የዛሬ ሃምሳ ዓመት ገደማ መሰለኝ የያኔው ወጣት የዩኒቬርሲቲ ተማሪው ኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵያዊው ማን ነው?” በሚል ርዕስ አንድ ጽሁፍ አቅርቦ ለውጥ ፈላጊውን የዩኒቬርሲቲውን ማህበረሰብ ጥም ለማርካት የሞከረው። አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ተማሪ የፊውዳል ሥርዓቱ አገሪቷን ወደፊት እንዳትራመድ ጠፍንጎ የያዛት መሆኑን የተረዱና ሥርዓቱ ካልተለወጠ የሕዝቦቿ አብሮነት ውሎ አድሮ መሸረሸሩ አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማናበብ መላ ይመቱ ነበርና የዚህ ንቁ ተማሪ ግጥም ጊዜውን ጠብቆ የመጣ ነበር።
በዚሁ ጊዜ ነበር ከተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች አንዱ የነበረው ዋለልኝ መኮንን የብሄር ጥያቄን አስመልክቶ ታሪካዊውን ጽሁፍ ያቀረበው። አንዳንዶች ያኔም ሆነ ዛሬ እነዚህን ጽሁፎችን አስመልክቶ ሁለቱን ንቁ የተማሪው ማህበረሰብ አባላትን አገሪቷን ለመበታተን ሆን ብለው ያቀረቧቸው አስመስለው ሲያወሩ ይታያሉ። በመጀመርያ ደረጃ የጽሁፉ አቅራቢዎች ወጣት በመሆናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሸመነበትን ድርና ማግ በውል አልተረዱትም ተብለው ተተቹ። ገፋ ሲል ደግሞ የሆነ የውጭ አካል እጅ ቢኖርበት ነው እንጂ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ ከመሃላቸው አንደኛው ከሌላው የተሻለ ጥቅም ያገኘ ይመስል ከእኩዮች መካከል የትኛው ነው ኢትዮጵያዊው ብሎ መጠየቅ እብደት ነው ያሉም ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን ዛሬም ተመሳሳይ አስተሳሰብ የሚያስተናግዱ ወገኖቻችን መኖራቸው ነው።
ይህንን አጭር ጽሁፍ ላካፍላችሁ ያነሳሳኝ አንድ ባለፈው ወር አዲስ አበባ ውስጥ ያጋጠመኝ ጉዳይ ነው። ታሪኩ ባጭሩ እንደዚህ ነው። የአገውን ሕዝብ 80ኛ ዓመት የፈረስ ጉግስ በዓል ላይ ተካፍለን ከበዓሉ በኋላ ከአዲስ አበባ የሄድን እንግዶች በሙሉ ባንድ ላይ በአይሮፕላን ተሳፍረን ቦሌ የአገር ውስጥ በረራ መናኸርያ አረፍን። ገና ወደ አዳራሹ ስንገባ አንዲት እንስት የኢሚግሬሽን ሠራተኛ እንደ ጄት ተስፈንጥራ መጣችና ከኛ ጋር በበዓሉ የክብር እንግዳ ሆኖ የነበረውንና ከፊቴ ተሰልፎ የነበረውን አኟክ ጓደኛችን ኦኬሎን “ፓስፖርት ፓስፖርት” እያለች ታጣድፈው ጀመር። ኦኬሎም ለነገሩ አዲስ አለመሆኑን በቁርጠኝነት ለማሳወቅ ይመስለኛል በዚያ በቁመቱ ልክ ገፍትሮአት ሲያልፍ አንዳች የሆነ በሕይወቴም አድርጌ የማላውቀው ነገር ከውስጤ ግንፍል ብሎ ሲወጣ ልጅቷን አንገቷን ጭምድድ አድርጌ ይዤ “ኢትዮጵያዊ ማለት ባንቺ ቤት እንደ አንቺ ቀላ ያለ መልክ፣ ሰልካካ አፍንጫና ሉጫ ጸጉር ያለው ብቻ ነው?” “እነ ኦኬሎን የመሳሰሉ ምኒልክ ጋምቤላን ሲያስገብር በቦታው የነበሩና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እንዳሉ አታውቂም?” ብዬ ባልወለደ አንጀቴ ሳንቧረቅባት በቦታው ደርቃ ቀረች። ዛሬ አድገው ራሳቸውን ችለው በሚኖሩ ልጆቼ ላይ አንዲት ቀን እንኳ እጄን አሳርፌባቸው የማላውቅ ሰውዬ በቦሌ አይሮፕላን ጣቢያ በማላውቃት የኢሚግሬሽን ሠራተኛ እህታችን ላይ እጄን ማሳረፌ አሳፍሮኝ፣ መለስ ብዬ ረጋ ባለ መንፈስ ኦኬሎን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ማወቅ እንዳለባት አስረድቼ ወደ ሻንጣ መረከቢያ አመራሁ። (ስለሁኔታው የነበረውን ስሜት ሳላነጋግረውና ሳላስፈቅደው በእውነተኛ ስሙ ላለመጠቀም ብዬ ነው እንጂ፣ ኦኬሎ እውነተኛ ስሙ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ)።
ኦኬሎ ግን ዞር ብሎ ምን እንደተፈጠረ ለማየት አንዳችም ጥረት ሳያደርግ ቀጥ ብሎ ከግቢው ወጣ። ላለፉት አርባ አምስት ዓመታት የፈረንጅ አገር ኑሮዬ በጥቁረቴ ብቻ ተመሳሳይ ማንነትን ፈተና ውስጥ የሚከቱ ብዙ አጋጣሚዎችን ስላሳለፍኩ የኦኬሎን ውስጣዊ ስሜት ለመገመት አልከበደኝም። በቆዳ ቀለምና የፊት ገጽታ ብቻ ከሰው ሁሉ ለይተው የአንድን ግለሰብ ዜግነት ለማጣራት መሞከር ቆሽጥ ያሳርራል። ያበግናል። ከመቶ በላይ ከምንሆን ኢትዮጵያውያን ተሳፋሪዎች መካከል ኦኬሎ ብቻ በቆዳው ቀለምና ገጽታው ምክንያት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይቶ ፓስፖርት ሲጠየቅ እውነትም “ኢትዮጵያዊ ማነው?” የተባለው የኢብሳ ጉተማ ጽሁፍ ዛሬም ወቅታዊ መሆኑ ታየኝ። ግን ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? አንድ መቶ አምሳ ዓመት ሙሉ በአንዲት ኢትዮጵያ በምትባል አገር አብረን እየኖርን እንዴት ይቺ የኢሚግሬሽን ሠራተኛ ኦኬሎን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያንም አንዳሉ መረዳት አቃታት? በየሚዲያው እየወጣን “ለዘመናት ተጋብተን ተዋልደን የኖርን” እያልን ስንለፍፍ እንዴት ለዚህ ሁሉ ዓመታት ጨውና ውሃ ሳይሆን ዘይትና ውሃ ሆነን በአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ቻልን? የትኛውን የተፈጥሮ ሂደት ብናጣምም ነው ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላ ልክ ኦቦ ኢብሳ ከአምሳ ዓመት በፊት እንዳለው ዛሬም “ኢትዮጵያዊ ማነው?” ብለን ለመጠየቅ የተገደድነው?
እኔ ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በፈረንጅ አገር ያሳለፍኩት ከነጮች ተለይቼ ማንነቴን የማስረዳት ተደጋጋሚ ክስተቶች ትዝ ብለውኝ ልጅቷን ቆሌዋን ገፈፍኳት እንጂ ከኔ ኋላ ተሰልፈው የነበሩ ሰዎችማ ምን እንዳናደደኝ የገባቸውም አይመስለኝም። እንዲያውም በዚያች ጠባብ የኢሚግሬሽን መተላለፍያ ላይ ቆሜ መንገዱን ዘግቼባቸው “ለልጅቷ ትምህርት ስሠጥ” ምን የዞረበት ሩታሜ ነው ብለው በልባቸው እንደሚረግሙኝ ይሰማኝ ነበር። አዎ! ለዘመናት “የኢትዮጵያ ታሪክ” እያልን ስንማር የነበረው የኢትዮጵያን ግዛትና ዳር ድንበር እንጂ በዚያች ግዛት ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አልነበረምና ኩሩ ኢትዮጵያዊው ኦኬሎ በፈረንጅ አገር ሳይሆን ተወልዶ ባደገባት ባገሩ በወንዙ ፓስፖርት ሲጠየቅ አይቶ ዝም የሚል ኢትዮጵያዊ ራሱ ኢትዮጵያዊው ማን እንደሆን በውል የሚያውቅ አይመስለኝም።
ልጅቷን በግልፍተኝነት አጎሳቆልኳት እንጂ ጥፋቱ ከሷ ሳይሆን ከሥርዓቱ መሆኑ ተረስቶኝ አይደለም። በፊውዳሉ ሥርዓት ዘመን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የኢትዮጵያውያን ምልክት ሆኖ ይቀርብ የነበረው ኢትዮጵያዊ ማንነት ከሞላ ጎደል የአማራ የኦሮሞና የትግራይ ሕዝብን ቋንቋ ባሕል አለባብስና አመጋገብ እንጂ የአኟኩንና የኑኤርን፣ የጉሙዝና ቤኒሻንጉልን፣ የወላይታና የዶርዜን፣ የሙርሲና የኮንሶን በአጠቃላይም የኒሎቲክና ኦሞቲክ ኢትዮጵያያንን ሕዝብ ያጠቃለለ አልነበረምና የወንድማችን ኦኬሎ ወላጆችና ዘመዶች ያኔ “ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች” እንጂ ኢትዮጵያውያን ተብለው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በመባል ከሚታወቁት ደገኞች (highlanders) እኩል እውቅና እንዳልነበራቸው ጠንቅቄ አውቅ ነበር። በኛው ዕድሜ እንዳየነው፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኒሎቲክና ኦሞቲክ ሕዝቦች በሕግ ፊት እንኳ እንደ አንድ ሙሉ ሰው ስለማይቆጠሩና ሥርዓቱ የኢትዮጵያን ልጆች በእኩልነት የማያስተናግድ በመሆኑ ነበር የማህበረሰባችንን ኢፍትሃዊ አሠራርን በመቃወም ያ ብሩህ ራዕይ የነበረው ዋለልኝ መኮንን በጊዜው “የብሄር ጥያቄ” የሚለውን ማኒፌስቶውን በአደባባይ ያቀረበው!
እኔን የሚያሳስበኝ ግን፣ እነዋለልኝና ኦቦ ኢብሳ ይህንን የኢትዮጵያዊነትን ጥያቄ ለሕዝብ ካቀረቡ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ዛሬም ልክ እንደ ያኔው ኦኬሎና ኦጁሉ በገዛ አገራቸው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ተለይተው ፓስፖርት መጠየቃቸው ነው። ሌላው እንኳ ቢቀር የፊውዳሉ ሥርዓት ከተገረሰሰ ከአምሳ ዓመት በኋላና አሃዳዊው ሥርዓት ጠፍቶ የኢትዮጵያን ሕዝቦች እኩልነት ያረጋገጠ ፌዴራላዊ ሥርዓት ከተመሠረተ ከሰላሳ ዓመት በኋላና “ብዝሃነታችን ውበታችን” እያልን በምንልፍፍበት አገር ቢያንስ ቢያንስ የኢሚግሬሽን ባላሥልጣኖቻችን እንዴት የእናት ኢትዮጵያ ሆድ ዥንጉርጉር መሆኑን ሳይረዱ ቀሩ? ኢትዮጵያም የዘጠኝ እኩል መብት ያላቸው የፌዴራል አባላት አገር ናት እየተባለ እንዴት ኦኬሎና ኦጅሉ ከባይሳና ጎዮቶም እኩል ኢትዮጵያዊ ሊሆኑ አልቻሉም? የኢሚግሬሽን እህታችን ዓይነቶች “ኢትዮጵያውያንም” በዘጠኙ ክልላት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተለያየ መልክ እንዳላቸው እንዴት እስከዛሬ አልተረዱትም? ጋምቤላ የተባለ ክልል መኖሩ እየታወቀ ጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምን ዓይነት መልክ እንዳላቸው እንዴት ሳይገባን ቀረ? ለማወቅ ዕድል ከማጣት ነው ወይስ ለማወቅ ፍላጎት ከማነስ?
ሁኔታው እጅግ በጣም ያሳስባል። ብዙዎቻችን የጋምቤላ፣ የጉሙዝና ቤኒሻንጉል እንዲሁም “የደቡብ ሕዝቦች” በመባል የሚታወቁ ክልሎች የዘጠኙ የፌዴራል አባላት መሆናቸውን እንጂ በነዚህ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ወገኖቻችን ምን እንደሚመስሉ ለማወቅ ፍላጎቱ ያለን አይመስለኝም። አያድርስና ጠላት በምዕራብ በኩል ያገራችን አካል የሆነውን ጋምቤላን ቢያጠቃ ግን “አያቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ያቆዩአት ምድራችንን አንዲት ስንዝር እንኳ አናሳነካም” ብለን እንዘምት ይሆናል። በጋምቤላ መሬት ላይ ከሚኖሩት ወገኖቻችን ይልቅ መሬቱ በራሱ የበለጠ ክብር ያለው ይመስለናልና! አያቶቻችንም ደማቸውን ያፈሰሱትና አጥንታቸውን የከሰከሱት በጋምቤላ ምድር ላይ ለሚኖሩት አኟኮችና ኑኤሮች ሳይሆን የጋምቤላን ምድር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ለማካለል ነበርና! የሚገርመው ዛሬ ከተለያየ አቅጣጫ እየታየ ያለውን የማንነት ጥያቄ “ዘረኝነት” “ጎሰኝነት” እያልን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስናወግዘው፣ እውነተኛውን በቆዳ ቀለም ላይ ብቻ ተመሥርቶ ያገራችንን ሕዝብ ለዘመናት የከፋፈለንን ይህንን የዘር መድልዖ እንኳን መፍትሄን ልንፈልግለት ይቅርና፣ የችግሩን መኖር እንኳ ለማወቅ ጥረት የምናደርግ አይመስለኝም።
ኦኬሎ ከማንኛችንም በላይ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና ለሰው ልጅ መብት መከበር በመላው ዓለም የአሜሪካን ኮንግሬስን ጨምሮ እየዞረ አጥብቆ የሚሟገት ኩሩ ኢትዮጵያዊ ሆኖ እያለ የኢሚግሬሽን ባላሥልጣኖቻችን ግን በአገሪቷ ውስጥ በሰላም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እኩል እንዳይዘዋወር መብት ሲነፍጉት ማየቱ እጅግ በጣም ያማል። ግን ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ? አውቃለሁ አንዳንዶቻችሁ፣ “ዝም ብለህ ታካብዳለህ እንደምትሉኝ”። ስዊድናውያን ነጭ ጓደኞቼም በየጊዜው በቆዳዬ ቀለም ብቻ ከሌሎች ስዊድናዊያን ለይተው ፖሊሶች እንደሚያንገላቱኝ ስነግራቸው “ሊሆን አይችልም፣ ዝም ብለህ ታጋንናለህ” እንደሚሉኝ ነውና አልፈርድባችሁም። የሚያመው የተቆረጠው ቦታ ብቻ ነው ይላል ኦሮሞ ሲተርት። ኦኬሎን እንደዚያ ሲያመናጭቁት ሳይ በኔ ላይ ይደርስ የነበረውን እያመላከትኩ ነበርና ሌሎቻችሁ ተመሳሳይ መድልዖ ያልደረሰባችሁ ለኔ የሚሠማኝ ስሜት ባይሰማችሁ አይከፋኝም ለማለት ያህል ነው።
በኔ ግምት ይህን ዛሬ በኦኬሎና በሌሎች የኦሞቲክ እና ኒሎቲክ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን የመድልዖ ባሕል ለማስወገድ ከባድ አይመስለኝም። ይህ ሁሉ አሳፋሪ አቀራረብ በሕዝባችንና በተለይም በመንግሥት በኩል ቅንነትና ፍላጎቱ ቢኖር ኖሮ በቀላሉ ሊቀረፍ ይቻል ነበር ባይ ነኝ። በየኤርፖርቱ ባሉ የኢሚግሬሽን ቢሮዎች፣ በጉምሩክ መሥርያ ቤት፣ በአየር መንገዱ ቲኬት መሸጫ ቢሮዎች፣ የአየር መንገዳችን የበረራ አስተናጋጆች፣ በባንክና በኢንሹራንስ መሥርያ ቤቶች፣ በትላልቅ ሆቴሎች እንዲሁም ትላልቅ የንግድ ተቋማት የኒሎቲክና ኦሚቲክ ወገኖቻችንን ቀጥረው “በፊተኛው ጠረጴዛ” (Front Desk) ላይ ቢያሰማሯቸው ኖሮ፣ ይህ ዓለም በሙሉ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያለውን የተሳሳተ እይታ ለማስተካከል ይቻል ነበር ባይ ነኝ። በፖስት ካርድ ላይ ብቻ ቱሪስቶችን ለመሳብ ከማሰብ የነዚህን የዘረኝነት ሰለባ የሆኑትን ወገኖቻችንን ፎቶ ከመለጠፍ ባሻገር፣ እነሱኑ ለዘመናዊ ትምሕርት አብቅቶ አስተምሮና አስመርቆ በመሃል አገር ካሉ ከሌሎች “ደገኞች” ኢትዮጵያውያን እኩል ማሰለፍ ይቻል ነበር። ይህንን ለሰዎች ለማስረዳት ስሞክር “እነሱ እኮ ስላልተማሩ ነው እንጂ በመንግሥት ተቋማት የስልጣን ወንበር ያልተሰጣቸው ሆን ተብለው የተረሱ አይደሉም” የሚል መልስ አገኛለሁ። የኔ መልስ ግን፣ አማራው ኦሮሞና ትግሬው፣ እንዲሁም ሃዲያና ከምባታው፣ ሲዳማና አገው የመማር ዕድል ሲያገኙ የነዚህ የኒሎቲክና ኦሞቲክ ወገኖቻችን አለመማር ራሱ የጭቆና ምልክት ነው ባይ ነኝ።
ወገኖቼ! እስቲ ላንዳፍታ ቆም ብለን ራሳችንን በኦኬሎ ቦታ አድርገን እናስብ። የኢትዮጵያን ግዛትን ዳር ድንበር እንዳትነካብን የምንቆረቆርላትን ያህል በዚያች ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ወገኖቻችንም በማንኛውም መስፈርት ከሌላው ደገኛ ኢትዮጵያዊ እኩል እንዲታዩ ካልተሟገትንና እኩልነታችን በተግባር እንዲተረጎም ካላደረግን ፍቅራችን ለኢትዮጵያ እንጂ ለኢትዮጵያውያን ያልሆነ የውሸት ፍቅር ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያን ግን ኢትዮጵያ የሚያሰኛት ግዑዙ መሬት ሳይሆን በውስጧ የሚኖሩ ሕያው ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው። ኢትዮጵያዊ መባል ደግሞ በሕግ ብቻ በተደነገገው እይታ ሳይሆን በተግባር ሁሉም እኩል ኢትዮጵያዊ ሲሆን ብቻ ነው። አለበለዚያ ዛሬ በቦሌ አየር ማረፊያ ያገር ውስጥ በረራ መዳረሻ ውስጥ እንደ ውጭ ዜጋ ተቆጥሮ ፓስፖርት የሚጠየቀው ኦኬሎ ነገም ልጆቹ ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይገጥማቸው ከላይ የጠቀስኳቸው አንዳንድ እርምጃዎች ካልተወሰዱ፣ ዛሬ ኦኬሎ ስለ ቁንጅናዋ በየዓለም ዳርቻው የሚሰብካትን ታላቋን ኢትዮጵያን ነገ ደግሞ “ይቺ ለአያቴም ላባቴም ያልሆነች ኢትዮጵያ ለኔም አትበጅም” ብሎ የሚነሳ ትውልድ ሊፈጠር ይችላልና በጥብቅ እናስብበት!
አውቃለሁ አንዳንድ አንባቢዎች ያው የተለመደውን የተሳሳተ ትርክት ይዘው “እኛ እኮ ለዘመናት አብረን ተከባብረን የኖርን ነን፣ ዛሬ ጽንፈኞች ገብተው አተራመሱን እንጂ ወዘተ” ብለው ይህንን የኔን መቆርቆር ለማጥላላት እንደሚሞክሩ። አንድ ትልቁ ያገራችን ሕዝቦች በተለይም የኤሊቱ በሽታ፣ አንድ ሕዝብ ወይም ቡድን በሆነ ምክንያት እኩልነት አልተሰማኝም ብሎ ስሞታ ለማቅረብ ገና ሲንደረደር፣ “ለዘመናት ተጋብተን ተዋልደን ተከባብረን የኖርን” በሚል ባዶ አባባል አደባብሶ ለማለፍ መሞከር መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል አለማወቃቸው ነው። የተጋባውና የተዋለደው ባብዛኛው የአማራ የኦሮሞና የትግሬ ሕዝብ ብቻ ነው። ኒሎቲኩና ኩሺቲክ ሕዝቦቻችን ግን ከአማራው ከኦሮሞውና ከትግሬው ጋር ሲጋቡና ሲዋለዱ አልነበረም፣ ዛሬም አይጋቡም አይዋለዱም። እንደ ውሃና ዘይት ግን ሳይዋሃዱ አብረው ጎን ለጎን ግን እየኖሩ ነው። እውነቱ ይኸው ነው። መጋባቱና ወዋለዱ ይቅርና አብሮ በመንግሥት ተቋማት በእኩልነት የመሥራት ዕድሉን እንኳ አላገኙም።
ከስንት ሚሊዮን የኒሎቲክና የኩሺቲክ ሕዝቦች መካከል ኢሚግሬሽን ኦፊሴር ወይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የሚሆን ሰው የጠፋ ይመስል ኢትዮጵያ ማለት በአየር መንገዱና በተለያዩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የምናያቸው የሓበሻ ልብስ የለበሱ ቆነጃጅቶችን ብቻ አድርጎ በማቅረብ የዓለምን ሕዝብ ማሳሳቱን እናቁም። ኢትዮጵያ ሌላ ገጽታ ያላቸውም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆችም አሏትና! እነዚህን ልጆቿንም “ከደገኞቹ” እኩል ወደ መድረክ እናምጣቸውና እውነተኛውን የኢትዮጵያዊነትን ቡራቡሬ ገጽታ መጀመርያ ለራሳችን ከዚያ ደግሞ ለመላው የዓለም ሕዝብ እናሳውቅ! ይህ ደግሞ ተግባራዊ እንዲሆን የአንበሳውን ድርሻ ሚና መጫወት ያለበት መንግሥት ቢሆንም፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በፈረቃ አገሪቷን ሲገዙ የነበሩና ዛሬም የችግሩ አካል የሆኑት ሶሶቱ ትላልቅ የኩሽ ሕዝቦችም የዚያኑ ያህል ኃላፊነት አለባቸው። በቆዳ ቀለም ላይ የተመሠረተ መድልዖ በሌሎችም ብዙ አገሮችም ሲከሰት የነበረ ስለሆነ፣ እነዚህ አገራት ለችግሩ እንዴት መፍትሄ እንዳገኙ ተሞክሮአቸውን በመዋስ ይህንን ለዘላለም የተጣበቀብንን እውነተኛውን የዘረኝነት ነቀርሳ ለዘላለሙ እንገላገለው።
ሁሉንም ልጆቿን፣ ባይሳና ኦኬሎን አደፍርስና ክብሮምን ኤርሳሞና ዴሌቦን በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በቅንነት የምናስብ ከሆነ ከሁሉ አስቀድመን የችግሮቻችንን ቅደም ተከተል በውል እንወቅና ቅድሚያ ሊሠጠው ለሚገባ አገራዊ ጉዳይ አስፈላጊውን ቅድሚያ እንስጥ። በእኩልነት የማይተያዩትን የኢትዮጵያን ልጆች ይዞ አንዲት ኢትዮጵያን እንገነባለን ብሎ መለፈፍ ራስን ማታለል ነው። ትርፉም ድካም ብቻ ይሆናል። ባይሳ ሰተት ብሎ ሲገባ ኦጁሉም ፓስፖርት ሳይጠየቅ የሚገባባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት በቅንነት እንነሳ።
በቸር ይግጠመን።
ጄኔቫ፣ 23 ፌብሯሪ 2020 ዓ/ም
ባይሳ ዋቅ-ወያ – email: wakwoya2016@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply