እኔማ የዚህ መንግስት ባህርይ ከቶውንም ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እንደ እኔ እንደኔ “መንግስት” ጃጅቷል ባይ ነኝ፡፡ በመጃጃት የሚታይ ስዕብና በዚህ መንግስት እያየሁ ነው፡፡ የአማራ ክልል መንግስት ጳጉሜ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ምን እንደታየው በውል ባላውቅም ከመሬት ተነስቶ የመንግስት ተሸከርካሪ አያያዝ፣ አጠቃቀምና የንብረት አስተዳደር መመሪያ አሻሽያለሁ ብሎ በሌጣ ደብዳቤ ለመንግስት ተቋማት ሰርኩላር አስተላልፎ ነበር፡፡ በክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ተላላኪነት ለክልሉ ቢሮዎች የተላከው ደብዳቤ ከመስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ወይም የሥራ ኃላፊዎች ለሥራ ጉዳይ ክልሉን ለቀው ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ የሚመሩትን ተቋም ተሸከርካሪ ይዘው እንዳሄዱ የሚያሳስብና በተማከለ መንገድ በከተማው በሚዘጋጁ ተሸከርካሪዎች መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳውቅ ነበር፡፡
በተማከለ መንገድ በሚዘጋጁ ተሸከርካሪዎች መጠቀም የሚችሉ ብሎ ደብዳቤው ያሳወቃቸው የሥራ ኃላፊዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ ም/ርዕሰ መስተዳድርና በዚህ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች፣ የክልሉ ም/ቤት አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የካቢኔ አባላት የሆኑት የቢሮ ኃላፊዎች፣ ዋና ኦዲተር፣ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች የዞን ዋና አስተዳዳሪዎችና የሜትሮፖሊታን ከተማ ከንቲባዎች ናቸው፡፡
የተጠቀሱት ኃላፊዎች አዲስ አበባ ለሚደረጉ ማንኛውም ስብሰባዎች ወይም ሌሎች ሥራዎች ወደ አዲስ አበባ በአይሮፕላን የሚሄዱ ከሆነ ከአይሮፕላን ማረፊያ የሚቀበላቸውና በቆይታቸው ወቅት በማዕከል አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ ተሸከርካሪዎችን ወይም በቀን 1200 ብር ያልበለጠ የመኪና ኪራይ በሕጋዊ ደረሰኝ መጠቀም እንደሚችሉ ያተተው ቀላጤው ለከተማ አገልግሎት ተጨማሪ ተሸከርካሪ ማንቀሳቀስ እንደሌለባቸው አስረድቷል፡፡
የተሽከርካሪ ስምሪትና የማስተዳደሩን ተግባር ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሥልጣን የሰጠው ይኸው መመሪያ በክልሉ የካብኔ አባላት የሆኑ ቢሮዎች ምክትል ቢሮ ኃላፊዎችና በምክትል ቢሮ ደረጃ የተሾሙ ሹማምንቶች ወደ አዲስ አበባ በአይሮፕላን የሚሄዱ ከሆነ በማዕከል በተዘጋጁ ተሸከርካሪዎች መጠቀም የማይችሉ ከሆነ በቀን ከብር 600 ያልበለጠ የመኪና ኪራይ በመጠቀም በህጋዊ ደረሰኝ ማወራረድ እንደሚችሉ ያትታል፡፡
በመመሪያው የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ተላልፎ የተገኘ የሥራ ኃላፊ ከተፈቀደለት የገንዘብ መጠን በላይ ያለውን ወጪ በግሉ እንደሚሸፍንና በመመሪያው ከተፈቀደው ውጪ ሂሳብ ያወራረደ የመ/ቤቱ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አስተዳደርም ተጠያቂ እንደሚሆን ያሳውቃል፡፡
ይህ ደብዳቤ በየተቋሙ ከደረሰ በኋላ መመሪያው የሚመለከታቸው የከፍተኛ አመራር ሹፌሮች ቅስማቸው በመሰበሩና መንግስት ጉሮሮአቸው ላይ በመቆሙ አለቆቻቸውን ከኤር ፖርት ለመቀበልና ለመሸኘት ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ከአንድ ተሳፋሪ ከባህር ዳር አዲስ አበባ 450 ብር የሚያገኙት የትራንስፖርት ገቢ ሲያጡ ቅሬታ አይሉት ሐዘን ኡኡታቸውን ባገኙት አጋጣሚ ማሰማት ጀመሩ፡፡
በቅሬታ መልክ የሚያስተጋቡት የተሻሻለው መመሪያ የአሽከርካሪዎች የሥራ ሁኔታ ያላገነዘበና ለይስሙላ የወጣ መመሪያ እንደሆነና ከመንግስት የሥራ ሰዓት ውጭ ከኃላፊዎች ጋር እስከ ምሽት እያመሸን፣ ቤተሰቦቻቸውን እያመላለስንና የቤት ወጪያቸውን እየገዛና ለምናደርስበት የትርፍ ሰዓት አገልግሎት አበል ሊታሰብልን ይገባል ብለዋል፡፡
የወጣው መመሪያ እርስ በርሱ እንደሚቃረን በክልሉ በየተቋማቱ ያሉ የግዥ፣ ፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች ቢናገሩም የክልሉ መንግስት ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ህሳቤ መመሪያው ለመተግበር ሲነሳ በመመሪያው የተጠቀሱ ክልሉ ካብኔዎች በአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ከተማ በማዕከል ደረጃ በሚዘጋጀው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ የተወከሉት የወያኔው ኤፈርት ድርጅት በሚያቀርባቸው ተሸከርካሪ መሆኑን የክልሉ መንግስት ሲያውቅ መመሪያውን ማሻሻል ገባ፡፡
ሰሞኑን በየተቋማቱ የተሠራጨው የማሻሻያ ደብዳቤ የክልሉን መንግስት መጨነቅ የሚያበስር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ በቁጥር አብክመ/ ገኢት/ክበ-01/450 በቀን 20/02/2010 ዓ.ም የተሠራጨው ደብዳቤ … በማዕከል ይዘጋጃሉ የተባሉት ተሸከርካሪዎች በግዥና በሌሎች ምክንያቶች ስለዘገዩ አመቻችተን በሌላ ደብዳቤ እስከምናሳውቃችሁ ድረስ ከዚህ በፊት በነበረው የተሽከርካሪ አጠቃቀም መመሪያ መሠረት እንዲፈጸም እናሳውቃለን ይላል፡፡
እኔን የገረመኝ ተሻሻለ የተባለው መመሪያ ሦስት ወራት ሳይሞላው ውድቅ መደረጉ ሳይሆን በማዕከል ይዘጋጃል የተባለው የትራንስፖርት አገልግሎት በወጉ ሳይቀርብ መመሪያ ለማሻሻል የገባው የአማራ ክልል ካብኔ ተግባር ነው፡፡
የክልሉ ካብኔ ውሳኔ አንድ አባባል አስታወሰኝ፡፡ አንዱ ባልንጀራውን የመጥረቢያ እጀታ በምን ተቆረጠ ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ተጠያቂው ባልንጀራም በመጥረቢያ ስል መለሰ፡፡ ጠያቂውም መልሶ መጥረቢያ ከመፈጠሩ በፊት ኧረ ቀደም ቀደም ብሎ ቢጠይቀው ምላሽ አጣለት ይባላል፡፡ የክልሉ መንግስትስ ከነገረ ቀደም የመንግስት ተሸከርካሪ አያያዝ፣ አጠቃቀምና የንብረት አስተዳደር መመሪያ ማሻሻል ያስፈለገው ለምን ይሆን? የኔ ጥያቄ ነው፡፡ ምላሹ መንግስት ቢጨንቀው ነው፡፡ (ከኢንተርኔት የተገኘው ፎቶ የብአዴን ቢሮ ነው)
ጲላጦስ ከጣና ዳር (ummp4.20@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply