
ከዚህ በታች የተጻፈውን ፕሬዚደንት ትራምፕ አለ ተብሎ ፌስቡክ ላይ ያገኘሁት ነው፤
- “ነፃነታችሁን ካገኛችሁ ከ50 ዓመታችሁ በኋላ ለሕዝቦቻችሁ አስፈላጊውን የመገናኛ ዘዴ ካልሠራችሁላቸው እናንተ ሰው ናችሁ?
- እናንተ በወርቅ ላይ፣ በዕንቁ ላይ፣ በዘይት ላይ፣ በማንጋኒዝ ላይ፣ በዩራኒየም ላይ ተቀምጣችሁ ሕዝቦቻችሁ የሚበሉት ሳይኖራቸው ሲቀር እናንተ ሰው ናችሁ?
- እናንተ በሥልጣን ላይ ሆናችሁ የጦር መሣሪያ ከባዕዳን ለመግዛትና ዜጎቻችሁን ለመግደል የማታመነቱ ከሆነ እናንተ ሰው ናችሁ?
- የናንተ ማኅበረሰባዊ ዓላማ ሕይወታችሁን በሙሉ በሥልጣን መንበር ላይ መቆየት ከሆነ እናንተ ሰው ናችሁ?
- እንደሚታደን አውሬ ዜጎቻችሁን የምትገድሏቸው ከሆነ ማን ያከብራቸዋል? ”
(ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም!) እነዚህ ሁሉ እውነቶች የሚያጠራጥሩ አይመስለኝም። ነገር ግን የሚያጠራጥሩ ነገሮች አሉ። የትራምፕ ዓላማ ምንድን ነው?
- የአፍሪካ መሪዎችን ለማረምና ለማሻሻል ነው?
- የአፍሪካ መሪዎችን አዋርዶና አሸማቅቆ ታዛዥ ባሪያዎች ለማድረግ ነው?
- የአፍሪካን ሕዝቦች የነፃነትና የመብት ትግሎች ለማበረታታትና ለማጠናከር ነው?
ትራምፕ ስለአፍሪካ መሪዎች የተናገረው እውነት የመሆኑን ያህል የትራምፕ ዓላማ የአፍሪካ ሕዝቦች ኑሮ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ለማድረግ አይደለም። እንዲያውም አንድ መሠረታዊ እውነት ያለጥርጥር ሆን ተብሎ አለመነሳቱ የትራምፕን ዓላማ ከተደበቀበት ያወጣልናል።
የአፍሪካ አገሮች በራሳቸው ገንዘብ መሣሪያ መግዛታቸው የማይካድ ቢሆንም አብዛኛውን መሣሪያ የሚያገኙት በርዳታ ነው። ዋናው የርዳታ ምንጭም አሜሪካ ነው። ከኮሪያ እስከ አፍጋኒስታን በሺዎች የሚቆጠሩ የብዙ አገሮች ሕዝቦች የሞቱበትና አካለ ጎዶሎ የሆኑበት የአሜሪካ መሣሪያ ነው። ዛሬም በኢራቅና በሶሪያ፣ በየመንና በአፍሪካ ቀንድ፣የሚካሄዱት ጦርነቶች ላይ የአሜሪካ መሣሪያዎች አሉ።
የትራምፕ ንግግር የአፍሪካ መሪዎችንn ለማሸማቀቅና ተከታዮቹ ለማድረግ የታቀደ ይመስላል። የአፍሪካ መሪዎች ነገሩን በትክክል ከተገነዘቡት ግዜ ሳይፈጁ ራሳቸውን ለማቃናትና አገሮቻቸውን ለማፅዳት ግዜው መድረሱን ማየት ይቻላል።
ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጥር/ 2010
(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)
(ፎቶ፡ ትራምፕ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በቡድን ሰባት ስብሰባ፤ ከኢንተርኔት የተገኘ)
መቼውንም ቢሆን ፓለቲካና ውሸት ተለያይተው አያውቁም። ለዚህም ነው የጦርነት ቀዳሚ ሟች እውነት ናት የሚባለው። በዓለም ዙሪያ የአሁኑን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሪ ሃሳብ በመደገፍና በመንቀፍ አያሌዎች ይናኮራሉ። ለእኔ ግን ያ ሁሉ ወሃ ወቀጣ ነው። ዝም ብሎ ድካም። ዘመኑ ራቀ እንጂ ምድራችን በወታደራዊው መንግስት ጊዜ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል መሪ መፈከር ነበር። ያ የልብን ሃሳብ ለመስረቅ ወስላቶች የነደፉት እንጂ ሃገር ያኔም ዛሬም በዘረኛው ወያኔ ቀድማ አታውቅም። ታዲያ በአንጻሩ የአሜሪካው መሪ ሃገሬ ትቅደም ማለታቸው የቀኝ አክራሪዎችን ልቦና ለመሳብ እንጂ እዚህ ግባ የሚባል እውነታ የለውም። በመሰረቱ ሁለቱ ፓርቲዎች በጠላትነት የሚተያዪ፤ አንድ ለሚቀጥለው ምርጫ ጉልበት አግኝቶ እንዳይመረጥ ከአሁኑ መጠላለፍን የሚፈጥሩ፤ ለመረጣቸው ከባቢ ህዝብ ቁራሽ ነገር ከፌደራል መንግሥቱ ካለተቸራቸው በቀር በማንም ነገር ላይ ለሃገር ይጠቅማል ብለው የማይስማሙ በአረጀና በአፈጀ እድሜ ውስጥ ያሉ ጥርቅሞች ናቸው።
ትራምፕ አፍሪቃንና ህዝቦቿን ቢጠላ በርሱ አልተጀመረው። ፓትርስ ሉቡምባን በሃገሩ ላይ የገደለው፤ ሳሞራ ሚሸልን የሚበርበትን አውሮፕላን መትቶ የጣለው፤ ኔልሰን ማንዴላን ለዘመናት እስር ቤት ያጎረው፤ አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ሥጋ የተቀራመተው በሊቢያና በኢትዮጵያ የተከለከለ መረዝ የተጠቀመው ነጩ ህዝብ ነው። I suggest to all who want to know the true color of American foreign policy to read “Confessions of an Economic Hit Man” by John Perkins. ይህን በዚህ እንተውና … እኛ በእኛው ላይ የምናደርሰው ሰቆቃ ማቆሚያው መቼ ነው ብለን ራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል። መከበር ከራስ ይጀምራል። ባህር አቋርጦ የመጣ ጠላትን የመከትን ይመስል ወንድምና እህታችንን ገድለን አካኪ ዘራፍ የምንል እኛው ራሳችን ነን። በዘር፤ በጎሳና በቋንቋ መስመር አበጅተን አንድ በላተኛ ሌላውን የበይ ተመልካች ያረግን እኛ ነን። ህዝባችንን ለረሃብና ለመከራ አጋልጠን ሁሌ ምጾተኛ ያደረግነው እኛ ነን። ዛሬ በዘራቸው አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ ወላይታ ወዘተ በማለት የሚመጻደቁ የጎሳ ብሄተኞችን የምጋብዘው አንድ ነገር አለ። Get a DNA kit and find out your lineage. I was surprised. I did not found my self as I claimed to be. One thing is for sure. My being Ethiopian was never questioned. If anything it was confirmed astoundingly!
ጊዜ የሻረውን የጉልተኝነት ፓለቲካ በመተው ለተጠቃለለ የህዝባችን አንድነትና ሰላም መታገልና ከግቡ ማድረስ እጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል። ነጩ ዓለም ስለ ጥቁሩ አለም የሚለፈው የአሁንና የአለፈ ፓለቲካ ለራሳቸው ጥቅም እንጂ ለእኛ አይደለም። ስለሆነ የአሜሪካ መሪ አፍሪቃንና መሪዎቿን በማናናቅ የህዝቦቿን ፍልሰት አልቀበልም ማለታቸው የውስጥ የፓለቲካ ፍጆታ ነው። የአፍሪቃ ችግር 70% ከራስ የመነጨ ነው። ሌላው ከነጩ ዓለምና ከአረብ ጣልቃ ገብነት የሚፈልቅ መርዝ ነው። ስለሆነም አለ/ተባለ/አሉ/አስባልን እያለን ወሬ ከምናናፍስ ራሳችንን በመቀየር የህዝባችንን ሰቆቃ እናቁም!
ጽሁፌን ኣትላጡ!! የጽሑፍ ነፃነትን ተማሩ!!