
አባት ያቆየዉን ልጅ እዲጠብቀዉ የተከበሩ ኮ/ል አስናቀ እንግዳ፤ ኢትዮጵያን ለሚረከበዉ ወጣት ትዉልድ አዘዉትረዉ እንዲህ ይሉ ነበር። “አንተ የዛሬ ትዉልድ ሆይ! አንድ ጊዜ ቆም ብለህ አዳምጠኝ። ከተቻለ አባቶችህ ከሠሩት ላቅ ያለ፤ በስተቀር የእነሱን ያህል ካልሠራህ ሐገር አይኖርህም። የእኔ ትዉልድ በስልጣኔ ኋላ ቀር ቢሆንም፤አባቶቹ ከሠሩት በላይ አከናዉኖ አደራዉን ተወጥቶ፤ሀገሪቱን አስረክቦሃል።አንተም ለልጆችህ ይህችን ጥንታዊ ሐገር በክብር ለማስረከብ እንድትችል፤ ወኔ ይኑርህ። ወኔ እንዲኖርህ ለሆድህ አትገዛ። ኩራት ራት ነዉ ብለህ፤ ለራስህ ኀሊና ተገዛ ” ይሉ ነበር።
እንግዲህ ይህን የመሰለ ቁምነገር ሲያስተምሩ የኖሩ አባት፤ የወጣትነት ጊዚአቸዉ ምን እንደሚመስል ከአርበኝነትና ከጠቅላላ የትግል ታሪካቸዉ የቀነጨብኩትን ከዚህ በታች በግጥም እያቀረብኩ፤ኮ/ል አስናቀ እንግዳ በርግጥ አደራቸዉን በቅጡ የተወጡ ታላቅ ዜጋ ለመሆናቸዉ የግማሽ ምዕተ አመት እዉቅናዪ ለምስክርነት ብቁ ያደርገኛል ብዪ አምናለሁ። ሀቀኛ ምስክርነት ለታላቅ ተክለ ሰዉነት !!
———————– ፡ ——————
አስናቀ እንግዳ።
ገና በልጅነት ገና በጉተና
ለአቅመ አዳም ሳይደርስ ጉልበቱ ሳይጠና
ሀገሩ ስትጠራዉ ለታላቅ ፈተና
አላፈገፈገም ከወንዶች ቀጣና።
ጀግኖች ሲፈለጉ ሌት ተቀን በመብራት
ለሀገረ ኢትዮጵያ ዘብ የሚቆምላት
አስናቀ ነበረ አንዱ ብቅ ያለላት።
መተማ አርማጭሆ በማጠቢያ ቋራ
በየሸንተረሩ በየወንዛወንዙ በወኔ እያቅራራ
ሊቀላቀል ቻለ ልቡ ከነደደ ከአርበኛዉ ጋራ።
እንደ አባቶቹ ሁሉ ጦር እየሰበቀ ፋሽሰትን ሊወጋ
ጥራኝ ዱሩ ጥረኝ ጋራዉ አለ ጠላቱን ፍለጋ።
ጠመንጃና ጥይት ከባንዳ ሊቀማ
እንደ ነብር ሲሳብ ደምፅ ሳያሰማ ።
በድንገት ደረሰ ግን ተስፋ እሚሰጥ ነገር
ደስታ አብሳሪ ነፋስ ሽዉ አለ በሀገር።
የንጉሠ ነገሥቱ ድምፃቸዉ ተሰማ
ክተት አዋጃቸዉ ደረሰ መተማ።
የእንግሊዝ እርዳታ ጠረፍ ላይ ደረሰ
መመልመል ጀመረ ተዋጊ ወታደር
እድል ተከፈተ በአርበኛዉ መንደር።
የልጅ ወታደር ሊሆን ተሰለፈ አስናቀ
ተቀበለ እድሉን በደስታ እየሳቀ።
ከትንሽ ግራ ቀኝ ከተኩስ ልምድ በኋላ
ጓንዴ ጨበጠና ጥይትም አጨቀ በሙሉ ጀበርና።
ያባቱን ጋሻ ጦር በአንድ አድባር ደበቆ
ጠላት ያስስ ጀመር በሽመለ ጋራ ባዳኝ አገር ጫቆ።
አርማጭሆ ገባ አቋምጦ ጓንዴዉን
እየተከተለ የቅርብ አለቃዉን
ሻለቃ ግሪንግሮስ ኮ/ሌ ዊንጌትን
ግፋ በለዉ አለ ወንድም አርበኛዉን
እያፈራረሰ እየደመሰሰ ካራቪኘሪዉን።
አርበኛዉ ተባብሮ ጠረፍ ላይ ቢያገሳ
ሀበሻ በመላ ለድል ተነሳሳ።
ብልቋሽና ሙንጣዝ ቀን ጨለማ ዋጠዉ
ስዓቱ ደረሰ የሚቀበልበት መከራ በቁናዉ።
የግፍ ጽዋ ሞልቶ እንዲያ ሲገነፍል
ወድቃ የምትቀር ኢትዮጵያ ስትመስል።
አልፋና ኦሜጋ እጆቿን ዘርግታ
የነበረች ያለች የጥቁር ሕዝብ ዋልታ
አትጠፋም ኢትዮጵያ ተዋጋለት በርታ።
ብሎ አምላክ ባሳየዉ አርበኛዉ ነጐደ
ጠላቱን እንደ ግንድ እየጐማመደ።
ሀገር ነፃ ወጣች የድል ችቦ በራ
መንግሥታችን ቆመ በአፍሪቃ ቀንድ ጮራ።
ሀገር ሲደላደል ሲመለስ ስርዓት
አስናቀ ቀጠለ በጦር ሠራዊት
ትምህርትም አገኘ በሆሎታ ገነት
ተመርቆ መጣ በኦፊሰርነት።
በችሎታዉና በቆፍጣናነቱ
አላመለጠዉም ደረጃ በደረጃ መኮነንነቱ።
ግን ለራሱ አልኖረም አሳቢ ለብዙ
ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የጠቅላላ ሕዝቡ
ሆኖ እንቅልፍ ቢነሳዉ እጅግ ተጨናቂ
ፍትህ ርዕትህ ወዳጅ ነፃነት ናፋቂ
በጐ እያሰበላት እንደ ጨርቅ አላቂ።
በባላባት ሥርዓት ማቃቂ ወገኑ
በራብ በበሽታ ክረምት ከበጋ ሲፈራረቅ ቀኑ።
እስከ መቸ ድረስ እንዲህ ይዘለቃል
በርግጥ የሥርዓት ለዉጥ በግድ ያስፈልጋል።
በማለት ሞከረ መንግሥት ለመገልበጥ
ከጓደኞቹ ጋር የንጉሡን አልጋ በሕዝብ ለመለወጥ።
ሳይቻል ቀረና ኮሎኔል አስናቀ
ከጓደኞቹ ጋር ከርቸሌ ወደቀ
ሰባት አመት ተኩል ወህኒ ቤት ማቀቀ።
ይህ የሕዝብ ልጅ ለፍቅር የቆመ
ቤተሰቡን ትቶ ላገር የታመመ
በአብዮቱ ዘመን ከወጣቱ ጋራ ትግሉን አፋፋመ።
አንድ ቀን በቤቱ ትኩስ ምግብ ሳይበላ
ሲንከራተት ኖረ ለሕዝብ ነፃነት ሕይዎቱን በመላ።
የሕዝብ ፤ለሕዝብ ፤በሕዝብ መንግሥት ካልቆመ
ከቤቴም አልገባ፤ ሀገርም አያምረኝ አለና ቆዘመ።
በእርጅና ዘመኑ ሲንከራተት ቆዪ
ሀገሩን ወገኑን በምናቡ እያዪ።
ጊዜዉ ደረሰና ሲጠራ በጌታ
ላገሩ እያሰበ ህልሙንም ሳይፈታ
በክብር አረፈና በሳጥን ተገታ።
ደግ ሰዉ አለፈ ……
ደግ ጊዜም አለፈ …..
ደግ ሰዉ፤ ደግ ጊዜ፤ ሁለቱም አለፉ
ሀገርን ባደራ ለቀጣዩ ትዉልድ እያስተላለፉ።
አንተ ነህ ቀጣዩ !!
ደግ የምታደርገዉ፤ጊዜን ሠርተህበት
በማያቋርጥ ትግል ዘዴና ብልሃት።
አደራዉ ለአንተ ነዉ ለቋሚዉ ተረኛ
አስረክቦህ አልፏል ፤ይህ ታላቅ አርበኛ
አስረክቦህ አልፏል ፤ይህ ታላቅ አርበኛ።
ከአበበ አምዴ (አባታቦር)
Email : abatabor@gmail.com
(ክቡር ሥራ አከናዉነዉ፤ለትዉልደ ትዉልድ ምሳሌ ሆነዉ ላረፉት ኮ/ል አስናቀ እንግዳ የቀረበ መታሰቢያ።)
Leave a Reply