ሰማያዊ፡- የሰማያዊ ፓርቲ ምሰሶ የሚባሉ ዋና ዋና የሚያራምዳቸው ፖለቲካዊ አቋሞች ምንድናቸው?
ኢ/ር፡ ይልቃል፡- ፖለቲካ በየጊዜው እንደሁኔታው የሚለወጥ& የሚሻሻልና የሚያድግ ቢሆንም! ሰማያዊ ፓርቲ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክና ካሉብን ችግሮች በመነሳት ዋና ዋና የምንላቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡-
አንደኛ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ አብረው የኖሩ የተለያየ ልማድ& ባህል& ቋንቋ እና እምነት ያላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የጋራ የወል ስነ-ልቦና አዳብረው በአንድነት የሚኖሩበት አገር ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይህም ስለሆነ፡- የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመሠረቱ ማተኮርና መነሳት ያለበት ከዜግነት እና ከግለሰብ መብት ላይ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህም የዜግነት እና ሰብዓዊ መብቶች እስከተከበሩ ድረስ የማይከበር የመብት ዓይነት የለም! ብሎ ነው ፓርቲያችን የሚያምነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያሉ መብቶች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ባለሙያዎች በሙያቸው ተደራጅተው የሚጠይቁት የጋራ መብት ይኖራቸዋል! ሠራተኞች በጋራ ተሰባስበው የሚጠይቁት መብት ይኖራቸዋል፡፡ ወጣቶችም በዕድሜያቸው& ሴቶችም በጾታቸው እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባህላቸውን& ዕምነታቸውን ለማበልፀግ የራሳቸው መብቶች አሏቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ መብቶች ከዜግነት እና ከሰውነት መብት በላይ አይደሉም፡፡ በመሆኑም፡- የዜግነት እና የሰውነት መሠረታዊ መብቶች በተከበሩ ጊዜ ሌሎቹ የጠቀስኳቸው መብቶች ሁሉ አብረው ይከበራሉ ብለን እናምናለን፡፡
ሁለተኛውና ዋናው ነገር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ድህነትና ግብርና ላይ የተመሠረተ ኋላ ቀር አኗኗር በመኖሩ! በዚህም ዓይነት የኑሮ ዘይቤ ብዙው የህብረተሰብ ክፍል በገጠሮች ውስጥ የሚገኝና ህልውናውን በመሬት ላይ መሠረት ያደረገ ስለሆነ& ይህ የህብረተሰብ ክፍል እንዲያድግ እና ኑሮው እንዲሻሻል ማድረግ የሚቻለው ሙሉ ነፃነቱን በማቀዳጀትና በመሬቱ ላይ ብቸኛ ወሳኝ ተዋናይ ለማድረግ መሬቱን የግል-ንብረቱ እንዲሆን በማስቻል ነው ብሎ ያምናል ፓርቲያችን፡፡ ይሄ በተለያዩ ጥናቶችም የተረጋገጠ ትክክለኛው አቋም ነው፡፡ ነፃነት የሌለው ህዝብ በምንም ዓይነት መንገድ ልማትን እንደማያመጣ! በአገራችን ያሉት ገበሬዎችም ነፃነት እስካላገኙ ድረስ ከኢትዮጵያ ውስጥ ችጋር እንደማይጠፋ የኛም አገር አንጋፋ-ምሁራን ያጠኑት ነው፡፡ ዓለማቀፍ ዕውቅ ምሁራንም ለምሳሌ አማርትያ ሴን (የኖቤል ተሸላሚ ኢኮኖሚስት) በጥናቱ በሚገባ እንዳብራራው ነፃነት ለልማት መሠረቱ መሆኑን ነው፡፡ ኘሮፌሰር መስፍንወ/ማርያምም Suffering under God’s Environment በሚለውና Rural vulnerability to famine in Ethiopia በሚለው መጽሐፋቸው በአመርቂ ሁኔታ እንዳስረዱት ገበሬው ነፃ እስካልወጣ ድረስ ችጋር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚቀጥል ነው፡፡ ስለዚህ ገበሬው ነፃ ይሁን ከተባለ የሚያርሰው መሬት የራሱ መሆን አለበት፡፡ በፊት የፊውዳል ጭሰኛ እንደነበረው ዛሬ ደግሞ የመንግሥት ጭሰኛ መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም የፓርቲያችን አቋም በዚህ ጉዳይ ላይ በገጠርም የሚታረሰው ሆነ በከተማ የሚኖርበት መሬት የዜጐች የግል ይዞታ መሆን አለበት ነው፡፡ በዚህም አግባብ ገበሬዎችም ሆኑ የከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ነፃነት እና ያለምንም ዋስትና-የማጣት ስሜት የመሬትን የገበያ ዋጋ በተገቢው መንገድ ለመጠቀም ይችላሉ፡፡
በተጨማሪ ገበሬውም ከካድሬና ከመንግሥት ጭሰኝነት ነፃ ከሆነ እምቅ አቅሙን አውጥቶ በመጠቀም መሬቱን የመጠበቅ& የመንከባከብ& የማልማት& በባንክ የማስያዝ እንዲሁም የማውረስ& የመሸጥ እና የመለወጥ መብት ይኖሩታል ማለት ነው፡፡ ይሄ ለቴክኖሎጂ ሽግግርም ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ አለው ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ እነዚህ የጠቀስኳቸው አቋሞች መሠረታዊ እሴቶቻችን ናቸው፡፡
በፌዴራል አወቃቀር ላይ ያለን አቋም ደግሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለዚህ ዓይነት የመንግሥት ቅርፅ እንግዳ ባለመሆኗ እና በተለያየ ጊዜ የዚህ አካባቢ ንጉስ የዚያ አካባቢ ንጉስ ከዚያም ንጉሠ-ነገሥት እየተባለ በሰፊው በባህላዊ የአገዛዝ ዘመንም የተለማመድነው በመሆኑ! ይህንኑ ማዳበርና ዘመናዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ያሻል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን የአስተዳደር ምቹነትን& መልክዓ-ምድርን& የህዝቦች አሰፋፈርን& ባህልን& ቋንቋን ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚደረግ እንጂ እንደው አሁን እንደሚባለው በጐሣ ከረጢት ውስጥ ያሉ ጎሳዎች ተስማምተው አገሪቷን ገና እንደአዲስ እየፈጠሯት እንደሆነ የሚያስመስለው አቀራረብ ትልቅ ስህተት ነው፡፡
ቀደም ብዬ እንደገለፅኩልህ ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የሀገረ-መንግሥትነት ታሪክ ያለውና የረጋ ህዝብ ብሎም የጋራ ስነ-ልቦና ያለው ህብረተሰብ የሚኖርባት አገር ነች፡፡ በመሆኑም፡- እነዚህ ግምት ውስጥ ገብተው የሚዋቀር ፌዴራላዊ ቅርፅ ነው ለሀገራችን የሚበጃት ብለን እናምናለን- እንደሰማያዊ፡፡
ታሪክን በመፈልሰፍ አንድ ጐሣና አንድ ጐሣ እንደተዋጉ የሚያስመስለው አቀራረብም በፍፁም የተሳሳተና አውዳሚ ነው፡፡ መንግሥት ከመንግሥት& የአካባቢው አገዛዝ ከአካባቢው አገዛዝ ተጣልተው ያውቃሉ እንጂ አንድ ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ ጋር በታሪክ ለዚያውም በታቀደ ሁኔታ ጎሣን መሠረት አድርጎ የተደረገ የፖለቲካ ትግል የለም በአገራችን ውስጥ፡፡ ይሄ ከቅርብ ጊዜ በኋላ በጥራዝ ነጠቅነት ሣር-ቅጠሉ ኮሚዩኒስት በነበረበት ከ66ቱ አብዬት ጋር ተያይዞ እንደወረደ ስለተቀበልነው የመጣ ነገር እንጂ የአገራችንን እውነተኛ ገፅታ የሚያሳይ አይደለም ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ መሠረት የጣልንባቸው እና አጥብቀን የያዝናቸው ዋና ዋና አቋሞቻችን፡፡
ሰማያዊ፡- አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዋነኛ ፖለቲካዊ ችግር ምንድነው ብላችሁ ነው የምትገነዘቡት? የብሔር ጭቆና ነው? የመደብ ልዩነት ነው? ወይስ አምባገነን የመንግሥት ሥርዓት?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እንግዲህ ኢትዩጵያ እስካሁን ድረስ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ አልሄደችም፡፡ ያለው አገዛዝ ከባህላዊ አገዛዝ የጀመረ እና በ1967 ለውጥም መጣ ተብሎ ከንጉሳዊ አገዛዝ ወደጠብመንጃ አገዛዝ ተዘዋውረናል፡፡ እስካሁን ያለው መንግሥት ድረስ ምርጫ በሚመስል ሁኔታ ልባስ ተሰጥቶት ቅቡልነት ያለው ለማድረግ ቢሞከርም የምር ፖለቲካውን ካየነው ኢትዮጵያ ከጠብመንጃ አገዛዝ እስካሁንም ድረስ አልተላቀቀችም፡፡ ስለዚህ የጉልበት አገዛዝ ነው መሠረቱ፡፡
አንዳንዶቹ ፍልስፍናዊ ቅርፅ በመስጠትና በውጭ አገር ከነበሩ የፖለቲካ እምነቶች ጋራ ለማዛመድ የየራሳቸውን ተቀፅላ ይጨምሩበት ይሆናል እንጂ እስካሁንም ድረስ ኢትዮጵያውያን በጠብመንጃ አገዛዝ ስር ነን፡፡ በመሆኑም ሰማያዊ የሚያምነው የሰዎች የዜግነት እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከተከበረ እንዲሁም ስልጣን የህዝብ ከሆነ ከዚያ በኋላ የሚመጡት ነገሮች በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ናቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩት፡- የዜጐች ባህላቸውን የማበልፀግ ጉዳይ& እምነታቸውን በነፃ የማራመድ መብት& በሙያቸው ተሰባስበው የሙያቸውን መብት የመጠየቅ ሁኔታ እና የመሳሰሉት ሁሉ ነገሮች ሥልጣን የህዝብ ከሆነ በኋላ የሚመጡ ቁም ነገሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዋናው ችግር ሥልጣን የአገሬው ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ ባለቤትነት ውስጥ ለመሆን አለመቻሉና በጠብመንጃ አገዛዝ ስር መውደቁ ነው፡፡ ሌሎች ፍልስፍናዊ ዓይነት ይዘት የተሰጣቸው ነገሮች ሁሉ ከዚህ በመለስ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡
ሰማያዊ፡- በቅርቡ የተካሄደውን የኢህአዴግ የስልጣን ሽግሽግ በተመለከተ ፓርቲያችሁ ያለው አስተያየት ምን ይመስላል?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እ….. በመጀመሪያ ደረጃ የተካሄደው የስልጣን ሽግሽግ አይደለም፡፡ እ…ባዶ ነበር ቦታው… በመሆኑም ያ ባዶ ቦታ መተካት ነበረበት፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚኒስትሩ በሌሉም ጊዜ ቢሆን የሚተኩት ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ጠ/ሚኒስትሩ ለዘላለሙም ሲሄዱ ከኋላ ዘሎ ከማምጣት ምክትሉን መተካት ይሻላል በሚል በዚሁ መሠረት ተካሄደ፡፡ ስለዚህም የተከናወነው የስልጣን ሽግግርም አይደለም! ሌላ ዴሞክራሲያዊ የተለየ ነገርም አልተደረገም፡፡ በታሪካችን እንዲሁ ያለውን ነገር ምናልባትም በተሻለ ሁኔታ የዛሬ 1ዐዐ ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ውስጥ ተደርጓል፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ በሞቱ ጊዜ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ንጉሠ-ነገሥት ሆነው ተሰይመዋል፡፡ የንግሥት ዘውዲቱም የቀብር ስነ-ስርዓት በተሟላ የመንግሥት ደንብ protocol በክብር ተፈፅሟል፡፡ የአፄ ኃ/ሥላሴም ንግስና ሥርዓት ጠብቆ ቤተክርስቲያን በጊዜው ባላት ሥልጣን መሠረት በአግባቡ ተፈፅሟል፡፡ እና ይሄ ዓይነቱ የስልጣን መተካት ከሆነ በፊትም ተደርጓል፡፡ ስለዚህም ኢህአዴግ ታሪክ ሠራ ተብሎ ኢህአዴግን የተለየ ሊያደርገው የሚችል ነገር አልተፈጠረም፡፡
የስልጣን ሽግግር ሊባል የሚችለው አንደኛ፡- ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ ቢሄድ ወይም ደግሞ አቶ መለስ እያሉ ተወዳድረው በሌላ አካል ተበልጠው ቢሸነፉ ነው፡፡ አሊያም ደግሞ በቃኝ ብለው ለቀው ሌሎች ተወዳድረው ቢያሸንፉ ያኔ የስልጣን ሽግግር ተካሄደ ሊያስብል ይችላል፡፡ ከሞቱ በኋላ ግን በሌላ ሰው መተካት ግዴታ ነው፡፡ ቦታው ባዶውን መቅረት የለበትምና! በመሆኑም ፓርቲው የመረጠውን ሰው ተካ፡፡ ስለዚህ ይህ የስልጣን ሽግግርም ሆነ ሽግሽግ ሊባል አይችልም፡፡
ሰማያዊ፡- የኢህአዴግ አብዬታዊ-ዴሞክራሲያዊ መስመር የራሱ የሆነ ሥልጣን የማሸጋገሪያ ቀመር እና አካሄድ አለው! ብለው የሚያነሱ የፓርቲው ሰዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ የስልጣን ሽግግር ከፓርቲው መጠበቅ የዋህነት ነው! የሚሉም አልታጡም፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ የፓርቲውን የመተካካት ጉዞ የሚታዘቡ ሰዎች ምናልባት ስልጣን በትጥቅ ከታገሉት ወደ ሲቪል-ኢህአዴጎች እየሄደ ከመጣ ተስፋ ይኖር ይሆናል! የሚሉ አሉ፡፡ እናንተ ደግሞ እንደተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ሊያሳትፋችሁ የሚችል የስልጣን መጋራት መንገድ ከኢህአዴግ ትጠብቃላችሁ?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እውነቱን ለመናገር እኔ መጀመሪያም ከኢህአዴግ ዓይነት ድርጅት የምር የምጠብቀው ነገር የለም፡፡ ፓርቲው በራሱ እጅግ የጠቅላይነት (Totalitarian) አስተሳሰብ ያለው አምባገነን ነው፡፡ አንድ ጠንካራ ፓርቲ በመመስረት እና የልማታዊ መንግሥት ምስል ለራሱ በመፍጠር ከዚህ በኋላ ለ3ዐ እና 4ዐ ዓመት ለመግዛት የሚያልም ፅኑዕ የሥልጣን ሱሰኝነት የተፀናወተው ድርጅት ነው፡፡ የአገዛዝን ነገር ፍልስፍና ለማላበስ የሚጥር! ለሥልጣኑ መቀጠል ሲል እጅግ በአያሌው ጂምናስቲክ ሲሰራ የኖረ ፓርቲ ነው፡፡
እንደ ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን ያሉ የማይዛመዱን አገሮችን በአርአያነት እየጠቀሰ እነዚህ አገራት በአንድ ወቅት ሲያራምዱት የነበረውን ፖለቲካዊ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ላይ በመጫን ለረዥም ዓመታት ሊገዛን የሚፈልግ አስመሳይ-አምባገነን ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ አገራት ግን በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት በነበረው የጐራ ልዩነት ከአሜሪካ ያገኙትን የዕርዳታ ቁሳቁስ የቴክኖሎጂ ድጋፍ& እና የገንዘብ እገዛ ካላቸው ልምድ ጋር በማቀናጀት በራሳቸው ሁኔታ ያደጉ ናቸው፡፡ ነባራዊ ሁኔታቸውም ከኢትዮጵያ ጋር በፍፁም አይገናኝም፡፡
እንደውም እኮ ኢህአዴግ እስከ 97 ሲል የነበረው ‘ጠንካራ ተቃዋሚ አጣን! ብናገኝ እስከግማሽ መንገድ ድረስ ሄደን እንቀበላለን!’ ምናምን የሚሉ ባዶ ቃላትን ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን 97 ላይ የዴሞክራሲው መንገድ እንደማያዋጣና ሥልጣንን በአጭር ጊዜ እንደሚያስለቅቅ ሲያውቁ አምባገነንነትን ፍልስፍና ለማላበስ የተፈጠረ አብዬታዊ-ዴሞክራሲ እንጂ የምር ስልጣንን ማጋራት የሚችል አሳታፊ ስርዓት አይደለም፡፡ በመሆኑም የኢህአዴግ መንግሥት አንድ ወጥ የሆነ አገዛዝ& ሌላውን ሁሉ የሚያንቋሽሽ የሚያቃልል& በመደብ ቅራኔ ውስጥ ነገሮችን ከፋፍሎ ወዳጅ እና ጠላት ብሎ የሚያይ እስካሁን ድረስ የሚታገልላቸውና የሚታገላቸው አመለካከቶች ያሉት እንጂ ፖለቲካዊ መስመሩን አስተካክሎ የሌላውንም ድምፅ ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚሄድ ሥርዓት ነው ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ በህዝብ የምር ትግል መለወጥ ይቻል እንደሆን እንጂ ኢህአዴግ በውስጡ በራሱ እያደገ በሚሄድ ዴሞክራሲ ይቀየራል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሰማያዊ፡- እንግዲህ የህዝብ የምር ትግል ሲባል ብዙ ጊዜ የሚነሳው ከ97 ወዲህ የህዝቡ ለፖለቲካ ፍላጎት የማሳየት ሁኔታ እጅግ እንደተዳከመ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ከዚህ ወቅት በኋላ! ሰው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተስፋ አድርጐ ከእናንተም ጋር አብሮ ቆሞም ቢሆን ወደነፃነት እና ዴሞክራሲ የሚጓዝ ይመስላችኋል? እናንተስ አዋጪ መንገድ አለን ትላላችሁ?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- የ97ቱ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይነገራል፡፡ ራሳችንን በተስፋ ለመመገብም ጭምር እየፈለግን እንጂ እኔ የ97ቱን ጉዳይ ብዙ ሰው በትክክል የተረዳው አይመስለኝም፡፡ እንዴት መጣ? የሚባለውን ነገር በትክክል ካየነው በ1993 ዓ.ም. ህወሓት ከኤርትራ ጦርነት በኋላ ከተከፋፈለ ጀምሮ! በብዛት አንድ ሰው ጐልቶ እየወጣ የነበረበት! የአፍሪካ መሪ እየተባለ የኔፓድ መሪ…. የዚህ መሪ…. በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አቶ መለስ የክብር ዲግሪ እያገኙ! ቀልብ የሚስብ ንግግር እያደረጉ እጅግ የተሞካሹበት ወቅት ነበረ፡፡ በዚህ ጊዜም ነበር አቶ መለስ ከነጆርጅ ቡሽ እና ከነቶኒ ብሌየር ጋር ትከሻ-ለትከሻ እየተሻሹ ዴሞክራሲን የህልውና ጥያቄ ነው ብለው በነርሱ ፊት ቅቡልነት እና የበለጠ ተወዳጅነት ለማትረፍ የሻቱት፡፡ ከጓዶቻቸው በተለየም እርሳቸው ዴሞክራሲያዊ መሆናቸውን ለማሳየት እና ብቻቸውን እየፈጠሩ ያሉትን ሥርዓት ለማደላደል ያንን በር በተለየ ሁኔታ ከፈቱት፡፡ ስለዚህ እንደልብ እንድንናገር” እንደልብ እንድንደራጅ ሆነ! ትላልቅ ሰዎች አይተን በማናውቀው ሁኔታ ወደፖለቲካው መጡ፡፡ በመሆኑም ያንን መደገፍ ከፖለቲካ ትግል ጋር በእኩል የሚነፃፀር አልነበረም፡፡ በቃ ነፃነቱ ተሰጠን! ከዛ ተከለከልን፡፡ መሪዎችም እስር ቤት ገቡ! ወጣቶች እኔን ጨምሮ በሺህዎች በየካምፑ ታጐርን፡፡ ከዛ በኋላ ሲፈቱ ተቃዋሚዎችም ተበታተኑ& ፖለቲካውም አበቃ ተባለ፡፡ ስለዚህ ያኔ ፖለቲካውም በትግል& በልምድ& በዕድገት& በጥንካሬ የመጣ አልነበረም፡፡ የተፈቀደ ነው፡፡ እንደገፀ-በረከት የተሰጠ ነው፡፡ ሲፈቀድልን የልባችንን ተናገርን! ስንከለከል እቤታችን ተቀመጥን፡፡ ስለዚህ ይሄንን የምር የፖለቲካ ትግል ብለን እንወስደው ያዳግታል፡፡ የምር የፖለቲካ ትግል የምንለው፡- በአገራችን አፋኝ ስርዓት አለ& ለረጅም ጊዜ ሊገዛን የተዘጋጀ መንግሥት አለ& ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን አይገባንም& ትልቅ ህዝብ ነን& ትልቅ ታሪክ አለን& የነፃነት ምልክት የሆንን ህዝቦች ነን! ብለን ተነስተን ክብራችንን እና ነፃነታችንን ለመቀዳጀት የምናካሂደው ነው፡፡ በዘመናቸው የነበሩ አባቶቻችን በዘመናቸው የሚጠበቀውን የትውልድ ድርሻ ተወጥተዋል፡፡ እኛም በዘመናችን አፋኝ ስርዓቶችን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመተካት የበኩላችንን ልናደርግ ይገባናል፡፡ በመሆኑም፡- ከነዚህ ነገሮች የሚነሳ ቁርጠኛ የሆነና በሃሳባውያን የተነሳ ርዕዬተ-ዓለማዊ ትግል ነው የምር ትግል ብለን የምንወስደው፡፡ በመበለጥ ስሜት& በቅራኔ ስሜት እና በሌላ ዓይነት ስሜት ሳይሆን በሃሳብ ዴሞክራሲን የምር ለማምጣት የሚደረግ! ራስን ለማህበረሰብ በመስጠት የሚደረግ የፖለቲካ ትግልና መነቃቃት አጠቃላይ ማህበራዊ መነቃቃት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ደግሞ በስራ የመጣ እንደሆነ ህዝቡ የለውጡ ባለቤት እና ተቆጣጣሪ ይሆናል! በልበ-ሙሉነትም እውነተኛ የስልጣን ሉዓላዊነቱን በሥራው ያረጋግጣል፡፡ አምባገነን ህዝብን አሸንፎ ሊቀጥል አይችልም፡፡ በመሆኑም ይህን አውቆ የሚያስከፍለውን ዋጋ ከፍሎ በትግል ዴሞክራሲና ነፃነትን ማምጣት ይቻላል፡፡ያንን ነው የምር ትግል የምንለው እኛ፡፡
ስለዚህ ተስፋ መቁረጥ ሰርተህ አልሳካልህ ሲል የሚመጣ ስሜት ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢህአዴግ በፈቀደልን ነገር ተነስተን ጀምረን ብዙዎቻችን ዋጋ ከፍለናል፡፡ ታስረናል& ተገርፈናል& ብዙ ሰው ሃብቱን አጥቷል& ተፈናቅሏል ያንን እየካድኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ ትግልና በፖለቲካ ልምድ በድል የመጣ ነገር እስካሁን አልጀመርነውም! መሥራት አለብን!
ሰማያዊ፡- ስለዚህ የያዛችሁት ትግል ረጅም ነው እያሉኝ ነው?
ኢ/ር፣ይልቃል፡- አድካሚ ነው በርግጥ! ብዙም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እ….ደግሞ ለመታገል መሠረታዊ የሚሆኑ በቂ ምክንያቶች ስላሉ የምር ከተሠራ ጊዜውንም ማሳጠር ይቻላል፡፡ የያዝከው እና ያነገብከው ዓላማ ነው ትግሉን ትልቅም ትንሽም የሚያረገው፡፡ ኢህአዴግ ምንም ዓይነት መሬት የያዘ የፖለቲካ መሠረትና ድጋፍ የሌለው! ያለችውን ትንሽ ሃብት ሰጪና ከልካይ ሆኖ ብቻ ነው ፖለቲካውን የሚያራምደው፡፡ ምንም ዓይነት የሃሳብ እና የእምነት መሠረት ያለው ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ ይሄን ለመለወጥ የምር በሃሳብ ኢህአዴግን የሚያሸንፍ እና የመሪነት ሚናን የሚጫወት ስብስብ እስከተገኘ ድረስ እኔ ትግሉ ረዥም አይመስለኝም፡፡ ግን ቁርጠኛነትን ይጠይቃል! ዋጋም ያስከፍላል!
ሰማያዊ፡- እንደሰማያዊ ተሰባስባችሁ ያላችሁት የፖለቲካ ተዋንያን ለመሪነት የሚያበቃው ልምድ& ዕድሜ& ራዕይ እና ቁርጠኝነት አለን ብላችሁ ታስባላችሁ? እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ ታስሬ ነበር ብለውኛልና ስለሱም ትንሽ ቢያብራሩልን?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- አይ….እሱ እንኳን እንደቁም ነገር የሚቆጠር ጀብድ አይደለም፡፡ በዛን ዘመን እኔም ገና ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቅኩ በሥራ ላይ 2 ወይም 3 ዓመት ያህል ነው ያስቆጠርኩት…. እና ክፍለ ሃገር ነበር የምሠራው፡፡ እ… እና ለዛ መነቃቃት ውስጥ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ወጣት ትላልቅና የተማሩ ሰዎች ወደፖለቲካው ሲገቡ እኛንም አነሳስተውን ስለነበረ በፖለቲካው ውስጥ መነቃቃትን ፈጥረን በንቃት በአካባቢያችን ተንቀሳቅሰን ነበር፡፡ ወዲያውም ኢህአዴግ ሁሉንም ነገር መጨምደድና ማጥፋት ሲጀምር በየጦር ካምፑ አሠረን፡፡ እና እኔም እዛው እሠራበት የነበረው አካባቢ ላይ በብር ሸለቆ ካምኘ ከብዙ ኢትዮጵያውያን ጋራ ቆይቻለሁ፡፡ በመሆኑም ከጥያቄዎችህ ጋር ሳያይዘው፡- ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለፖለቲካው ቅርብ ስለነበርን ድካሙንም ጥንካሬውንም በቀጥታ ለማየት ዕድል አግኝተናል፡፡ እ… በመውደቅ በመነሳት ውስጥ አልፈናል፡፡ መሪዎችንም በታሪክና በስማ በለው ሳይሆን በቅርበት ለማየት ችለናል፡፡ ስለዚህ መማር የሚችል ልቦና ካለ ከዛ በቂውን ነገር ተምረናል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ከዛ በተረፈ መሪነት አሁን እንደሚባለው ‘ ከሞቱም በኋላ ራዕይ አለንና እንደመንፈስ አባት በዛ መንገድ ይመራል!’ የሚለው ሳይሆን! ፓርቲያችን የሌሎችን ችሎታ መጠቀም ነው መሪነት ብሎ በዋናነት የሚገነዘበው፡፡ ሰዎችን ለጋራ ዓላማችን ብለው የመጨረሻውን እምቅ ሃይላቸውን አንጠፍጥፈው እንዲጠቀሙ ማስቻል ነው መሪነት፡፡ በመሆኑም ሰማያዊ፡- ኢትዩጵያውያን ችሎታና አቅማቸውን በያላቸው ሙያ አውጥተው እንዲጠቀሙ የማሰባሰብ& የማስተባበር& ሃሳብ የማሳየትና! ይህንን የተለያየ እምቅ ሃይል ወደ አንድ በጐ እሴት መለወጥ እንጂ የሁሉ ነገር አዋቂ መሆን አያስፈልገውም-መሪ ለመሆን፡፡ መሪ ኃላፊነት ያለው& መልካም ስነ-ምግባር ያለው& ከራሱ አብልጦ ለሀገሩ ዋጋ መክፈልን እንደክብርና እንደጥሩ ዓላማ የሚቆጥር እስከሆነ ድረስ የሁሉ ነገር አዋቂ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ አይችልምም! መሪ ምናልባትም በባህሪው እና በስነ-ምግባሩ የሚከበርና ጓደኞቹም እሱ የሚለውን የሚያዳምጡት& ያላቸውን ችሎታ ሁሉ ለበጐ ነገር አነሳስቶ ሊጠቀም የሚችል ሰው መሆን ብቻ ነው ወሳኙ እና አንኳሩ ጉዳይ ያም እንዳለ ሆኖ ግን በአንፃራዊ አቅጣጫ ብቃት የሚለውን ስናወዳድር! የተማሩና ትላልቅ ሰዎች ይህንን ፓርቲ ለመደገፍ ባልተለመደ ሁኔታ በየቢሮአችን እየመጡ ያላቸውን ልምድና ሃሳብ ለማካፈል ከዚህ ወጣት ጋር ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሰማያዊ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ ነው ማለት ነው፡፡
በተረፈ ብዙዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በግል ሙያ ከ1ዐ ዓመት ባላነሰ ጊዜ የተሰማሩ እና የዩኒቨርሲቲ ምሩቆች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ አሁን ባለበት ሁኔታ እንኳ ሀገር ቢመራ ከኢህአዴግ የተሻለ እንደሚሆን እኔ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ነገር ግን መረሳት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር የመሪነት አካሄድ አንድ ቡድን ይሄን ያውቃል አያውቅም ሳይሆን! ሌላውን ለማሰባሰብና የኢትዮጵያውያንን ችሎታ በሙሉ ባሉበት ቦታና ሁኔታ ጭምር ለሃገር እንዲጠቅም ማድረግ ስለሆነ እኔ በችሎታና በልምድ ችግር ይፈጥራል ብዬ አላስብም፡፡
ሰማያዊ፡- በዚህ ረገድ ሃገር-አቀፍ ፓርቲ እንደመሆናችሁ መጠን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለውን የኢትዮጵያ ህዝብን የሚወክል አጀንዳ በማንሳት ምልዓተ-ህዝቡን ማነቃነቅ ግድ ይላችኋልና! ከዚህ አኳያ እናንተ እንደሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ ድጋፍና ተቀባይነት እናገኛለን ብላችሁ የምታስቡበት የተለየ አካባቢ ይኖር ይሆን? ወይንስ እንደአገር-አቀፍ ፓርቲነታችሁ ሁሉንም መማረክ የሚችል ሃሳብ አለን ነው የምትሉት?
ኢ/ር፡ ይልቃል፡- በኛ እምነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክዓ-ምድር ላይ ከኢህአዴግ ጋር ተያይዞ የመጣው ይሄ በጎሣ፣ በመንደር፣ በሰፈር የመደራጀቱ የአየር-ባየር የፖለቲካ ንግድ ሰው-ሰራሽ እና በተለይም በፖለቲካ ልሂቃኑ አካባቢ ጐልቶ የሚታይ የእበላ-ባይ እኩይ ቁማር ነው፡፡ ቅድምም እንደገለፅኩልህ በ196ዐዎቹ አካባቢ ይነፍስ በነበረው ዘመን-አመጣሽ ባዕድ ሃሰብ ሳር ቅጠሉ ሁሉ የኮምዩኒስት አስተሳሰብ ተሸካሚ በነበረበት ጊዜ የአገራችን የዚያ ዘመን ወጣቶች በጥራዝ-ነጠቅነት በላያችን ላይ የጫኑብን የታሪክ መሠረትም ሆነ ተጨባጭ ነባራዊነት የሌለው ወንጋራ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያዊነት ስነ-ልቦና ከዕድሜ-ጠገብነቱ እና ረዥም የታሪክ ትስስሮሹ አንፃር ከጎሣ ፖለቲካ ልቆ በኢትዮጵያውያን ነፍስ ውስጥ በደማቁ የታተመ አሁንም ህያው ቀዳሚ-ማንነታችን በመሆኑ ኢህአዴግ-ወለድ የጎሣ ፖለቲካን የምር እንደሚያሸንፍ ቅንጣት ታክል አንጠራጠርም፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን ይህንን በኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት ላይ ያለንን የማያወላውል ልበ-ሙሉነት ባለማወቅ ወይም በግንዛቤ እጥረት ከአክራሪ-ብሔረተኝነት /ultra nationalism/ እና ጀብደኝነት ጋር አምታተው እንዳይመለከቱብን ማሳሰብ እንሻለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ያለ! ህዝብ የሚደግፈውና የሚያምንበት! አብሮ የኖረበት! ብሎም አብሮ የሞተለት ጭምር የጋራ ማንነት ነው፡፡ እኛ በኢህአዴግ የብሔር-ብሔረሰቦች ዘመን ያለን ሰዎች እኮ! ሌሎች ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሰዎች በመሠረቷት ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር ነን- በአጉል አካሄድ ሄደን እስካላፈረስናት ድረስ! በመሆኑም ይሄ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተገነባ ፅኑዕ እምነት ኢትዮጵያን ከነሙሉ ነፃነቷ እና ክብሯ ጠብቆ ያኖረ፣ ስሟን በዓለም ያስጠራ፣ ህዝቦቿን በአንድነት የያዘ፣ በማህበራዊ ህይወት ያስተሳሰረ የኢትዮጵያውያን ሁሉ መተሳሰሪያ ገመድ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ በአላዋቂነት በጣጥሰን ጥለን አንበሳ የማናስር የተበጣጠስን ድር እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ኢትዮጵያውያን እኮ በታሪካቸው ለኢትዮጵያዊነት ሞተዋል! ከአራቱም አቅጣጫዎች ተሰባስበው ሄደው ለኢትዮጵያዊነት ሞተዋል፡፡ ባንዲራችንን ግመሎቻችን እንኳን ያውቁታል የሚሉት የዳር-አገር ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ የተሰውለት ነው-ኢትዮጵያዊነት! በመሆኑም፡- ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከትናንሽ ሃሳብና ላንድ የግል የፖለቲካ ጥቅም ሲባል ወደየጎሣ ኮሮጆው ካልገባ በስተቀር! እኔ ኢትዮጵያዊነት ዛሬም አሸናፊ እንደሚሆን ከልብ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነት አሁንም ከኢትዮጵያውያን ልብ ላይ ያልተፋቀ እንደውም ውስጥ-ውስጡን ስር-እየሰደደና እየተብላላ የሚሄድ እጅግ ግዙፍ የማንነት መሠረታችን ነው፡፡ ከዚህም በላይ ኢህአዴግ ብቸኛ ˜ውቅና የሚሰጠው መጤ ፖለቲካዊ የጎሣ ማንነት አሁን አሁን እውነተኛ መልኩ እየታየበትና አመኔታ እያጣ የመጣ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መነገጃ ሆኖ እየተጋለጠ ነው፡፡ የቅርቡን የኦህዴድ ሁኔታ ብቻ መመልከቱ ለዚህ በቂ ነው፡፡ የጎሣ-ኢንተርኘረነሮች (ነጋዴዎች) ለግል ቁሳዊ ፍላጎታቸው የሚጠቀሙበት የሀሰት መሳሪያ ነው-የጎሣ ፖለቲካ፡፡ በመሆኑም ይህ ለኢትዬጵያውያን ባዕድ የሆነ አስተሳሰብ በስነ-ልቦናችንም ውስጥ ጭምር ያልተዋሃደ ስለሆነ ምንም እንኳ ለጊዜው እንደግርዶሽ ሆኖ ባይናችን ላይ ቢያጠላብንም በቀላሉ የሚገፈፍና የሚናድ ዓይነ-ጥላ ነው፡፡
ሰማያዊ፡- እዚህ ላይ ግን አንዳንድ የኢህአዴግም ባለሥልጣናት እንደሚያነሱት- የብሔርን ወይንም ደግሞ እንደናንተ አገላለፅ የጎሣን ፖለቲካ ሊያመጣ የቻለ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ነባራዊ የመገለል ሁናቴ እንደሆነ ነው፡፡ በብሔር-ምክንያት የመጎዳት እና ከሥልጣን የመራቅ ሁኔታ ያመጣው ነው ባዬች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር-ጭቆና በኢትዮጵያ ውስጥ መሠረት የሌለው ነው! የሚሉም አሉ፡፡ እናንተ እንደሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ የኋላ ታሪክ ውስጥ የግዛት ማስፋፋት በሚደረግበት ጊዜ የተካሄዱ ነገሮችን እንዴት ነው የምትመለከቷቸው?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- አንደኛ፡- መሪ ስትሆን እ….. በመርህ ደረጃ…… የምር መሪ ከሆንክና …..ለታክቲክና ለፖለቲካ ብለህ ብቻ የማትናገር ከሆነ……እ……. የኋላውን አስከፊ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ማየት ያለብህ የፊቱን ብሩህ መዳረሻ ጭምር ነው፡፡
ህዝብን የሚከፋፍለውንና በአንድ የታሪክ ወቅት ያጋጠመን ችግር ሳይሆን! በጋራ አንድ የሚያረገውንና ወደፊት አብሮ የሚያኖረውን ነው፡፡ በቂም-በቀል ተነሳስቶ ሂሳብ ለማወራረድ ፖለቲከኛ ፖለቲካ ውስጥ አይገባም፡፡ ለዛውም በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ፡፡ ይህ አንድ ራሱን የቻለ የመርህ ጉዳይ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ ስንሄድ ደግሞ፡- ለኢትዮጵያ ብቻ አዲስ የሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረ የተለየ ታሪክ የለም፡፡ አሜሪካ እንደዚህ ዓይነት አገር ሆኖ የተፈጠረው እንዴት ነበር? እና ማንም አገር በፊሽካ… በቃ! ከዚህ ጀምሮ ልክ እንደ ኦሪት፡- ‘ብርሃን ይሁን አለ-ብርሃንም ሆነ!'” ‘እንዲህም ይሁን አለ- እንደዚያም ሆነ!’ እንደሚለው ሳይሆን! በሰዎች የኑሮ ዑደትና ሂደት ውስጥ ነው አገር እየተመሠረተ የሚሄደው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያም በአገር-ግንባታ ሂደት ውስጥ በተለይም በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ የባህል፣ የእምነትና፣ የቋንቋ ተፅዕኖ ነበረ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች አሁን ጥያቄ ናቸው ወይ? አይደሉም! አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው ሌላ ነገር ነው፡፡ እንደዛ ዓይነቱን ነገር ላድርግ ብሎ የሚመጣ መንግሥት የለም! እንደዛ ዓይነቱም ነገር አሁን በዜጎች ውስጥ የለም! በማለያየት ይሄንን የታሪክ እክል አስታውሶ፣ ቆስቁሶና፣ እንዳይሽር ነካክቶ ለራስ የፖለቲካ ጥቅም ማዋል ነው አሁን የተያዘው ፈሊጥ! እንደውም በዘር ተቧድኖ በእኔ እበልጥ! እኔ-እበልጥ! ስሜት አገርን ሊጐዳና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነገር ያለው አሁን ነው፡፡ የብሔረሰቦችን ችግር ፈታሁ የሚለው ኢህአዴግም ይህንን ለራሱ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎትና የስልጣን ጥማት አውሎታል፡፡ የብሔረሰብ አስተዳደር እኮ የለም አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ! ብሔረሰቦች በውክልና ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ከሆነ አቶ መለስ ለ21 ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አልነበረባቸውም፡፡ እንደእነሱ የጎሣ ፖለቲካ ቀመር ከሆነ፡- የኦሮምኛ ተናጋሪው ብዙ ቁጥር አለው፣ አማርኛ ተናጋሪው ብዙ ቁጥር አለው- ስለዚህ በውክልና ከሆነ ከነዚህ ቋንቋ ተናጋሪዎች የመጡ ሰዎች ናቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ያለባቸው፡፡ በጎሣ ስም ተደራጅቶ በተቀነባበረ እና ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ ላይ ጭቆና እየተካሄደ ያለው እንደውም አሁን ነው፡፡ ሌሎች ቀደምቶችስ ህይወትን ለመግፋትና በአገር-ግንባታ ሂደት ውስጥ በደመ-ነፍስ በመውተርተር የተፈጠረ ስህተት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አገር ሲገነባ የሚጠበቅ ሂደት ነው፡፡ የትም አገር የሆነው እንዲሁ ነው! በተጨማሪ አገር እንዲሁ ዝም ብሎ ቀጥ ያለ ታሪክ አይኖረውም፡፡ የግለሰብም ይሁን፣ የድርጅትም ይሁን፣ የአገርም ታሪክ የራሱ ደካማና ጠንካራ ጎኖች ያሉት እንጂ እንደመላእክት ታሪክ እንከን-የለሽ አይደለም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ታሪክም በዚሁ መልክ መታየት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ምናልባትም እኮ በአገር-ግንባታ ረገድ በኢትዮጵያ ታሪክ የተፈጠረው ስህተት ከሌላው አገር ጋር ሲነፃፀር ቀለል ያለና እዚህ ግባ የማይባል ይሆናል፡፡ በአሁኑም ጊዜ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለ መሠረታዊ ችግር የለም፡፡ በአገዛዙና በዜጎች መካከል ግን ሁልጊዜም ችግር ይኖራል- ከአገዛዝ እስከአልወጣን ድረስ ጠመንጃ የያዘው ሃይል ሁሉንም ነገር በጉልበቱ ከማድረግ ወደኋላ ስለማይል ችግር ውስጥ መቆየታችን አይቀርም፡፡ ይሄንን መለወጥ የምንችለው ሥልጣን የህዝብ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደህዝብ ሲተላለፍ የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች ሁሉ የሰውነት እና የዜግነት መብቶችን ጨምሮ አብሮ መከበር ይጀምራሉ፡፡ እንጂ፡- የባህልም፣ የእምነትም፣ የቋንቋም ተፅዕኖ በአገር-ግንባታ ሂደት ውስጥ ነበረ፡፡
ሰማያዊ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ በብሔር ስም የተደራጁና መንግሥትን በአመፅ ጭምር ገርስሰው ‘ነፃ መውጣት’ የሚሹ የፖለቲካ ሃይሎች አሎ፡፡ እና እነሱንስ እናንተ እንደፓርቲ እንዴት ነው የምትመለከቷቸው? እነዚህን ዓይነት ጥያቄዎች ሲከሰቱስ ምላሽ የምትሰጡበት አግባብ እንዴት ያለ ነው? ፓርቲያችሁ እንደሚለው ህዝባዊ-መንግሥት/ዴሞክራሲ/ በዚች አገር ቢመሰረት የእነዚህ ኃይሎች ዕጣ ፈንታና ጥያቄ ምን ይሆናል?
ኢ/ር፡ ይልቃል፡- አንደኛ እነዚህ በብሔር-ስም የተደራጁ ነፃ አውጪ ድርጅቶች እያደጉ ነው ያሉት ወይስ እየከሰሙ? የሚለውን ብናይ /መሠረታዊ የሆኑ ምክንያቶች እያሉ እንኳ! በመንግሥት አሠራር ውስጥ ቅር የሚያሰኙና ወደ ዳር የሚገፉ ነገሮች እንዳሉ እኛም እናምናለን/ ለጥያቄው ከፊል-ምላሽ ይሆናል፡፡ ይህ ጊዜ እያለፈበትና እየሳሳ የሄደ ከንቱ አማራጭ ነው፡፡
ነገር ግን ከነዚህ ኃይሎች ጋር በችግሩ ላይ እንደመስማማታችን መጠን በመፍትሄው አቅጣጫ ዙሪያ እንለያያለን፡፡ ፍፁም ተቃራኒ ነን ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ከጠመንጃ ትግል ይልቅ የፖለቲካ ትግልን መርጠን በሃሳብ የበላይነት ለማሸነፍ የምንጥር ህጋዊ ድርጅት ነን እኛ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በዜግነት መብት ላይ ተንተርሰን መብቶችን ሁሉ ያለመሸራረፍ እስካከበርን ድረስ! እነዚያ ድርጅቶች ህዝባዊ የፖለቲካ ሥልጣን በተመሰረተ ማግሥት እነርሱ እንደፖለቲካ አጀንዳ የሚያነሱት ጥያቄ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡ እዛጋ ያበቃል ሁሉም ነገር! አሁን እኮ እነዚህ ኃይሎች እያሉ ያሉት፡- ‘የፖለቲካ ትግል ማድረግ አይቻልም! መንግሥቱ አፋኝ ነው! ሥልጣን የህዝብ አልሆነም!’ ነው፡፡ በመሆኑም ከጎሣ አቅጣጫም ሆነ ከሀገር- አቀፍ አቅጣጫ የሚመጡት የኃይል-አማራጭ የሚከተሉ የፖለቲካ ቡድኖች የሚያነሱት ዋነኛ ጥያቄ ከመሠረቱ ካየነው ከህዝባዊ መንግሥት አለመኖር የሚመነጩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይሄ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ከተቀየረ እነዚህ ድርጅቶችም በጠመንጃ የሚዋጉት ኃይል አይኖርም-የጠመንጃ መንግሥት በሌለበት ሁኔታ፡፡ ጥያቄው በመሠረቱ እዚያ ላይ አብቅቷልና! አሁንም አንተ ስትጠይቀኝ ከጥያቄህ ውስጥ ያለው ግምታዊ መነሻ /presumption/፡- አንድ የፖለቲካ ቡድን ስልጣን እንደወሰደ አርገህ በማሰብ ነው! እንጂ ስልጣን የህዝብ መሆኑን እና ሥልጣኑን የያዘው ቡድንም በተወሰነ የጊዜ ገደብ ከህዝብ የተሰጠው አደራ እንደሆነ አርገን ብናየው በዚህ ሁኔታ እነዚያ ኃይሎች የሚታገሉት ቡድን አይኖርም እዛጋ፡፡ በጎሣ መደራጀት እንፈልጋለን ብለው ካሉ ጥያቄያቸውን ለህዝብ በግልፅ የፖለቲካ መድረክ ያቀርባሉ! የሚጠቅምና የሚያምንበት ሆኖ ሲገኝ ይደግፋቸዋል ካልሆነም ይጥላቸዋል፡፡
ሰማያዊ፡- ስለሰላማዊ ትግል ይሄን ያህል ተስፋ የሰጣችሁ ነገር ምንድነው? ብዙዎች እንደሚያነሱት እጅግ አፋኝ ህጎች (የፀረ ሽብርና የመያዶች የመሳሰሉት) ባሉበትና እንዲሁም አሁን እንኳን በቅርቡ እንደምናየው በጣት የሚቆጠሩ አማራጭ የኘሬስ ውጤቶች እየታገዱ ባሉበት ሁኔታ! ይሄን ያህል ተስፋ ያሰነቃችሁ ነገር ምንድነው?
ኢ/ር፣ይልቃል፡- እንግዲህ ተስፋ እንድንሰንቅ ያረጉን እነዚሁ ችግሮች ናቸው በራሳቸው፡፡ በእኛ እምነት እነዚህ ነገሮች የሚያሳዩን፡- ኢህአዴግ ምንም ዓይነት የፖለቲካ መሠረት አጥቶ ጉልበቱ ብቻ እንደቀረ ነው፡፡ አንድ ጋዜጣ በታተመ ጊዜ መንግሥቴ ይፈርሳል ብሎ ከሰጋ! በህዝብ ሠራሁት እና አደረግሁት የሚለው ነገር ሁሉ የሀሰት መሆኑንና እርሱም አየር ላይ ተንጠልጥሎ የቀረ መንግሥት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ይህንን ፖለቲካው ያለበትን ዙር ተረድቶ የኢህአዴግ ጭቆና ማብዛት ቅጥ እያጣ ከመጣ ፍርሃትና ከአቅመ-ቢስነት መመንጨቱን መገንዘብ አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ከፍራቻና ከአቅመ-ቢስነት የመጣ እንጂ ከጥንካሬ አይደለም፡፡ ስለዚህ በፖለቲካ ትግል በቀላሉ የሚለወጥ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ደርሰናል፡፡ ሆኖም ግን ሰው ብዙ የማይረዳው ነገር ሰላማዊ ትግል የጠመንጃ ትግል የሚያስከፍለውን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው! ሞትን፣ ስቃይን፣ መሰደድን፣ ሁሉንም ነገር ያደርጋል፡፡ ይሄ እንደውም ከመሪዎቹ የሚጀምር ክስተት ነው-ባብዛኛው፡፡ ይሄን ዋጋ ለመክፈል እስከተዘጋጀን ግን ለመለወጥ እጅግ ቀላል ነገር ነው፡፡ በሃሳብ ስትሸነፍ ነው ከባድ የሚሆነው፡፡ አንድን የፖለቲካ ትግል ከባድ የሚያደረገው በህዝቡ ውስጥ ስር-ያልሰደደን ሃሳብ አሳምነህ አስተምረህ በዛ ውስጥ አሰባስበህ ያንን እምነት በተግባር ለመለወጥ የሚደረገው ጉዞ ነው፡፡ አሁን በኛ በኩል በሃሳብ ችግር የለብንም፣ነባራዊ ሁኔታን በመረዳትም ችግር የለብንም፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ተስፋ የሚሰጥ ሀይል ሆኖና ዋጋ ከፍሎ ብሎም ያንን ውጤት እንደሚያመጣ አሳይቶ የፖለቲካ ትግል ማድረግ ነው፡፡
ስለዚህ የችግሮቹ መባባስም የሚያመላክተው ነገር ቢኖር ችግሮቹን ለመለወጥ መነሳሳት እንዳለብን ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት እንደዜጋ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነውና፡፡ ሌላው ደግሞ፡- ይሄ ሁኔታ የሚያሳየው ኢህአዴግ በህዝቡ ውስጥ እንደሌለና ሥርዓቱን ለመታገልም በጣም ቀላል እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ነገሮች በተስፋ እንድንሰራና ነገሮችን እንድንለውጥ የሚያበረታቱ ናቸው፡፡
ሰማያዊ፡- ከዚህ አንፃር ከዚሁ ጋር ተያይዞ የህዝበ-ሙስሊሙ የእምነት ነፃነት ጥያቄና ጥያቄውን እያቀረበበት ያለውን መንገድ ከሰላማዊ ትግል አንፃር ፓርቲያችሁ እንዴት ይገመግመዋል?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- ስለዚህ ጉዳይ በጣም የሚገርመው እና የሚደንቀው ነገር፡- ዜጎች መንግሥት በሀሰት ክስና በሀሰት ወንጀል ተጠያቂ አድርጐ ያስረኛል ብለው እጅግ ሰላማዊና ህጋዊ ለመሆን ሲጥሩ” በአንጻሩ መንግሥት ደግሞ ኃላፊነት የጎደለው ሥራ ሲሰራ መታየቱ ነው፡፡ መንግሥት አገርን ለመረበሽ፣ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ጋር ለማናከስ፣ በሃይማኖቶቹም ውስጥ ሰርጐ-በመግባት ለመከፋፈል ሲጥርና ሰላማዊያንን በሽብርተኝነት ሲከስ ማየቱ” በሌላ በኩል ዜጎች ደግሞ ከልክ በላይ ሲጠነቀቁ ለማስተዋል ተችሏል፡፡ ይሄ በእውነት በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነገር ነው፡፡ ዜጎች ይህን ያህል ለእውነትና ለህጋዊነት ሲጠነቀቁ፣ መንግሥት ደግሞ ሌላ እኩይ መንገድ ሲከተል ማየቱ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ መንግሥት ለ17ቱ የህዝበ-ሙስሊም ኮሚቴዎች ዕውቅና ሰጥቶ ሲደራደር ከቆየ በኋላ፣ በዚህ ነጥብ ተስማማን፣ በዚህ ነጥብ አልተስማማንም ሲል ከርሞ መጨረሻ ላይ ጥያቄያቸው የህዝብ ድጋፍ ሲያገኝ ሽብርተኛ ናቸው ብሎ አሰራቸው፡፡ እነዚያን ሰዎች ሲያስራቸው ደግሞ እባክህን ፍታልን ብለው ነጭ መሃረብ እያውለበለቡ ድምፃቸውን ሳያሰሙ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ሃሳባቸውን ገለፁ፡፡ እና ይሄ የኢትዮጵያ ህዝብ የምር በእውነት የሚመራው ካገኘና የጋራ የሚያደርጉትን አስተሳሰቦች ወደፊት ይዞለት ከወጣ ለሰላማዊ ትግል ዝግጁ መሆኑን ያየሁበት ሁኔታ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሰሞኑን አንድ አሜሪካዊ በሰራው ፊልም ሳቢያ በአረብ አገራት በሙሉ ብዙ የንብረት ውድመት፣የህይወት መጥፋት፣ ያለመረጋጋት ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይሄ ሁሉ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ችግር እንኳ እያለ ጉዳዩ በዚያ መልኩ አልተገለፀም፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ከሃይማኖትም፣ ከጎሠኝነትም በላይ ነው ብለን ስንናገር ይሄ የተግባር ማሳያ ምሳሌው ሊሆነን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ነብዩ መሃመድን ሳይወዷቸው ቀርተው አይደለም-እንዲህ ያለውን ነገር ያላደረጉት፡፡ ከሳዑዲ-አረቢያ በፊት እስልምናን የተቀበለች አገር ናት ኢትዮጵያ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ሃይማኖታቸውን ያከብራሉ! ነገር ግን አንድ አሜሪካዊ ሰውዬ ነብዩ መሃመድን የሚያቃልል ነገር ሰራ ተብሎ ፀረ-አሜሪካ ወይም ፀረ-መንግሥት የሆነ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይገባ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በአስተዋይነታቸው ተረድተዋል፡፡ በሙስሊምነታቸው ከሆነ አረቦች ያደረጉትን ነገር ማድረግ ነበረባቸው፡፡ የሆነው ግን ያ አልነበረም፡፡ ስለዚህ፡- ኢትዮጵያዊነት የማመዛዘን የጨዋነት ምልክት ነው ስንል የምር ይሄ ነው የሚነግረን፡፡ ከዚህ በላይ ምን ነጋሪ ያስፈልገናል?!
ሰማያዊ፡- ፓርቲያችሁ ከአዲሱ የአቶ ኃ/ማርያም አስተዳደር የሚጠብቀው እና ተስፋ የሚያደርገው ነገር አለ?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እንግዲህ እሱ ገና አቅጣጫው ያልተለየ ጉዳይ ነው፡፡ ምናልባትም የበለጠ ጭቆናው የበዛበት ነገር በሁለት መልኩ ካየኸው፡- ሊነጋ ሲል ይጨልማል ዓይነት ነገርም ሊሆን ይችላል” አሊያ ደግሞ በበፊቱ መንገድ የመቀጠልና ራስን በራስ የማጥፋት /suicidal/ ጉዞ ሊሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም አሁን ያለው የኘሬስ አፈናና እቀባ ዘላቂ የሆነ ስልት ላይሆን ይችላል፡፡ ኢህአዴጎች አያያዙን ሊያውቁበት ይገባል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ሰው ሥራ-አጥ ነው፣ የኑሮ ውድነቱ በተለይ የምግብ ዋጋ ንረት ሰማይ ደርሷል፣ ሙስናው በየቦታው ተንሰራፍቷል፣ በመንግሥት አስተዳደር ላይ የሚታየው አለመተማመን እና የህዝቡ አመኔታን ማጣት ከፍተኛ ሆኗል፡ይሄ ሁሉ ነገር ተደማምሮ ሌላ ጣጣ ሊያመጣ ይችላል ቢባል እርግማን መጥራት አይሆንም፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ወደማንመኘው ማህበራዊ ቀውስ እንዳንገባ ያሰጋናል፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት የፖለቲካ አሳታፊነቱ እና መድረኩ ከፈት ካልተደረገ፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በችግሩ ላይ መረባረብ ከሌለ፣ በአገሩ ኃላፊነት በተሰማበት ሁኔታ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ሰው የየራሱን ድርሻ ካልወሰደ፣ ኢህአዴግ ሁሌም እንደሚለው ችግሩንም የማውቀው እኔ ነኝ መፍትሄውም እኔ ነኝ ካለ መጀመሪያ እንደ ድርጅት የሚጐዳው ኢህአዴግ ራሱ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ እንደአገር የምንጎዳው-ኢህአዴግ የአገር መሪ በመሆኑ የተነሳ የድርጅቱ ጉዳት ለአገሪቱም ጉዳት ስለሚፈጥር!
እንግዲህ በተስፈኝነት የምናምነው ነገር ቢኖር ኢህአዴግ ለራሱም ሲል ይስተካከላል የሚለውን ነው፡፡ ያ እማይሆን ከሆነ ግን ለሁላችንም የማይበጅና እንደአገርም የተደከመውን ነገር ሁሉ ወደኋላ የመመለስ ነገር ሊመጣ ይችላል፡
ሰማያዊ፡- ነገር ግን የአቶ ኃ/ማርያም አካሄድ ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ብዙም ያልተለየ እንደሆነ በቅርቡ ከቪ.ኦ.ኤ. ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ ጥቁምታ ሰጥቷል፡፡ በታሰሩ ጋዜጠኞችና በመሳሰሉት ጉዳዬች ላይም ተመሳሳይ አቋም አራምደዋል፡ ታዲያ እንደው ዕድል ለመስጠት ያህል ብቻ ነው ኢህአዴግ ይስተካከላል እያሉ ያሉት ወይስ አቶ ኃ/ማርያም አንዳች አዲስ ሙከራ ይሞክሩ እንደሆን ብለው ነው?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እኔ የነገሮች ተፈጥሯዊ ውጤታቸውን /Natural consequence/ ነው እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ ኢህአዴግ ይህን ማድረግ ግዴታው ነው” በአቶ መለስ ጊዜ እየተከማቹ እየተከማቹ የሄዱ ችግሮች እና በውል ያልተፈቱ በማለባበስ ብቻ እየተድበሰበሱ የመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ በዚሁ መንገድ እቀጥላለሁ ካለ ኢህአዴግ ወደገደሉ እየተጓዘ እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡ ይሄ ትንቢት ተናጋሪ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ሥራ-አጥነት፣ ችጋር እና ድርቅ እኮ ንጉሱንም አውርደዋል፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት እና የህይወት ዋስትና ማጣት ውስጥ እንዴት በስልጣን ተደላድሎ መቀጠል ይችላል?
በተፈጥሮ ህግም ቢሆን ስርዓት ያረጃል፣ ቅቡልነቱ እየሳሳ እና እያለቀ ካፒታሉን እየበላ በሄደ ቁጥር ስርዓት እርስ-በራሱም ተጠላልፎ ይወድቃል፡፡ የኛ ሚና ህዝብን አደራጅቶ የሚመጣው ለውጥ የተጠና የታቀደና አስቀድሞ የተመራ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ የህዝብን የፖለቲካ-ንቃት ማሳደግ ነው ሚናችን፡፡ ስለዚህ ለውጡ በግድም ሆነ በውድ አይቀሬ ነው፡፡
ሰማያዊ፡- በዚህ ረገድ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ተቀራርቦና ጥምረት ፈጥሮ የመስራት እንቅስቃሴያችሁ ምን ያህል ነው?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ ረገድ፡- እ—- እንደኢህአዴግ ቃል አታርግብኝ እንጂ፡- ምንም በሌለበት መልካም ጅምሮች እያለ ተስፋ የሚሰጠን ነገር አለ እና—-/ፈገግታ/ እና እነዚህ ነገሮች በጥንካሬና በራዕይ ጥራት ከተያዙ መልካም የሆኑ ጅምሮች አሉ፡፡ በፊትም እንደገለፅኩልህ እንደ አዲስና ጀማሪ ፓርቲ ሳይሆን ትላልቅ ሰዎች የፓርቲ አባል ሳይሆኑ ወጣቶችን ለመደገፍና የራሳቸውን ዜግነታዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ የሆኑበት ምናልባት በፖለቲካ ታሪካችንም የመጀመሪያው በሆነ መልኩ ፓርቲያችንን ለመደገፍ የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ደግሞ፡- በአሰራርና በፖለቲካ እምነት ተለያይተን ብንወጣም አንዳንዶቻችን አንድነት ውስጥ የነበርን ከመሆናችን አንፃር ከፓርቲው ጋር አዎንታዊ ግንኙነት አለን፡፡ ፓርቲያችንን ስናቋቁምም ተጋባዥ እንግዶች ነበሩ፡፡ በቅርብ ጊዜም የነእስክንድር እና አንዷለም አንደኛ ዓመት መታሰር ምክንያት አድርጐ የሻማ ማብራት ዝግጀት ሲያደርግ እኛም ተጋብዘን ተገኝተናል፡፡ እኔም ተናጋሪ ነበርኩ በዚያ ዝግጅት ላይ፡፡ ስለዚህ በፖለቲካ ተለያይተን እንኳ መልካም ግንኙነቶቻችን ቀጥለዋል፡፡ ከመኢአድም ጋር እንዲሁ ኘሮግራሞቻቸው ላይ እየተካፈልን ነው፡፡ ባለፈው የአድዋ ድልን ሲያከብሩም ጠርተውን ነበር፡፡ ከመድረክ አመራሮችም ጋር ቢሆን ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ ስለዚህ ይሄን የማዳበር ነገር ነው ያለብን፡፡
አሁን እንደበፊቱ የመፈራረጅ ነገር ጠፍቶ እንደአቻ ተከባብረን እየሰራን ነው በተግባር፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች በየደረጃው እያደጉ እንዲሄዱ ማድረግ ደግሞ ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ የፖለቲካ ባህላችንም እጅግ ዳርና ዳር የቆመ ከመሆኑም አኳያ፣ በፖለቲካ መሸናነፍ እንደመልካም ባህል መታየት ገና ባለመጀመሩ፣ ፓርቲዎች ብዙ ጊዜ የሚመሰረቱት በግለቦች ስብዕና ላይ በመሆኑ እጅግ አያሌ ስራ ይጠበቅብናል፡፡
ሰማያዊ፡- እንግዲህ ከተነሳ አይቀር በግለሰብ ተክለ-ስብዕና ላይ ካለመመስረት አንፃር የናንተ ፓርቲ እንዴት ነው? ይህንን መጥፎ ባህል ቀርፏል ይላሉ?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እሱ በሽታ ቀስ እያለ ካልመጣ እኛጋ ብትሄድ አሁን ሰማያዊን የሚያውቀውን ያክል ሰው ይልቃልን እንደፓርቲው ሊቀመንበር የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ ይሄ ለኔ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ምክንያቱም፡- ከሊቀ-መንበሩ በፊት ስለፓርቲው ብዙ ሰው አወቀ ማለት እንግዲህ ፓርቲው በመሪው ላይ አልተንጠለጠለም ማለት ነው ለኔ የሚገባኝ፡፡ ከዛ አለፍ ስትል ደግሞ ብዙዎቻችን ለረዥም ጊዜ ጓደኛማቾች ሆነን በቅርብ ለመተቻቸት በድፍረት ለመነጋገር እና በጋራ አቋም ለመውሰድ በተመሳሳይ ዕድሜና የግንዛቤ ደረጃ ላይም በመሆናችን አንዱ የሌላው ተገዢ እንዳይሆን መልካም አጋጣሚ ይፈጥርልናል፡፡ ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፅዕኖ ያላቸው እንደዕድሜ፣ በትምህርት መራራቅ፣ በባህልና በአስተሳሰብ መራራቅ የለም ብዙዎቻችን ጋር፡፡ስለዚህ አንዱ ከላይ አንዱ ከታች ላለመሆን መልካም አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ችግሩንም ደግሞ አስቀድሞ መገንዘቡ አለ፡፡ ያንንም ነገር ለመከላከል በፓርቲያችን መዋቅር ውስጥ ባሉ አግባቦች ተጠቅመን የየራሳችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡ አንድ ሰው ሁሉን ነገር የሚሰራና የሚመራ እንዳይሆንም በተለይ በደንባችን ውስጥ በሰፊው ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ እና ያ ዓይነቱ አደጋ በኛ ውስጥ እንደማይከሰት ተስፋ አለን እንግዲህ፡፡
ሰማያዊ፡- በአቶ መለስ አስተዳደር ወቅት በእንጥልጥል የቀሩ ጉዳዮች አሉ ሲሉ የሚደመጡ አካላት አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የአሰብን ወደብ የማግኘት ጉዳይ፣ ያልተቋጨው የባድመ መሬት መካለል ጉዳይ፣ የዋጋ-ግሽበት ንረትን መቆጣጠር ያለመቻል፣ ሙስናን መግታት ማቃትና እንደውም ‘መንግሥታዊ-ሌባ’ አለ ብሎ እስከማመን ጫፍ ላይ የደረሰ የአስተዳደር ንቅዘት፣ወዘተረፈ… በነዚህ ጉዳዮች ላይ ፓርቲያችሁ ምን መፍትሄ ይዞ መጥቷል?
ኢ/ር፡ይልቃል፡- እነዚህ ሁሉ ነገሮች በራሳቸው ችግር ሳይሆኑ የችግር ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የችግሮቹ መለኪያ-ጠቋሚዎች /Verifiable Indicators/ የሚባሉት ናቸው በኘሮጀክት ቋንቋ፡፡ በመሆኑም መሠረታዊ ችግሩ ስልጣን የህዝብ አለመሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ከግራ ርዕዬተ-ዓለም የተቀዳና ማዕከላዊ-ዴሞክራሲያዊነት በሚል ሁሉንም ነገር በራሱ የያዘ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ ስልጣን ለማስጠበቅ ሲባል ነው እንደዚህ ዓይነት ነገሮች የሚፈጠሩት፡፡ አሰብን ለኤርትራ ባይሰጥና ኤርትራ ያኔ እፎይታ ባይሰጠው የአቶ መለስ መንግሥት መደላደል አይችልም ነበር፡፡ እንደዚሁም ደግሞ፡- በህዝብ ተቀባይነት የሌለው መንግሥት ስለሆነ የኢትዮ-ኤርትራን ጉዳይ እንዲሁ ተለባብሶ እንዲቀር ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለመስጠት የተቸገረው የፈረንጆች ተፅዕኖም ተጨምሮበት ቡድኑንም እስከመክፈል ድረስ የሄደው ለህዝብ ተጠያቂ የሆነ መንግሥት ያለመኖር ናቸው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካውም ደግሞ ህዝብን በማገልገልና በሃሳብ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በጥቅም ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ነው፡፡
ሰማያዊ፡- ለምዕራባውያን ኃይሎች በተለይ ለኢህአዴግ አጋር ሆነው ለቆዩት የሚያስተላልፉት መልዕክት ይኖራል?
ኢ/ር፣ይልቃል፡- ፈረንጆቹ ለጥናት እንዲመቻቸው ሲሉ ከፋፍለው ያጠኑትን የኢትዮጵያ ታሪክ ወደፖለቲካዊ አተያይም አምጥተው የኢትዮጵያን ገፅታም በተከፋፈለ ሁኔታ ለማየት ባይሞክሩ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ እኔ እሱን ሊረዱት ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ፡- የኢትዮጵያ መረጋጋት የመጣው በገዢው ፓርቲ ላይ ባለው የጦር-ኃይል ወይም የአመራር ብቃት ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪነት ነው ብለው ያምናሉ ሁልጊዜ፡፡ እሱ ግን በጭራሽ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን አጠቃላይ የወል ስነ-ልቦናቸው የሰላም፣ የጨዋነት፣ አብሮ የመኖር፣ የእርቅና የሽምግልና ነው፡፡ የመረጋጋታችንም ምንጭ ይሄው ነው፡፡ ሌላ አይደለም! በመሆኑም እነዚህ የምዕራብ ኃይሎች ከህዝቡ ጋር ቢቆሙና ለዴሞክራሲ ቢታገሉ ኪኢትዮጵያ ጋር በአቻነት የተመሠረተ አጋርነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቀጠናው በኢህአዴግ ሞግዚትነት ካልተዳደረ በቀር ይተራመሳል ብለው ባያስቡ መልካም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንደህዝብ በአቻነት፣ በእኩልነት ለቀጠናችንም ሆነ ለዓለም-ዓቀፍ ሰላም አስተዋፅኦ የማድረግ ታሪክ ያለን እንደመሆናችን ይህንኑ ምኞታቸውን ከአምባገነን አገዛዞች ጋር ሳይሆን ከህዝብ ጋር ቢያደርጉት ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡ ቀጠናውን የሚያረጋጋው ጠመንጃ ወይንም በአንድ የፖለቲካ ቡድን እንዳልሆነ አውቀው ከህዝብ ጋር ቢቆሙ መልካም ነው እላለሁ፡፡
ሰማያዊ፡- በብዙ ዘርፈ-ብዙ የሞራል ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ለሆነው ወጣት ፓርቲያችሁ ምን መልዕክት ይኖረው ይሆን? እናንተም ባብዛኛው ወጣቶች ከመሆናችሁ አንጻር—–
ኢ/ር፣ይልቃል፡- እንግዲህ —-እ—— ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ በራሱ በምርጫው ያደረገውም አይደል ወጣቱ፡፡ ይሄ ከከተሜነት ህይወት ጋር የተያያዘ ውጥንቅጥ ያለበት፣ ድህነት ያለበት፣ የዓለም-ዓቀፍ የባህል ተፅዕኖዎች ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ-እነዚህ ነገሮች ሁሉ ተደምረው ካቅሙ በላይ ሆኖ በነዚህ ነገሮች ቢሸነፍ የሚገርም አይሆንም፡፡ ነገር ግን ሽንፈቱ ዘላቂ እንዳይሆን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ወደአሸናፊነት ለመውጣት ሁልጊዜ ተሸንፌያለሁ በቃ! ብሎ አለመቅረት አንዱ ወሳኝ የመፍትሄ ጉዞ ነው፡፡ ከዛ ባለፈ ደግሞ የህይወት መርህ መመዘኛውን ወይም የሞራል እሴት መሠረቱን /Value-Judgment/ መቀየር ነው፡፡ ሰው አካል አለው፣ አእምሮ አለው፣መንፈስ አለው፡፡ ለአካሉ ነው የሚመገበው፡፡ ይህ የእንስሳነት ባህሪያችን ነው፡፡ እኛን ከእንስሳት የለየን ሰውነታችን በሞራል-መመዘኛ ስለሌሎች ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ይህም ነው የሰውነት ልዩ ባህሪያችን፡፡ ስለዚህ፡- ስለሌሎች ማሰብ፣ ኢ-ፍትሃዊነትን አለመቀበል፣ አለመስረቅ የሞራል መርሆዎቻችንና የሰውነት መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ ሰው ስንባል አምላክ ሲፈጥረን ይሄ አብሮ የተሰጠን ነገር ነው፡፡ በመሆኑም አምላክ የሰጠኝን ሰውነቴን አላዋርደውም ይበል-ወጣቱ! ስጋዬ ብቻውን አልተፈጠረም-አካልም፣ አእምሮም፣ መንፈስም አንድ ላይ ያለኝ ነኝ ሊል ይገባዋል፡፡ ስለዚህ የአእምሮዬን የመንፈሴንና የሰውነቴን ባህሪ ትቼ በእንስሳነቴ ብቻ አልኖርም ብሎ ቆራጥ አቋም መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ያ በሆነ ጊዜ ከወድቀታችንም ለመቃናት ራሳችንንም ተጠያቂ ለማድረግ ዕድል ይሰጠናል የሚል እምነት አለኝ፡፡
Leave a Reply