ከዓመታት የንባብ ብህትዉና በኃላ በቀጣይ ሳምንት በመጽሃፍ መልኩ ብቅ የሚለዉ በዕዉቀቱ ስዩም፣ በርከት ያሉ ሞጋች ሃሳቦችን በሥነ-ጽሁፋዊ ለዛ እያዋዛ ወደ አደባባይ እንደሚያወጣ ጥርጥር የለዉም፡፡ “ከአሜን ባሻገር” ምን አለ? . . . የመራቂዉን ማንነት መፈተሸ …? ጥልቅ መጠይቅ …? ወይስ ለየት ያለ ፍንገጣ? … ብቻ ብዙ ነገር ይጠበቃል፡፡ በተለይ ጽዮን ተኮር ኃይማኖታዊ ባህልና መስመር ያለፈ ጥብቅ ብሄርተኝነት ስላጎበጣት ኢትዮጵያ “ከአሜን ባሻገር” ብዙ የምትለን ይመስለኛል፡፡
ታሪክን ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና ከኃይማኖታዊ ጥብቅና በጸዳ መልኩ ለማየት የሚጥረዉ በዕዉቀቱ፣ ንባብ የፈጠረለት አቅሙን ተጠቅሞ በግሉ ከደረሰበት የታሪክ ምልከታ አኳያ የሚያካፍለን ብዙ ነገር እንደሚኖር እጠብቃለሁ፡፡ ባለመርማሪ ልቦናዉ በዕዉቀቱ፣ የጊዜችን ቋሚ ሽፍቶችን በተመለከተ ሽሙጥን በተሻገረ መልኩ መረር ያለ ሂስ እንደሚሰነዝር እሙን ነዉ፡፡ በተለየም የነጻዉ ፕሬስን ቅርቃር በነገስታቱ ዘመን ለአዝማሪዋች ይሰጥ ከነበረዉ ነጻነት አኳያ እያነጻጸረ ትዝብቱን እነደሚያካፍለን ግምቴ ነዉ፡፡ የሃገሪቱን ዳቦ አልባ ልማት፣ እንደ ግዙፍ ፋብሪካ አንድ አይነት ምርት እያመረቱ ስላሉት ዩኒቨርስቲዎቻችን፣ የንፉቅቅ ሚሄደዉን “ዴሞክራሲ” ያችንን በቸልታ የሚያልፋቸዉ አይመስልም፡፡ ማህበራዊ ሞገድ የሚንጠዉን የከተሜ ነዋሪ በሥነ-ጽሁፋዊ ለዛ እያዋዛ በብዕሩ ለስላሳ ኩርኩም የሚያሳርፈዉ በዕዉቀቱ፣ በዚህ ሥራዉም የእሽባይነት (አሜን ባይነት) ዝማሜውን በተመለከተ የሚያነሳችዉ ጭብጦች የመጽኃፉ አንኳር ሃሳብ እንደ ሚሆን ይጠበቃል፡፡
በሎንደን ኦሎምፒክ ከራሞቱ፣ በሰሜን አሜሪካ የሾዉ ጉዞና በብራዉን ዩኒቨርስቲ የፌሎዉሺፕ ምርምር ከፊል ቆይታዉ ከዳያስፖራዉ ማህበረሰብ የታዘባቸዉን ማህበረ-ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ከምዕራባዊያኑ ነባራዊ ክስተቶች ጋር እያዛመደ የሚያወጋን ጉዳይ መኖሩ አይቀርም፡፡
የበዕዉቀቱ የፍንገጣ ጽሁፍ ለጽዮን ብሄርተኞች የሚመች አይደለም፡፡ አሰላሳዩ ልጅ ብዕሩን ማንሳት ሲጀመር በድብድብ የጽድቅ በር የሚከፈት ይመስል የኃይማኖት “አርበኛች” ራሳቸዉን ለዱላ ያዘጋጃሉ፡፡ የነገር ጂራፋቸዉ የተፈተለ ነዉና ዘለፋና ስድብ ከአንደበታቸዉ አይጠፋም፡፡ ሃሳብን በሃሳብ መመከት የከሸፈዉ በገዢዎቻችን በኩል ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ጎረምሳ “ኃይማኖተኛች” ጭምር ነዉ፡፡ ንግድና ክህነትን አጣምረዉ የሚጓዙ ምግባረ-ክብሪት የሆኑ ዲያቆናት የዚህ መሰል ድረጊት አራጋቢዎች ናቸዉ፡፡ ነገር በማቀጣጥሉ ረገድ የቤንዚልን ሚና ያስንቃሉ፡፡ ለአንዳንዶቹማ ከክህነት ትምህርቱ ጋር አብሮ የተሰጣቸዉ እስኪመስል ድረስ የነገር አራጋቢነት “ችሎታ”ቸዉ ከፍ ያለ ነዉ፡፡
ለሁሉም፤ ድብርት ተጫጭኖት ለከረመዉ የኢትዮጲያ ሥነ-ጽሁፍ ገበያ ጥሩ መነቃቃትን የሚፈጥር መጽሃፍ ገበያዉን ለመቀላቀል እያኮበኮበ ያለበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ፡፡ እናም የመታከት ወራት እያለፉ ነዉና አይናችንን ከመስኮቱ ወደ በሩ እናማትር፤ ልትናፈቅ የሚገባት ድርሳን ቀርባለችና፡፡ የቀኑ ሰዉ ይበለን፡፡ “አሜን” እያልን “ከአሜን ባሻገር”ን እንጠብቅ፡፡
ሙሉአለም ገ.መድህን
Firew Ayenachew says
I hop will read it.
Yikir says
Nuro tefnegona asro adirgognal ye ferenj doro.