መቼ አስቤው አውቃለሁ?
መች አልሜዋለሁ…?
ያ! የውሸት-ቋት ‘መስኮት’ – አንጀት አቃጣዩ፣
ቆሽት አሳራሪው – ሽበት አስበቃዩ፣
ድንገት ባንድ ቅጽበት – አክሮባቱን ሰርቶ፣
“ቅበዓ-ቅዱስ” መድኅን – ሃሴት ተቀብቶ፣
ስነግረው የኖርኩትን – መልሶ ሲነግረኝ፣
ወይ ጊዜ ወርቃማው – አፌን አስከፈተኝ፣
…በቅጽበት የሆነው፣ – ምትሃት ያለበት፣
ከሰማይ የወረደ – እሚመስል አስማት..፣
በፍትህ-አልባው ስርዓት – በግፍ የታሰሩ…፣
የሰቆቃውን ገጽ – ቀርበው ሲናገሩ፣
በኢቲቪ ዜና – በእርግጥ ሰማሁ እንዴ?
ጆሮዬን ልኮርኩር – እስኪ ዳግም አንዴ፤
በሕዝብ-አንጡራ ሃብት፣
በኢቲቪ መስኮት…
…ቴዲ አፍሮን፣ ብርሃኑን…፣ ታማኝን አየሁት?
እስኪ እረጋግጡልኝ? ዐይኔ ነው? ወይ ቅዠት?
… አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ባንዲራ፣
በዚያች “ጠባብ” መስኮት በድምቀት ሲያበራ፣
አይቻለሁ ልበል? በዐይኔ በብረቱ፣
የምር ይሆን እንዴ? ይሄ ጉድ በእውነቱ?!
ተደራረበብኝ – ሆነብኝ ድንገቴ፣
‘ኢሳት’ ነው? ‘ኢ-ቲ-ቪ’? – እማየው ከፊቴ?!
በ’ፈጣሪው‘ አዝኜ – በድርጊቱ አፍሬ፣
ዐይኑን ላፈር ብዬ – ስጸየፈው ኖሬ፣
በዞረበት ላልዞር – ምዬ የነበረ፣
በመደመር ቋንቋ – ጊዜ ተቀየረ፤
… የወገኔን ደስታ – ያገሬን ውሎ-አዳር፣
የእግዜሩን በረከት – የመለኮት ነገር፣
በቀጥታ ትዕይንት – ሲያመጣው ደምሮ፣
አንባቢውን ሳይቀይር – ንባቡን ቀይሮ፣
በመገረም ተዐምር – ከስሩ እምተኛ፣
ሆኜላችኋለሁ – “የኢ-ቲ-ቪ- ሱሰኛ”።
ጌታቸው አበራ
ሐምሌ 2010 ዓ/ም
(ጁላይ 2018)
akele says
አይ ጊዜ ስንቱን ያሣየናል።እድሜ ይሥጠን ብቻ ቡዙ እናያለን