ባለፈው ዓርብ በተከፈተው የመሬት ሊዝ ጨረታ በአንድ ካሬ ሜትር 305 ሺሕ ብር ቀረበ፡፡ ይህ ዋጋ በከተማው ታሪክ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ የሊዝ ጨረታን የወቅቱ አነጋጋሪ ክስተት አድርጓል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ በርበሬ አካባቢ 449 ካሬ ሜትር ቦታ ለጨረታ ቀርቧል፡፡ በካሬ ሜትር የቀረበው ገንዘብ ሲሰላ ይህ አነስተኛ ቦታ 136.9 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሆኗል፡፡ 20 በመቶ ብቻ የተከፈለበት ይህ መሬት ከነወለዱ እስከ 300 ሚሊዮን ብር በ30 ዓመት ሊደርስ እንደሚችል ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡ ይህ ክስተት ለአዲስ አበባ ሊዝ ሥሪት ባለሙያዎች እንዲሁም በጨረታው ለታደሙ ባለሀብቶች የቀረበው ዋጋ ብዥታን ፈጥሯል፡፡ በጨረታው ላይ ሁለተኛ ሆኖ የቀረበው ዋጋም ከዚህ ቀደም ቀርቦ የማያውቅ ሲሆን፣ የቀረበውም በካሬ ሜትር 288 ሺሕ ከ90 ሳንቲም ነው፡፡ “በአዲስ አበባ የሊዝ ዋጋ ላይ ቆም ተብሎ ካልታሰበ አደገኛ ውጤት ሊኖረው ይችላል፤” ሲሉ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሊዝ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
መርካቶ በርበሬ ተራ ለሚገኘው ለዚህ 449 ካሬ ሜትር ቦታ በካሬ ሜትር 305 ሺሕ ብር ያቀረበው ዝዋይ ኢንተርናሽናል የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ቀደም ሲል ከዚህ ቦታ አጠገብ መሬት በሊዝ ገዝቶ የንግድ ማዕከል ያቋቋመ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ለዚሁ ቦታ በካሬ ሜትር 288 ሺሕ ከ90 ሳንቲም ያቀረበው ደግሞ ኤንኤስኤ የተባለ ኩባንያ ነው፡፡ ይህ ኩባንያም ቦታውን ማሸነፍ ባይችልም ያቀረበው ገንዘብ ግን በከተማው ታሪክ ቀርቦ የማያውቅ ነው፡፡ በከተማው ታሪክ ክብረ ወሰን ሆኖ የቆየው ከወራት በፊት በስምንተኛው ዙር ሊዝ ጨረታ ቦሌ አካባቢ ከኤድናሞል ወረድ ብሎ የሚገኝ ቦታ ነበር፡፡ ቦታው 158 ካሬ ሜትር ስፋት ሲኖረው፣ ለዚህ ቦታ በካሬ ሜትር 65 ሺሕ ብር ያቀረበው ኤስኤንአይ ትሬዲንግ ነው፡፡
በ11ኛው ሊዝ ጨረታ በካሬ ሜትር የቀረበው 305 ሺሕ ብር ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦ ከነበረው 65,000 ብር በ4,692 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በርካታ የመሬት ሥሪት ባለሙያዎች ይህ ዋጋ ምናልባት ለዓመታት ክብረ ወሰን ሆኖ ይቆያል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ ነገር ግን በከተማው የሚገኙ አንዳንድ ነጋዴዎች የሚወስዱትን አደጋ መገመት የሚያስቸግር በመሆኑ በቅርቡ አይሻሻልም ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ገንዘብ በማንኛውም መመዘኛ ጤነኛ ኢኮኖሚያዊ አካሄድ አይደለም ካሉ በኋላ፣ ሁኔታው ቆም ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ነው ይላሉ፡፡
አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለጨረታ የቀረበው ይህ ቦታ ብቻ ነው፡፡ ቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ ደግሞ 57 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበዋል፡፡ ሚሊኒየም አዳራሽ ጀርባ የወጡ ሁለት ቦታዎች ከፍተኛ ዋጋ ቀርቦላቸዋል፡፡
በዚህ ቦታ ለወጣ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ቤተልሔም ብርሃን የተባሉ ባለሀብት፣ በካሬ ሜትር 55,244 ብር አቅርበዋል፡፡ ወ/ሮ መኪያ የተባሉ ባለሀብት ደግሞ ለ403 ካሬ ሜትር ቦታ በካሬ ሜትር 51,111 ብር አቅርበዋል፡፡
ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ሁለት ቦታዎች ለጨረታ የቀረቡ ሲሆን፣ 12,000 እና 15,000 በካሬ ሜትር ቀርቦላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቦሌ ክፍለ ከተማ በብዛት ኮንዶሚኒየም ቤቶች እየተገነቡበት ባለው ቀጠና በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ መኖሪያ ቤት እየገነባ ባለበት አካባቢ 52 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ቦታዎች እስከ 15,000 ብር የቀረበላቸው ሲሆን፣ ራሕማ ጀማል የተባሉ ባለሀብት በዚህ አካባቢ በካሬ ሜትር 15,221 ብር ሲያቀርቡ ከዚሁ ቦታ አጠገብ ዘገየ ዘመዴ የተባሉ ባለሀብት 2,489 ብር አቅርበዋል፡፡
በዚህ አካባቢ ብዙም ጨረታ ወጥቶ የማያውቅ በመሆኑ የቦታውን ዋጋ ለመስጠት ባለሙያዎች ተቸግረው ነበር፡፡ በሁለቱ ባለሀብቶች መካከልም የቀረበው ዋጋ ልዩነቱ ከዚህ መነሻነት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በዚሁ አካባቢ በተነፃፃሪ ዝቅተኛ ዋጋ አቅርበው አሸናፊ የሆኑ አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ውብነሽ ሀብቴ በካሬ ሜትር 3,189 ብር፣ አሰፋ ታምሬ በካሬ 2,689 ብር፣ ብርቄ መለስ 1,805 ብር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እንዲሁ የዋጋ መነሳት የታየበት ሲሆን፣ በካሬ ሜትር 18,000 ብር ቀርቧል፡፡
የአዲስ አበባ የመሬት ዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ ለዚህ ምክንያቱ አስተዳደሩ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በቅርብ ከኢብኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ የመሬት ዋጋ እንዲንር መንግሥት እንደማይፈልግና አልሚዎች ያላቸውን ካፒታል መሬት በመግዛት ሳይሆን፣ ለልማቱ በማዋል ማደግ እንደሚኖርባቸው አስታውቀው ነበር፡፡ ነገር ግን የከተማው የመሬት ዋጋ በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ ላይ መገኘቱ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ ችግሮ ሊዳርግ እንደሚችል በመግለጽ ባለሙያዎች ማሳሰቢያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
Abe says
This shows how the country is in crisis and leading abnormal Economy. Where did all these so called ” Investors” brought the money from while the people of the country is languishing in abject poverty and lacks in even daily food items to survive?What was the source?and were there any justifiable and plausible economic activities going on in the country as such in the past two and half decades that could earn/reward them to offer and spend this much on a piece of land at this time except corruption? Its shame and even immoral for these biders to rush to grab the poors land while many are seen thrown on the streets and looking for food-is that to improve the fate of the many poor or to dance on thier death bed?