• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የኢትዮጵያን ፍላጎት ያልተረዳ መንግስት ኢትዮጵያን ሊመራ አይችልም

November 28, 2016 02:35 am by Editor Leave a Comment

በቅርቡ ፋና ብሮድካስት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ “ኢሕአዴግን” የወከሉት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ምክትል ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን  ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ ጥቂት ለመወያየት ነው የዛሬው አሳቤ። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ እኚህ ሰው የተናገሩት ብዙው ነገር ከተለመደው የተለየ ባይሆንም በተለይ የኢትዮጵያን ፍላጎት በተመለከተ የፓርቲያቸው አመለካከትና ጥናትና ምርምር ምን መሰረታዊ ችግር እንዳለበት መመርመር የዚህን መንግስት መሰረታዊ ችግሮች እንደገና ለማሳየት ይጠቅማል። በመጀመሪያ ይህ ውይይት ለምን ተዘጋጀ? ካልን ምን አልባትም በሃገሪቱ የተነሳውን ግዙፍ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የተለያዩ ሃይሎች መንግስት ዲያሎግ እንዲያደርግ ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ የተዘጋጀ ይመስላል። ታዲያ የግብር ይውጣ ነገር ብቻ መሆኑን የሚያሳየው የህዝብ ልብ ያረፈባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥናታዊ ፅሁፍ እንዲያቀርቡ አለመደረጉ ነው።

የውይይቱ ርእስ  ‹‹የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከየት ወዴት? ፈተናዎችና መልካም ዕድሎች›› የሚል ነበር። አቶ በረከት በዚሁ ስብሰባ ላይ ሲናገሩ የኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ እንደሆነ ዴሞክራሲ ችግሮች ቢኖሩም እያደገ እንደሆነ ገልፀዋል። አቶ ልደቱ ደግሞ እድገቱን “አስደናቂ” ይሉታል። በዚህ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ጥቂት ትችት ላቅርብና ወደ ዋናው ትችቴ እመጣለሁ። የኢኮኖሚ ልማትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ህዝብ እድገት አለ የለም  እያለ መከራከር ርባና አለው ብሎ የሚያምን አይደለም። ከሚታየው እድገት ተጠቃሚ ነን ወይስ አይደለንም? የሚለው ጥያቄ ነው ሚዛን የሚደፋው።1 ምን አልባት ለገዢው ፓርቲ አባላትና ለአቶ ልደቱ ፓርቲ አባላት ትምህርት የሚሰጥ ከሆነ አዲስ አበባ በነበርኩበት ጊዜ የገጠመኝን ላውጋችሁ። ይህን ገጠመኝ የማነሳው ምሳሌው መጠቃለል የሚችል (generalize ሊደረግ የሚችል) ጥሩ ማሳያ ስለሚሆን ነው።

እንግዲህ ይሄውላችሁ ሙዚቃ በጣም እወዳለሁ። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን ወደ ሸራተን አዲስ አመራሁ። ሸራተን አልፎ አልፎ የምሄደው ለምንም አይደል። በአንድ ነገር ተማርኬ ሰለነበር ነው። ሸራተን ጀርባ አንድ ፋውንቴን አለ። እዚህ ፋውንቴን ውስጥ እቀመጥና የውሃዎችን ወረብ ማየት ደስ ያሰኘኝ ነበር። የዘንባባ ማር ነሽ … እያለ ለስላሳ ሙዚቃ ሲደምቅ የተለያየ ቀለም ያላቸው ውሃዎች የሚያደርጉት ትርኢት በጣም ይመሰጣል። ነፋሻው የአዲስ አየር ከዚህ የውሃ ወረብ ጋር የውነት ደስታን  ያድላል። ታዲያ እንደለመድኩት አንድ ምሽት ወደዚያው አመራሁ። ከወትሮው ለየት ያለ ነገር በር ለይ ገጠመኝ። በግምት አንድ አምስት ስድስት የሚሆኑ ወጣቶች ከሰኪዩሪቲው ጋር አተካራ ይዘዋል። ሰኪዩሪቲው እነሱን ገፋ እያደረገ እኔን ይግቡ ይለኛል። ሁኔታው እንዲገባኝ ፈልጌ ነበርና ቆሜ ማዳመጤን ቀጠልኩ። እጆቿን አጣምራ ፈንጠር ያለችውን ወጣት ጠጋ ብየ ጠየኳት።

ምን ሆናችሁ ነው ሲስተር?

አላስገባ ብለውን ነው… ፊቷን አኮማትራ

ለምን?… ገርሞኝ ነበርና ጠየኩ።

አይ… ዛሬ ቀኑ የነዚያ የሁለቱ ጓደኞቻችን የጋብቻ (የልደት ብዙ እርግጠኛ አይደለሁም) ልናከብር  ነበር። አለች።

እሺ…

እና… እዚህ ፎቶ እየተነሳን ልናከብር ነበር።

እሺ…

ዘበኛው የሚለው አገልግል ይዞ መግባት አይቻልም ነው የሚለው። ሻይ በፔርሙዝም ይዘን ነበር አለችኝ።

ምንም መልስ ሳልሰጥ እንደገባኝ በጭንቅላቴ ገልጨላት ጉዳዩን መከታተል ቀጠልኩ። ሰኪዮሪቲው በትህትና የሚያስረዳ ይመስላል ከለከላቸውና እነዚያ ወጣቶች በተንተን ብለው ወደ ሁዋላ ጉዞ ቀጠሉ። እኔ የያዝኩት የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር ባለመኖሩ እንደገና እንድገባ በትህትና ተጋበዝኩ። ገባሁ። ከዚያው ከፍውንቴኑ ውስጥ ቁጭ ብየ ማሰላሰሌን ቀጠልኩ…

የኔ ቅሬታ ለምን እነዚህ ወገኖች ሻይና እንጀራ በወጥ  ይዘው መግባት አልቻሉም አይደለም። ነገር ግን ከዚህ በፊት ሰዎች ይዘው ይገቡ እንደነበር ሰምቼ ነበር። ይህ ሰኪዩሪቲ የሚከለክለው እነዚህን ብቻ ይሁን የክልከላ ትእዛዝ ከሆቴሉ ማነጅመንት ይተላለፍ አላውቅም። ይሁንና ግን ሆቴሉ ወስኖ ከሆነ ውሳኔው ትክክል ሊሆን ይችላል። ይህን ከፈቀደ ሆቴሉ ሊከስር ይችላልና። ቢዝነስ ነውና። አላማውም አይደለምና። በመሆኑም ሰኪዩሪቲውንም የሆቴሉን ማኔጅመንትም ውስጤ አልከሰሰም። ከዚህ ይልቅ የተማርኩት ኢትዮጵያን በትልቅ ስኮፕ ማየትን ነበር።

አቶ በረከት ቢገባቸው አለ የሚሉት ልማት ይህን ይመስላል። እነዚህ ወጣቶች በዚህ ሆቴል ውስጥ ሻይ እንኳን ለመጠጣት የሚያስችል አቅም የላቸውም። በዚህች ውብ ቀናቸው ብቻ ሻይ እንኳን ይዘው ዘና ለማለት አይችሉም። በርግጠኝነት ሻይና ለስላሳ በዚህ ሆቴል ውስጥ መግዛት ቢችሉ ሻይ ቤታቸው አፍልተው አይመጡም ነበር። ሻይ መግዛት ቢችሉ ሁሉን ትተው በሻይ እንኳን ይደሰቱ ነበር። ግን አይችሉም። ይህ ነው የኢትዮጵያ እድገት። ጥቂት ታይተዋል የተባሉ ዘመናዊ ግንባታዎች ለብዙሃኑ አይቀመሱም። በህንፃዎች ጎን ቆሞ ፎቶ መነሳት የሚሰጠው ርካታ ካለ ያ ብቻ ነው ለብዙሃኑ ያለው ትርፍ። ለአንዳንዱ ደግሞ ርካታ ሳይሆን ሃዘንን ያመጣል። ከሚያየው ነገር ጥቂት መጠቀም ካልቻለ ስነ ልቡናው ይጎዳል። እነዚያ ሸራተን እንዳይገቡ የተከለከሉ ወጣቶች ገብተው ቢሆን ብለን እናስብ። የራሳቸውን  ሻይ በእጀራ በልተው ፎቶ ተነስተው ቢሄዱ ምን አይነት ማስታወሻ ውስጣቸው ይቀራል? ሙሉ ደስታ የሌለው የዘመኑን ያልተመጣጠነ እድገት ነው የሚያስታውሳቸው። የወጣቶቹ ጉጉት ግን ያሳዝናል።

በአጠቃላይ ግን እድገቱ ህዝቡን ተጠቃሚ ያላደረገ ነው። መንግስት እድገት አለ ካለ የሚጠየቀው ጥያቄ የኑሮ ሁኔታ መሻሻልን ነው። እድገቱ የሰራተኛውን ትዳርን የማሸነፍ አቅም አጎልብቷል ወይ? ገበሬው ይዞታውን እያሰፋ ምርትን እያሳደገ ነው ወይ? ህፃናት አልሚ ምግብ እያገኙ ይማራሉ ወይ? ጡረተኞች ከግሽበቱ ጋር የሚፎካከር ገቢ ያገኛሉ ወይ? አስተማሪው ከትናንቱ ዛሬ ተሽሏል ወይ? ማህበራዊ ተቋማት የህዝቡን ፍላጎት እያረኩ ነው ወይ? የመብራት አቅርቦት ህዝቡን አርክቷል ወይ? ወዘተ ነው… መታየት ያለበት። አቶ ልደቱ በበኩላቸው በተሰራው አስፋልት ላይ መኪና እየነዱ እድገት የለም የሚሉ እንዳሉ ይገልፃሉ። መኪና እየነዱ እድገት የለም የሚሉ ካሉ እነሱ ከሰፊው ህዝብ የወገኑ ናቸው። መንገድ አልተሰራም አይደለም ጥያቄው። መንገድ መሰራቱን አይደለም የሚነቅፉት። መንገድ በጣም አስፈላጊ ነው። ነገር ግን  የአውቶቢስ ከፍሎ መሄድ የማይችል ህዝብ በዝቶ በባዶ እግሩ የሚኳትነው ገበሬ ይህ እድገት አያስደንቀውም። እድገት በመሰረቱ የህብረተሰብን ፍላጎት ማርካት ማለት ነው።ብዙዎችን ድሃ እያድረጉ ጥቂት የናጠጡ ሃብታሞችን ማውጣት ጭካኔ እንጂ እድገት አይባልም።  በአጠቃላይ እድገቱን በሚመለከት እንዲህ ካልኩ አቶ በረከት ሲናገሩ ትኩረቴን በጣም ወደሳበው ጉዳይ ልመለስ።

እኚህ ሰው ምን አሉ? በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ብዙዎች ያልተረዱት ነገር አለ አሉ። ይህ ብዙዎች ያልተረዱትና ገዢው መንግስት የተገለጠለት እሳቸው በምክትል ሃላፊነት የሚመሩት የፓሊሲና ምርምር ተቋም የደረሰበት  ነገር ደግሞ ኢትዮጵያ የገበሬ አገር መሆኗ እና ይህ 80 በመቶ የሚሆነው ገበሬ ደግሞ ያለው ፍላጎት አንድ ፍላጎት መሆኑን ነው። ይህ ነገር በርግጥ አዲስ ነገር ነው። ትኩረት ይስባል። እንደዚህ ሰው አባባል ገበሬው አንድ ፍላጎት ብቻ ስለሆነ ያለው ያንን አንድ ፍላጎት የሚያሟላ አንድ ፓርቲ ከተገኘ በቂ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የኢትዮጵያን ገበሬ አንድ ፍላጎት ኢህአዴግ የተባለው ድርጅት ስላሟላ ተቃዋሚዎች በገበሬው ውስጥ ቦታ የላቸውም ነው የሚሉት። ይሄ በጣም ገራሚ ነገር ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ህብረተሰብ አንድ ፍላጎት ብቻ ነው ያለው ብሎ ማመኑ በራሱ የስህተቶች ጥግ ነው። መንግስት ይህን እምነት ብሎ “ፈንዳመንታል ሃቅ” ማለቱ በራሱ ያስገርማል። በህብረተሰብ ሳይንስ ውስጥ ፓለሲ ለመቅረፅም ይሁን የእድገት አቅጣጫ ለመተለም የህብረተሰብ ፍላጎት (need assessment የምንለው ነገር) ወሳኝ ነው።  የህብረተሰብ ፍላጎት ውስብስብና ብዙ ነው። ይህ ፍላጎት መጠናትና ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ህብረተሰብ የማይፈልገው ልማት ቢሆንም እንኳን ዋጋ የለውም። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ህዝብ ዋና ችግር የውስጥ ለውስጥ ድሬኔጅ ወይም መፋሰሻ ሆኖ  መንግስት የጠገበ ቀለበት መንገድ ቢሰራ ልማቱ የህብረተሰብን ፍላጎት ያላስቀደመ ይሆናል። ወንዞች ሁሉ ቆሽሸው ህዝቡ በየደጁ የሚደፋው ውሃ መሄጃ አጥቶ እያለ ከፍተኛ የቀለበት መንገድ ቢሰራ ልማቱ የህብረተሰብን ዋና ፍላጎት ያላስቀደመ ይሆንና እንደ ዶክተር አክሎግ ቢራራ አገላለፅ ብልጭልጭ ልማት (glitz  economy) ይሆናል። የቀለበት መንገድ መስራቱ አስፈላጊ ቢሆንም የብዙሃኑን ፍላጎት ያስቀደመ ካልሆነ ልማቱ ልማት አይባልም።

እንግዲህ አቶ በረከት ኢትዮጵያን ስንት ውስብስብ ችግር ያለባትን አገር ባለ አንድ ጥያቄ ሲያደርጓት ያሳዝናል። ለመሆኑ ያ የገበሬው አንድ ፍላጎት ምን ይሆን? ምን አልባት ግብርናውን ማሳደግ ከሆነ ለዚህ እድገት ለመሆኑ ገበሬው አማራጭ የፓለሲ አቅጣጫዎች ሁሌም ከደጁ አይሻምና ነው አንድ ፓርቲ ይበቃል የሚባለው? ግብርና እኮ ሰፊ መስክ ነው። ግብርናው ያድግ ዘንድ የግብርናው ኢንዱስትሪ መለወጥ አለበት። መብራት ስልክ ያስፈልጋል። ገበሬው ጤናማ መሆን አለበት።ትምህርት ይሻል ወዘተ. ለመሆኑ የመድብለ ፓርቲ ፅንሰ ሃሳብ መነሻውስ ይሄ ነው ወይ? ለአንድ ጥያቄ  አንድ ፓርቲ ለሁለት ጥያቄ ሁለት ፓርቲ የሚሉ ፍልስፍናስ ከየት መጣ?  ለመሆኑ የገበሬው ጥያቄ አንድ ከሆነ የከተሜው ከአንድ በላይ ስለሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ ትንሽ ቦታ አላቸው ከሆነ ነገሩ ከተሜው መብራት ውሃ ስልክ…. ስለሚፈልግ አንድ ፓርቲ ለመብራት አንድ ፓርቲ ለውሃ ወዘተ ነው ማለት ነው የመድብለ ፓርቲ ፅንሰ ሃሳብ? ያሳዝናል። በመሰረቱ የገበሬውን ጥያቄ እንድ ናት ማለት በራሱ ገበሬውን መሳደብ ፍላጎቱን መርገጥ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ገበሬ በጥያቄ የተከበበ የታል?  ለመሆኑ ከተሜው የሚፈልገውን የውሃ የመብራት የስልክ የጤና የመንገድ ፍላጎቶቹ ገበሬው አይሻም? የኢትዮጵያ ገበሬ ፍላጎት ብዙ ነው። ይህን መረዳት ከፓለቲከኞች ከፓሊሲ አውጭዎች ይጠበቃል።  በህብረተሰብ ሳይንስ ውስጥም የሰው ልጅ ፍላጎት ውስብስብ ነው። ገበሬው ብዙ መንፈሳዊና ስጋዊ ፍላጎቶች  አሉት። አቶ በረከት   የተጠቀሙት ሎጂክ ማለትም

“ገበሬው አንድ ፍላጎት ነው ያለው

80 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ገበሬ ነው

ስለዚህ ኢትዮጵያ አንድ ፍላጎት ነው ያላት።”

የሚል ነው።

በሳቸው ትንታኔ ደግሞ ለአንድ ጥያቄ እንድ ፓርቲ ይበቃልና ኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን አትፈልገውም አይነት ነው ዋናው መደምደሚያ። መድብለ ፓርቲን እያኮሰሱ ነው። የሚያሳዝነው ለዚህ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር ለሚያቀነቅነው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ የፈጠሩት የሙገታ ሃሳብ argument በጣም የወረደ ነው። ኢትዮጵያ አንድ ፓርቲ ነው የሚያሻት ብሎ ሰው ያምን ዘንድ ይህ ሙግት አደባባይ መውጣት አልነበረበትም።እኚህ ሰው በዚሁ ኮንፈረንስ ላይ ሲናገሩ ቀደም ብለው ያሉት ነገር ቢኖር ህዝቡ ተቃውሞ የሚያሰማው ፍላጎቱ ስላደገ ነው ይላሉ። ይህ አባባል ኢትዮጵያ ባለ አንድ ፍላጎት አገር ናት ከሚለው እምነት ጋር ይላተማል። የሆነ ሆኖ እሳቸው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ  ጎዳና የወጣው እድገት እየገፋው በተፈጠረ ፍላጎት አይደለም። ትናንት መብላት የምንችል የምንበላው አጣን ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም ነው ጥያቄው። ከዚህም በላይ ህዝቡ የሃገሩ ህልውናም አሳስቦታል።

ለድንበር ለህዝቦች አንድነት የሚሰራ መንግስት ባለመሆኑ በቡድኖች መካከል ቅራኔን በመፍጠሩ ህዝቡ ለዘለቄታው ሃገሪቱ ወደ ችግር እንዳትገባም ስጋት ስላደረበት የመልካም አስተዳደር እጦት ስላንገበገበው ነው ጎዳና የወጣው እንጂ አቶ በረከት እንደሚሉት ጥጋብ የፈጠረው ተቃውሞ አይደለም።  ወጣቱን ጥጋብ አይደለም ለስደት የዳረገው። ወጣቱ የሚለው ስራ ጠፋ ነው። ስራ የለም ስንል መንግስት ራሱ መፍጠር ያልቻለውን ስራ ፍጠሩ እንባላለን። ጢም አውጥተን ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅ አቃተን ነው ጥያቄው። ከአቶ በረከት የተረዳነው የዚህን ህዝብ ብሶት የወለደውን ተቃውሞ መነሻ መንግስት እያንጓጠጠበት ነው። እድገት ያመጣው…ጥጋብ የወለደው …እያለ ይቀልዳል ማለት ነው። ይህ ዝንባሌ ለህዝቡ ጥያቄ ስድብ ነው። የሆነ ሆኖ ዋናው ነገር የመንግስት የፍላጎት አሰሳው ኢትዮጵያን የሚያይበት መንገድ ምን ያህል በሩቅ የተሳሳተ እንደሆነ የገዢው መንግስት ሰዎች መረዳት አለባቸው። ይህን መንግስት በየዋህነት የሚደግፉ ካሉ ሊጠይቁና ሊቃወሙ ለመድብለ ፓርቲ ስርአት መጠናከር ለለውጥ ሊታገሉ ይገባል። የህብረተሰቡን ፍላጎት የማያውቅ መንግስት ሊመራን አይገባም።

እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ይባርክ

geletawzeleke@gmail.com


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

Print Friendly, PDF & Email

60

SHARES
Share on Facebook
Tweet
Follow us
Share
Share
Share
Share
Share

Filed Under: Uncategorized Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • በጋምቤላ ህወሃትንና ኦነግ ሸኔን ትረዳላችሁ ተብለው የታሰሩ እንዲፈቱ ተጠየቀ January 25, 2021 03:07 pm
  • “…ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ አይደለም የሚሉ አካላት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው” – ዶ/ር ሙሉ ነጋ January 25, 2021 01:02 pm
  • የሶማሌና ኦሮሚያ መሥተዳድሮች ወሰንን በተመለከተ የሰላምና የጋራ ልማት ስምምነት አደረጉ January 25, 2021 12:50 pm
  • 125ተኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት ሊከበር ነው January 25, 2021 09:34 am
  • በመቀሌ ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የህክምና ግብዓቶች ክምችት መኖሩ ታወቀ January 25, 2021 02:47 am
  • ዊንጉ አፍሪካ (wingu.africa) በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የመረጃ ማዕከል ሊገነባ ነው January 24, 2021 01:23 pm
  • ኢትዮጵያ ድሮኖችን ማምረት ልትጀምር ነው January 24, 2021 02:40 am
  • የአየለ ጫሚሶ ቅንጅት ፈረሰ January 18, 2021 02:31 pm
  • ህወሓት ተሠረዘ!!! January 18, 2021 01:32 pm
  • ዓሲምባ፣ ሣልሳዊ ወያኔና ባይቶና ከመፍረሳቸው በፊት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተነገራቸው January 18, 2021 01:00 pm
  • ቤተሰቦች አስከሬን መውሰድ እንደሚችሉ ተነገረ January 14, 2021 06:48 pm
  • ስብሃት፤ “ከሞትን ቆይተናል፤ … አሁን የቀብር ሥነ-ስርዓታችን” እየተፈጸመ ነው January 14, 2021 01:37 pm
  • “ተመልሰን እንነሳለን” ያሉት ህወሓቶች ተመልሰው ወደማይነሱበት ተሸኙ January 13, 2021 01:12 pm
  • አፋር ነፃ አውጪ (ኡጉጉሙን) ለመጠቀም የታቀደው የህወሃት ሤራ ከሽፏል January 13, 2021 01:10 pm
  • ህወሃትን ወደ ጅቡቲ ለማሻገር ሲሰሩ የነበሩ የአፋር ታጣቂዎች በሰላም ወደ ክልሉ ገቡ January 13, 2021 06:47 am
  • በታህሳስ ወር ብቻ ከ344 ሚሊየን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ January 13, 2021 06:10 am
  • የብልፅግና ፓርቲ ቀጣይ ፈተና ምን ሊሆን ይችላል? January 13, 2021 04:10 am
  • ለትምህርት እንዲሆነን January 11, 2021 01:20 pm
  • “ከተቀበሩበት የጃርት ጉድጓድ ነው ያወጣናቸው” መቶ አለቃ ስዩም ቱርቦ January 11, 2021 12:11 pm
  • የተደመሰሱና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የወንበዴው አባላት ይፋ ሆነ January 7, 2021 01:16 pm
  • ዐቢይና መኮንኖቹ በመቀሌ፤ “ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” December 13, 2020 02:36 pm
  • ወንበዴው ህወሓት ከ1.4 ትሪሊዮን ብር በላይ ዘርፎ በውጭ አገራት ባንኮች አስቀምጧል December 8, 2020 01:05 am
  • ማይካድራ – የትህነግ የዘር ማጥፋት ጥግ ቋሚ ምስክር December 8, 2020 12:57 am
  • የወልቃይት ጠገዴ እናቶች ሰቆቃ ሲታወስ December 8, 2020 12:50 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2021 · Goolgule