ሰሞኑን ህወሃት/ኢህአዴግ በሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደውን ኢፍተሃዊ ውሳኔ በመቃወም ሪያድ ከተማ ውስጥ አርብ ኦገስት 7 2015 ምሸት ኢትዮጵያዊው ህዝበ ሙስሊም አንድነቱን ጠብቆ ተቃውሞውን አሰምቷል።
ቁጥሩ ከፍተኛ እንደሆነ ህዝብ የተገኘበት ይህ ታላቅ ተቃውሞ የአካባቢውን ድባብ ለውጦት እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል። የተከሰተው ነገር በራሳችን እንደደረሰ ተሰምቶን በሶስት ቀን ውስጥ በተጠራ የተቃውሞ ጥሪ ይህን ያህል ህዝብ አንድነቱን ጥብቆ ለተቃውሞ በነቂስ መውጣቱ የትግሉ አንድነት ጥንካሬ መገለጫ መሆኑን የገለጹት ሼክ ሲዒድ አህመድ ህዝበ ሙስሊሙ በአገዛዙ ከባድ ፈተና እንደ ተጋረጠበት አውስተዋል፡፡ ሲቀጥሉም ይህ ፈተና አዲስ ሆኖብን ሳንደናገጥ ትግሉን በበሰለና በሰለጠነ መንገድ በማጠናከር እስከ ድል መቀጠል እንደሚገባ በቁጣ የወጣውን ህዝብ ሙስሊም በማረጋጋት በአባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ሼክ ሰዒድ በማስከተል አቡበከር በአንድ ወቅት በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ፀጥታ ሃይሎች ወህኒቤት ግፍ እየተፈፀመበት “ፍ/ቤቱም የኛ፤ ፖሊሱም የኛ፤ አቅቤ ህጉም የኛ፤ መርማሪውም የኛ ስለሆነ የፈለከውን የመከላከያ ምስከር ብታመጣ፣ ብትወጣ፣ ብትወርድ ከፍርድ አታመልጥም እኛ ነን የምንፈርድብህ” ተብሎ በሥርዓቱ ካድሬዎች በምጸት ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፊት ተነግሮት የነበረውን በተግባር ማየቱን ሼኩ ለተስብሳቢው በመጥቀስ በመሪዎቻችን ላይ የተፈፀመው ደባ ሊያስደንቀን እንደማይገባ ገልጸው የፍ/ቤቱን ኢፍታሀዊነት ለተሰብሳቢው በተጨባጭ አስረድተዋል።
በዕለቱ የወጣውን ህዝብ ለማስተናገድ ተይዞ የነበረው ቦታ በመጨናንቁ የነበረውን የሪያድ የአየር ሙቀት በመቋቋም ከምሽቱ 1 ስዓት ጀምሮ እስከ ሊሊቱ 9 ስዓት ድረስ በዘለቀው በዚህ ፀረ ጭቆና ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ አንዳንድ የስብሰባው ተሳታፊዎች ህዝበ ሙስሊሙን በገዛ ሃገሩ የሚያስር የሚገድለውን የህወሃት/ኢህአዴግ ስርዓት እንዲያጠፋላቸው እያለቀሱ ለፈጣሪያቸው ፀሎት “ዱአ” አድርሰዋል።
ሰሞኑን የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በህዝበ ሙስሊም ተወካዮች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ሥርዓቱ በመላ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ላይ እየፈጸመ ያለው ሃይማኖታዊ ጭቆና ግፍና በድል አንዱ አካል መሆኑን የገለጹት የስብሰባው ተሳታፊዎች ከእንግዲህ ትዕግስታቸው መሟጠጡን ጠቅሰው በዚህ አምባገነን ስርዓት ላይ የጀመሩትን ትግል እስከ መጨረሻ አጠናክረው ለመቀጠል በመወሰን የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።
በሳውዲ አረቢያ ድምጻችን ይሰማ ደጋፊዎች እያካሄዱ ባለው ሃይማኖታዊ ፀረ ጭቆና ትግል የህወሃት/ኢህአዴግን ስርዓት የቦንድ ሽያጭና መሰል የሥርዓቱን እንቅስቃሴ በማሽመድመድ የታወቁ ግንባር ቀደምና ጠንካራ መሆናቸው ይታወቃል።
በዕለቱ የተደረገውን የፀሎት ስርዓት ከዚህ በታች ይገኛል።
(መረጃው ከድምጽና ምስል ጋር የተላከው በኢንጂነር መሃመድ አባስ ከሪያድ ሳውዲ አረቢያ ነው፡፡ ፎቶው ቀደም ብሎ ሳውዲ አረቢያ ድምጻችን ይሰማ ካደረገው ስብሰባ የተወሰደ)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply