ከጳጉሜን 2 እስከ 3 ቀን 2005 ዓ.ም. ሦስተኛ ጉባዔውን በመቐለ ከተማ ያካሄደው ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና ትግራይ) ፓርቲ በቀድሞው የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አስራት ምትክ፣ የፓርቲውን የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በርሄን ፕሬዚዳንት አድርጎ መረጠ፡፡
የሕወሓት መሥራች አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ በፈቃዳቸው ከፓርቲው አመራር መልቀቃቸው ታውቋል፡፡
በአቶ ገብሩ አስራት የቀረበው የፓርቲው የሦስት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት የተገመገመ ሲሆን፣ በክልልም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የማያሠራ ቢሆንም በዚሁ ሳይደናቀፍ ዓላማውን እያሳካ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በክልሉ ውስጥ በበርካታ ከተሞች በሕገወጥ መንገድ ቤቶች መፍረሳቸውን የተመለከተው ፓርቲው፣ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደርና በፖለቲካ ነፃነት ችግር ውስጥ እንደሚገኝ መገምገሙን አስታውቋል፡፡
የፓርቲውን ፕሮግራምና ሕገ ደንብ የገመገሙ ጉባዔተኞች፣ ከተወሰኑ ማሻሻያዎች በስተቀር ከፍተኛ ለውጥ ያላደረጉ መሆኑን ለሪፖርተር የገለጹት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳርና በተለይ በክልሉ ውስጥ በአባላቱ ላይ እየደረሰ የሚገኘው አፈና ይገኙበታል ብለዋል፡፡ አፈናው ከፍተኛ መሆኑ የተገመገመ ቢሆንም፣ በቀጣይ ፓርቲው አባል የሆነበት መድረክ ወደ ሙሉ ውህደት የሚያመራ በመሆኑ፣ አፈናውን ተቋቁሞ ለውጥ ለማምጣት መወሰኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚሁ ሦስተኛው የፓርቲው ጉባዔ የሕግ ባለሙያውና የቀድሞ የሕወሓት አባልና ታጋይ አቶ ብርሃኑ ኃይሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፣ አቶ ጎይቶም ፀጋይ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ተመርጠዋል፡፡
በማኅበራዊ ድረገጾች በተለይ የሕወሓትና የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ናቸው የሚላቸውን በመተቸት የሚታወቀው ወጣት አብርሃ ደስታ፣ ጉባዔውን ከአቶ ገብሩ አስራትና ከወ/ሮ አረጋሽ አዳነ ጋር በመሆን መምራቱንና በመጨረሻም የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ መመረጡ ተገልጿል፡፡
በ2000 ዓ.ም. በትግራይ ክልል የመጀመሪያ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ የተመሠረተው ዓረና ትግራይ ፓርቲ ከዚህ በፊት 90 የነበረውን የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ቁጥር ወደ 130 ከፍ እንዲል ማድረጉ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አሥራ አንድ ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ቁጥር ከ21 ወደ 25 ማሳደጉም ተወስቷል፡፡ ከእነዚህ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል 15 የሚሆኑት አዳዲስ ተመራጮች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ (ሪፖርተር)
Leave a Reply