
“ኧረ ጎራው፣ ኧረ ደኑ፣ ኧረ ናማ!
እባብ አረጀ አሉ፣ አባብ መለኮሰ – ጠመጠመ ሻሽ፣
የዛለ ሰው ቢያገኝ በመርዝ ሊያበለሽ።” ሲል ያቅራራቀው የጎጃም አርሶ አደር ወዶ አይደለም ግፉ ቢበዛበት ነው።
እባብ በህይወት እያለ ጉንዳንን ይበላል። እባብ ሲሞት ጉንዳኖች ይበሉታል። ጊዜ በማንኛውም ሰዓት ይለወጣል በህይወት ዘመንህ የማንንም ዋጋ አታሳንስ ምናልባት አንተ ሀይለኛ ትሆን ይሆናል ጊዜ ግን ካንተ የበለጠ ጉልበተኛ ነው አስብ አንድ ዛፍ መቶ ሺ ክብሪቶችን ሲሰራ አንድ ክብሪት ግን መቶ ሺህ ዛፎችን ታቃጥላለች። አንድ መጥፎ ስራም ብዙ መልካም ነገሮችን ታጠፋለች። ዋናው ነገር ለአንድ አገር በአስተሳሰብ መልካም የሆነ ድርጅት፣ መንግስትና ሕዝብ ያስፈልጋል። መልካም አስተሳሰብ ብቻውን አገር አይገነባም፣ ታሪክም አይሰራም።
ድርጅት በሉት መንግስት የሕዝብ ማንነትን ካረከሱ በሕሊናቸው ማዘዝ ይሳናቸዋል። ባህልና ታሪክ ሳያዛቡ ከስህተት እየተማሩ የሕዝብን ማንነት ጠብቆ መምራት ከተሳናቸው የሚያስከትለውን ቀውስ መቀልበስ ይቸግራል።
ለመሆኑ የሰላም ዋጋው ስንት ነው? ብዙዎቻችን ችግር በራሳችን ደርሶ ካላየነው በስተቀር የሰላም ውድነት አይገባንም። እንኳን አገርና ክልል ይቅርና በየቤታችን ሰላም ስናጣ ቅጡ የሚጠፋን ስንቶቻችን ነን? በእርግጥ ምን ሰላም አለና ነው ስለ ሰላም የምትዘላብደው የሚለኝ ባይጠፋም በአማራ ክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የክልሉ ህዝብ በተረጋጋ መንገድ የእለት ከእለት ህይወቱን ያለምንም ስጋት እንዲመራ በማድረግ በኩል የአዋጁን በጆሮ እንዳይሆንብኝ እንጂ አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት ከሕዝብ የተሰጣቸውን ሥልጣን በአግባቡ እየተገበሩት እንዳልሆነ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።
በዚህ ዓመት ብቻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለውን ብናነሳ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ በባህር ዳር፣ በቆቦና በሌሎች ከተሞች ከማንነትና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዙ ጥያቄዎች ተቃውሞ አይሉት ሰላማዊ ሰልፍ ሁለት ሜትር በአንድ ሜትር መጠን ያለው ባነር እያነገቡ ጥያቄያቸውና ቅሬታቸው ዱባና ቅል የሆነ አመለካከት እያንጸባረቁ ሁከት ከመፍጠራቸው በላይ ሰርክ በባህር ዳር ከተማ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት አቤቱታ ለማቅረብ ከየወረዳው የሚመጣውንና የሚኮለኮለውን እንዲሁም ደጅ የሚጠናውን የኅብረተሰብ ክፍል ላስተዋለ ድርጅቱም ሆነ መንግስት ሊያስተካክሉት የሚገባ ጉዳይ እንዳለ ደረቴን ነፍቼና አፌን ሞልቼ እናገራለሁ።
ሆደ ሰፊነቱ ችግርን የሚፈታ መሆን ሲገባው አዳሜ የሚኖርበትን ወረዳና ዞን እየዘለለ መጮሁ የመዋቅሩን ብልሹነት ከማሳበቁ በላይ የችግሩን ግዝፈትም ያመላክታል። ያም ብቻ አይደለም የተዘረጋው የአሰራር ስርዓት ብልሹነትና የተመደበው አመራር አቅመ ደካማነትን ያሳያል።
በያ ሰሞን በክልሉ ባሉ አንዳንድ ከተሞች ማንነታቸው በውል ባልታወቁ ግለሰቦች አነሳሽነት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ታሪፍ ይሻሻልልንና አዲሱ የኤስ.ኤም.ኤስ የትራፊክ ህግ ማስከበር ተጀምሯል በሚል ሀሰተኛ ወሬ ተነሳስተው ተቃውሞ በማሰማታቸው አብዛኛው መንገዶች በመዘጋታቸው የክልሉ ሕዝብ ተስተጓጉሏል። ተቃውሞው ያቀጣጠሉትን ተዋናዮችን በመለየትና ሌሎችን በሚያስተምር በኩል ዕርምጃ ባለመወሰዱ ዳግም ችግሩ ላለመከሰቱ ዋስትና አሳጥቶታል። ይህም ከሆደ ሰፊነት የመጣ ነውጥ ነው።
በአገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ የፈጠረውን የነፃነት መንፈስ በመጠቀም ዜጐች በመሰላቸው መንገድ በተናጠልም ሆነ በቡድን ሃሳባቸውን የመግለጽ መብታቸው እንዲከበር ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር የተፈጠረውን የለውጥና የነፃነት እንቅስቃሴውን የሚጐዱ አዝማሚያዎች ከመታየታቸው በፊት ህብረተሰቡ ከተግባር እየተማረ በትግሎ ያገኘውን የነፃነት ጐህ መልሶ እንዳይጨልምና ራሱ እንዲጠብቀው ቅድሚያ መሠራት የሚገባው ጉዳይ ባለመሰራቱ የክልሉን ህዝብ ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጡና የፀጥታ ስጋቶች እየታዩ ነው። ከስጋት አልፎም የበርካታ ወገኖቻችን ህይወት የቀጠፈ፣ አካል ያጐደለና በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጐችን ንብረት ያወደመና ቤት አልባ ያደረገ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት እየተፈፀመ ይገኛል።
ይህ አሳዛኝ ድርጊት የሚፈፀመው የአማራ ክልል እንዳይረጋጋ ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በስተጀርባ በሚለገሳቸው ዳጎስ ያለ ገንዘብና ጥቅማጥቅም፣ በቅማንት ስም የተደራጁ የጥፋት ሃይሎችና በአማራ ስም እየማሉና እየተገዘቱ አማራን ለጥቃት የሚያጋልጡ የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነ ቢታወቅም አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት ችግሩ ሲጠናበትና ማጠፊያው ሲያጥረው ሰሞኑን የመስተዳድር ምክር ቤት መግለጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማውጣት ተገዷል። ይህ ደግሞ ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት የሚያስከትለው ዕርምጃ ነው።
መግለጫውም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣቱን የምደግፈው ጉዳይ ቢሆንም ጊዜው ዛሬ እንዳልሆነ ግን አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት ሊገነዘቡት ይገባል። ክልሉ ክራሞቱን ህዝባዊ ሳይሆኑ ህዝባዊ መስለው ለጥፋት በተሰማሩ ሃይሎች በፈጸሙት ጥፋት ንፁሃን የክልሉ ዜጐች ለዕልፈተ ሕይወትና ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርገዋል። ይህንን የጥፋት እንቅስቃሴ ድርጅቱም ሆነ መንግስት በማስታመሙ የጥፋት ቅርሻው ትናንት የትክሻና የወገብ መሳሪያ ፈቃድ በተሰጠበት ማግስት በየሰፈሩ ምሽትን እየጠበቁ ሲተኮስ የነበረው ጥይት የሕዝቡን ሰላም እንደነሱትና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የአማራ ክልል ተማሪዎች ተቀብሎ ባስተናገደው ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ድርጊት የክልሉ ሕዝብ አንገት አስደፍቶታል።
እሽሩሩ ለሕጻን ልጅ እንጂ ነፍስ ላወቀ አይጠቅምም። ሆደ ሰፊነቱ ይብቃ። ለሁሉም ልክ አለው። አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት ሆደ ሰፊነቱንም ሆነ ሆደ ባሻነቱን በልክ ይዞ የሕዝቡን ሰላም መጠበቅ ግዴታው ነው። በመንግስት መዋቅር የተዘረጉ አሰራሮች በሕግ በሕግ እንዲተገበሩ፣ በኔት ወርክ የተሰባሰቡ አመራሮችንና በጥቅም እየተገዙ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎችን ሕዝቡ በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተላቸውና እንዲያጋልጣቸው ጥብቅና ሊቆምላቸው ይገባል። ክልሉ የማንም ሕገወጥና ጋጥወጥ መፈንጫ ሳይሆን ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት የሚወጣበት ክብሩንና ማንነቱን ጠብቆ፣ ለፍቶ አምርቶ፣ ጥሮና ግሮ፣ ወልዶና ከብዶ፣… የክልሉ ሰላም አስጠብቆ በአብሮነት የሚኖርበት ክልል እንዲሆን አዴፓና የክልሉ መንግስት ሊሠሩ ይገባል አለበለዚያ ዕልቂቱ ከዚህ የከፋ እንደሚሆን እገምታለሁ።
(ummp4.20@gmail.com)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply