እንደ – መግቢያ
በኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ላይ ብዙ ልዩነቶች ይስተዋላሉ፡፡ የልዩነቶቹ ሥረ-ምክንያት እንደ ጸሐፊው ማንነትና የሥርዓታቱን ባህሪ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የኢትዮጵያን የቀደመ ታሪክ የሚቃኙ የተለያዩ ኃይለ-ሐሳቦች በየጊዜዉ እንዲጸባረቁ ግድ ብሏል፡፡ የታሪክ ትንቅንቁ በአጥቂነትና በተከላካይነት የሚበየን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ፍልሰት፣ መስፋፋት፣ ብሔራዊ ጭቆና፣ ቅኝ ግዛትና መሰል ቃላት ላለፉት አርባ ዓመታት፤ በተለየ መልኩ ደግሞ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት የታሪክ ሙግት አጀንዳ አስቀማጭ ቃላት ሆነዋል፡፡ ባሳለፍነው የሩብ ክፍለ ዘመን ጉዟችን የታሪክ ጉዳይ እጅግ አብሰልሳይና ውርክብ የበዛበት ሊሆን የቻለው አገዛዙ ለኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ በጎ እይታ የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የታሪክ ነክ ሙግቶች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዱላ ቀረሽ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
በአንድ ወቅት በኢዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ላይ አስተያየቱን የሰጠው የዘመኑ አዳሽ ምሁር ገብረህይወት ባይከዳኝ ይህን ብሎ ነበር ‹‹ታሪክን መማር ለሁሉ ስው ይበጃል፡፡ … እውነተኛውንም ታሪክ ለመፃፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ …. መጀመሪያ ተመልካች ልቦና የተደረገውን ለማስተዋል፣ ሁለተኛ የማያዳላ አእምሮ በተደረገው ለመፍረድ፣ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ›› እንደሚረዳ አፅኖት ስጥቶ ተናግሯል፡፡ ገብረህይወት ልክ ነበር፡፡ የገብረህይወት ምክረ-ሀሳብ የሚሰራው ግን ታሪክ የፖለቲካ እስረኛ መሆን ስታቆም ብቻ ነው፡፡ በዘመናችን ታሪክ የአሸናፊዎች ደንገ-ጡር ናት፡፡
ከገብረህይወት አስተያየት በፊትም ሆነ በኋላ ታሪክ በጸሐፊው ማንነት /ኃይማኖታዊ ማንነቱንም ያካተተ/ እና በስርዓታቱ ባህሪ ሲከተብ ኖሯል፡፡ (አልፎ አልፎ የነገስታቱን ጉልህ ጥፋቶች የፃፉ ደብተራዎችና ሊቃውንት እንዳሉ ሳዘነጋ) ከዚህ የተጣባዉ ባህሪያችን ዛሬም ተከትሎን ዘልቋል፡፡ እናም በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ ክርክሮች ሲፈጠሩ ማጠንጠኛቸው ከላይ በተገለጹት ቃላት (ፍልሰት፣ መስፋፋት፣ ብሔራዊ ጭቆና፣ ቅኝ ግዛት…) የትርጉም ልዩነት ዙሪያ ሊሆን ግድ ብሏል፡፡ ለዚህም ይመስላል በተፎካካሪ የኢትዮጵያ ታሪክ ትርጉም አቀንቃኞች መካከል የታሪክ ገመድ ጉተታው ሊቋጭ ያልቻለው፡፡
ፖለቲካን የታከከ የታሪክ ትርጉም ጮክ ባለ መልኩ የሚያራግበው ኢህአዴግ፣ ታሪክን ከፕሮፌሽናል ባለሙያዎች መዳፍ ነጥቆ የካድሬዎቹ መጫወቻ ካደረገው በኋላ ደግሞ የአብሮነታችን ጠንቅ የሆኑ፣ በሰነድም ሆነ በሥነ-ቃል ደረጃ ያልተዋረሱ (ያልተደገፉ) ትርክቶች ኃውልትን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ርዕዩተ ዓለም ይዘው ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ታሪክ በጊዜ ምጣኔ እየተከፈለ፣ እንደ ዘመኑ የህብረተሰብ አስተሳሰብ ዕድገትና የባህል ይዞታ እንዲሁም አካባቢያዊ (regional) ቅኝትን በንፅፅር እያሳየ እስካልተፃፈ ድረስ የታሪክ ትርጉም ቅርቃር ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መሀል ስለ ቡድን ፍላጎታቸው ሲሉ መሓኑን ታሪክ ለማዋለድ ጥረት የሚያደርጉ የታሪክ አዋላጆች ይፈጠራሉ፡፡ ታሪክን ከብሔራዊነት ግንባታ አኳያ ሳይሆን ከቡድን ፍላጎት አንጻር አጣመው የሚፅፉና የሚተረጉሙ አካላት በመስመር መሀል ትግላቸው ለተራዛሚ ስልጣንና ለኪስ አብዮት መሆኑን ያላስተዋለ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይኖር ይሆን? እጅግ የበዛ የመርማሪነት ልቦናን የሚሻው የታሪክ ምርምርና ዘገባ ስራ አርበኝነት ባጠቃቸው ‹ፀሐፍት› በመወርሩ ከረጅሙ የታሪክ ጉዟችን እንደ አገር የሚያስማማ ገዥ-ሐሳብ ለማግኘት አልታደልንም፡፡ የአንዱ ጀግና የሌላው ሒትለር የሚሆንበት አጋጣሚ በአንድና በሁለት ነገስታት ብቻ አይታይም፡፡ የመቻቻል ትርጓሜ እና የአንድነት ሐሳብ ላይ ያሉን ብያኔዎች በጠርዝ የተወጠሩ ናቸው፡፡ የታሪክ ወቀሳና ሮሮ ዛሬም እንደ አዲስ ሲነሳ መስማት የተለመደ ነው፡፡ በጥቅሉ የታሪክ ተከላካይነትና አጥቂነት ግብግቡ የሰሜን Vs ደቡብ ምዕራብና ምስራቅ ኢትዮጵያ መገለጫ ሆኗል፡፡
ተወደደም ተጠላም በሀገረ-መንግሥት ምስረታ ጊዜ አውንታዊና አሉታዊ ክስተቶች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ አዉንታዊው ክስተት አንድነት የፖለቲካል-ኢኮኖሚ የኃይል ምንጭ የመሆኑ ጉዳይ ሲሆን፣ አሉታዊው ክስተት ደግሞ በሀገረ- መንግስታት ምስረታው የሚደርሰው ሰዋዊና ቁሳዊ ውድመት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህን ሁነት ከ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት መመዘኛዎች ጋር ማነፃጸር የሚሹ ‹‹ዘመነኞች›› የዘመናዊት ኢትዮጵያን አፈጣጠር አብዝተው ሲኮንኑ ይሰማል፡፡ የነገሩ ምጸታዊነት፣ ምኒልክ ያቀናትን አገር እያስተዳደሩ /ለማስተዳደር እየቋመጡ አቅኝውን መኮነናቸው ነው፡፡ የአውሮፓውያኑን የሀገረ-መንግስት ግንባታ ጨምሮ በየትም ዓለም ኃይልን መሰረት ያደረገ የሀገረ-መንግስት ግንባታ እንግዳ ክስተት አይደለም፡፡ የታሪክን ክስተት በጊዜ ምጣኔ መረዳት የተሳናቸው ወገኖች ምኒልክ የምርጫ ኮሮጆ ይዞ በህዝብ ውሳኔ ‹ኑ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት እናጠናክር› ለምን አላለም አይነት ጥያቄ ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡
ከላይ የተጠቀሰውንና መሰል የታሪክ ውዝግቦችን ከፖለቲካዊና ኃይማኖታዊ (የኢትዮጵያን ታሪክ ኦርቶዶክሳዊ ተፈጥሮ ሳንዘነጋ) ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ በታሪክ ሜታፈርም (ታሪክ፡- ዳኛ፣ ወቃሽ፣ ተወቃሽ፣ መካሪ፣ አተላና ዕድፍ ያለው፣ የሚበቃው፣ የሚቆም…) መሆኑን በመተንተን ትውልዱን የሚያንጽና ትውልዱ በየአቅጣጫው ለሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ እገዛ የሚሰጥ የብሔራዊ ግንባታ አካል እንዲሆን ለማስቻል ታሪክ ለታሪክ ባለሙያዎች ነፃ ሊሆን ይገባል፡፡ ይሁንና አፄ ኢህአዴግ በመንግሥት ዩኒቨርስቲዎችና በምርምር ተቋማት ይህ እንዲሆን አንዳች ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ታሪክ ከፖለቲካ እስረኝነት ነጻ ልትወጣ አልቻለችም፡፡
በርግጥ የታሪክ እስረኝነት በንጉሱ ዘመን የነበረው ሰለሞናዊው ሥርወ – መንግሥት አፈታሪክ፣ በወታደራዊው መንግስት ለአስራ ሰባት አመታት የዘለቀው የሶሻሊዝም አስተምህሮትን የመደባለቅ ጉዳይ እንዲሁም የአፄ ኢህአዴግ የ100 ዓመት የታሪክ ትርክት (በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሊኒየም በዓል በደመቀ ሁኔታ የተከበረበትን አግባብ የታሪክ ንስሃ እንበለው?) የኢትዮጵያ ታሪክ ፈተና ትላንት የተፈጠረ እንዳልሆነ የሚነግረን እውነት አለ፡፡ ችግሩ አሁን ከፋ እንጂ፡፡ ኢህአዴግ አገር ‹‹መምራት›› ከጀመረ በኋላም ‹‹History 102›› የተሰኘው፣ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁሉ የሚማሩት የኢትዮጵያ ታሪክ ኮርስ መቅረቱና የዩኒቨርስቲዎች የቅበላ መጠን በ70/30 (የተፈጥሮ ሳይንስ 70% ማህበራዊ ሳይንስ 30%) የትምህርት መስክ አቀባበል ተግባራዊ መደረጉን በውል ስናጤን ኢህአዴግ ታሪክን ያሰረበት እግረ-ሙቅ ከቀደሙት አገዛዞች የተለየ ያደርገዋል፡፡
ፖለቲከኞቹ ለፖለቲካ ትርፍ ሲሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ያደረጉት ጫና ሕዝብ ከታሪክ የሚፈልገውን ጥቅም እንዲያገኝ አላስቻለውም፡፡ ይህን ክፍተት ለመድፈን ከታሪክ ሙያ ውጪ በሌላ ሙያ የተሰማሩ ዜጎች የሕዝባዊ ታሪክ ፀሐፊና መርማሪ በመሆን ወደ አደባባዩ ሲወጡ ማየትየተለመደ ነዉ፡፡ (አንዳንድ ጸሐፍት ለማንነታቸዉ ቅድምና እየሰጡ ታሪክ ቢበርዙም) በዚህ አግባብ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› የሚል መጽሃፍ ይዞ ብቅ ያለው በዕውቀቱ ሥዩም፣ ኢትዮጵያ የታሪክ ውዝግብ የወለደው ሕዝባዊ ታሪክ ጸሐፊና መርማሪ ሆኗል፡፡ ረዘም ያለ መግቢያ ለመጠቀም የተገደድኩት የኢትዮጵያ ታሪክ አተራረክና ትርጓሜ ቅርቃር ላይ ያለ ስለመሆኑ አዲስ ነገር ባልናገርም ጉዳዩን ማስታወስ ተገቢ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡
የበዕውቀቱ ሽግግር (?)
የኢትዮጵያ ታሪክ በተለየ መንገድ አብሰልሳይና ውርክብ የበዛበት ለመሆኑ በመግቢያዩ ላይ ለማመላከት ሞክሬአለሁ፡፡ በዕውቀቱ ሥዩም (ከዚህ በኋላ በ.ሥ) የኢትዮጵያ ታሪክ በእጅጉ ያብሰለሰለው ይመስላል፡፡ ‹‹ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ መጻፍ ማለት የበደለኝነት ስሜት ማሸከም ማለት ሆኗል›› (ገጽ 9) የሚለው አገላለጹ አስረጅ ምሳሌ ይሆናል፡፡ ወደ ታሪክ ምርምር እንዲገባ የገፋው፣ በትምህርት ያካበተውን ዕውቀትና ምሑራዊ ስብዕናውን በሚመጥን መልኩ ለበጎ ነገር ሳይጠቀምበት የሞት ጥላ እያረፈበት ያለው ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ ቲቪ ላይ ቀርቦ ‹‹ታሪካችን ይጫነናል›› የሚል ነሻጭ ቃል በመናገሩ ‹የታሪክ ሸክሜን ለማራገፍ ተነሳሁ› የሚለን በ.ሥ፣ የሙሉ ጊዜ ደራሲነቱ ዕድል ስጥቶት ራሱን ወደ ታሪክ ምርምር እንዳሻገረ ይዞት ከቀረበው ሥራ መረዳት ይቻላል፡፡ የታሪካችን ውዝግብ በፖለቲካ ትርጉም የተቃኘ በመሆኑ ‹ታሪክን ነፃ እናውጣ› የሚሉ ሕዝባዊ የታሪክ ጸሐፍትና መርማሪዎች እዚህም እዚያም ብቅ ማለታቸዉ ቀጣይነት ያለዉ ስለመሆኑ የበ.ሥ ሽግግር የሚነግረን እውነት አለ፡፡ በመስመር መሀል እንድ ጥያቄ እናንሳ ‹በ.ሥ በዚህ ሽግግሩ ጸንቶ ይቆያል ወይስ ያፈገፍጋል? ለፍልስፍና ልቡ ቅርብ የሆነች ገልማሳው ጸሐፊ ተጨማሪ ነሻጭ ቃል እስከሰማ/እስካነበበ ድረስ ሽግግሩን ወደፊት ማለቱ የሚቀር አይመስልም፡፡ መርማሪ ልቦናው ለግራ ቀኙ ቅንጭብ ጩኸት (Sound bites) እጅ የሰጠች እንደሆን ግን ሽግግሩ ወደ ማፈግፈግ (ወደ ቤሳ ልቦለድ) ይተካ ይሆናል፡፡ ለሁሉም በ.ሥ እና ጊዜ መልስ አላቸው፡፡ ለጊዜው የበ.ሥን ሽግግር እንኳን! ብለን እንቀበለው፡፡
የመጽሐፉ ይዘትና አቀራረብ
‹‹ከአሜን ባሻገር›› በጉዞ፣ ታሪክና ፖለቲካ ቀመስ መስመሮች እየተመላለስን የምናነባቸው አስራ ዘጠኝ መጣጥፎችን አካታለች፡፡ ደራሲው ለመጽሃፉ የሰጠውን አርዕስት ከመጣጥፎቹ ቆፍረን እናገኘዋለን እንጅ እንዲሁ በብላሽ እንካችሁ አይለንም፡፡ በ246 ገጽ ከተቀነበበው የደራሲው ስራ ውስጥ የውይይት አጀንዳ የፈጠሩትን አንኳር እንኳር መጣጥፎችን በደምሳሳው ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
የብሔራዊ ድል እጦታችን ከግራና ቀኝ በሚያላትም ማህበራዊ ሞገድ እንድንናጥ ምቹ መደላድል የፈጠረ ይመስለኛል፡፡ ቦሌ በተባለ የከበርቴዎች መንደር የምትመለከቱት ማህበራዊ ዝግጠት መልኩን ቀይሮ ሰራተኛ ሰፈር ላይም ታገኙታላችሁ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያስተዋላችሁት ምሁራዊ ቅሌት ባንድ ክልል የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ በሚያስተምር መምህር ላይ ፈልጋችሁ አታጡትም፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ ሚሊዮን ብሮችን በሚዘርፍ ባለ ስልጣን ቆሽታችን ሲቆስል ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ የመንግስት ካዝና ከመመዝበር ተሻግሮ የኩላሊት ነጋዴ የሆነ የመንግስት ሹመኛ ያጋጥመናል፡፡
ኢትዮጵያ ለቃላት አጠቃቀም በማይመች ማህበራዊ ቁልቁለት ላይ ነች፡፡ የቱን ችግራችን ጠቅሰን የቱን እንደምንተው እስኪጨንቀን ድረስ በችግር ታጥረን ያለን ዜጎች ሁነናል፡፡ በ.ሥ የህዝቡን በማህራዊ ሞገድ በምጥን ዓረፍተ ነገር አጠቃቀም ‹‹ደስታና ቀቢጸ ተስፋ›› በሚለው መጣጥፉ ገልጾታል፡፡ ውሃ ልማት በተሰኘው ሰፈሩ የታዘባቸው መልከዓ-የሥሪያ መድረኮችና ማህበራዊ ብልግናዎች የሰፈሩ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ከሞላ ጎደል የዛሬይቱ ኢትዮጵያ መልክ ነው (ገፅ 20) የሚለን በዕውቀቱ፣ የሰውን ልጅ በማነጽ ረገድ ተስተካካይ ሚና የሌላቸው መጽሐፍቶች የሚሸጡበት ቦታ በስጋዊ ደስታ መተካታቸው የነገዋን ኢትዮጵያን እንድንፈራት ያደርገናል፡፡ ከመንፈሳዊ (አዕምሯዊ) ፍላጎት በላይ ስጋዊ መሻት በደራባት ኢትዮጵያ ነገን ማሰብ ‹‹ከንቱ›› መሆኑን ‹‹የኔ ዘመን ጀግና›› (ገጽ 23) በሚል በትውልዱ አንደበት የሚናገረው በዕውቀቱ፣ ሐሳቡን በመስመር መሀል ተመላልሶ ለሚያነብ አንባቢ ዜጎች ይህን በመሰለ ስጋዊ መሻት (Obsession) ውስጥ የመነከራቸው ምስጢር ፖለቲካዊ ጭቆና ያመጣው ጣጣ መሆኑን (ገጽ 21) መረዳት ይቻላል፡፡ በበኩሌ ወደ አዕምሯዊ መሻት የሚገፋን ብሔራዊ ድል እንዲመጣ ተስፋ ከማድረግ ባሻገር አገዛዙን መገዝገዝ ብቸኛው የማህበራዊ ሞገድ ማምለጫ መንገድ ይመስለኛል፡፡
የበዕውቀቱ ጉዞ ቀመስ መጣጥፍ፣ ሎንደንና ሰሜን አሜሪካን ብቻ ሳይሆን የአገር ቤቶቹን ላስታ ላበሊበላንና አክሱምንም ያስቃኘናል፡፡ አመል ሆነና በዚህኛው መጣጥፍም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የጽዮን ብሔርተኞችን ማስቆጣቱ አልቀረም፡፡ ለአብነት፡- ‹‹የላሊበላን አዳራሾች ማየትና መዳሰስ በቀላሉ የማይበርድ ምርቃንና ያጎናጽፋል›› (ገፅ 26) (ምርቃንና ልብ ይሏል)፣ በዳግም የጣልያን ጦርነት ጊዜ ቀ.ኃ.ሥ ወደ ላሊበላ ለጸሎጽ መጓዙን የሚተርክልን በ.ሥ ‹‹የላሊበላ ውቃቤ ድል ባይሰጣቸወም፣ የስልታዊ ማፈግፈግ ጥበብ አልነፈጋቸውም›› (ገጽ 33 ) (ውቃቤን ልብ ያሏል) በቤተክርስቲያናት የሚሰቀሉ ስዕለ – ዐድኖዎችን(የቅድስና ቀለም) ያጠየቀበት አግባብ ልክ ቢሆንም፤ አሁንም ለአክራሪ ጽዮን ብሄርተኞች ቃሉ የሚጎረብጥ ይመስላል ‹‹ቤተ መድኃኒዓለም ውስጥ ጣቱን በሽጉጥ ቅርጽ የቀሰረ ሚል ጊብሰንን የመሰለ ባለሰማዊ ዓይን ፈረንጅ ኢየሱስ ሆኖ ቀርቧል›› (ገጽ 32) (ጣቱን በሽጉጥ ቅርጽ፣ ሚል ጊብሰንን የሚሉ ቃላትን ልብ ይሏል)፣ የላሊበላን ቅዱስ ሀገርነት በገለጸበት አግባብ እንዲህ የሚል አገላለጽ እናገኛለን ‹‹ቅምቀማና ቅድስና የሚጋጩ ሚመስላችሁ ካላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ የግዜር ምርጦች እነኖህ፣ እነሎጥ፣ እነሶሎሞን ይቀመቅሙ ነበር፡፡ እየሱስ በቃና ዘገሊላ ተገኝቶ የውሃ በርሚሉን ወደ ወይን በርሚልነት ቀይሮት ነበር›› (ገጽ 33) እያለ ይቀጥላል፡፡
በዕውቀቱ በአንድ ወቅት ‹‹…ኢትዮጵያ ውስጥ የግዜርና የብሔር ነገር ለወሬ አይመቹም›› ብሎ ነበር፡፡ እውነት ነው፡፡ እውነታውን ለመነጋገር በሚያስችል ማህበረ-ፖለቲካዊ መደላድል ላይ አለመሆናችንን ስናስብ የደራሲው ቃላት አጠቃቀም አቧራ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ከሰሞኑ እያየነው ያለው የግራ ቀኙ ድንፋታ መገለጫም ይሄው ነው፡፡ ከብጥስጣሽ ድንፋታዎች ባሻገር አምስት ኪሎ ግድም ካለው ህንፃ የሚመጣዉን የመልስ – ምትም ሆነ ሲ.ኤም.ሲ አካባቢ ባለ ደብተራ የሚለቀቀውን የነገር ክብሪት ለመታዘብ ደራሲው ዝግጁ መሆኑን የቀደመ ልምዱ የሚነግረን እውነት አለ፡፡ በበኩሌ ደራሲ የቃላት ወላጅ አባት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ አምጦ ለወለደቸው ቃላቶች አባትነቱን (ቃላት አጠቃቀሙን) አከብርለታለሁ፡፡ በነፃ ፈቃድ (free will) የማምን ሰው ነኝና፡፡ ችግሩ ያለው በዕውቀቱ ኢ-አማኝነቱን በተዳጋጋሚ ለገበያ ማቅረቡ ላይ ነው፡፡ በዚህኛው ስራውም የሦስተኛ ዓመት የሳይኮሎጅ ተማሪ እያለ “The future of an illusion” የተባለውን የሲግመንድ ፍሮይድን መጽሃፍ በማንበብ ከኃይማኖት ጋር ፍቺ መፈጸሙን ይናገራል (ገጽ 40)፡፡ ወደረኞቹ ይህችን ገጠመኝ ታከው የመልስ ምቱን እንዲሰጡት ‹የማርያም መንገድ› (የሲግመንድ መንገድ እንበለው?) ከፍቶላቸዋል፡፡ የአንባቢው የንባብ አረዳድ ችሎታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ መጽሃፍ የሰውን ልጅ አመለካከት የመቀየር አቅም ሊኖረው ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ኃይማኖትን ያህል መንፈሳዊ ርዕዮት በአንድ መጽሐፍ ፍቺ መፈጸም ‹ቀድሞውንም ቢሆን ኃይማኖቱን በጥሩ መደላድል ላይ አልያዘውም ነበር› ያስብላል፡፡
ከፊትና ከኋላ አገላብጨ ባስተውለው አልገባህ ያለኝ በዕውቀቱ ኢ-አማኝነቱን ለገበያ ያቀረበበት ሁኔታ ነው፡፡ (ምናልባት ጽሁፎቹን በኢ-አማኝነት ጠርዝ እንድንተረጉምለት ስለፈለገ ይሆን?) የሆነው ሆኖ አንደ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ተለዋጩ ደራሲ ለመጽሀፉ ከሰጠው ርዕሰ አኳያ አሻግሮ ማየት የግሉ ኃላፊነት ይመስለኛል፡፡
‹‹ከአሜን ባሻገር›› እዚህም እዚያም የምትረግጥ ዘመን አሳሽ፣ ወቃሽና ነቃሽ መድብል ብቻ ሳትሆን ብሔራዊ ጀግናም አወዳሽ ነች፡፡ እልፍ ሲል ደግሞ ሲቪል ጀግናም ታስታውሳለች፡፡ ‹‹የመጨረሻው ምሳ›› ላይ የሚተረክለት ሲቪል ጀግና በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ታሪክ የራሱ የሆነ አንድ ምዕራፍ ያለው ብርቱ የሙያ ነው፡፡ ‹ፍጡነ ልሳኑ ወ ጭቁን ሕዝቦች› ተመስገን ደሳለኝ፡፡ በዕውቀቱ እንዳለው፣ ተመስገን የሀሳብ ነጻነቱን ለማፈን ሌት ተቀን ከተጉት ገዥዎቻችን ባልተናነሰ ከአንዳንድ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች የሚሰነዘርበት የብዕር ዱላ ብዙዎቻችንን ያሳዘነ ተግባር ነበር፡፡
አሁን ሳስበው ምቀኝነት ቅርጹ እንጂ ይዘቱ እንድ ነው፡፡ ንግድ ላይ የምናስተውለው ምቀኝነት ቁመናውን ቀይሮ ሙያተኞች መካከልም ይንፀባረቃል፡፡ የሙያ ምቀኝነት ደግሞ አቅም የሌላቸው የትንሽ ሰዎች መንገድ ነው፡፡ በሰፊዋ እስር ቤት – ኢትዮጵያ ፤ ቆሻሻ ማስወገጃ ትቦ ውስጥ ከሚፈሰው ፍሳሽ ይልቅ በገዢዎች የአፈና ትቦ የሚያልፈው ዜጋ ይበልጣል፡፡ በመሀንዲሶቹ አልቦ – ዕውቀት አለያም ምዝበራ የተነሳ ፍሳሽ ቆሻሻው ከትቦው የሚያፈነግጥበት ዕድል ቢኖርም ዜጎች ግን ከመንግስታዊ የአፈና ትቦ አያመልጡም፡፡ የተመስገን ዕጣ ፈንታ ደግሞ ከዚህ የከፋ ነው፡፡
የበዕውቀቱ ሶስቱ ኤልሻዳዮች፡- ግዝት፣ ጠመንጃና ገንዘብ (ገፅ 89-96) ከትላንት እስከ ዛሬ የተጓዝንበትን የዘመን ከፍታና ዝቅታችን በውል የመግለፅ አቅም አላቸው፡፡ በዚህ መጣጥፍ የተጠቀሱ መሰረተ ሐሰቦች ፍልስፍናዊ እሳቤን ያካተቱ ናቸው፡፡ በተለይ የመፅሀፈ ብሉያት አንድምታ ትርጓሜን መነሻ አድርጎ ደራሲው በገባው መጠን የአንድምታ ትርጓሜውን ያስቀመጠበት መንገድ ለተጨማሪ ምርምር የሚጋብዝ ዕይታ ይመስለኛል፡፡ ቃየል በቅናት ወይም በከሸፈ ፍቅር ምኞት ምክንያት ወንጀል የፈፀሙ ወንዶች ምሳሌ ነው (ገጽ 90) ያለበት አግባብና ለሴት የሚደረገው ትግል ዝርያን ለማስቀጠል ከሚደረገው ተፈጥሯዊ ትግል ጋር ያቆራኘበት መንገድ ሰዋዊ ባህሪንና ፍላጎትን ለማወቅ የጥቁምታ ፍንጭ ይሰጣል፡፡
ደራሲው እንደስቀመጠው ግዝት፣ ጠመንጃና ገንዘብ በታሪካችን ውስጥ አምላክ አከል አቅም ነበራቸው፡፡ በተለይም ግዝት እንዲህ እንዳሁኑ መንግስታዊ ቅርጹ ሳይቀየርና የእምነት መሰረቶች ከመንሸራተታቸው በፊት፤ ነገስታቱ አልገዛ ብሎ ያስቸገራቸውን ወደረኛ የቤተክህነት መሪዎችን ተንተርሰው ያለምንም ጦር የሚማርኩበት ዘዴ ነበር፡፡
ሃምሳ ዓመታትን ያልተሻገረው የቅርቡ ትዝብታችን እንኳ የሜጫና ቱለማ ማህበር መሪ የነበረው፤ የብሔራዊ ጦር ዋና አዛዥ ብ/ጄነራል ታደሰ ብሩ ከማህበሩ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከንጉሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብቶ በሸፈተበት ጊዜ፤ ሊቀ ሥልጣናት አባ ሃብተማርያም በንጉሱ ተልከው ወልመራ ድረስ በመሔድ ጄነራሉን በመገዘት የመለሱበትን በኃላም በካህኑ በኩል ለጄነራሉ የተገባለት ቃል ተሸሮ የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበት “የግዝትና ግዞት” ፀሐፊ ኦለና ዞጋ ይተርክልናል፡፡ ይህ የታሪክ ክስተት የግዝትን ፖለቲካዊ መሳሪያነት አጉልቶ ያሳየናል፡፡ ግዝት ወደ ታሪክ ድርሳንነት ከተቀየረ በኋላ ጠመንጃና ገንዘብ ልዕለ – ኃያል ሆነው ወጥተዋል (ገፅ 92-9) ይህን አገላለፅ ከዘመኑ መንፈስ ጋር ስናዋድደው፡- የትላንት ተጋዳላዮች የጨበጡት ጠመንጃ ህንፃ መውለድ ጀምሯል፡፡ በሕይወት ካሉት የወያኔ ታጋዮች ውስጥ ፎቅ ያልሰራው ብቸኛው ታጋይ አህያ ይመስለኛል፡፡ ፎቅ ያልሰሩ ቢኖሩ እንኳ ለፎቅ መስሪያ የሚሆን መሬት በቅርምት ይዘዋል፡፡ ተስፋ የሚባለው አስማት ግዙፍ ሥጋቶችን የሚደመስስበት ጉልበት አለው (ገጽ 88) እንዲል በዕውቀቱ “ከአሜን ባሻገር” መጠየቅ ስንጀምር እንደ ግዝት ሁሉ ጠመንጃም ወደ ታሪክ ድርሳንነት የሚቀየርበት ጊዜ ይመጣል፡፡
በዕውቀቱ እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ
“ከአሜን ባሻገር” የበዕውቀቱን አደባባይ ያልወጣ “ማንነት” (“ማንነት” የሚለው ቃል መሬት ላይ ካለው ሀቅ አኳያ የሚፈጥረው አወዛጋቢ ትርጉም እንደተጠበቀ ሆኖ) ታስተዋውቀናለች፡፡ ደራሲዉ ያባቱን የትውልድ ሀረግ ከአጎቱ ጠይቆ እንደተረዳው በዕውቀቱ ሥዩም – በዳዳ – ደስታ – ወየሳ ነው (ገጽ 98) የአያት ቅድመ አያቶቹ መነሻ አምቦ በቀድሞው አጠራር ጅባትና ሜጫ (ገጽ 99) መሆኑን ከሐሰሳ-ማንነቱ እንደተረዳ ይነግረናል፡፡
አንዳርጋቸው ጽጌ ምሑራዊ አቅሙን ባሰየበት ‹‹ነጻነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ›› በሚለው መጽሃፉ ‹‹ከመንዝና ከምንጃር ዘሬን የምቆጥረውን ያህል፣ ከአድአ ኦሮሞዎችም መቁጠር እችላላሁ፡፡ …. አያቴ በትንሽነቴ እንዳልረሳ ያስተማሩኝን አስታውሳለሁ፡፡ ስማቸው ተሰማ ሮቢ፣ ይባላል የዘር ሀረጋቸው ይህን ይመስላል፡፡ ተሰማ – ሮቢ – ዶዩ – ቱፋ – ቡሌ – ቦሬ – ጉቶ ነው›› (አንዳርጋቸው xix) በማለት የዘር ሀረጉን ይዘረዝራል፡፡ እንዳርጋቸው እውነታውን ማረጋገጥ የሚፈልግ አድአ ወርዶ የአያቶቻቼን ቤተሰብ ማነጋገር ይችላል፡፡ ሲል በትህትና ይገልጻል ‹‹በኦሮሞ ጉዳይ አያገባህም የሚለኝ ስንቱ የኦሮሞ ድርጅት መሪ ይሆን እንደኔ ሰባት ቤቱን ሊቆጥር የሚችለው›› የሚለው፣ አንዳርጋቸውም ሆነ በዕውቀቱ የሚጋሩት የጋራ ስሜት ያለ ይመስለኛል፡፡ ለሁለቱም የአደባባይ ሰዎች፣ ከዘር ቆጠራ ነጻ የሆነው የማንነት መገለጫ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው፡፡ በዕውቀቱ ይህን ጉዳይ ለማድመቅ በሚመስል ሁኔታ ‹‹እንዲያው ልፉ ቢለን እንጅ፣ ዜግነታችን እንጅ ዘራችን ግልጽ አይደለም›› (ገጽ 112) ይለናል፡፡
አሁን በዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠመዝማዛ መንገድ ባያሌው የተፈተነ አንድ ሀቅ ትዝ አለኝ፡፡ ሚኒሶታን የሙጥኝ ብሎ የቀረው ባለቅኔው ሰለሞን ድሬሳ በአንድ ወቅት ይህን ሀይለቃል ተናግሮ ነበር ‹‹በሴት አያቶቻችን ጎጆ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የእኔን ጥሩ አሮሞነት እግዚአብሔርና የሴት አያቶቼ ብቻ ነው የሚያውቁት›› አዎን! ‹‹ከአሜን ባሻገር››ን ከማንበቡ በፊት የበዕውቀቱን ‹‹ንጹህ ጎጃሜነት›› የሚጠራጠር ነበርን? የአንዳርጋቸውን የኦሮሞ ዘር ሀረግ እስክናነብ ድረስ ይህ ነው ብሎ የገመተ ማን ነበር? … አሁን አንድ እውነት መቀበል ግድ ይለናል፡፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስተ የጸናው በነገስታቱ ጉልበት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ዘላን ተስፋፊነት (ወደ ሌላው አካባቢ በመሄድ የፈጠረው ስብጥር፣ ቅልቅል)ተከትሎ በተከታታይነት የታየዉ ማበራዊ ተራክቦ ኢትዮጲያ የተሸመነችበትን ድርና ማግ በማጠንከሩ ነዉ፡፡ የታሪክ ገመድ ጉተታ ተጫዋቾቹ ዛሬም ትግል ላይ ናቸው፡፡ የማንን ታሪክ ከማን እንደሚለዩ ግን በውል አልተረዱትም፡፡ በርግጥ በመስመር መሀል ሁለት ነገር ልብ እንላለን፣ የስልጣን ቁማር ላይ እንዳሉና የኪስ አብዮት በማፋፋም ላይ መሆናቸውን፡፡
በዕውቀቱ ከጀርባ ወደ ፊት!
በቋሚ ሽፍቶቹ የአፈና ተግባር የሰማዕትነት ዕጣ በደረሰባት ‹‹ፋክት› መጽሔት ግንቦት 2006 ዓ.ም (ፋክት ቁ.47) ‹‹ምኒልክና አርሲ›› በሚል ርዕስ፣ ‹‹ወርቁ ፈረደ›› የተባለ ጸሐፊ የአኖሌ ሀውልት ርዕዮት አለም አራማጆችን የማያፈናፍን መጣጥፍ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ከዚያ በኋላም በወጣ ገባ ጸሐፊነት መጽሔቷ እስከተዘጋችበት ጊዜ ድረስ እየተበረዙ ያሉ ታሪኮችን የኢትዮያ የታሪክ ምንጮችን (ዜና መዋዕል፣ የሊቃውንት ጸሑፍ፣ የህዝባዊ ታሪክ ጸሐፊዎችን መጽሀፍ) ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በተመለከተ በተለይም የደቡብ ምዕራብ ዘመቻዎችን በተመለከተ በውጭ አገር ጸሐፍቶች (ተጓዦች፣ ወዶገቦች፣ ሰባኪዎች፣ ቆንስሎች…) የጻፏቸውን መጽሀፍቶች በታሪክ ሚዛን ላይ እያስቀመጠ መተንተኑን ቀጠል፡፡ በወቅቱ የ‹‹ወርቁ ፈረደ›› ጽሑፎችን ለመሞገት የደፈረ አንድም የአኖሌ ሀውልት ርዕዮት አለም አራማጅ አልነበረም፡፡ ‹‹ፋክት›› መጽሔት የሰማዕትነት ዕጣዋን ከተቀበለች በኋላ ይህን መሰል ሐሳብ የሚሸራሸርበት ሚዲያ አላስተዋልኩም፡፡ የዛ ሞጋች ጽሁፎች ባለቤት፤ ውሃ ልማት በተባለ ሰፈር የሚኖር፤ ሽሮ፣ አትክልትና መጽሃፍትን አዘውትሮ የሚመገብ፣ የሠላሳ ስድስት አመት ጎልማሳ …. በዕውቀቱ ስዩም የሚባል ታዋቂ ደራሲና ገጣሚ ይሆናል ብሎ የገመተ አንድም ሰው አልነበርም፡፡ እውነታው ግን ይሄ ነው፡፡
‹‹ከአሜን ባሻገር›› ውስጥ የተካተቱ መጣጥፎችና የበዕውቀቱን የታሪክ ሰነድ አገላባጭነትና መርማሪነት ጮክ ባለ መልኩ የሚመሰክሩ ናቸዉ፡፡ ‹‹የጎበና ቀኝት››፣ ‹‹ስለ ገብረ እግዚአብሄር››፣ ‹‹ጁገልን ጥሰዉ የገቡ ሐሳቦች››፣ ‹‹ምኒልክና አርሲ››፣ ‹‹ሲደጋገሙ እውነት የሚመስሉ ውሸቶች›› እና ‹‹የንቀት ውሃ ሙላት ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› የሚሉት መጣጥፎች በዕውቁቱን ወደ ሕዝባዊ የታሪክ ጸሐፊነትና መርማሪነት አሻግረውታል፡፡
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በአጨቃጫቂነቱ የሚነሳውን የአፄ ምኒልክን የግዛት ማስፋፋት እና የአርሲዎችን የመከላከል ፍልሚያ ተከትሎ በአጥቂውም ሆነ በተከላካዩ ወገን ያለቀው በቁጥር እንደሚለቅ እሙን ነው (ገጽ 178) በዕውቀቱ በታሪክ ሚዛን ላይ ለመቆም ካደረጋቸው ጥረቶች ውስጥ አንደኛው ገላጭ ማሳይ ይህ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች በአርሲ ዘመቻ ወቅት የነበረውን የእጅ ቆረጣ (የፍትሐ-ነገስትን መሰረት ያስታውሷል) አልተፈጸመም ብለው በሚክዱበት ጊዜ፤ በዕውቀቱ ፈረንሳዊውን ሰባኪ ማርቴል ደ. ሳልቪያክን ዋቢ አድርጎ ራስ ወለድ ገብርኤል የአርሲዎችን አይበገሬነት ለመስበር ባንድ ቀን ብቻ ያራት መቶ አንጋፋዎችን ክንድ አስቆርጧል (ገጽ 178) ይለናል፡፡ በአንድ ወገን አውነት ብቻ የሰከነ አገር መገንባት አይችልም፡፡ ታሪክ ተደጋግሞና ተስተካክሎ መዳፍ እንዳለበት አምናለሁ፡፡
ይህ ሲባል ግን የታሪክ ምንጫችን ምንን መሰረት ያደረገ ነው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የማንነት ፓለቲካን በታከከ የታሪክ ትርጓሜችን ውስጥ ዜና መዋእልንና የሊቃውንትን ጽሁፎች ብቻ የታሪካችን ምንጮች አድርጎ መውሰድ ተገቢነቱ አይታየኝም፡፡ ኢትዮጵያን በተመለከተ የጻፉ የውጭ አገር ጎብኝዎች (ተጓዦች)፣ ወዶገብ ወታደሮች፣ ሰባኪዎች፣ ቆንስሎች ወ.ዘ.ተ ተጨማሪ የታሪካችን ምንጮች አድርጎ መቀበል የውዴታ ግዴታ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ላይ የቤተ መንግሥት እጅ ረዥም ነው›› የሚሉ ወገኖች ካለፈው ታሪክ ተነስተው የሰነድ ማስረጃ ቀርቶ የፎክለር ዘዉጎች ጥቁምታ በማይሰጡበት ሁኔታ ‹‹በአርሲ ዘመቻ የሴቶችም ጡት ተቆረጧል›› የሚሉ የፈጠራ ታሪኮች ኩነቱን ታከው ቀርበዋል፡፡ የዚህ መሰል ትርክት ዋነኛ አራጋቢው ፕ/ር አባስ ገነሞ ሲሆን፤ እርሱ በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ ጡት ቆረጣ መፈጸሙን የሚያሳይ አንድም የታሪክ ሰነድ ማቅረብ አልቻለም (ገጽ 188)፡፡
በስሜት በሚነድ የብሔር ፖለቲካችን ውስጥ ታሪክ ትልቅ ማገዶ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ጸሐፍቶች ኢትዮጵያን በተመለከተ የተጻፉ የታሪክ ድርሳናት በጥንቃቄ የሚመረምሩበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ የታሪክ ኩነቶችን ታከው የሚፈበረኩ ውልድ-ታሪኮች መቆሚያ የላቸውም፡፡ የታሪክ ቁረሾዎችን በመለጠጥ የፖለቲካ ጥቅም መሸመት የለመደው ኢህአዴግ፤ በአርሲና በሌሎች የደቡብ ምዕራብ ዘመቻዎች ላይ የደረሱ እልቂቶችን ባንድ ብሔር ጫንቃ ላይ ማሳረፍ ቀሎታል፡፡ ይህን የታዘበው በዕውቀቱ ‹‹ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ወሳኝ የነበሩ ሰዎች ከተለያየ ብሔረሰብ የተገኙ እንደ ሆኑ ሁሉ በማስገበር ዘመቻ የተሳተፈው ሰራዊትም እንዲሁ ሕብረብሔራዊ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይልቁንም ኦሮሞ ያልተሳተፈበት የምኒሊክ ዘመቻ ማግኘት ይከብዳል (ገጽ 184) በማለት ይሞግታል፡፡
የአኖሌም ሆነ የጨለንቆ ሀውልቶች የታሪክ ዕዳን ላንድ ብሔር ለማሸከም ታልመው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ‹‹ባባቴ ላይ የደረሰውን ግፍ አልረሳም የሚል ሰው አባቱ በሌሎች ላይ ያደረሰውን ግፍም አብሮ ለማስታወስ ወኔው ሊኖረው ይገባል›› (ገጽ 183) የሚለው ሀይለ ቃል፣ አርሲዎች ለክብር ሲሉ በየጊዜው በወጡበት ያሰቀሯቸውን የሌላ ብሔር ተወላጆችን ብቻ ሳይሆን የሚያስታውሰን፣ በመካከለኛው ዘመን የተካሄደው የኦሮሞ መስፋፋት ያስከተለውን እልቂትና ማንነታዊ ጭፍለቃ ለማስታወስ እንገደዳለን፡፡ እንግዲህ የኋላ ዘመን የታሪክ ግድፈቶችን እንቁጠር ከተባለ እዚህ ድረስ መምጣት ግድ ሊለን ነው፡፡ ለነዚህኞችስ ሀውልት አያስፈልግ ይሆን? ሌላም አይጠፋም፡፡ … በኢማም አህመድ ኢብራሂም (አህመድ ግራኝ) የጦር አዝማችነት ከምስራቅ እስከ ሰሜን ማዕከል ድረስ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ ስለደረሰው እልቂት ስለወደመው መንፈሳዊ እሴት፣ … አፄ ዮሐንስ 4ኛ ወሎ ቦሩ ሜዳ ላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ያደረሰዉን ጭፍጨፋና ኃይማኖታዊ ጭፍለቃ (በግድ ማጥመቅ) የሚያስተውሱ ሀውልቶች እንዲሰሩላቸው የሚጠይቁ የማህበረሰብ ክፍሎች ላለመፈጠራቸው ዋስታዉ ምንድር ነው? እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የቀደመውን ዘመን የታሪክ ግድፈት በአኖሌና በጨለንቆ ሀውልት ልክ ማየት ከጀመሩ የሀገሩቷ ህልውና አደጋ ላይ አይወድቅምን?! ይህን ለመካድ እንድ ተራ ካድሬ መሆን በቂ ነው፡፡ እንደ አንድ ለኢትዮጵያ ቀናኢ እንደሆነ ዜጋ ለሚያስብ ሰው ግን አደጋው ወለል ብሎ የሚታየው ይሆናል፡፡ የበዕውቀቱ የታሪክ ሙግት ነገን ከመፍራት የመነጨ ነው፡፡ የአብሮነታችን ጠንቆች በአርበኝነት ስሜት ሳይሆን በመርማሪ ልቦና ዳግሞ ሊፈተሹ ይገባል፡፡
በዕውቀቱ፣ ዛሬም በቴዎድሮስ ትክሻ ላይ!?
የዘመናዊት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መሀንዲስ የሆነው አፄ ቴዎድሮስ ብሩህ አዕምሮ የነበረውና ውርሶቹ ዘመን የተሻገሩ መሪ ነበር፡፡ አዳዲስ ሐሳቦችን ለመረዳት እና ጠቀሜታቸውን ለመገንዘብ የነበረውን አቅም አለማድነቅ ንፉግነት ነው፡፡ በተለይም ቴዎድሮስን በተለያዩ የህዝብ አስተዳደር ተግባራት፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ዙሪያ የማማከር ዕድል የገጠማቸው እንደ ፕላውዴን እና ጆን ቤለን የመሳሰሉ የውጭ ዜጎች ከቴዎድሮስ ጋር የፈጠሩት መቀራረብና ጅምር ለውጦች የቴዎድሮስ ንቃት ከፍ ያለ እንደነበር የታሪክ ግምገማ ማድረግ ይቻላል፡፡
በዕውቀቱ በብዙ መልኩ የቴዎድሮስ ነገር የማይዋጥለት ጸሐፊ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ይጽፋቸው በነበሩ መጣጥፎች፤ አፄ ቴዎድሮስን የሞራል አርዓያነት የሌለዉ ኋላ ቀርና ጨፍጫፊ መሪ አድረጎ ያቀርበው ነበር፡፡ የበዕውቀቱ ብዕር ቴዎድሮስ ላይ ስትደርስ ትዝላለች፡፡ የመረጣ ንባብ (selective reading) እየተከተለ እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ዳግማዊ ግራኝ›› ለማለት ይከጅለዋል፡፡ የታሪክ ምንጮቹ የዋድለው አስጋኋኝና መሰሎቹ ናቸው፡፡ ዕይታው በዘመን ልኬት የታጀበ ሳይሆን ለንጽጽር በማይመች መልኩ ቴዎድሮስን ከፍና ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የቀደመ መጣጥፎቹን የሚመለከት ነው፡፡ደራሲው ‹‹ከአሜን ባሸገር›› ላይ ቴዎድሮስን በስልታዊ መንገድ በብዕር ዱላው ሊወግጠው ሞክሯል፡፡ ‹‹ ገመና ገላጭ›› በሚለው መጣጥፉ ‹‹አምባገነን ጌቶች በዜጎቻቸው ልብ ውስጥ የሚጉላላውን ሐሳብ ካላወቁ እንቅልፍ አይወስዳቸውም›› (ገጽ 129) የሚለን በዕውቀቱ፣ አስራ ስድስት ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እህል እርዳታ በሚፈልግባት ሀገር፤ የዜጎቹን የዕለት ተዕለት ውሎ ለመሰለል በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ከሚያባክነው ኢህአዴግ ጋር በንጽጽር ያቀረበበትን አግባብ ስናነብ ጸሐፊዉ ቴዎድሮስ ትክሻ ላይ ምን እንደሚሰራ ለመጠየቅ ግድ ይለናል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በዕውቀቱ ስሙን ባልጠቀስልን ጸሐፊ የተጻፈና በቴዎድሮስ ዜና መዋእል ውስጥ የተገኘ ነው፡፡ በሚል አፄ ቴዎድሮስ የሚያምኑትን ዘበኛቸውን ይዘው አልባሌ መስለው ከጨለመ በኃላ በየሰፈሩ እየዞሩ የባላገሩን ጎጆ ይሰልላሉ፡፡ በአንድ ጎጆ ውስጥ ባልና ሚስት በግብረ ስጋ ሲጣሉ ይሰማሉ፡፡ ባል በልመናው መሀል ‹በይ በቴዎድሮስ ሞት እንድትሰጪኝ› ሲላት በርሱ የመጣማ ብላ ሰጠችው፡፡ ይህን ሁሉ የጎጆ ውይይትና ቅድመ-ስሪያ ድርድር የሰማው ቴዎድሮስ በማግስቱ ባልና ሚስቱን አስጠርቶ የሆነውን ሁሉ እንደጠየቀ፤ ባል እውነቱን ለንጉሱ ሲያስረዳ ንጉሱ መሳቁን ሴቲቱም ማፈሯን ሰረዝ እየጨመረ ይተርክልናል፡፡ (ገጽ 130) ይህ ትረካ ሐቅ ይሁን ልቦለድ ማረጋገጥ አልቻልኩም (ገጽ 131) የሚለን በዕውቀቱ፣ ተረኩን ከኢትዮጵያ የጸረ – ሽብር አዋጅ ጋር ለማስተሳሰር ይሞክራል፡፡
እንደሚታወቀዉ የኢትዮጵያ የጸረ – ሽብር አዋጅ ከወጣ በኋላ ወትሮውንም እኛነታችን የራሳችን ሆኖ በማያውቅባት አገር ‹‹የጸረ ሽብር ግብረ – ኃይል ቡድን›› ለሚባል የምድር እግዜር ሁለመናችንን የመበርበር ሙሉ “ሥልጣን” ሕግን ተሞርክዞ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ የጸረ ሽብር ግብረ ኃይል ስልክ፣ ፋክስ፣ ኢ-ሜል፣ ፖስታና የመሳሰሉ የግንኙነት መረቦችን ባሻው ሰዓት መጥለፍ ይችላል፡፡ ለሥልጣን በሚያሰጉ ዜጎች መኖሪያ ቤትና የስራ ቦታ አካባቢ ስውር የደህንነት ካሜራዎችን በመትከል እንዳሻው የመሰለል ‹‹ሕጋዊ ሥልጣን›› አለው፡፡ ይህን ተከትሎ እስክንደር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል (አበበ ቀስቶ)፣ ሀብታሙ አያሌው፣ አብርሃ ደስታ፣….ለቁጥር የሚታክቱ የአደባባይ ሰዎች የጠሉትን መምቻ ሆኖ የሚያገለግለው የጸረ ሽብር አዋጅ እየተጠቀሰ ወደ ወህኒ ተግዘዋል፡፡
በዕውቀቱ ሁለት በንጽጽር መልክ ሊቀርቡ የማይገባቸውን ነገሮች አቅርቦ፣ የኢህአዴግ ሁለገብ የአፈና ተግባር ትንቢቱ ከቴዎድሮስ እንደጀመረ ሊያሳምነን ይሞክራል፡፡ ይህን መጣጥፍ ሳነብ ትዝ ያለኝ ነገር ቢኖር፣ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ደቂቃ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ያደረገበትን አጋጣሚ፣ ከደርግ አሰቃቂ የቀይ ሽብር መንግስታዊ ፍጂት ጋር ለማዛመድ ጥረት የሚያደርጉ ምሁራን ማብራሪያ ነው፡፡ በሁለቱ አገዛዞች መካከል ያለውን የዘመን ክፍተትና የማህበረሰብ እድገት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ንቃት አስተውሉ፡፡ የደርግ መንግሥታዊ ፍጅት የመነጨው የበታችነት ስሜቱን በወታደራዊ የበላይነት ለማሳየት በሄደበት የጭካኔ ተግባር የተነሳ እንጂ ከአፄ ዘርዓ ያዕቆብ የፍርድ አፈጻጸም ሥነ-ልቦና ተጋርቶ አይመስለኝም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዕዉቀቱ ልቦለድ ይሁን ሐቅ ምነቱን በውል ባልለየው ታሪክ ውስጥ፤ የአፄ ቴዎድሮስ ሁነት ከአፄ ኢህአዴግ የጸረ ሽብር አዋጅ ጋር በትይዩ የሚቀርብ የማንጸሪያ ምሳሌ ሊሆን አይችልም፡፡
ነገሩ ያለው ወዲህ ነው፡፡ የበዕውቀቱ ብዕር ለአፄ ቴዎድሮስ አትተኛም፡፡ ‹‹አባቶቻችን የፈጸሙት ጥፋት የኖሩበትን ዘመን መሰረት ያደረገ በመሆኑ መታየት ያለበት በዛ መልኩ ነው›› የሚል ጸሐፊ ቴዎድሮስ ላይ ይህን መሰል ምስባክ አይጠቀምም፡፡ የዋህ ልሁንና፡- አፄ ቴዎድሮስ ከመቃብር ተነስቶ የበዕውቀቱን መጣጥፎች በሙሉ ቢያነብ፣ ሰይፉን ከሰገባው የሚያወጣበት አይመስለኝም (ለምን?) የቴዎድሮስ ራዕይ የግዛት አንድነቱ የተጠናከረ ማዕከላዊ መንግስት መመስረት ብሎም ዘመናዊነትን መላበስ በመሆኑ፤ በመጀመሪያ በወደረኛው አፄ ዮሐንስ 4ኛ ድንበር ጠባቂነትና ተከላካይነት ለጥቆ ደግሞ በልጅነቱ በምርኮ ይዞት በነበረው አፄ ምኒልክ እልህ አስጨራሽ ትግል ዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ እውን መሆኑን ስለሚመለከት በሰይፉ ፋንታ በአለቃ ዘነበ የግዕዝ አንደበት ይህን የሚለው ይመስለኛል ‹‹ለዘኒ፡ ተንሣእኩ፡ ራዕይ፡ ዘአፈጸሞ፡ ደቂቀ፡ ራእይየ፡ እንዘ፡ ትሴብሐ፡ ወለምንት፡ ትኳንነኒ ፡ሊተ?›› (ተዛማጅ ትርጉም፡- የተነሳሁለትን ዓላማ ያስፈጸመውን የራዕይ ልጄን እያወደስክ ስለምን እኔን አባቱን ትኮንናለህ?) የበዕውቀቱ መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል ባላውቅም፣ አፄ ቴዎድሮስ አሁንም በአለቃ ዘነበ የግዕዝ አንደበት ‹‹ባሕቱ፡ ጸገውከኒ፡ በወልድየ›› (በልጄ ግን ካስከኝ) በዕውቀቱ የምኒልክን አገር የማቅናት ዘመቻ የቴዎድሮስ ራዕይ ቅጥያ መሆኑን ሊነግረን ባይፈቅድም ዘመቻው የዘመኑ መንፈስ መሆኑን ነግሮናል ቴዎድሮስ ምስጋና የሚነፍገው አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ ቴዎድሮስ ግዕዝ መናገርም ማጻፍም ይችል ነበር፡፡ በአለቃ ዘነበ የግዕዝ እንደበት ያልኩት ሰውየው ሸርዳጅ ቅኔ አዋቂና አስተዋይ ልቦና ያለው በመሆኑ ለምን ይቅርበት ብየ ነው፡፡
የበዕውቀቱ ትጋት!
‹‹ከአሜን ባሻገር›› የአንድ በጋ ትጋት አይደለም፡፡ ይልቁንስ በዓመታት የንባብ ብህትውና የተወለደ እምቅ ሐሳቦች ያሉበት እንጂ፡፡ ትላንትን ያልካደ፡፡ ነገን ዛሬ ላይ እንስራ በሚል የዘመን መለከት የሚነፋ የትውልድ ማንቂያ ደወል፡፡ መንደርተኞችን መካሪ፡፡ ብሔራዊ ጀግና ቆፋሪ፡፡ የግለሰብ ጥረት፡፡ የሀገር ወረት … ‹‹ከአሜን ባሻገር››፡፡
በዕውቀቱ ይህን መጽሐፍ ሲያዘጋጅ አማርኛ ቋንቋን ሳይጨምር በአራት ቋንቋዎች (ግዕዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣሊያንኛን ፈረንሳይኛ) የተጻፉ ልዩ ልዩ የታሪክ ድረሳናትን አገላብጦ እንዳነበበ ብሎም እንደመረመረ የግርጌ ማስታወሻዎች አብይ ማስረጃ ናቸው፡፡ የመንደር ሃሜት የወግ መጽሐፍ፣ የቀበሌ አሉባልታ የፖለቲካ መጽሃፍ፣ ዱላ ቀረሽ የቃላት ውርጅብኝ የታሪክ መጽሃፍ፣ የመሸታ ቤት ልፊያና ስሪያ የፍቅር ጥበብ (ሥነ-ልቦና?) መጽሐፍ … በሚል ወደ አንባቢ የሚደርሱ መጽሃፍቶች በበዙበት በዚህ ዘመን እንዲህ አጀንዳ አስቀማጭ የሆነ ኮርኮሪና አወያይ የሆነ መጽሃፍ ለህትመት ብርሃን ማብቃት ምን ያህል ጥረት እንደሚጠይቅ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡
አንድ ሰው መጽሐፍ ለመፃፍ ሲነሳ በትንሹ አራት ነገሮች እንዳሉት እርግጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ ፍላጎት፤ ተገቢነት፤ አቅምና በቂ ዝግጅት፡፡ በዕውቀቱ አራቱንም ነገሮች በሚገባ ያሟላ ፀሐፊ ለመሆኑ የቀደመ ስሙ ሳይጫነን “ከአሜን ባሻገር” ውስጥ የተካተቱ መጣጥፎች ጮክ ብለው ይነግሩናል፡፡ መጽሐፉ ወደ አንባቢ እጅ በመድረሱ ምስጋናው ለበዕውቀቱ ብቻ ሳይሆን የምርምር ስራዎቹን ሲሰራ ቤተ-መጽሃፍታቸውን ለፈቀዱለት ምሁራን ጭምር ሊሆን ይገባል፡፡
የበዕውቀቱ ዳገት!
በዕውቀቱ የብሔርተኝነት መናፍቅ ነው፡፡ መናፍቅነቱ ያስቆጣቸው የብሔርተኝነት ምእመናን ከያቅጣጫው የነገር ሰይፋቸውን መዘውበታል፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ላይ የተካተቱ አምቅ ሐሳቦች ከግራ ቀኙ ጽንፍ መጠኑ ተገማች ያልሆነ የጩኸት አቧራ ማስነሳታቸው አይቀሬ መሆኑን የተረዳዉ በዕውቀቱ ‹‹በዚች መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች የማንም ቡድንና ሕዝብ ወክየ አልጻፍኳቸውም፡፡ በሐሳቤ ምክንያት የሚመጣውን መዓት ለብቻየ ራሴን ችየ ልጋፈጠው ዝግጁ ነኝ›› (ገጽ 10) በማለት ተጠባቂውን ጩኸት ለመመከት የሚያስችል የሥነ- ልቦና ዝግጅት እንዳደረገ በመስመር መሀል ነግሮናል፡፡
አርፋጅ ብሄርተኞም ሆኑ ሰንባቾቹ ኢኮኖሚያዊ ህልውናቸውን የተመሰረተው‹‹አንሞትለታለን›› በሚሉት ‹‹ብሔር ብሔረሰብ›› ላይ ነውና የብር ማተሚያ ማሽናቸውን የሚፈታተን አንዳች ቴክኒካዊ ችግር አይታገሱም፡፡ በመጽሃፉ ውስጥ ከተካተቱ ታሪክ ነክ መጣጥፎች ውስጥ ‹‹ባልተገባ መልኩ›› ትርጓሜ የተሰጠው የታሪክ ክስተት ቢኖር እንኳ በሰከነ መንፈስ መወያየት እየተቻለ ብዙዎች የብሔርተኝነት ምእመናን በማህበራዊ ድረ-ገፆች መናፍቁ-በዕውቀቱ ላይ የስድብና የዘለፋ ውርጅብኞችን በማዝነብ ላይ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ወያኔ የሃሳብ ነጻነትን ለማፈን ከተጓዘበት ርቀት በላይ የግራ ቀኙ ጽንፍ የሄደበት መንገድ ሩቅ መስሎ ይሰማኛል፡፡ አርፋጆቹም ሆነ ሰንባች ብሄረተኞች በዕውቀቱን ለማጥቃት በታክቲክ ተዛምደው ሳይ ስሜት ይሉት ወረርሽኝ ከኒዩክለር ቦንብ በላይ ሀገሬን እንደሚበታትናት አስተዋልሁ፡፡
ሐሳብን በሐሳብ መመካት የተሳናቸው ብሔርተኞች “መጽሃፉን በፒ.ዲ.ኤፍ አዘጋጅተን በማህበራዊ ድረ-ገፆች እንለቀዋለን” በማለት ሲዝቱ ተስተውሏል፡፡ በዕውቀቱን ከገበያ ማውረድ ይቻል ይሆናል፡፡ የማይቻለው ግን ከትውልድ አብሪ ኮከብነቱ ማውረድ ላይ ነው፡፡ አባቶቻችን የሕይወት ሰማዕትነት ለከፈሉላት ኢትዮጵያ፤ የበዕውቀቱ የኪስ ሰማዕትነት (ለዛውም ከተሳካላቸው ነው) የዘመኑን ልክነት የተሻገረ ትልቅ ገድል ነው፡፡ የሽግግር ወቅት ፈተና ይበዛበታል፡፡ በዕውቀቱ በሽግግሩ የሚጸና ከሆነ በነገዋ ኢትዮጵያ “ታላቁ የሕዝባዊ ታሪክ ጸሐፊና መርማሪ በዕውቀቱ ሥዩም” በሚል ስሙ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ለጊዜው አንድ ነገር ለመመስከር ግድ ይለኛል፡፡ በዕውቀቱ የኢትዮጵያ የታሪክ ውዝግብ የወለደው የሕዝባዊ ታሪክ ጸሐፊና መርማሪ መሆኑን፡፡
ማሳረጊያ
የትላንቷ ኢትዮጵያ ጦርነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ሊለዋወጥ የሚችል የግዛት ወሰን ነበራት፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሊጠናከሩ እና ሊዳከሙ የሚችሉ የነገድ ነገስታትም ነበሯት፡፡ የመሳፍንት እና የባላበት አስተዳደር ለብዙ ዓመታት ሰፍኖ በኖረበት ዘመን ፤ በሺዎች ለሚቆጠሩ አመታት በቋሚነት ሳይቀያየር የኖረ የግዛት ወሰን እና የህዝብ አሰፋፈር የሚጠብቅ ካለ እርሱ ለኢትዮጵያ ታሪክ እንግዳ ነው፡፡
አባቶቻችን ለግዛት ወሰን ስፋት ቀናኢ ነበሩና ወታደራዊ የበላይነት ማሳየት የቻሉባቸውን ወደረኞቻቸውን በማስገበር ዘመናዊት ኢትዮጵያን መመስረት ችለዋል፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ስንል የትላንቷ ኢትዮጵያ ቅጥያ እንጂ ከጠፈር የመጣች እያልን አይደለም፡፡ ከቀደም ጀምሮ ሲጠብና ሲሰፋ የኖረውን ግዛት በጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት የበላይነት ለመቆጣጠር ሲባል የተፈጠረው የታሪክ ክስተት መታየት ያለበት ከዘመኑ መንፈስ ጋር ነው፡፡ ችግሩ ያለው የማንነት ፖለቲካን የታከከ የታሪክ ትርጓሜ መስጠት መጀመሩ ብቻ ሳይሆን በታሪካችን ነባሩን ከአዲሱ ጋር የሚያቻችል የርዕዮት ዓለም ሽግግር ካለመኖሩም ጋር በተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በታሪካችን ውስጥ ክብረነገሥትን የመሳሰሉት ትረካዎች ቦታና እርሱን ለመጣል ሲወስን ይህ ነው የሚባል ተተኪ የታሪክ ፓራዲየም ባለመዘጋጀቱ ብዙ ነገሮች ለባዶነት ተጋልጠዋል፡፡ ለሁሉም ነገር፣ በቤተ-መጽሐፍቶቻቸው ውስጥ አንገታቸውን ደፍተው የሚያነቡ የታሪክ ፕሮፌሽናሎች በዩኒቨርሲቲ መ/ራን ማህበር መጽሄቶች ላይ ስለ ታሪክ ጽንሰ ሐሳብ ማብራሪያ ከመስጠት ባሻገር የህዝባዊ ታሪክ ሙያ መገንባት ሌላ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደ በዕውቀቱ ያሉ ፀሐፊዎችን መደገፍ የሙያ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታም ነው፡፡ (በተለይ ለጎልጉል የተላከ)
ሙሉአለም ገ.መድህን
Alem wec says
I appreciate your detail comment, but why did you say about 5 killo (mahibere kidusan ) and CMC debetera ( D . Daniel kibret), they have the right to oppose the literature of Beweketu sieyoum, for his discuss things word about the church ( lalibela & other). who oblige you to wright this detail comment?? who did not permitted to wright this article?? is their any body right to protest you? no??? why you say this kind of worst word??? Sorry Yihe erasu hasaben yemegeletsena yemekawem mebeten yigafal be ante lay sihon ayeseram??? Mulu sew atan bizu Tiru tisefalachihu tiru gen atinagerum weyem atasebum……ahunem tige lemeyaz timokeraleh….Lemesale ke ante hasaboch yemalesemamachew alu gen Beka yihe yesu hasab new beye tewekut lemen tsafk endet endi tilaleh biye be Kifu linagereh ayigebam kechalku hasabeken behasab memoget kalchalku weyem kalfeleku metew, gena legena yehonu gileseboch weyem mahiber yitsefal weyem yikawemal belo neger neger malet yasazenegnal.
Dagnachew Fisseha says
Instrumental !!!
I take my hat off to you sir.
” I like the truth & the people who said it ”
Best regards,
DF
Mulualem Asegidew says
በመጀመሪያ እኔ የታሪክ አዋቂ አይደለሁም ነገር ግን በዚህ ፅሁፍ ላይ ካነበብከኳቸው ሀሳቦች ውስጥ ባጠቃላይ ለማለት በሚያስችለኝ ደረጃ ይስማሙኛል በተለይ በተለይ ያለፍት አባቶቻችን የሰሩት መጥፎም ሆነ ጥሩ ስራ መመዘን ያለበት በጊዜው በነበረው ርዕዮተአለም አና የአስተዳደር ሰርአት መነፅር መሆን አለበት የሚለው ነገር በጣም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡በተጨማሪም የተፃፍም ሆኑ በአፈታሪክ የሚተላለፍ ታሪኮች ሁሉ እውነት ናቸው ብሎ መቀበል ትክክል አይመስለኝም በአጠቃላይ “ከአሜን ባሻገር” የሚለው ርዕስ በራሱ የሰማነውን ወይም ያነበብነዉን አሜን ብሎ ከመቀበል ባሻገር ማለት በመሆኑ ከላይ ለመግለፅየሞከርኩትን በሙሉ በአንድ ሀረግ ይገልፀዋል፡፡