እንዴትሀገር (ህዝብ) ይጥፋ?
ያለመተማመን ስለዘራን ዘር
እንሰበስባለን የማያልቅ ‘መከር’።
‘’መግዛት’’ እውቀት ሆኖ፣ ገንዘብና ሀይል
አቋራጭ ጎዳናው ‘መቦልተክ’ ሆኗል።
ሃይማኖት ተንቃ ስትሆን መቀለጃ
የእግዚአበሄርም ቃል ሆነ ምነገጃ።
ሳይሰሩ ያገኙት ሀብት፣ ክብር – ዝና
ያስከብር ጀመረ መናቁ ቀረና።
ፈረሀ – እግዚአብሄር ከልባችን ወ’ቶ
ህገ – አውሬ ይገዛናል ሰው-ከሰው አባልቶ።
ለመሾም – መሸለም፣ መክዳት – መከዳዳት
ምግባራችን ሆኗል ዋናው ሀይማኖት።
እያለን የሌለን ስለሆን ተመፅዋች
መጠሪያችን ሆነ እናንተ ለማኞች።
እውነት ተገንዞ ስለተቀበረ
ውሸት ገዥ ሆነና ሰው ለ’ሱው አደረ።
ፍቅርና ሰላም ፈላጊ ስለአጡ
ተባረው ሄደዋል በአገር እንዳይመጡ።
በሌሎች ደም – እምባ፣ ንዋይ ማካበት
ስልጣኔ ሆነ ዘመናዊነት።
መተሳሰብ – ማዘን፣ ቅንነት – ጨዋነት
ሲወራም አንሰማም በተረትነት።
ወገን – ሀገር ማለት ወንጀል አድርገነው
ዘመናት አሳለፍን ቃሉን ከሰማነው።
ቁምነገር ተጠልቶ ስለተሰደደ
‘’ወቶ-ፎቶ’’ ወሬ እጅግ ተወደደ።
ምቀኝነታችን ቦታውን ያዘና
እንነጉደዋለን በጥፋት ጎዳና።
በክፋት በተንኮል ቀኑን አጨልመን
እርስ በርስ ተላለቅን አልተያይ ብለን።
መብቱን አሳልፎ ዜጋው ሰለሰጠ
በእጅ ያለውን ትቶ ማዶ ቀላወጠ።
እራሱን በራሱ ሰው ሰለአስናቀ
ባ’ገሩ እየኖረ ሀገሩን ናፈቀ።
ለስልጣን ነው እንጅ ‘’ለነብር ጅራት’’
ጊዜም የለን እኛ ድህነት ለማጥፋት።
ፍትህ – እኩልነት፣ ’ዲሞክራሲ’ እያሉ
መቀለድ ተለምዷል በህዝብ እየማሉ።
የጋራ መሆኗ ሀገርም ቀረባት
የበይ ተመልካች ፆም አዳሪ ሞላት።
ጥቂቶች በስልጣን በድሎት እንዲያድሩ
ስደተኛ ሆነ ሰው በገንዛ ሀገሩ።
እጅግ ስለከፋ የ’ኛ ሰው ጥላቻው
ይታመሳል ሀገር በሆነው ባልሆነው።
መግዛት ያቃተው ለመገዛት ሲሮጥ
ትውልድ ሁሉ አለፈ ያለነፃነት።
ጥፋት በጥፋት ላይ እያየን ሲስፋፋ
ቆም ብሎ የሚያስብ ‘’በቃ!’’ የሚል ጠፋ።
ህሊና ሰለአጣን ለምንሰራው ሥራ
ወገን ይነግዳል በወገን መከራ።
ፍርሀታችን በልጦ፣ ከሞት ፍርሀት
በቁም እንሞታለን በማይቀረው ሞት።
ሞት እንደሆን ላይቀር በዚህ ቢሉት በዚያ
እንዴት ሀገር (ህዝብ) ይጥፋ? የሌለው መተኪያ።
——–//———
ፊልጶስ / e-mail: philiposmw@gmail.com
Leave a Reply