ሃገራችን በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው። ይህ ቀውስ ወደ እርስበርስ ጦርነት እያመራ ይገኛል። ጉዳዩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ላይ ጥቅም ያላቸው የውጭ ዜጎችንም ማሳሰቡ አልቀረም። በሆላንድ፣ ዘ ሄግ ከተማ፣ ዲያማንት ኮሌጅ 24 ሴፕቴምበር 2016 በተደረው በዚህ ወርክሾፕ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና የሆላንድ ዜጎች ተገኝተው ነበር። በወርክሾፑ እንዲወያዩ የተጋበዙት ታዋቂው ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ፣ መስፍን አማን እና ገረሱ ቱፋ ናቸው። አወያዮቹ ሚ/ር ፍራንስ እና አብይ አሸናፊ ነበሩ።
ተናጋሪዎቹ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ከፍተኛ ቀውስ በማስረጃ እያጣቀሱ ካብራሩ በኋላ የገዥው ፓርቲ አጠያያቂ ህጋዊነት እና የማክተሙ አዝማምያን ያመላከተ ድምዳሜ ሰጥተዋል።
መጪውን ሁኔታ የሚጠቁሙ ሶስት ቢሆኖች (Scenarios) ላይም የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።
አንደኛው ቢሆን (Scenario) የፕ/ር መስፍን ወልደማርያም፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና የዶ/ር ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጩ አስተያየቶች ሲሆኑ፤ በጥቅሉ ኢትዮጵያ ወደ እርስበርስ ጦርነት እንደምታመራ የሚጠቁመው እይታ ነው።
ሁለተኛው ቢሆን በገዥው ፓርቲ እየተነገረ ያለው የተሃድሶ ለውጥ የሚለው እንቅስቃሴ ሲሆን፤
ሶስተኛው ቢሆን ደግሞ የሽግግር መንግስት ይቋቋማል፣ ከዚያም ፍትሃዊ ምርጫ ይደረጋል የሚለው ግምት ነው።
ሶስቱም ተናጋሪዎችም ሆኑ በአዳራሹ ያሉ ተሳታፊዎች ሁለተኛው እና ሶስተኛው ቢሆኖች የማይታሰቡ እንደሆኑ አስምረውበታል። በተለይ ሁሉንም አካላት ያካተተ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ፍትሃዊ ምርጫ ቢደረግ ችግሩ እንደሚፈታ ፕ/ር ጆን አቢንክ ተናግረዋል። ነገር ግን ከገዥው ፓርቲ የረጅም ግዜ ተመክሮ እና ባህርይ አንጻር ይህ ሊሆን አይችልም። ገዥው ፓርቲ ለትይታ ብቻ የሚሆን ቅርጻዊ ለውጥ (cosmetic changes) በማድረግ መቆየት መርጣል ይላሉ።
መስፍን አማን እና ገረሱ ቱፋም አንደኛው ቢሆን ላይ ነው የሚያመለክቱት፣ “ከሁሉም ቢሆኖች እርስበርስ ጦርነቱ መጥፎው አማራጭ ቢሆንም፣ ይህ ሊሆን ግድ ሆኗል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የህዝቡን ጥያቄ ለማፈን ሰራዊቱን ሲያዙ ነው ጦርነት ያታወጀው። ሃገሪቱ አንደኛውን በርስበርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች” ባይ ናቸው።
የዲያስፖራው ሚናም በውይይቱ ተነስቷል። ዲያስፖራው ከዘር እና ከጎሳ ውይይት አልፎ በጋራ ችግሮች፣ በብሄራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያይ ፕሮፌሰር አቢንክ መክረዋል።
ገረሱ ቱፋ እና ከመስፍን አማንም የኦሮሞ እና አማራ ተወላጆች በግል የማንስማማባቸው ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን በሃገሪቱ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር እና መፍትሄ ለመፈለግ ችግር የለብንም ብለዋል። ከስብሰባው በኋላ የኦሮሞ እና አማራ ኮሚኒቲ አባላት የጋራ መድረክ ለመመስረት ተስማምተዋል።
እንደዚህ አይነት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይት ሲካሄድ የሆላንድ ዜጎች በተለምዶ ተገኝተው አያውቁም ነበር። በዚህ ውይይት ላይ አሁን ለመገኘት የፈለጉበት ምክንያትም ግልጽ ነው። በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ አመጽ የሆላንድን ብሄራዊ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የዳች ሜዲያ ተቋማት እየገለጹ ነው። በአስር ሚሊዮን ዩሮ ኢንቨስትመንት ከአመት በፊት ኢትዮጵያ በመግባት አበባ ምርት የተሰማራው ኩባንያ በባሕርዳር ህዝባዊ አመጽ ሙሉ በሙሉ ወድሞ ስራውን በይፋ አቁሟል። ጊንጪ ላይም የሆላንድ የእርሻ ኩባንያ ከጥቅም ውጪ መሆኑ በዜና ተሰምቷል። ይህ ጉዳይ ሄነከን ቢራን ጨምሮ ለተቀሩት 130 የሚሆኑ የሆላንድ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
ክንፉ አሰፋ
Mulugeta Andargie says
ጓዶች!! የሌለ ነገር እየፈጠራችሁ ሰው አታደናግሩ! ሁሉም ሰው በሰላም ለመኖር ይፈልጋል! የምትጠቅሷቸው ሰዎች ሁሉ ፋይዳ ሰጪዎች አይደሉም!! ወሳኙ ሃገር ውስጥ ያለው ህዝብ ነው!
ማህሌት says
የምትሰጠው አስተያየት ማንነትህን ስለሚያሳይ መልስ ባያስፈልግህም የበላህን እያከከው እንደሆነ ያስታውቃል ወያኔ ሞቱ ደርሶ ሲፈራገጥ እንዳንተ ያሉ ደጋፊዎቹ እውነቱ አልዋጥም ቢላችሁ አይገርምምናት!!