የፍርሀት ሁሉ – ፍርሀት እሚባለው
ካሉት በታች አ’ርጎ በቁም እሚገለው፤
እንደጥላ ሆኖ – የማይርቅ ቢርቁት
ከራስ መሸሽ ነው ፍርሀት የሚሉት።
አላማ ያለው ሰው አይፈራም። ፍርሀት ብዙውን ግዜ ከአላማ ቢስነተና ካለመተማመን ጋር የተያያዘ ነው። አላማ ያለው ሰው ግብ አለው። ስለዚህም አላማ ያለው ሰው ከወዲሁ ሊገጥመው የሚችለውን ነገር ጠንቅቆ ያውቃልና ይዘጋጃል። ለያዘው አላም ሙሉ ግዜውን፣ ሀብቱን፣ እውቀቱንና የሚያስፈልገውን ሁሉ ይጠቀማል። አስፈላጊም ከሆነ ህይወቱን ሳይቀር መሰዋዕት ለማድረግ ዝግጁ ነው። እርግጥ ነው አላማን ለማስፈጸም ኢሰባአዊነትን መጠቀም ግፍ ነው፤ ወያኔያዊነት ነው።
የህዝብን ብሶት አንግቦ ከገዥዎች ጋር ለመታገል የፈለገ ወይም የተመረጠ መሪ፤ ተከታዮችና ደጋፊዎች ለማፍራት አርዕያ መሆን ብቻ አይደለም፤ ለያዘው ሀገራዊ አላማ እንደአስፈላጊነቱ በድፍረትና በመተማመን ፊት ለፊት መጋፈጥ አለበት። መሪነት አስትማሪነት ነው። መሪነት ሀላፊነት ነው። በተለይም የነጻነትና የአንድነት ትግል መሪ መሆን ደግሞ ጀግንነትንና ቆራጥነትን ይጠይቃል፤ መከራም ነው፤ ግን ደግሞ ለራስ የህሊና የክብር አክሊል መቀናጀት ሲያድል፤ የሀገርና የወገን ኩራት መሆንም ነው።
እንደወያኔ ያለውን አገዛዝ ለመታገል የሚነሳ ግለሰብ ሆነ ቡድን ወይም ድርጅት ከወዲሁ ማወቅ ያለበት ነገር ቢኖር እስራት፣ ድህነት፣ ግርፋት፣ ውርደት፣ ሞት፤ በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ስቃዮችና መከራወች የተባሉ ሁሉ እንደሚፈጸምበት ነው። ወያኔ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለው በመግደልና በማስገደል፤ ብሎም ለኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያን ይጠቅማሉ ብሎ ያሰባቸውን ነገሮች ሁሉ በማፍረስ፣ በማጥፋት፣ በመሸጥና በማውደም ነው። ግን እንደ ዶ/ር መረራ ጉዲና የመሳሰሉ ተቃውሚዎች እድሜ ልካቸውን ከወያኔ ጉያ ውስጥ እንዳልመሸጉ ሁሉ፤ “እኛ የኢህአዴግን ጠመንጃ እንፈራለን፤ ኢህአዴግ ደግሞ የ97 ቱን የህዝብ ጎርፍ ይፈራል……” ይሉናል። ዶ/ር መረራ ጉዲና አሜሪካ አገር በነበሩበት ወቅት ከኢሳት ራዴዮ ለቀረበላቸው ጥያቄ ” ኢሳት እኮ እሳት እየትፋ አስቸገረ። ከእናንተ ጋር ቃለ ምልልስ አላደርግም። መንግስትን እፈራለሁ።” ነበር ያሉት። ፍርሀት….ፍርሀት…..ፍርሀት…..።
ሌላው የተቀዋሚ ጎራ ባልደረባቸው ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ”…..የባህር ማዶ ስደተኛ ሀምሳ ዶላር ስጥቶ መንግስትን እንድንገለብጥለት ይፈልጋል።…” ሲሉ ተደምጠዋል። እስቲ በእግዜር ስም እንጠይቀዎት፤ ”የባህር ማዶ ስደተኛ ምን ያህል ዶላር ቢሰጠዎት መንግስትን ይገለብጡታል?” ለካስ ይህን ያህል ዘመን በተቀዋሚነት የኖሩት፤ የሚበቃወትን ያህል ዶላር ስለ አላግኙ እንጅ፤ ቢያገኙ ኑሮ ወያኔን ያስወግዱልን ነበር?… ያውም አኮ ለባህር ማዶዎቹ ነው እንጅ፤ ለሀገር ቤቶቹ በምን ያህል ገንዘብ ወያኔን እንድሚጥሉልን አላሳውቁንም። ደሀ ህዝብ ነው ብለው አዝነውልን ይሆን? እባከዎት ያሳውቁን። ወይስ ወያኔ እንዳይገለብጡት በቂ ዶላር እየከፈለዎት ነው?
በኦጠቃላይ ማለት ይቻላል፤ ለቁጥር የምታስቸግሩት የተቃዋሚነት ታርጋ የለጠፉችሁ ቡደኖችና ድረጀቶች ለደጋፊዎቻቸሁና ቁሜለታለው ለምትሉት የመከራን ገፈት ለሚጋተው ህዝባቸሁ የምታስተላላፉት መልዕክት፤ ፍርሀትንና ከትላነቱም ሆነ ከዛሬው ወያኔ ምንም አለመማራቸሁን ሲሆን፤ ለገዥዎቻችን ደግሞ እንፈራችኋለንና እንደተለመደው እየረገጣችሁ ግዙን፣ ሀገሪቱንም ማፈራረሱንና መዝረፉን አጠናክራችሁ ቀጥሉብት መልዕክታችሁን በአደባብይ ታውጃላችሁ። ወያኔዎች እኮ የእናንተ ትወልድና የእድሜ እኩያችሁ ይሁኑ እንጅ በእውቀትም ሆነ በግንዛቤ ከእናንተ ያነሱ ጠባብ መንደርትኞች ናቸው። ታዲያ ‘ራሳችሁን ገና ከፍርሀትና ከሆድ-አደርነት ሳታላቀቁ፤ አርባ ዓመት ሙሉ ህዝብን እንመራለን ስትሉ፣ እንዴት ሀፍረት የላችሁም? እንዴት ህዝብስ ይታዘበናል አትሉም? ታሪክና ትውልድ ምን ይለናል አትሉም? ”ወይ መአልቲ!….. “ የኛ ትውልድ እኮ እየሰበሰበ ያለው እናንተና መሰሎቻችሁ የዘራቸሁትን መከራ ነው።….
የክህደት የተንኮል፣ ዘር ስለ ዘራችሁ
እንሰበስባለን እኛ ልጆቻችሁ።
ተቃዋዎሚ ነን ባዮች አሁንም እየሰበካችሁ ያላችሁት፤ የ’ናንተን ፍርሀተና አላማ ቢስነት አልበቃ ብሎ፤ ሌላው ዜጋም የ’ናንተን አርዕያ እንዲከተልና ወያኔን እየፈራ ተገዥ ሆኖ እንዲቀጥል ነው። የ 97ቱ ጎርፍ የተገታውና ለሌላ ዙር የወያኔ አገዛዝ የተዳረግነው፤ ህዝብ ሆ! ብሎ ጎርፍ ሆኖ ሲወጣ፤ ተቀዋሚዎች ግን “ፈርታችሁ’’ በወሰዳችሁት የፍርሀት ውሳኔ፤ የወያኔ ጠመንጃ ወገኖቻችን በላ። ታዲያ ብዙዎቻችሁ ፍርሀታችሁ ከውርደትና ከእስራት አላዳናችሁም። አሁንም ታግሎ በማታገል ፋንታ፤ በተቀዋሚነት ስም የወያኔን እድሜ እያራዘመአችሁ፣ በህዝብና በሀገር ላይ አገዛዙ ከሚፈጽመው ግፍ ባለነሰ፤ ግፍ እየፈጸማችሁ ያላችሁት አናንተ ”ፈሪዎች” ተቃዋሚ ነን ባዮች ናችሁ።
”ፈሪዎች ሳይሞቱ፣ ሲሞቱ ሲኖሩ መልሰው መላልሰው
ጀግና ግን፣ የሞቱን የሞተለታ ነው ጣዕሙን የሚቀምሰው።
(ሼክስፒር/ ትርጉም ተገኘ በቀለ)
የወያኔ ተቃዋሚዎችን ፍርሀት ሳስብ በልጅነቴ ያነበብኩት አንድ ተረት ያስታውሱኛል። ተረቱ በአጭሩ እንደሚከተለው ነው።….
”ሶስት ጓደኛሞች ወደ ሩቅ አገር ይጓዛሉ። ጉዟቸውን እያረፉና እየተነሱ ሙሉ ቀን ተጓዙ። ይሁን እንጅ ጀምበር ወደ ማደሪያዋ አዘቀዘቀችና ጠለቀች፤ ቀኑ በጨለማ ተተካ። ጓደኛሞቹም ተዳክሙና ለሊቱን ተኝተው ለማሳለፍ ወሰኑ። አንደኛው ግን ከመተኛት ሲሄዱ ማደሩ እንደሚሻል ለሁለቱ ጓደኞቹ ለማስረዳት ሞከረ። እነሱ ግን ስልደካማቸውና እንቅልፋቸውም ስለአስቸገራቸው መተኛቱ እንደሚመረጥና ለነገው ጉዞ እርፍት መውሰድ እንዳለባቸው አስረዱት። ጓደኛቸው ግን በ’ነሱ ሀሳብ ለመስማማት ከበደው። እነሱም ምክንያቱን ጠየቁት። በለሊት በማያውቁት ሀገር፤ ሜዳ ላይ ወይም ሆነ ጫካ ውስጥ ቢተኙ፤ አውሬ ሊበላቸው እንደሚችል ፍርሀቱን ገለጸላቸው። እነሱም ”ምክንያትህ አውሬ ይበላናል ከሆነ፤ ከ’ኛ መሀል ትተኛለህ።” አሉትና ተስማምቶ በሁለት ጓደኞቹ መሀል ገብቶ ተኛ። ትንሽ ግዜ እንደተኙ ”ቅጭጭጭ…ግጭ….. ጭ.ጭጭ…..”’ የሚል ድምጽ ሰሙና ”የምን ቅጭጭ….ግጭ….ጭጭጭ. … ነው የምንሰመዋ?” ሲሉ እርስ በ’ርሳቸው ተንሾካሾኩ። መሀከላቸው ያስተኙት ጓዳቸው ተነፈስ….”ዝም በሉ!… እንዳንጨረስ!….ጅብ የ’ኔን እግር እየበላ ነው።” በማለት ምክሩን ለገሰላቸው።
ታዲያ እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ መድረክ፣ ህብረት በሚሉት ፈሊጥ ተሰባስበን ተደራጅተናለ እያላችሁ፤ አምባገነናዊነት ከማንኛውም ግዜ በባሰ ህዝብን ሲያሸብርና ሲያስጨንቅ፣ እስር ቤት ሲወረውር፣ ሲያሳድድና ሲገድል፣ አንጡራ ሀብታችን ሲዘረፍና ለበዳን ሲቸበቸብ፣ ህዝብ በድህነትና በችግር ሲጠበስ፣ ዘረኝነት በየቤቱ ሲያንኳኳ፣ ሀይማኖቶች የወያኔ መፈንጫና መራገጫ ሲሆን፤ ሀገሪቱ ተገፍታ ተገፍታ ገደል አፋፍ ላይ ስትደርስ፤ መሰረታዊ የተቀዋሚነት መብታቸሁን ተጠቅማችህ፤ ህዝብን ለሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት አለማሰባችሁና ራሳችሁን ለምንም አይነት ትግል አለማዘጋጅታችሁ አልበቃ ብሎ፤ ”አኛ ፈርተናልና እናንተም ፍሩ!” እያላችሁ በሽታችሁን ታስፋፋላችሁ። በዚህ ትውልድ ላይ የፍርሀትን የበረዶ ውሀ ትቸልሳላችሁ። ግን እስከመቼ?
ፍርሀታችን በልጦ፣ ከሞት ፍርሀት
በቁም እንሞታለን በማይቀረው ሞት።
ሞት እንደሆን ላይቀር፣ በዚህ ቢሉት በዚያ
እንዴት ሀገር ይጥፋ፣ የሌለው መተኪያ።
ወያኔ በሽብርና በፍርሀት እንድንገዛው ካ’ሰማረው ሆድ አደር ኦሮሞ፣ አማራ፣ ደቡብና ተቀዋሚ ነኝ ባይ በተጨማሪ፤ የቤተ-አምልኮት “መሪዎች” ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። በተለይም ”’በኢትጵያ ቅኝ የተገዙት” ሻአቢያና ወያኔ አስመራንና አዲስ አባባን በተቆጣጠሩ ማግስት፤ የፍርሀቱንና የመኮብለሉን ቦይ የቀደዱት ”ለእግዚአብሄር እራስችን አሳልፈን ሰ’ተን፤ የክርስቶስን መስቀል ተሸክመናል።” ያሉት የኦርቶዶክስ ጳጳሳት ናቸው። የሚመጣባቸውን መከራ ሁሉ በጽናትና በትዕግስት፤ በጸሎትና በሱባኤ፤ ለወገናቸው ተምሳሌት ሆነው የመፈሳዊ ተጋድሏቸውን ማስመስከር ሲችሉ፤ ምዕመናንን አሳዝነው፣ ለወያኔ ተኩላዎችና ሆድ-አደር ሎሌዎች በትነው፤ እነሱም ወደ ምዕራቡ አለም “የድሪም ገዳም” ገደሙ። አሁንም እግዚአብሄር መንገድ ከፍቶላቸው፤ በሀገራቸውና በወገናቸው መሀል ተግኝቶ የሚጠይቀውን መሰዋዕትነት እንደመክፈል፤ እንደ ተቃዋሚ ነኝ ባዮቹ “የፌስቡክና የመግለጫ” ነብር መሆንን መርጠዋል። ይሁን እንጅ ዛሬም “ጴጥሮሳዊነትን” ከመረጡ፤ መሸባቸው እንጅ አልጨለመባቸውም።
እስቲ እናስበው፤…. ባለፉት አመታት ወደ ባዕዳን ሀገር በፍርሀትም ይሁን በሌላ ምክንያት የኮበለለው ተቀውሚ፣ ጋዜጠኛ፣ ልሂቃን፣ የሀይማኖት አባት፣ ወ.ዘ.ተ. በሀገር ውስጥ ሆኖ ትግሉን ቢቀጥል አሁን የት እንደርስ ነበር? የቅንጅት አባላት ብቻ ትግላቸውን በእስር ቤት እንደ አሉ ቢቀጥሉ? …… በ’ርግጠኛነት እንዲህ እንደአሁኑ የኊልዮሽ መጓዛችን ቀርቶ፤ ሌላው ቢቀር የእውነተኛ ዲሞክራሲን መሰረተ ድንጋይ በጣልን ነበር። ነበር። ነበር ብለን ግን ተስፋ አንቆርጥም። አሁንም ቢሆን የ’ነ ”መድረክና ህብረት” ነን ባዮችን የፍርሀትን ቀንበር የሰብሩ፣ ለፍትህና ለኩልነት ሲሉ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በየቀኑ የሚገደሉ፣ የሚታሰሩና የክብር መሰዋዕትነት የሚከፍሉ ወገኖቻችን ነገ ከነገ ውዲያ እልፍ- አእላፍ ይሆናሉ። እንሆናለን።
አለን ፔተን ” ከፍርሀት ባርነት፤ከባርነት ፍርሀት፣ የሚገላግለን ጎህ መቼ ይቀድ ይሆን? ማን ያውቃል?” ይለናል፤ እሬ በይ አገሬ በተሰኘው መጸሀፉ መደምደሚያ ላይ። አዎ አለን ፔተን እንዳጠየቀው ”ማን ያውቃል?” ….እሱ ነጻ ደቡብ አፍሪካን ለማየት ባይታደልም ወገኖቹ ግን አሁን በነጻነት ይኖራሉ። የግዜ ጉዳይ እንጅ እኛም ከፍርሀት ባርነት፤ ከባርነት ፍርሀት ተላቀን፣ ሁሉም ዜጎቿ ልዕልነዋ በተከበረች ኢትዮጵያ በፍትህ፣ በእኩልነትና በባለቤትነት የምንኖርበት የ‘ጋራችን ሀገር እንገነባለን። ማን ያውቃል?
e-mail: philiposmw@gmail.com
Hilina Berhanu says
ሁላቸንም አምስት ጣቶቸ ያለን ይመስለኛል! ይህንንም ማንቀበል ካልሆነ! የሌባ ጣት የምትባል ደግሞ አለች፣ ከነዚህ ውስጥ! ይህች ጣት ብድግ ብላ ሌላው ላይ ልታመለክት የተነሳች እንደሆን ደግሞ፣ አንደኛው አውራ ጣታችን ወደ ሰማይ እያሳየ የእግዜር ያለህ ሲል፣ ሶስቱ ደግሞ ወደ እራሳችን እየጦቆሙ ጣትህን ሌላው ላይ ከመቀሰርህ በፊት እራስህን መርምር ይላሉ! ኣረ አስቲ ማሰብ! እንጀምር! ይህ በውጭ ሀይሎች ወተትና ማር እየተኮተኮተ 21 አመት ሙሉ ሲጨፍርብን የኖረን መንግስት ለማስወገድ መላው ጠፍቶን አንጎል ሆነናል ያስኛል አሁንስ! ለምን ቢባል፣ አስራ አምስት ሺ ቦታ ከመከፋፈልና፣ ጣታችንን ሌላው ላይ ከመቀሰር ሌላ የምናውቀው ነገር የለም ነው ይምለው! እዚህ ሌላው ቢቀር ለመናግገር ና ብሶት ለማስማት መብት ባሉባቸው አሜሪካና ምእራብ አውሮፓ፣ ይህ 21 አመት ሙሉ አንጎል ያረገንን መንግስት እሹሩሩ እያሉ ያቆዩ ሃገሮች ውስጥ እየኖርን እነዳንድ ህዝብ ብድግ ብለን አንድ ስሞን እንኩዋን በወጉ ሳንንነሳ! ነጋ ጠባ ዳውላውን ካህያው ላይ ና ውረድ እንላን፣ የተሸከምዋቸውን አህዮች ፈርተን እዚሀ ጉያቸው እየኖርን! ያገር ቤቶቹን ላገር ቤቱ ትተን እስቲ የራሳችንን የቤት ስራ እንወጣ! የሌባ ጣቱን ሰብሰብ አርገን ሌሎቹን ሶስት ጣቶቹንና አውራ ጣታችንን እናስተውል! በተለይም ክርስትያኖች፣ እስላም ወገኖቻችን እነኩዋን እንደ አንድ ሰው ሆነ ከተነሱ አመት አለፈ!
https://www.goolgule.com/misguided/
https://www.goolgule.com/the-i-box/