በትናንትናው ዕለት በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ታሪክ ውስጥ ሥልጣን ካንዱ ጠ/ሚንስትር ወደ ሌላው ሲሸጋገር በአደባባይ በማየቴ ለማመን እየተቸገርኩኝ ነው። በጠ/ሚንስትሩ ንግግር ውስጥም ላለፉት አርባ ዓመታት የለመድናቸው “ጠላት” “ጸረ ሰላም ኃይሎች” “እናሸንፋለን” የመሳሰሉ ካድሬያዊ አነጋገሮች ለመጀመርያ ጊዜ በመሪያችን አፍ አለመነገሩን፣ ተፎካካሪ እንጂ ተቃዋሚ እንደሌለ መስማት፣ የተለየ አስተሳሰብ ስላስተናገዱ ብቻ የተገደሉትን የፖሊቲካ መሪዎችና በጨቅላነታቸው የተቀጩትን አስታውሶ ይቅርታ መጠየቅ፣ ከልብ ይቅር ተባብሎ ያለፈውን ምዕራፍ ዘግቶ ወደ ፊት ለመራመድ መጋበዝ፣ ከኤርትራ ጋር በሰላም ለመኖር ከማሰብ አንጻር ንግግር ለመጀመር ዝግጁ መሆን፣ ከሁሉም በላይ ለዘመናት እንደ “ገበና” ተቆጥሮ የማይነገረውን የግልን ህይወት ለአደባባይ ፍጆታ ቀርበው ስናዳምጣቸው ለመጀመርያ ጊዜ ህዝብ ህዝብ የሚሸትና ሰብዓዊ ፍጡር የሆኑ መሪ በማግኘታችን ተደስቻለሁ ብል ማጋነን አይሆንብኝም።
ምናልባት ጠ/ሚንስትሩ እንደሌሎች ለምሳሌ፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አስራ ሰባት አመት ሙሉ ዜጎቻችንን ሲገድሉ እንደነበሩ አንጋፋ የህወሃት አባላት ተዋጊም አሸናፊም ተማራኪም ያልነበሩና ኢህአዴግንም ገና በወጣትነታቸው ከተቀላቀሉት በኋላም በሙያቸው እንጂ የተቃዋሚ ኃይሎችን አባላት ያልገደሉ ወይም ያላስገደሉ በመሆናቸው ነው መሰለኝ የሞራል የበላይነትና በራስ የመተማመን መንፈስ ይታይባቸዋል። ይህ፣ “ተቃዋሚዎችን በማሸነፍና በማሰር ወይም በመግደል” የማይኩራራ ግን ደግሞ በራሱ ቅንነት ላይ ጥንካሬን የመሰረተ መሪ ማግኘታችን አንዳች አይነት ተስፋን ይሰጣል የሚል ግምት አለኝ። ለመጀመርያ ጊዜ የህወሓት መሪ ያልሆነ ወይም በህወሓት ያልተደገፈ የኢህአዴግ አባል ድርጅት መሪ ለጠ/ሚንስትርነት መብቃቱ በራሱ የህወሃትን የሩብ ምዕተ ዓመት የበላይነት የገረሰሰ ትልቅ ድል ስለሆነ ማወደስ ያለብን ይመስለኛል።
ጠ/ሚንስትሩ ከወረሷቸው ችግሮች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡
ሀ) ለስድስት ወራት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በኮማንድ ፖስት ፊታውራሪነት በተግባር ተተርጉሞ የተወሰኑ ወጣቶችን ገድሎና ሌሎችን አስሮ በማሰቃየት ላይ ነው።
ለ) የጸረ ሽብር ዓዋጁን ተፈጻሚነት አስከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ መሰረተ ቢስ በሆነ የሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በተለያዩ ያገሪቷ እስር ቤቶች ለሰቆቃ እየተዳረጉ ዜነው።
ሐ) ህገ መንግሥታዊና መሰረታዊውን የሰው ልጆች መብቴን ተገፍፌአለሁ ብሎ ለዓመታት ያለማቋረጥ በእንቢተኝነት በሰልፍ ወጥቶ ድምጹን ያሰማ የነበረው ወጣት፣ አዲሱ ጠ/ሚንስትር ለተነሱት የመብት ጥያቄዎች አዎንታዊ መልስ ይሰጡኛል ብሎ በተስፋ እየጠበቀ ነው። የሚያረካ መልስ ካላገኙ እንደገና ወደ ጎዳና ለመውጣት በተጠንቀቅ ቆመዋል ማለት ነው።
መ) ኢህአዴግ ሁሌም የሚነግረንና ለችግሮቹ ሁሉ አልፋን ኦሜጋ አድርጎ የሚያቀርበው አንድ ድብቅና በጣም ኃይለኛ የሆነ፣ ነባራዊውን ሥርዓት በምንም መልኩ እንዳይቀየር የሚፈልግ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚባል ተጽዕኖ ፈጣሪና መንግሥት ሊቆጣጠረው ያልቻለ መሆኑ የሚነገርለት ቡድን ዛሬም በህይወት ስላለ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ይህንን ኃይል አሸንፈው የሚያመረቃ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ወይ? ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን አንገሽግሾ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ያስገደዳቸው ሁኔታስ እንዳለ ነው ያለው ወይስ ተቀይሮአል?
የምኞታችን ሰሌዳ፣
ባገሪቷ የሰፈነው ቀውስ የያንዳዳችንን በር ስላንኳኳ ሁላችንም አንዳች ዓይነት ለውጥ መመኘታችን ተፈጥሮአዊ ነው፣ አሁን ካለንበት ባብዛኛው ሰው ሰራሽ በሆነው ችግር ምክንያት በውሸት የኤኮኖሚ እድገት ፕሮፓጋንዳ አየር እየተሞላን የህዝቦቻችንን በድህነት አዘቅት ውስጥ ተወዝፈው ከሚኖሩበት የተሻለ ህይወት ከመመኘት አንጻር ለለውጥ ያለንን ፍላጎት ከዳር እስከዳር ማሰማታችንና ወደ ጠ/ሚንስትሩ ጆሮ እንዲደርስ መወትወታችንም ተገቢ ነው። የጸረ ሽብርና የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጆች ሰለባ ሆነው በየእስር ቤቱ በመማቀቅ ላይ ያሉት ዜጎቻችን እንዲፈቱና፣ መንግሥት አሰልጥኖ ባሰማራቸው ነፍሰ ገዳይ አግዓዚና መከላከያ ሠራዊቱ ኃይላት በግፍ ለተገደሉት ሰላማዊ ወገኖቻችን ፍትህ መጠየቃችን አግባብ ያለው ጥያቄ መሆን ብቻ ሳይሆን የዜግነት ግዴታችንም ይመስለኛል። ተቃዋሚ ኃይላት በእኩልነት የሚወዳደሩበትና የመወዳደር ያው ሜዳውም ለሁሉም እኩል የሆነበት አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ፣ ብሎም ህዝቡ ያላንዳች ተጽዕኖ የራሱን መሪዎች እንዲመርጥ ያለማቋረጥ ድምጻችንን ማሰማታችን ላገሪቷ በጎ ከማሰብ እንጂ የወያኔ መሪዎች እንደሚሉት “ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ” ስላልሆነ ጥያቄያችን አግባብ ያለው ነው። አገሪቷ የጥቂት ባለጊዜ የኢህአዴግ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ሳይሆን የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆና የተፈጥሮ ሃብቷም ሆነ ምርቶቿ የመላ ዜጎቿ ሃብት መሆኑን ማሳሰባችን መብታችንም ግዴታችንም ነው። የምኞታችን ሰሌዳ ከዚህም ሊሰፋ ይችላል።
በኔ ግምት ጠ/ሚንስትሩ ለማምጣት የያቀዱት ጥገናዊ እንጂ አብዮታዊ ለውጥን አይመስለኝም። በመሆኑም፣ የምንመኛቸውን ለውጦችና የጠየቅናቸውን የፍትህ ጥያቄዎች ጠ/ሚንስትሩ ሊፈጽማቸው ወይም ሊመልሷቸው ሙሉ በሙሉ ፈቃደኛ ናቸው ብለን ብናስብ እንኳ፣ ሂደቱ በጣም ዝግ ያለ ይሆናል። ዶ/ር ዓቢይ ሥርዓቱ ኮትኩቶ ያሳደጋቸውና የሥርዓቱ ምርት ስለሆኑ በድርጅታቸው ውስጥ ያለውን የበሰበሰ አሰራር ቀስ በቀስ ያሻሽሉ እንደሁ እንጂ ሥር ነቀል የሆነ አብዮታዊ ለውጥ ሊያደርጉ የሚችሉ አይመስለኝም። የድርጅታቸውን ኢዲሞክራሲያዊ አሰራርና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ አለመቻል ከቡድናቸው መሪ ከኦቦ ለማ መገርሳ ጋር ሆነው ከማንኛውም የኢህአዴግ አባል ቀድመው በመንቃትና ለህዝብ በማስታወቃቸው ራሳቸው ተካፋይ የነበሩበትን ጸረ ህዝብ ድርጊት ጥገናዊ ለውጥ አድርገው የማስተካከል ብቃትና ፍላጎት ግን ያላቸው ይመስለኛል።
ችግሩ ግን፣ የህዝቡን ጥያቄ ሳይመልሱ ቢቀሩ ህዝቡ ላልተመለሰው ጥያቄው ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዳል የሚለው እጅግ በጣም አሳሳቢ ይመስለኛል። ከታች ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ የምሞክረው የህዝቡ ችግሮች ደግሞ ፋታ የማይሰጡ በመሆናቸው፣ ባስቸኳይ መልስ ካልተሰጣቸው፣ ቄሮና ፋኖም ወደ አውራ ጎዳናዎች ወጥተው የተለመደውን ጥያቄ ማሰማት ይቀጥላሉ፣ ለዓመታት ላነሷቸው የመብት ጥያቄዎችም ተገቢ መልስ ተንገፍግፈው ጎማ ማቃጠልና “የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ንብረት” ናቸው ብለው በፈረጇቸው ላይ እርምጃ መውሰድ ይጀምራሉ፣ ሰራዊቱ ደግሞ “ጸጥታ ለማስፈን” በማለት ተኩሶ መግደል ይጀምራል፣ ወደ ለመድንው የጥፋት አዙሪት ውስጥ ተመልሰን እንገባለን ማለት ነው። ምኞታችን እንግዲህ ጠ/ሚንስትሩ ህገመንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣን ተመርተውና በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(4) መሰረት ተጠያቂነታቸውና ተጠሪነታቸው ለህገ መንግሥቱ፣ ለመረጣቸው ህዝብና ለኅሊናቸው፣ ብቻ መሆኑን አውቀው፣ የሚቻላቸውን ጥገናዊ ለውጥ አድርጎ ለጊዜው እንኳ ቢሆን ሰላምና መረጋጋትን እንዲያመጡ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥን የማምጣት ችሎታና ክሀገ መንግሥቱ አንጻር ሲታይ፣
ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለይም ዛሬ ኦህዴድና ብአዴን አብላጫ ድምጽ ባላቸው ፓርላማ ውስጥ፣ ህገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ ብቻ፣ በተደጋጋሚ ተጠይቀው መልስ ላልተሰጣቸው የህዝብ ጥያቄዎች የማያዳግምና አጥጋቢ መልስ ሊሰጡ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ። በመጀመርያ ደረጃ የህገ መንግሥቱን አንቀጽ 73 (1)(2) ተጠቅመው ለህዝባዊው ዓመጹ መቀስቀስና ለተለያዩ ያገሪቷ ችግሮች ምክንያቶች ነበሩ ተብለው የሚታሰቡ ሚኒስትሮችን ለምሳሌ ያህል የህዝብ ደህንነት ኃላፊውንና የመከላከያ ሚንስትሩን ከሥልጣን አውርደው፣ እጃቸው ንጹህ በሆኑ ህዝብ ህዝብ በሚሸቱ ግለሰቦች መተካት አለባቸው። የመከላከያ ሠራዊቱንና የደህንነቱንም መዋቅር በአዲስ መልክ ማደራጀት ይችላሉ። እንደ ጦሩ ጠ/አዛዥነታቸው፣ የጦር ኤታ ማጆር ሹሙንም ማንሳት ይችላሉ። የትግራይ ብሄር ተወላጆች ብቻ የያዙትን ከፍተኛ የጦር አመራር ቦታዎች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እኩል ብቃት ባላቸው የሌሎች ብሄር ተወላጆች እንዲሞሉና ጦሩ በተጨባጭ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የማድረግ ህገ መንግሥታዊ ኃይል አላቸው። እንዲሁም የህገ መንግሥቱን አንቀጽ 81 (1)(2)ን በመጠቀም፣ ፍትህ አጉድለዋል በመባል የሚታወቁትን የፌዴራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሹማምንትን በሌሎች ቅን ዳኞች ከመተካት የሚያግዳቸው የለም።
ሌላው፣ ጠቅላይ ሚንስትራችን ያለ ምንም ውጣ ውረድ ባስቸኳይ ሊፈጽሙት የሚችሉ፣ እጅግ በጣም አስፈላጊና ሳይደረግ ቢቀር አገራዊ ቀውሱን የሚያባብስ እንጂ የማያረግብ አንድ ዓቢይ ጉዳይ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትንና የተለየ አስተሳሰብ በማራመዳቸው ብቻ በሽብርተኝነትና በሌሎች ተመሳሳይ መሰረተ ቢስ ወንጀሎች ለዘመናት ታስረው ስቃያቸውን በማየት ላይ ያሉትን የፖሊቲካ እሥረኞችን በአስቸኳይ የመፍታቱ ጉዳይ ነው። ባላፈው የኢህዴግ ማዕከላዊ ስብሰባ ላይ የተወሰነ ጉዳይም በመሆኑ፣ ለጠ/ሚንስትራችን ያንኑ ውሳኔ በተግባር ማዋል ነውና እስረኞቹን የመፍታት ሂደት ከማፋጠን የሚያግዳቸው ኃይል ያለ አይመስለኝም።
ለህዝባዊ ዓመጹ መቀስቀስና ላስከተለውም የሰውና የንብረት መጥፋት ምክንያት የሆነውን የመልካም አስተዳደር ጉድለት በዋናነት ተጠያቂ ነኝ ብሎ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ በአደባባይ ህዝባችንን ይቅርታ የጠየቁበት ጉዳይ በመሆኑ፣ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ሲባል ይህንን ህዝቡ የተነፈገውን መልካም አስተዳደር በተግባር ለማዋል ጠ/ሚንስትራችን ዛሬውኑ ቁርጠኛ እርምጃ ለመውሰድ ይችላሉ። ህዝቡን ያላካተተ ውይይትም ሆነ ውሳኔ ደግሞ ተፈጻሚነቱ ላይ እክል ሊገጥመው ስለሚችል፣ መልካም አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ህዝቡ ከመንግሥት እኩል የሚሳተፍበትን መድረክ ማዘጋጀት ለጠ/ሚንስትራችን የሚሳናቸው አይመስለኝም።
ከላይ እንዳስቀመጥኩት ለፓርላማው ሳያቀርቡ እንደ ርዕሰ ብሄርነታቸው ሊፈጽሙ የሚችሏቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ብዙዎቻችን ግን የቀድሞው ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና ህገ መንግሥቱን በመጣስ ጊዜያዊ ዓዋጆችንና መመርያዎችን ሲያወጡና ሲወስኑ ተለማምደን፣ ያሁኑም ጠ/ሚንስትርም ልክ እንደ አቶ መለስ “ሁሉ በጄ ሁሉም በደጄ” ብለው ዛሬውኑ የአስቸኳይ ጊዜና የጸረ ሽብር ዓዋጁን እንዲያነሱ የምንመኝ ብዙ ዜጎች አለን። ምኞቱ ሰብዓዊና ትክክለኛ የሆነውን ያህል፣ አምባገነኑ አቶ መለስ ህገ መንግሥቱን ጥሰው አምባገነናዊ ዓዋጅና መመርያ ያወጡ ስለነበረ ያ እንደትክክለኛ አሰራር ተተርጉሞ፣ ዶ/ር ዓቢይም ህገ መንግሥቱን ጥሰው አምባገነናዊ መመርያ እንዲያወጡ መገፋፋት ግን ጥሩ አካሄድ አይመስለኝም። በአንጻሩ ግን በፓርላማው ውስጥ የጥገናዊ ለውጥ ደጋፊዎቻቸው አብላጫ መቀመጫ እስካላቸው ድረስ፣ ህገ መንግሥቱን ብቻ ተከትለው ጥገናዊ ለውጥ በማምጣት የህዝቡን ጥያቄ ለለመለስ ይችላሉና ጠ/ሚንስትራችን የሚከተሉትን ዓቢይ የህዝብ ጥያቄዎች ያለመዘግየት ለፓርላማው አቅርበው የማስጸደቅ ግዴታ አለባቸው ባይ ነኝ።
ሀ) ከመጀመርያውም አስፈላጊነቱ ያልታመነበትና የጥቂት ቡድኖችን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ተብሎ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜውን ዓዋጅ እንዲነሳ ፓርላማው ውይይት እንዲያደርግበት ማቅረብ አለባቸው። በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 93/3 የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመው ዓዋጁን ለፓርላማው አቅርበው ያስጸደቁ የቀድሞው ጠ/ሚንስትር ያደረጉትን ያህል ያሁኑም ጠ/ሚንስትር፣ ዓዋጁ ያደረሰውን ጉዳትና ጥቅም ገምግመው ለዜጎች መብት መከበር ቅድሚያ ይሰጥ ዘንድ በአስቸኳይ እንዲነሳ ማድረግ ከቤት ሥራቸው የመጀመርያው መሆን አለበት ባይ ነኝ።
ለ) ለብዙ ኢትዮጵያውያን መታሰርና መሰቃየት መሞትና መሰደድ ምክንያት የሆነውን የጸረ ሽብር ዓዋጁን በአስቸኳይ እንዲነሳ ለፓርላማው ማቅረብ አለባቸው። ከታሳሪዎቹ መሰቃየት ባሻገርም ይህ በሰፊው የተነገረለት “ከተፎካካሪ ኃይሎች ጋር የመነጋገር” እቅድ፣ ዓዋጁ ብዙዎቹ ተፎካካሪ ኃይላትን በሽብርተኝነት ስለፈረጃቸው፣ የታቀደው ውይይት የታሰበለትን ግብ እንዲመታ ከተፈለገና በዕውነትም የፖሊቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ከተፈለገ፣ የጸረ ሽብር ዓዋጁ ያላንዳች መዘግየት እንዲነሳ ጠ/ሚንስትሩ ለፓርላማ አቅርበው አባላቱ እንዲወያዩበት ማድረግ ከቀዳሚ ተግባራቸው አንዱ መሆን ያለበት ይመስለኛል።
በተለያዩ መድረኮች በተለይም ጠ/ሚንስትራችንን ያቀፈው የኦቦ ለማ ቡድን በተደጋጋሚ ሲያውጁ የነበረው “ከተቃዋሚ ኃይሎች ለመደራደር ዝግጁ መሆን ብቻ ሳይሆን የመፎካከርያ ሜዳውም ለሁሉም እኩል ሆኖ እንዲደላደል “የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ” ቃል ስለገቡ፣ ጠ/ሚንስትሩ ይህን ቃል በተግባር ለመተርጎም ይረዳቸው ዘንድ፣ የጸረ ሽብር ዓዋጁን ከማንሳት ባሻገር፣ አዲስ የምርጫ ዓዋጅና በዓዋጁም መሰረት ሁሉን ዓቀፍ የሆነ አዲስ የምርጫ ቦርድ እንዲሰየም አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ባይ ነኝ። ሁሉን ዓቀፉም የምርጫ ቀን ካሁኑ በግልጽ ቢነገርና ተፎካካሪ ኃይላትም ከያሉበት መጥተው ለምርጫው የሚያበቃቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ መጋበዝ ተያያዥ የሆነ የጠ/ሚንስትሩ አስቸኳይ የቤት ሥራ ይመስለኛል።
በኔ ግምት፣ በኢትዮጵያ የታቀደው ጥገናዊ ለውጥ፣ የደቡብ አፍሪካን የአፓርታይድ ሥርዓትን ለማጥፋትና የሶቪዬት ሕብረትን ዓላማውን የሳተ ሶሺያሊስት ሥርዓትን ለመለወጥ ዴክለርክና ጋርባቾቭ ካካሄዷቸው እንቅስቃሴዎች ጋር አንዳች ዓይነት ተመሳሳይነት ያለው ይመስለኛል። በመጀመርያ ደረጃ የሁለቱም የጥገና ለውጥ ጠንሳሾቹ ማለትም ዴክለርክና ጋርባቾቭ ልክ እንደ ጠ/ሚንስትራችን ሥርዓቱ ኮትኩቶ ያሳደጋቸውና በታሪክ አጋጣሚ ለመሪነት የበቁ ናቸው። ህዝባዊው እንቢተኝነት ገፍቶ እስካወጣቸው ድረስ በደቡብ አፍሪካም ሆነ በሶቪዬት ሕብረት ነባሩን ሥርዓት የመለወጥ ችሎታ ያለው ምድራዊ ኃይል ያለ አይመስልም ነበር። ባገራችንም እንደዚሁ እስካለፈው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ውይይትና ምርጫ ድረስ የህወሃትን የበላይነት ንዶ ኢህአዴግ ይመራበት የነበረውን ዲሞክራሲያዊ ማዕከልነትን የመሻር ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ የገመተ አልነበረም። ግን ያልታሰበው ተፈጸመ። ኦሮማይ!
በደቡብ አፍሪካ ዴክለርክ በነበራቸው ቁርጠኛ የሞራል የበላይነት ተመርተውና የራሳቸውን ፓርቲ የዘመናት የአድልዖ መሪህን በመቃወም ጥገናዊ ለውጥ ለማምጣት ሲወስኑና ለሃያ ሰባት ዓመት እስር ቤት የነበረውን ማንዴላን ፈትተው የመሪነቱን ቦታ በህዝባዊ ምርጫ ውጤት እንዲረከባቸው ሁኔታዎችን ሲያመቻቹላቸው፣ ከፓርቲው አባላት ይህ ነው የማይባል ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር። ሳይደግስ አይጣላም የሚሉት ሆነና ማንዴላም የትጥቅ ትግሉን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ ህዝቡን ለሥልጣን ለማብቃት ተስማማ። ሁሉም እንዳሰቡት ተስተካከለና ማንዴላም አሸነፎ የአፓርታይድም ሥርዓትም ተቀብሮ ያላንዳች የርስ በርስ ግጭት የዛሬዋ ደቡብ አፍሪካ ሬፑብሊክ የግዛትና የህዝቦችዋን አንድነት ጠብቃ ለመኖር ቻለች። በሶቭዬት ሕብረት ግን ታሪክ ባልታሰበ መንገድ የራሱን ቦይ ተከትሎ ፕሬዚዴንት ጋርባቾቭ የጀመሩት “የህዳሴና ግልጽነት” መመርያ አቅጣጫውን ስቶ ወደ የርስ በርስ ግጭት አመራ። ተቀናቃኛቸው ዬልሲን የጥገና ለውጡ ደጋፊ ሆኖ ከጎናቸው እንደመቆም ይባስ ብሎ ጥቂት የሌሎች ብሄር መሪዎችን አሰባስቦና አሳምኖ ሶቪዬት ሕብረት እንድትፈርስ መዶለት ጀመረ። ያሰበውም ተሳክቶለት ከሰባ ዓመት አብሮነት በኋላ አገሪቷ ለአስራ አምስት ተከፈለች። ሶቭዬት ህብረትም ፈረሰች።
የጋርባቾቭ የጥገና ለውጥ ጅማሬ ያልታሰበ አሉታዊ ውጤት ሊያመጣ የቻለው፣ የለውጡን መሰረታዊ ሃሳብ ከልብ የሚደግፉና በተግባር እንዲተረጎም የሚታገሉ አጋሮች ስላልተገኙ ይመስለኛል። አዎ የምዕራቡም ዓለም አገሪቷ እንድትፈራርስ ለዓመታት ይታገሉ ስለነበር የጋርባቾቭ ጥገናዊ ለውጥ ለነሱም ትልቅ ቀዳዳ ከፍቶላቸው ነበር። የፕሬዚዴንት ለማን ቡድን የጥገና ለውጥ እንቅስቃሴንና፣ ለውጡን ከግብ ለማድረስ ዶ/ር ዓቢይን ለጠ/ሚንስትርነት ሲያጩት፣ በሁኔታው ያልተደሰቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ምንኛ ይቃወሙ እንደነበር ብዙ አመላካች ነገሮች የታዩበት ነው። በምርጫው ወቅት ከአርባ አምስቱ የህወሃት አባላት አንድም ግለሰብ እንኳ በስህተት ለዶ/ር ዓቢይ ድምጽ አለመስጠቱ ዋና አመላካች ነው። የጠ/ሚንስትራችንም ትልቁ ፈተና ጥገናዊ ለውጡ ሁሉንም በዕኩልነት እንዲያስደስት ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ አጄንዳ ማዘጋጀት ይመስለኛል። አዎ ጠ/ሚንስትሩ የፈለጉትን አጄንዳ ለፓርላማው ቢያቀርቡ የኦህዴድና የብአዴን ወዳጅነት እስከቀጠለ ድረስ ተደምረው የቁጥር የበላይነት አላቸውና ያላንዳች ጭንቀት ሊያስጸድቁ ይችላሉ። ችግሩ ግን “ማሸነፉ” ላይ ሳይሆን በአብላጫ ድምጽ የተላለፈው ውሳኔ አንዳንድ ቡድኖችን አስቀይሞ አላስፈላጊ ወደ ሆነ አገራዊ ቀውስ እንዳያመራን ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ባይ ነኝ። ይህ የለመድነው “ተቃዋሚ ላይ ድል መቀዳጀት” ብሎ ነገር መቆም አለበት። ባገራችንም ብዙ ኢትዮጵያውያን ዴክለርኮች ያሉትን ያህል ብዙ ዬልሲኖች እንዳሉም መገንዘብ አለብን ለማለት ያህል ነው።
የኛ ሚና፣
ሳያድለን ቀርቶ ሥልጣንን በጉልበት እንጂ በሰላማዊ መንገድ ካንደኛው ርዕሰ ብሄር ወደ ሌላው ርዕሰ ብሄር ሲተላለፍ በህይወት ዘመናችን ስላላየን፣ የዛሬውን የሥልጣን ሽግግር ስንመለከተው ስሜታችን መደበላለቁ ተፈጥሮያዊ ይመስለኛል። በዚያው ልክ ደግሞ አብዛኛውን ዕድሜያችንን በተቃዋሚነት ላሳለፍን ያንጋፋው ትውልድ ሰዎች፣ ጠ/ሚንስትራችን ያስተላለፋቸውን መልዕክቶች በቅንነት ለመቀበል ያስቸገረን ይመስለኛል። ይህም ደግሞ ተፈጥሮያዊ ይመስለኛል። ሥር ነቀል አብዮታዊ ለውጥ ፈላጊ ጓደኞቼ በጠ/ሚንስትሩ ንግግር ውስጥ አንዳችም አዲስና ጋባዥ ነገር ያላገኙ የመሆናቸውን ያህል፣ ጥገናዊ ለውጥ ፈላጊ ጓደኞቼ ደግሞ በንግግሩ የተመሰጡና አንዳች ዓይነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን አይተውበታል። እኔም በጠ/ሚንስትሩ ንግግር ውስጥ አንዳች ዓይነት ተስፋ ስላየሁበት ከዚህ ቀጥሎ የማሰፍራቸውን አንዳንድ የግሌን ሃሳቦች እንደ አንድ ጥገናዊ ለውጥ ደጋፊ ለማቅረብ ተመኘሁ። ይህንን ስል፣ ጠ/ሚንስትሩ የደረደሯቸው ችግሮችና አብረን መፍትሄ እናግኝላቸው ዘንድ በጋበዙን ብቻ ረክቼ ሙሉ በሙሉ የህዝቡ ጥያቄ ተመልሷል ብዬ ካማሰብ ሳይሆን፣ ብልጥ ልጅ ያገኘውን ይዞ ያለቅሳል እንደሚባለው፣ ጠ/ሚንስትሩ ያስቀመጧቸውንና ቃል የገቡልንን እነዚህን ጉዳዮች “ባንድ አፍ” ብዬ፣ አየር ሳይገባበትና ሳይሟሽሽ ባስቸኳይ እንዲፈጽሙልን እጠየቅሁ መሰረታዊዉን ችግር በጋራ የምንፈታበትን ሰፊ መድረክ እንዲያመቻቹ ከማለት አንጻር ነው። በፖሊቲካ ሳይንስ ቋንቋ “ሂሳዊ ድጋፍ” የሚባለው መሆኑ ነው። እንዳስፈላጊነቱ ድጋፌን ለመስጠት፣ ካላመንኩበት ደግሞ የማንሳት መብቴን መጠቀም ማለት ነው።
በኔ ግምት አሁን ጠ/ሚንስትራችን እፈጽማቸዋለሁ ብለው የደረደሯቸውን የቤት ሥራዎች ለብቻዬ እወጣቸዋለሁ ብለው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታንጎን ለመደነስ ሁለት መሆን ያስፈልጋል እንደሚባለው የኛም ድርሻ አለበት ለማለት ያህል ነው። አዎ የማስፈጸሙ ኃይል ከኛ ይልቅ በሳቸው እጅ ቢሆንም፣ በበኩላችን ባሁኑ ሰዓት ልናደርግ የምንችለው ብሄራዊ ዕርቁን ለማምጣት በሚደረገው ሙከራ ውስጥ ለመካፈል ዝግጁ መሆናችንንና ለዚህም ደግሞ ጠ/ሚንስትራችን በአስቸኳይ የጸረ ሽብር ዓዋጁን እንዲያስነሱና ተፎካካሪ ኃይላት ባገሪቷ ውስጥ በነጻ ለመዘዋወርና ውጭ አገር ያሉትም በተለይም በሽብርተኝነት የተፈረጁ የፖሊቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ተመልሰው ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያላንዳች እክል የሚገናኙበትንና የሚወያዩበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ እንጠይቃለን። ጠ/ሚንስትራችንም እነዚህንን ቃል የገቡልንን ጉዳዮች በተግባር መተርጎም ከጀመሩ እኛም ከሳቸው ጋር በመሆን የምንመኘውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት በሚደረገው ርብርቦሽ ውስጥ ያላንዳች ማመንታት ተካፋይ ለመሆን ዝግጁ ነን። ዋናውና መሰመር ያለበት ጉዳይ ግን የለውጡን ሞተር ማስነሻ ቁልፍና የተሽከርካሪውን መሪ የጨበጡት ጠ/ሚንስትራችን መሆናቸውና እሳቸው እንደ ሾፌር የሚሄዱበትን አቅጣጫና መድረሻቸው በግልጽ ካልተነገረን አብረን ለመሳፈር የሚከብደን ይመስለኛል። ስለዚህ ክቡር ጠ/ሚንስትር፣ በኛ በኩል እፈጽማቸዋለሁ ያሉትን ተግባራት በሙሉ መዝግበን ይዘን እስዎ “ሜዳው ተደላድሏልና ኑና ታንጎ እንደንስ” ብለው ፊሽካ እስኪነፉ ድረስ በተጠንቀቅ ቆመን እየጠበቅን ነው። ኳሷ ያለችው በስዎ ሜዳ ነውና ጊዜ ሳይፈጁ ወደ እኛ ሜዳ ቢመልሷት ደስ ይለናል። ያሰቡትና ቃል የገቡልንን ጉዳዮችን እንዲፈጽሙ ደግሞ ፈጣሪ ይተባበርዎት ዘንድ በሃሳባችንና በጸሎታችን አንለይዎትም።
*****
ባይሳ ዋቅ-ወያ፣ ጄኔቫ 3 አፕሪል 2008 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Mulugeta Andargie says
እናንተ ጨበርባሪዎች!!! በህገ መንግስቱ ቅንጣት እንኳን ድርድር ኣናደርግም። ህገ መንግስቱ ይታረም ወይም ሌላ ነጥብ ይካተትበት የምትሉ ከሆነ ነጥቡን ኣቅርባችሁ ፓርላማው ሳይውል ሳያድር የማከናወን ግዴታ ኣለበት። ምንም ዓይነት ተፅዕኖም ይሁን ጭፍለቃ ኣይደረግም። ለማንም ፈረንጅ እየዞርክ ብታመልክት፤ ፈረንጅ ባገራችን ጉዳይ ኣይመለከተውም። ሁለተኛ፣ የፀረ ሽብር ዓዋጁን በተመለከተ ከሆነ፣ያለጥርጥር ዓዋጁ ኣካባቢን፣ሃገርን፣ኣሕጉራዊን ተስተውሎ የተደፈ እንጂ፣ በዘፈቀደ፣ ሲያሻው የሚደለዝ፣ ካልሆነም ወደ መደርደሪያ የሚሸጎጥ ኣይደለም። የሚስተካከልበትን ቦታ መጠቆም ያባት ነው።