ብሏል፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ ጠቅሶ አዲስ ዘመን እንዳስታወቀው ቱሎ ኦይል በጋና፣ በዩጋንዳና በኬንያ ካከናወናቸው ስኬታማ ስራዎች በመነሳት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከነዳጅ ፍለጋው ጋር በተያያዘ የተዛቡ ዘገባዎች እየወጡ ናቸው፡፡ “የነዳጅ ፍለጋ ስራው በጥሩ ኩባንያ እጅ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ “የቁፋሮ ሥራው እንደቀጠለ ነው፤ ውጤቱንም በሂደት የምናየው ይሆናል ብሎ ከሚገለፅ ውጪ አዲስ ነገር የለም” ብለዋል።
በኦሞ የነዳጅ ቤዚን የእንግሊዝ ኩባንያ ቱሎ ኦይል 50 በመቶ የነዳጅ ፍለጋ ድርሻ አለው፡፡ 30 በመቶው የአፍሪካ ኦይል ሲሆን፤ 20 በመቶው ደግሞ የአሜሪካው ማራቶን ኩባንያ ድርሻ ነው፡፡
ወይዘሮ ስንቅነሽ እንዳሉት ቱሎ በዘርፉ የቴክኒክ ብቃቱ የዳበረና በጥሩ ሁኔታ ስራውን የሚያከናውን ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ በኦሞ አካባቢ የጂኦ ሳይንስ ስራውን አከናውኖ እ.ኤ.አ ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም በይፋ ቁፋሮ ጀምሯል፡፡ ኩባንያው ሶስት ጉድጓዶች የሚቆፍር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የአንዱ ጉድጓድ ቁፋሮ ከ1ሺ 400 ሜትር በላይ ጥልቀት ደርሷል፡፡ የቁፋሮው ውጤት የሚጠናቀቀውም አንዱ ጉድጓድ 2ሺ 600 ሜትር ጥልቀት ላይ ሲደረስ ነው፡፡ ኩባንያው አንድ ጉድጓድ ለመቆፈር 50 ሚሊዮን ዶላር በራሱ ወጪ ያደርጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የነዳጅ ቤዝን (ተፋሰስ) ተብለው በተለዩት የመቀሌ፣ የዓባይ፣ የጋምቤላ፣ የመተማ፣ የኦሞና የኦጋዴን ቤዚኖች የነዳጅ ፍለጋ እየተካሄደ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሰፊውና ከ350ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው የጋዝ ግኝት ያለው የነዳጅ ምርመራ የሚካሄደው በኦጋዴን ቤንዚን ነው፡፡
ኩባንያዎቹ በእነዚህ አካባቢዎች የተለያዩ የስነ ምድርና የጂኦ ፊዚክስ ስራዎችን ካከናወኑ በኋላ ወደ ቁፋሮ ገብተዋል ያሉት ወይዘሮ ስንቅነሽ፤ ቁፋሮው ግን የፍለጋው አካል እንጂ ነዳጅ ተገኝቷል የሚያሰኝ አይደለም ብለዋል፡፡ የአንዱ ጉድጓድ ቁፋሮ እንኳን ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ምንም ማለት እንደማ ይቻልም ተናግረዋል፡፡
«ኩባንያው ሶስት ጉድጓድ ለመቆፈር ፍላጎት ማሳየቱና ወደ ተግባር መግባቱ መንግስትን አስደስቷል፡፡ ኩባንያውም ደስተኛ ሆኖ እየሠራ ነው፡፡ የቁፈራውን ውጤት አብረን እያየን ለኅብረተሰቡ ይፋ የምናደርገው ካለ እናደርጋለን፡፡ ዋናው ነገር ጥሩ እንቅስቃሴና ተነሳሽነት ያለው ኩባንያ መሆኑ ላይ ነው» ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ ምን እያደረገች ነው?
የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር በኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የሚያጥላላ ትችት በሰነዘሩ ማግስት ኢትዮጵያ የ25 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አድርጋለች። የሳውዲ የገንዘብ ሚኒስትር፣ አዲስ አበባ ተገኝተው በፈጸሙት ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል ተደራራቢ ታክስን የሚያስቀር ስምምነት መፈረሙን ያስታወቀው ሪፖርተር ነው።
ባለፈው ማክሰኞ በግብፅ በተካሄደው የዓረብ አገሮች የውኃ ምክር ቤት መድረክ ላይ የተገኙት የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እያካሄደች ያለችው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለግብፅና ለሱዳን የውኃ ፍላጐት አደጋ መሆኑንና የኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሌለውና ከዚያ ይልቅ በግብፅና ሱዳን ላይ የተቃጣ ፖለቲካዊ ሴራ ነው በማለት፣ መንግሥታቸውን በጭራሽ በማይመለከት ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ ትችት ሰንዝረዋል፡፡
ከዚህ የምክትል ሚኒስትሩ ንግግር ሁለት ቀናት በኋላ የሳዑዲ ዓረቢያ የገንዘብ ሚኒስትር ዶክተር ኢብራሂም አብዱላዚዝ አል አሳፍ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ቢሆንም፣ ተልዕኳቸው ግን የመከላከያ ምክትል ሚኒስትሩ ንግግርን ለማስተባበል አይደለም፡፡ ሳዑዲ አረቢያ እያራመደች ያለው ጉዳይ የሰሞኑ ታላቅ ጉዳይ ሲሆን መንግስትም በግልጽ አቋሙን አሳይቷል።
Leave a Reply