• ችጋር ምንድን ነው? ሰፊ ቦታንና ብዙ ሕዝብን የሚሸፍን፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ፣ ምንም የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ እንስሳት (ሰውንም ጨምሮ) ዕለት በዕለት የራሳቸውን አካል እስኪያልቅ ድረስ “እየበሉ” በመጨረሻም የሚሞቱበት ሁኔታ ነው፤ ረሀብ አካል ሲዳከም አካልን ለመገንባት የሚደረግ ጥሪ ነው፡፡
• ችጋር የሚያጠቃው ማንን ነው? ትልቁና ዋናው የችጋር እንቆቅልሽ የዚህ ጥያቄ መልስ ነው፤ አብዛኛውን ጊዜ ችጋር የሚያጠቃው ከገበያ ጋር የማይገናኙትን ምግብ አምራቾችን ገበሬዎችን፣ በተለይም እያመረቱ ከእጅ ወዳፍ ብቻ የሚኖሩትን ነው፤ እነዚህ ገበሬዎች የገጠሩ ሕዝብ፣ ማለትም የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጨረሻ ደሀዎች ናቸው፤ ኑሮአቸው ሁልጊዜም በችጋር አፋፍ ላይ ነው፡፡
• ችጋር ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት እንዴት ነው? ከላይ እንደተባለው በችጋር ላይ የሚወድቁት ገበሬዎች ከገበያ ጋር እምብዛም ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፤ ይህም እምብዛም ጥሬ ገንዘብ የላቸውም ማለት ነው፤ ስለዚህ በገበያ ላይ እህል ቢኖርም የመግዛት አቅም የላቸውም፤ ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት የጠበቀ ነው፤ ምርታቸው መቶ በመቶ በተፈጥሮ ችሮታ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ስለዚህም ተፈጥሮ በትንሹ እንኳን ፊቱን ካዞረ ምርቱ ያንሳል ወይም ጭራሹኑ ይጠፋል፡፡
• ተፈጥሮ ፊቱን የሚያዞረው እንዴት ነው? ብዙ መንገዶች አሉ፤የእርሻ ምርት በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የተመሠረተ ነው፤ መሬት (አፈር)፣ ውሀ፣ የዓየር ጠባይና ጉልበት፣ ተፈጥሮ በነዚህ ላይ ፊቱን ማዞሩ የሚገለጥባቸው ዋና ዋናዎቹ፡-
• ዝናብ ወይ ይበዛል ወይ ያንሳል፤
• የዝናቡ ወቅት ይቀድማል፤ ወይም ይዘገያል፤
• ምርቱን ውርጭ ይመታዋል፤
• ምርቱን ተምች ይመታዋል፤
• ምርቱን በሽታ ይበላዋል፤
• ምርቱን ከባድ ጎርፍ ወይም ከባድ በረዶ ያጠቃዋል፤
• ሌላም፣ ሌላም፣
• ተፈጥሮ በአንድ ምክንያት ፊቱን ሲያዞር ለወትሮው በችጋር አፋፍ ላይ የነበሩት ደሀ ገበሬዎቸው ወደችጋሩ ገደል መግባት ይጀምራሉ፤
• ችጋር ሕዝብን በጅምላ የሚጨፈጭፍበት ጊዜ ከስድስት እስከስምንት ወራት ይፈጃል፤ የተፈጥሮ ችግር መኖሩ ከታወቀ ጀምሮ ከስድስት አስከስምንት ወሮች ሰዎች አካላቸውን “እየበሉ” ይቆያሉ፤ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ተከሰተ የተባለው ድርቅ ሰዎችን በችጋር መረፍረፍ የሚጀምረው በሚያዝያና በመጋቢት ነው፤ ገበሬዎቹ ከአሁን ጀምሮ እስከ መጋቢት ምንም ሰፊና ትልቅ ዘላቂ እርዳታ ካላገኙ በመጋቢትና በሚያዝያ ሰው እንደቅጠል የሚረግፍበት ጊዜ ይሆናል፤
• ልብ በሉ የመጀመሪያው የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ወይ የተዘራው ጠፍቶአል፤ ወይ ቀንሶአል፤ ወይ ተበላሽቶል፤ ስለዚህም ገና በክረምት ወራት አዝመራ እንደማይኖር ይታወቃል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አስከመጋቢትና ሚያዝያ ቢያንስ ስምንት ወራት አሉ፤ በዚህ ጊዜ ሰዎች ወደችጋሩ ገደል እንዳይገቡ የሚያግደው፡-
ሀ) እያንዳንዱ ሰው ወይም ቤተሰብ ለክፉ ቀን ለመጠባበቂያ የሚሆን እህል በጎተራ ለምን አያስቀምጥም?
ለ) ለክፉ ቀን ጥሬ ገንዘብ በባንከ ለማን አያስቀምጥም?
ሐ) አገዛዙ የእርሻ ምርት የሚቀንስ ወይም የሚጠፋ መሆኑ ከታወቀ ጀምሮ ተጠቂ ለሚሆነው ሕዝብ በቂ ምግብ ለምን አያዘጋጅም? ሕዝቡ ራሱ ለችጋር አደጋ እንዳይጋለጥ በየወረዳው “የእህል ባንክ” ለምን አያቋቁምም?
መ) ከእጅ ወደአፍ የማያልፍ ምርት የሚያመርቱ (ሁሌም ለችጋር የሚጋለጡት) ገበሬዎች ለምን ግብርና ሌሎችም መዋጮዎች እንዲከፍሉ ይገደዳሉ? እንዲያውም በአንጻሩ አገዛዙ እነዚህ ለአደጋ የተጋለጡ ገበሬዎች ማኅበራዊና መዋዕለ ንዋያዊ አቅማቸው አቅማቸው እንዲዳብርና እንዲበረታ የማያደርገው ለምንድን ነው? ደሀነታቸውንና ደካማነታቸውን የሚፈልገው ለምንድን ነው?
ሌሎች፣ ሌሎች ጥያቄዎችም …
• የመጨረሻውና ዋናው ነጥብ ማናቸውም ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ከችጋር ጋር በቀጥታ የተያያዘ አለመሆኑ ነው፤ ከአደጋው በፊት ለማኅበረሰቡ የኑሮና የአስተዳደር ግንኙነት የተገነባው ሕጋዊ የነጻነትና የልማት ሥርዓት መኖር ወይም አለመኖር በአንድ በኩል፣ አደጋውን ተከትሎ እያንዳንዱ ግለሰብ በተናጠል፣ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ያደረጉትን ወይም ሊያደርጉት የሚገባውን አብረን ስንመለከተው በተፈጥሮ አደጋውና በችጋር መሀከል ያለው ረጅም የጊዜ ርቀት ችጋርን የአገዛዝ ውላጅ ያደርገዋል፤
• ስለዚህም ለልማትም ሆነ የተፈጥሮ አደጋን ለመቋቋም ግለሰቡ በሕጋዊ ሥርዓት ስር በሙሉ ነጻነት የማይኖር ከሆነ ከችጋር የሚወጣበት መንገድ አያገኝም፤
• ሁላችንም በየቀኑ የሚያጋጥመን ረሀብና ለብዙ ወራት ቆይቶ ሥጋን ጨርሶና አጥንትን ፍቆ ለሞት የሚዳርገው ችጋር አንድ አይደሉም፤
• ድርቅ የሚባለው የተፈጥሮ አደጋና በሰው ልጆች ቸልተኛነት የሚከሰተው ችጋር አንድ አይደሉም፤ ሁለቱን አንድ ለማድረግ የሚሞከረው ኃላፊነትን ለመሸሽ ነው፡፡
ኅዳር 2008
Leave a Reply