የጎልጉል ርዕሰ አንቀጽ
በቅድሚያ ለጎልጉል ወዳጆችና አንባቢያን እንዲሁም ጠላቶች ለመጥፋታችን በርካታ አጥጋቢ ምክያቶች ቢኖሩንም በቅድሚያ ይቅርታ ለመጠየቅ እንወዳለን። መረጃ ከእኛ ለማግኘት ፈልጋችሁ ለበርካታ ወራት ሳታገኙ በመቅረታችሁ እናዝናለን። “የት ጠፋችሁ?” በማለት በተደጋጋሚ ስትጠይቁን ለነበራችሁ ቅኖች ምስጋናችን የላቀ ነው። የእናንተን መሰሉ ቅንነት ወደፊትም በብርታት እንድንቀጥል የሚያደርገን ነውና መልካምነታችሁ ወደፊትም አይለየን። በመጥፋታችን ደስ ብሏችሁ የነበረ የበለጠ ደስ ይበላችሁ እንደወጣን አልቀረንም፤ መጥተናል።
አገራችን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለከተው በርካታ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ሲደረጉ ብንመለከትም ያንን የሚያፈርስ እኩይ ተግባር ሲፈጸምም እናያለን። የተደፈውን ቀዳዳ መልሰው የሚቆፍሩ ክፉዎች የመኖራቸውን ያህል ላገራቸው ምንም ጩኸት ሳያሰሙ ተግተው የሚሠሩም እንዳሉ ይታወቃል። ቀን አልፎ ሌላ ቀን በተተካ ቁጥር “ዛሬስ ምን ክፉ ነገር ልናገር?” የሚል የተበላሸ አእምሮ ያላቸው በተለይ በሚዲያው ዘርፍ ያሉትን ያህል “ዛሬስ ስለአገሬ ምን ጥሩ ልሥራ?” ብለው በቀኝ ጎናቸው የሚነሱ ጥቂቶች አይደሉም። አፋቸውን በከፈቱ ቁጥር ክፋት ከመትፋት የማይቆጠቡ የመኖራቸውን ያህል ቢጽፉ፣ ቢናገሩም፣ ቢተቹም፣ መነሻቸው ቅንነት የሆኑ እጅግ ብዙዎች አሉ።
አገራችን ባሁኑ ጊዜ የምትፈልገው ህጸጿን እየነገረ ነጋ ጠባ የሚነዘንዛተን አይደለም። የሚታወቅ፣ የተመዘገበ፣ ታሪከም ሕዝብም የሚረዳው ዘርፈብዙ ችግሮች አሉባት። የአገራችን የወቅቱ ፍላጎት መሪዎችን ያለገደብ ቀንተሌት በመተቸት ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥልባትን አይደለም።
በተለይ በሚዲያው መስክ የምንገኝ የአገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጣም ሊያሳስበን ይገባል። እኛ የምናገረው፣ የምንጽፈው፣ የምንተነትነው፣ ወዘተ የሰውን አስተሳሰብ ይነካል። ውጤቱም ለበጎ ወይም ለመጥፎ ይሆናል። ከድርጊት በፊት ሃሳብ ይቀድማል። በተደጋጋሚ ሲሰማ የቆየ ሃሳብ እውነት እየመሰለ መጥቶ ወደ ተግባር ይቀየራል፤ ይህም በቅጡ ካልተገራ አገር የሚያፈርስ ይሆናል። አገር ከፈረሰች በኋላ “ወይ አገሬ” ብሎ ማልቀሻ ቦታም አይኖርም።
በተለይ በአመራር ላይ ያለውን ኃይል ለማጥላላት በተያዘ አባዜ እና በዚያም በተከተለው ጭፍንነት ህወሓትን እስከመደገፍ እነ መለስን እስከማሞገስ የሚደርስ የሚዲያ ልፈፋ ዐቢይን ሳይሆን የሚጎዳው አገርን ሲቀጥልም ራስንና ቤተሰብን ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘመን ፍዳ ወህወሓት ፈጽሞ ያልታየና አገራችንን እንደ ወረርሽኝ እያጠቁ ያሉት ሁለት ነገሮች ናቸው፤ የሃሰት ወሬ እና ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ነው፤ የዚህ ፈብራኪ ማን እንደሆነም በውል ይታወቃል። ዓቅም ኖሮን ሁለቱንም በማስቆም አገራችንን ብንታደግ ደስ ባለን ነበር። ነገርግን አንድ ነገር ማድረግ እንችላለን ብለን እናምናለን፤ ለሕዝባችን በምንችለው ሁሉ ተዓማኒነት ያላቸውን መረጃ በማድረስ አገራችንን ከመጣባት መዓት ለመታደግ ውሳኔያችን በማድረግ ወደሥራ ተመልሰናል።
ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።
gizachew abebe says
ለመሆኑ አንድ የአገር መሪ ስልጣን በቃኝ፣ አገር መምራት አልቻልኩም የሚለው መቼ ነው!? አገርና ሕዝብስ ምን ሲሆኑ ነው!? የዐብይ አሕመድን ድክመት ማጋለጥ ለውጥን መቃዎም አይደለም… ለውጡን ሕያው ለማድረግ መስራ እንጅ!
bezuneh tessema says
glad you back
Getachew Abera says
እንኳን በሰላም ተመለሳችሁ!!
ጊዜው : ከማንኛውም ጊዜ በላይ እንደናንተ አይነት ቅን አሳቢ: ለሀገር ህልውና እና ለህዝብ ሰላምና ልዕልና የሚጨነቅና የሚተጋ ዜጋ : ሃቀኛ: ቁምነገር ያዘለና መልካም አቅጣጫን የሚመራ ሃሳቦችን የሚያካፍል በእጅጉ የሚፈለግበት ነው::
መልካም ሃሳባችሁና ዓላማችሁ ለሀገራችን የሚፈለገውን መልካም ግብ ይመታ ዘንድ ልባዊ ምኞቴን እየገለፅኩ: በርቱ! በያለንበት እንበርታ እላለሁ!
አክባሪ ወንድማችሁ ጌታቸው አበራ
ሳምሶን says
ጎልጉልን ማንበብ በመረጃ ጠቅሞኛል።