የሀገሪቱ ም/ፕሬዝዳንትና ጠ/ሚኒስትርን ጨምሮ 10 ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሰረቀውን ቆርቆሮ ወስደዋል ተብሏል።
የኡጋንዳ የክልሎች ሚኒስትር ጎሬቲ ኪቱቱ ከቤት ክዳን ቆርቆሮ ዝርፊያ ቅሌት ጋር በተያያዘ ፋሲካን በእስር ቤት ያሳልፋሉ።
ሚኒስትሯ ለእስር የተዳረጉት በሀገሪቱ የተፈፀመው የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ዝርፊያ ላይ ተሳትፈዋል በሚል እንደሆነ ቢቢሲ አስነብቧል።
የክልሎች ሚኒስትር ጎሬቲ ኪቱቱ በኡጋንዳ ሰሜን ምስራቅ ክልል ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የተዘጋጀውን 14 ሺህ የቤት ክዳን ቆርቆሮ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ነው የተጠረጠሩት።
ሚኒስትሯ ባሳለፍነው አርብ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ እስካሁን የጥፋተኝነት ውሳኔ ባሳያልፍባቸውም የዋስትና መብት ግን ከልክሏቸዋል።
10 የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሰረቀውን የቤት ክዳን ቆርቆሮ እንደተቀበሉትም ዘገባው አክሏል።
ቆርቆሮውን ከተቀበሉት ሰዎች መካከልም የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የፓርላማ አፈ ጉባዔ እንዲሁም ሌሎች ሚኒስትሮች ይገኙበታል ነው የተባለው።
የኡጋንዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ በመጠየቅ ሌሎችም ባለስልጣናት ቆርቆሮዎቹን እንዲመልሱ ጥሪ ማቅረባቸውም ተነግሯል።
የሀገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባዔ አኒታ የተቀበሉትን የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች መመለሳቸውን ለምክር ቤቱ ተናግረዋል ነው የተባለው።
አንድ ስማቸው ያልተገለፀ ሚኒስትርም ለፍየሎቻቸው መጠለያ አልብሰውት የበረውን የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ማንሳታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል። (AlAin)
ሌብነት እንደ ሰደድ እሣት በተስፋፋባት አገራችንም ተመሳሳይ እርምጃ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ካልተወሰደ ሌብነት መብት እየሆነ ይሄዳል። ሕዝብ ከወሬ ባለፈ በሌብነት የሚያውቃቸውን ባለሥልጣናት በሹመትና ዝውውር ከማገላበጥ ፍትሕን መበየን በርካታ ጥቅሞች አሉት። ከዚህ ውጭ ሻርኮቹ በአይነኬነት እንደፈለጉ አገር እንዲዘርፉ ፈቅዶ ጥቃቅን ጉቦኞችን እዚህና እዚያ እያሰሩ ሌብነትን እዋጋለሁ ማለት ዐባይን በጭልፋ ነው። ለመንግሥታዊ መዋቅሩም ትልቅ ሥጋት ሆነው በመቀጠል ለአገር መፍረስ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ይሆናል።
ጎልጉል የድረገጽ
Leave a Reply