አቶ ዠ ከጸሃፌ-መፈክር ወደ ጸሃፌ-ተውኔት እሸጋግራለሁ ብለው መፈከራቸው እንዳለ ሆኖ፣ ይንን አስመልክቶም ለኢሃዴግ ፍቅር ቴአትር ቤት ሥራ አስቀማጭ ደብዳቤ መላካቸው እንዳለ ሆኖ፣ … ከወራት በኋላ የአቶ ዠ ባለቤት ወይዘሮ ዘ ቡና አፍልተው ከአቦል እስከ በረካ ተጠጥቶ እንዳለቀና ሥኒ እያጠቡ እያለ…
ወይዘሮ ዘ ገረሙህ?“ባልና ሚስት ካንድ ባህር ይቀዳል” ሲባል አልሰማህም?ባላቸው ዠ ከሆኑ እሳቸው ከ ዘ ሌላ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?ዠ እኮ ባርኔጣ የደፋ ዘ ነው።ከምሬ ነው። ካላመንከኝ ሥለ ቃላትና ፊደላት የሚፈላሰፉ “ዲባቶ”ዎች ፈልግና ጠይቅ። ሥምህ ጨ ከሆነ የምታጫትና የምታገባት ኮረዳ ጠ ነው የምትባለው። እና ቡና ተጠጥቶ እንዳለቀ፣ አቶ ዠ ከባለቤታቸ ጋር “ጨዋታ” ጀመሩ።
“ጨዋታ“ው ሲያልቅ ጻፉት፣ አቶ ዠ፣ ጸሃፌ-ተውኔት። ገጸ-ባህርያት ዠ እና ዘ ብለው ጀመሩ።
ዘ እኔ የምልህ?ጠባብ ብሄርተኝነት ምንድነው?
ዠ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ያልሆነ ማለትነው?
ዘ “ውሃ ሲወቅጡት እምቦጭ አለ” አሉ። ልዩነቱ ምንድነው?
ዠ ጠባብ ብሄርተኝነትማ ልክ እንደምታጥቢው ሥኒ ማለት ነው።(አሉ አቶ ዠ የሚታጠበውን ሥኒ እያዩ።)
ሥኒ ውስጥ ከጀበና ቡና ብትቀጂበት ያው ያቺኑ የተቀዳችውን ብቻ ነው የሚይዘው። ከዚያ በላይ አይችልም። ጠባብ ነዋ! በተፈጥሮው፣ ባሰራሩ ጠባብ ነዋ!ያ እንግዲህ የጠባብ ብሄርተኝነት ምሳሌ ሊሆን ይችላል።
ዘ አሃ!(የገባቸው አይመስሉም፣ ወ/ሮ ዘ)
ዠ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ደግሞ እንደ ጀበናሽ ነው። የያዘውን ሁሉ የሚያከፋፍል። አየሽ ጀበና ታጋሽና ለጋሽ ነው። እሳት ላይ በዝምታ ተጥዶ፣ ቡና ተፈልቶበት፣ ያን ሁሉ ችሎ፣ በኋላ ለሥኒዎች ሁሉ የያዘውን ያከፋፍላል።
ዘ አሃ!ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት እንደ ጀበና ነው?ከሰል ላይ እንደምጥደው ጀበና ነው?እሳት ጠግቦ ግንፍል ግንፍል እንደሚለው ጀበናዬ ነው?
ዠ ኤዲያ ያንቺ ነገር፣ ቢገነፍል ባይገነፍል የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መብቱ ነው።
ዘ እንግዲህ ቡናዬን በሰላም ለመጠጣት፣ ግንፍል ግንፍል ባዩን ጀበናዬን፣ ከፊሉን ቡናዬን አፍሳሹን ጀበናዬን፣ በዚህም ምክንያት ከሰሌን የሚያዳፍነውን ጀበናዬን፣ ከከሰል አውርጄው እሲኪሰክን በዝምታ መጠበቅ ያለብኝ ጀበናዬ ነው የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ምሳሌ ነው የምትለኝ?
ዠ እንዴ ይሄን ሁሉ አመት ታግሰሽ ኖረሽ የለም እንዴ?“ግንፍል፣ ግንፍል የሚለውን፣ ሁሌ እሲሰክን መጠበቅ ያለብኝን” ብለሽ የምትታዘቢው?
ዘ ህምምምምም… እሱስ ልክ ነው። ታግሼ ችየዋለው። ሲሟሽ፣ ሲሟሽ ከከረመ፣ ከዛሬ ነገ ይሻለዋል ብዬ ችየዋለሁ።
(ጀበና ትተው የወሬ ርዕስ ቀየሩ፣ ወ/ሮ ዘ)
እኔ የምለው? ምሥር ደግሞ “ኢትዮጵያን እወራለሁ፣ አባይ ይነካና ዋ!” ብላ ትፎክራለች አሉ። እኔ እንኳን ጭምጭምታ ነው የሰማሁት። እሳት ላይ ተወርቷል አሉ። “ይቼ ጥሬ፣ ይቺ ምሥር፣ ካደረች አትቆረጠምም” አሉ አበው።
ዠ ዛሬ ደግሞ ከበደ ሚካኤልን መሆን አማረሽ እንዴ?ምነው ተረትና ምሳሌ አበዛሽ?። ግብጽ በማለት ፈንታ ምሥር የምትይውና የምትተርቺው?ደግሞ የእሳት ወሬ አታምጭብኝ። እሳት ማለቴ “ኢሳት ይፋጃል” ሲባል አልሰማሽም?ሲፈጃቸው እኔ ዠ የእሳቱ ማብረጃ፣ ማጥፊያ መሆን አልፈልግም። “ግብጽ ብትመጣ እንዘምታለና!ግብጽ ምናባቷ እንዳትሆን ነው?እስኪ ትምጣና እናያለና!” ነው የሚባለው።
ዘ ፉከራ!መፈከር ብቻ!
ዠ መፈከር ሥራዬ እንደነበር አጣሽው እንዴ?
ዘ ዘመቻ?ዘመቻ?የምንበላው የሌለን ሰዎች በባዶ ሆዳችን ነው የምንዘምተው?አሃ!
(አሉ ወ/ሮ ዘ ወደሰማይ አንጋጠው፣ መንግስተ ሰማያት ተከፍቶ የሆነ ነገር የነገራቸው መስለው ተናገሩ።)
አሃ! ስኳር! ስኳር ፋብሪካ ይስፋፋ የተባለው ለዚህ ነው ለካ!ስኳር እየበላን እንዘምታለና። ኢሃዴግ ስኳር እየቃመ ተዋግቶ አይደለም እንዴ ነጻ ያወጣን?ከተመክሮ የተገኘ መላ ነው። የስኳር ፋብሪካ ይስፋፋ!
(አቶ ዠ ለመናገር አፋቸውን ከፈቱ። ልክ ያኔ…)
ዠ ደግሞ ይህንን ግንፍል፣ ግንፍል ባይ፣ ገሚሱን ቡናዬን ደፊ ጀበና ከዛሬ ጀምሮ አልፈልግም ብለው ጀበናውን ወለሉ ላይ ከሰከሱት።
አቶ ዠ ይህንን “ጨዋታ” ጻፉና ወረቀቱን ኪሳቸው ውስጥ ከተው ወደ ኢሃዴግ ፍቅር ቴአትር ቤት አቀኑ። በመንገዳቸው ላይ የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ቆሞበት የነበረው ቦታ ላይ አንድ ሰውዬ ቆመው አዩ። ሰውዬ የአቡኑን ሃውልት የሚፈልግ ይመስላሉ። አቶ ዠ አልፈዋቸው ሊሄዱ ሲል ሰውዬው ጮክ ብለው ተናገሩ። የተናገሩት መንገደኛው፣ አላፊ አግዳሚው እንዲሰማቸው አልነበረም። አቶ ማሞ፣ ወፍጮ ቤታቸውና መኖሪያ ቤታቸው ለባቡር መሄጃ ተብሎ የፈረሰባቸው፣ አቶ ማሞ ለራሳቸው ተናገሩ።
“እኔና የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት የትም ወድቀን መቅረታችን ነው?”
Gilentufagonji says
Please speak freely, you are born free.So,why you go all around?