
በክፉ ያነሳ ወርቃማውን ስምሽን፣
በሃሜት ያጎደፈ ፀዐዳ ክብርሽን፣
በክፋት ፈረሱ ወዳንቺ የጋለበ፣
በእሾኸም ምላሱ ሊወጋሽ ያሰበ፤
ሰላምሽን የነሳ፣ ባንቺ ላይ ሊሳለቅ፣ ሊቀልድ የቃጣ
መልካም ህይወት ትክዳው! ነፍሱ ሰላም ትጣ!!
ብርሃንሽን ሊያጠፋ ውበትሽን ሊያከስም፣
መዐዛሽን ሊበክል ህይወትሽን ሊያጨልም፣
በክፋት ያቀደ በሻገተ ህሊናው፣
ብርሃኑ ይደፈን ! ጨለማ ይውረሰው!
ስትለመልሚ ስትፈኪ አይቶ፣
በአርኪ ፈገግታሽ በቅናት ተውጦ፣
የቆሸሸ እጁን ባንቺ የዘረጋ፣
ሽባ ይሁን ይስለል! አንደበቱ ይዘጋ!
የዘመናት ስምሽን ዝናሽን ሊያጎድፍ፣
ከባዕድ አብሮ ወዲያ ሲያነፈንፍ፣
ህይወቱን በሙሉ ሳይሰራ ቁም-ነገር፣
ገብቶ ሲሽሎኮሎክ ከጢሻ ከቆንጥር…፤
ሊነክስ ያደባ የጠባውን ጡትሽን፣
ሊያጠፋ የቃጣ ሃቀኛውን ልጅሽን፣
የታሪክ መጠሪያ ቅርሳ-ቅርስ ውበትሽን፣
ሕዝብሽ ያፈራውን ጥሪት ንብረትሽን…፣
ሊያወድም ያለመ ስድ-አደግ መደዴ፣
እልም ብሎ ይውደም! ለሁሌም ለአንዴ!
የጫረው ፍም-እሳት እሱኑ ያንድደው!
ለብልቦ አቃጥሎ ጨርሶ ያንጨርጭረው!
ባንቺ ያሰበው ሁሉ በሱ ላይ ይርከፍከፍ!
የዶጋ-ዐመድ ይሁን! ምናምኑ አይትረፍ!
በአቋም ጥንካሬሽ ሆዱ እየዋለለ፣
ሰናየ-ተፈጥሮሽ ልቡን ነክቶት ሳለ፣
ከአድናቆት ይልቅ ለንቀት ያደላ፣
በሬት የመሰለ የማርሽን ወለላ፣
በምድር አይመቸው! ሆኖ ይቅር ከንቱ!
ከሞቱም ባሻገር ሲዖል ትሁን ቤቱ!
ይፈለጥ! ይቆረጥ! ይቃጠል በስብሶ!
ትቢያ ብናኝ ይሁን! ይረገም ጨርሶ!
ቃለ፡ሕይወት፡ያሰማልን።