የዛሬዋ ዓለማችን በደረሰችበት የእድገት ደረጃ ስልጣኔን ወይም ብልጽግናን ከቴክኖሎጂ ለይቶ ማየት ያስቸግራል። የሰለጠነ ህብረተሰብ ማለት ቴክኖሎጂን ያዳበረ ህብረተሰብ ማለት ነው። ባንጻሩም ቴክኖሎጂን ያላዳበረ ህብረተሰብ ማለት ደግሞ ያልበለጸገ ህብረተሰብ ነው። የሰለጠነ ህብረተሰብ ስንል ደግሞ ድኅነት የተረታበት፤ በሽታ የመነመንበት፤ ትምህርት የተስፋፋበት (እውቀት የለመለመበት)፤ ዲሞክራሲ የሰፈነበት፤ የመገናኛና ቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በስፋት የተንሰራፋበትና ህግ የበላይ የሆነበት ህብረተሰብ ማለታችን ነው።
ቴክኖሎጂ እላይ ለተጠቀሱት ለሰው ልጆች አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ የሆነ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አለው። ይሄን ሲይደርግ ግን ቴክኖሎጂ ከህብረተሰብ ውጪ ሆኖ በታዓምር ወይም ትእዛዝ በመስጠት ሳይሆን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የሚተገብሩት፤ ሌሎች የህብረተሰብ ምግባራትም ለምሳሌ ትምህርት፤ ኢኮኖሚ፤ ዲሞክራሲ በየፊናቸው ተጽእኖ የሚያደርጉበት ምግባር ነው።
ቴክኖሎጂ ከተጸኖ ነጻ ያልሆነ ቢሆንም፤ ገና ከጥንቱም የሰውን ልጆች የአራዊት አይነት ከነበረው ከአዳኝና ለቃሚነት ህይወት ያላቀቀ፤ እጅግ አስፈሪና አድካሚ የተፈጥሮ ጫናዎችን ያቀለለለ፤ የችግሮች መፍቻ ቁልፍና ዘዴም ስለሆነ ተገቢው ትኩረት ከተሰጠው በተጽኖም ስር ሆኖ ህብረተሰባዊ ተልእኮውን መወጣት የሚያስችለው አቅም አለው። ይህም አቅም የሚመነጨው ቴክኖሎጂ ከችግር ፈቺነቱ በተጨማሪ ለፈጣሪው፤ አድራጊው ወይም ከዋኙ ለሆነው ለሰራተኛው ህዝብ አጋዥና ታዛዥ በመሆኑና ከዋኙና አድራጊው ደግሞ አብዛኛው ህዝብ በመሆኑ ነው።
በዚህ መጣጥፍ ሊተዋወቅ የተፈለገው መጽሀፍ አርእስት፤ ኢትዮጵያና የቴክኖሎጂ እድገት ፈለግ የተባለ ነው። መጽሀፉ የዚህን ሀያል የሰው ልጆች ምግባር ቴክኖሎጂን ዘርዘር ባለ መንገድ ኢትዮጵያውያን እንድንነጋገርበት ተከጅሎ የተጻፈ ነው። ለምን ቢባል ቴክኖሎጂ በአለማችን ከማንኛውም የህብረትሰብ ክስተቶች ሁሉ ከነገስታቱ (ከጥንቶችም ሆነ ከዘመናዊ)ና ከቤተ እምነትም በላቀ መንገድ ህብረተሰብን መቀየር የቻለና የሚችልም ሀያል የሰዎች ምግባር በመሆኑ።
መጽሀፉ በአራት ክፍሎች፤ ሃያ ምዕራፎችና በ330 ገጾች የተዋቀረ ነው። ብረትን በእሳት፤ ሸክላን በውሃ፤ መሬትን በማረሻ፤ እንጨትን በስለት፤ ጥጥን በማዳወሪያ፤ ሙዚቃን በማሲንቆ እየቃኙ የህይወትን ቁስ በማምረት አገራችንን እንድ አገር ያቆዩልንን ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቴክኖሎጂስቶቻችንን ከዘከረ በኋላ፤ ለመጀመር፤ ቴክኖሎጂ ለምን? ቴክኖሎጂ ምንድን ነው? የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ይንደረደራል።
ክፍል አንድ፤ የጥንቱና የአዲሱ የድንጋይ ዘመናት ሰዎች ከሌሎቹ ፍጥረታት እራሳቸውን ነጥለው ሊያወጡ ያስቻሏቸውን የሾለ ድንጋይና እንጨት ምሳሪያዎችን፤ የንግግር ችሎታ (የመጀመሪያው የኮሙኒኬሽን ተክኖሎጂ) መጀመርን፤ እሳትን የመግራትና የመጠቀም ጥበብን በእጃቸው ከደረጉበት የመጀመሪያዎቹ ዘመናት እስከ የግብርና (የእርሻና የከብት እርባታ ጥምረት) አብዮት የተፈጠሩትን ቴክኖሎጂዎች ያያል።
ክፍል ሁለት፤ የስልጣኔ ዘመን በመባል ከሚታወቀው ከዛሬ አምስት ሺህ አመታት በፊት በአባይ በኤፍራትስ-ታይግረስና ሌሎችም ታላላቅ ወንዞች አካባቢ ከከተሙ ህዝቦች ጀምሮ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ የተገኙትን አውራ ቴክኖሎጂዎች ግኝት ያያል። በወፍ-በረር ለማየት ያህል የጽሁፍ ችሎታ፤ የዘመን መቁጠሪያ (አንድን አመት በውራት ወርን በሳምንታት፤ ሳምንትን በቀናት፤ ቀንን በሰአታት ወዘተ መሸንሸንን) ካሌንደር፤ የሂሳብ ስሌትን፤ ብረታት የማቅለጥንና ማዘዝን፤ የህንጻ ቴክኖሎጂዎችን ያያል። በመቀጠልም የጥንታዊ አውሮፓ ቴክኖሎጂዎችን ለማየት ከግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ከዚያም ወደ ሮማ እንዲያም ሲል የሌሎች አውሮፓውያን ቴክኖሎጂዎችን ይዳስሳል። ከቴክኖሎጂዎቹም መሀል የንፋስና ውሃ ሀይሎችን የመግራት፤ የከፍተኛ ትምህርት ደብሮችን አደረጃጀት፤ የጊዜው የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂዎችን፤ የባህር ላይ ቴክኖሎጂዎችንና የህትመት ቴክኖሎጂዎችን ያያል።
አስከትሎም ለኢንዱስትሪው አብዮት አጥቢያ የነበሩትን ዋና ዋና ክዋኔዎችን ያነሳል። ከነዚህም መሀል ሳይንሳዊ አብየት በመባል የሚታወቀውን፤ የትራንስፖርትን እድገት፤ የካፒታልን መጠራቀም፤ ማእድን ማውጣትን፤ የሰለጠነ የሰው ጉልበት ማዘጋጀትን፡ የግብርና ቴክኖሎጂ ያሳየውን እድገት፤ ስነ-ልቦናዊ ዝግጅትን፤ የመንግስታትን ሚና ይዳስሳል።
ከዚያም ወደ ኢንዱስትሪው አብዮት ይገባና ስለ ብረት(እስቲል) የድንጋይ ከሰልና የእንፏሎት ሞተር በአብዮቱ ስለተጫወቱት ሚና፤ ስለ አዲሱ ምርት አደረጃጀት ካይየን በኋላ አዲሱ አብዮት የፈጠረውን አዲስ ህብረተሰብ እንዳስሳለን።
ቀጠል አድርገንም ከኢዱስትሪው አብዮት በኋላ ስለተገኙ ቴክኖሎጂዎች ባጭር ባጭሩ አድርጎ ያነሳል። ያንንም ለማድረግ በመጀመሪያ የግብርናን ቴክኖሎጂ ያደረገውን እድገት፤በጋዝ የሀይል ምንጭ አጠቃቀም የተደረጉ መሻሻሎችን፤ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ እድገቶችን፤ የምርት አሰባሰብን፤ የህንጻ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን አዲስ አድገት፤ የኬሚካል ቴክኖሎጂን፤ የምግብ አዘገጃጀት ቴክኖሎጂና እሱ የወለዳቸው እንዱስትሪዎችን፤ በጦር መሳሪያዎች ቴክኖሎጂ የታዩ እድገቶችን፤ ዘመናዊ የምርመር ተቅዋሞች ስለመከሰት፤ ቴክኖሎጂ በሴቶች ህይወት ላይ ስላስከተለው ለውጥ፤ የቴክኖሎጂ እድገት በስራ ላይ ስላደረገው ለውጥና በትምህርትና በቴክኖሎጂ ስለተፈጠረው አዲስ ግንኙነት አይቶ ይህ ክፍል ይጠናቀቃል።
ክፍል ሶስት፡ ከላይ የተጠቀሱትን የቴክኖሎጂዎች እድገት መነሻ በማደረግ ቴክኖሎጂ እራሱ ሲያድግ የተከተለውን የእድገት ፈለግ ለመዳሰስ ይሞክራል። ቴክኖሎጂ ሲያድግ ድረጃ በደረጃ ነው። ይህን የቴክኖሎጂን በየደረጃው ከቀላል ወደ ውስብስብ የማደግ ሂደት ለማሳየት ሁለት አውራ የቴክኖሎጂ ረድፎች ተመርጠዋል። እነሱም የቁሳት (የማቴሪያል)ና የሀይል (ኤነርጂ) ቴክኖሎጂዎች ናቸው።
በቁሳት (ማቴሪያል) ረድፍ ሴራሚክስን፤ ብረታትን (ብረታ ብረትን)፤ ፖሊመርንና ባዮቴክኖሎጂን ያካትታል። እነዚህንም ሲያይ ገና ከጥንት ጀምሮ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች የሰልጆች እንዴት ሊጀምሯቸው እንደቻሉና በየዘመኑና በተለያዩ ህብረተሰቦች በየደረጃው ትንንሽ መሻሻሎችን በማድረግ ነባር ክህሎቶችንና ቴክኒኮችን አንዱን ከሌላው በማጣመር አዲስና ያልነበረን በመገንባት አሁን ወደ ደርስንባቸው ዘመናዊ ወደምንላቸው ማቴሪያሎች እንዴት እንደተደረሰ ለመጠቆም የሞክራል።
በሀይል (ኢነርጂ) ረድፍም የእንፏሎትን፤ የጋዝን፤ የኤሌክትሪሲቲንና የኤሌክትሮኒክስን (ከኤሊክትሪሲቲ ጋር የተያያዘ በመሆኑ) ያካትታል። በሀይል በኩልም እንደዚሁ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ የሰው ልጆች ከእነዚህ የሀል ምንጮች ጋር እንዲት ሊተዋወቁ እንደቻሉ፤ የሀይል ምንጮቹንም ለመግራትና ለመገልገል ያሳለፏቸውን ውጣ ውረዶችና የገኟቸውን ስኬቶች አንኳር አንኳሮቹን ያይና ወደኋለኞቹ እድገቶች ያመራል።
ወደ መጨረሻ ገደማ ደግሞ ቴክኖሎጂ በህብረተሰብ እድገት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና፤ እድገት ስንል ምን ማንት እንደሆነ፤ በእድገትና በቴክኖሎጂ መሀል ያልውን ትስስር ያገናዝባል። መለስ ብሎም የቴክኖሎጂን የስተዳደግ ፈለግ ዘርዘር አድርጎ ካነሳ በኋላ ክፍሉ ይደመደማል።
ክፍል አራት የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኩራል። ለዚህም ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂዎች ጀምሮ አሁን እስከተደረሰበት ድረስ ያሉትን አጠር አጠር አድርጎ ያይና ወደ ኋላ ላይ ወደፊት ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ እንዲያድግ ጽሁፉ ጠቃሚናቸው የሚላቸውን ሀሳቦች ይሰነዝራል።
እንደመነሻ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድርና ያም እያስከተለ የነብረውንና አሁንም ያለውን የአየር ፀባይ በማንሳት የሀገሪቱ ጥንታዊ ስልጣኔ እንደሌሎች የጥንት ስልጣኔዎች (እንደ ምሳሌ ግብጽ) ወንዝ ዳር የነበረ አለመሆኑን ያካካሰው መልክዓ ምድሯና የአየር ጠባይዋ መሆናቸውን ይጠቅሳል።
ከጥንታዊት ኢትዮጵያ (አክሱማዊት እትዮጵያ) ጎላ ያሉ ቴክኖሎጂዎች መሀል እጽዋትን ማወቅ (ምሳሌ ቡና ጤፍ የኮባ ቆጮ)ና ለአለም ማስተላለፍ፤ በበሬ ጉልበት ማረስ ከጀመሩት አንዷ መሆኗ፤ የብረታትና የሰራሚክ ቴክኖሎጂዎችን መተግበሯና የጽሁፍ ችሎታ ማዳበሯን ዘርዘር አድርጎ ያያል።
በኋለኖች ዘመናትም በፊት ከነበሩት ብዙም ባይሻሻሉ የግብርና የብረታት ስራ ስራሚክ በፖሊመር ቴክኖሎጂም ጥጥን ቃጫን ቆዳን ዘይት ጨመቃን በመተግበር እንደቀጠለች ያነሳል። ከውጪ ተሸጋግረው ኢትዮጵያ የገቡ ቴክኖሎጂዎችንም በመጠኑ ያያል።
የአለም ቴክኖሎጂ ባለፉት ሶስት መቶ አመታት ፈጣን እድገት ቢያሳይም የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግን ባለበት የቆመ በመሆኑ በርካታው የዚህ ክፍል የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ወደፊት እንዴት ሊያድግ እንደሚችል ለማየት ይሞክራል። ለዚህም ካደጉና ተሸጋግርው በመጡ ቴክኖሎጂዎችና በአገር-በቀሎቹ ቴክኖሎጂዎች መሀል ያለመጣጣምና የሆድና-ጀርባ አይነት ግንኙነት ወደ መቀራረብና መጣመር ወደ መፍጠር እንዲቀየር አስፈላጊነት ያወሳል።
ቴክኖሎጂ የሚያድገው የተለያዩ ክፍሎቹ እየጣመሩ በመሆኑም ነባሩ ከአዲሱ ሊጣመሩ እንደሚችሉ የቴክኖሎጂ እድገት ተመክሮ ስለሚያስተምር የማይቻል አለመሆኑን ለማስጨበጥ ሙከራ ተደርጓል። ስለቴክኖሎጂ ጥምረት ሂደትም የአገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በምሳሌነት ተጠቅሞ ያገር በቀል ቴክኖሎጂዎችም እራሳቸው ተጣምሮ በማደግ ቀመር ውስጥ በማምራት አሁን ካሉበት ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያድጉ እንደሚችሉም ይጠቁማል።
ወደ ኋላም አገራችን በቴክኖሎጂ እንድታደግ ዜጎች፤ ከፍተኛ የትምህርት ደብሮችና መንግስትም ሊያደሩት የሚጠበቅባቸውን ሀሣቦች ይሰነዝራል። በአገራችን ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ደረጃ እንዲይስድግ የግድ ያደጉት ምዕራባውያን ያሳለፉትን ረጂሙን የሶስት መቶ አመታት
መፍጀት እንደሌለበት ከሀምሳ አመታት በፊት እንደኛው ሁላ ቀር የንበረችወንና አሁን ያደገቸውን ደቡብ ኮሪያን በመጥቀስ መጽሀፉ ያልቃል።
ቀደም ሲል እንደተጠቀስው የዚች የመጽሀፍ ዋና አላማ ህዝባችን በቴክኖሎጂ አስፈላጊነት ላይ እስካሁን ሲያደርገው ከነበረው በተሻለ በመነጋገር አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት እንዲጀመር ነው። ቴክኖሎጂ ለተሻለች ኢትዮጵያ መምጣት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነውና ። ቴክኖሎጂ እጅግ ሰፊና ጥልቅ የሰው ልጆች ምግባር ነው። ስለሆነም ስለቴክኖሎጂ በባለ 300 ገጾች ትንሽ መጽሀፍ ሁሉንም ማለት ባለመቻሉ ከቴክኖሎጂ ኃያልነት አንጻር ስትታይ መጽሀፏ ልበ ሰፊ እንጂ አቅሟ ደካማ ነው። ሆኖም ግን አሁን እየሰፈነ ካለው ዘምታ ጥቂቶቻችንን እንኳን ካነጋገረች የበኩሏን ጠጠር ወርውራለች ማለት ይቻላል።
በ tadniga44@gmail,com ኢሜይል በኩል የመጽሀፏን ኮፒ ለማግኘት ይቻላል።
ከሁለትና ሶስት ሳምንታት በኋላ ደግሞ እዚህ ድህረ-ገጽ ላይ ትገኛለች።
Leave a Reply