የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና አለአግባብ ለመበልጸግ ያሰቡ አውሮጳውያን በአሜሪካ አካባቢ ያሉትን አገሮች በጥጥና በሸንኮራ አገዳ እያለሙ መጠነሰፊ ሃብት ለማጋበስ በሰላም የሚኖሩ አፍሪካውያንን በግፍ እያጋዙ ዓለማችን እስካሁን ዓይታ የማታውቀውን ዓይነት የባርነት ሥርዓት ለበርካታ ዓመታት አካሂደዋል፡፡ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ በግፍ የተጋዙት ወገኖች በመንገዳቸው ያሳለፉት መከራና ከዚያም ለማሽን እንኳን የሚሰጠው ዕረፍትና ጥገና እነርሱ ተነፍገው ለመቶዎች ዓመታት ከምንም ጋር የማይወዳደርና የማይነጻጸር ሰቆቃ አሳልፈዋል፡፡ የዚህ መራራ ግፍ ውጤት አሁንም አብዛኛውን የዓለማችንን ክፍል እየናጠው ነው፡፡
በዚህ አስከፊ ዘመን በባርነት ሥር የሚማቅቁት እንደ ንብረት ይቆጠሩ ስለነበር በምርጫ አይሳተፉም ነበር፡፡ ሆኖም ካላቸው ከፍተኛ የህዝብ ብዛት አኳያ ባሪዎችን አስቆጥረው በርካታ የምክርቤት ወንበር ለማግኘት የተመኙት የደቡብ ፖለቲከኞች አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው አንድ ባሪያ እንደ 3/5 ሰው ይቆጠር የሚል ድርድር ላይ ደርሰው ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር ከአምስት ባሪያ ሁለቱ ለቁጥር አይገቡም፤ መኖራቸው አይታወቅም፤ ምንም ናቸው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰቆቃ የበዛባቸው ግፉዓን በየጊዜው የሚችሉትን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ እጅግ በርካታ የሕይወት መስዋዕትነት ተከፍሎ ነጻነት ይፋ ቢሆንም በአሜሪካ የሚገኙ ጥቁሮች ግን አሁንም ስልታዊ የዘር ጥቃት ሰለባዎች ናቸው፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ለነጻነት እጅግ ውድ የሆነውን ህይወታቸውን የከፈሉ ያልተዘመረላቸው በርካታ ጥቁሮች እያሉ አሁንም የባሪያ ሥርዓት ከማስወገድ ጋር የችግሩ ጠንሳሾች የሆኑት ነጮች የመፍትሄው ፈር ቀዳጆችና ፋና ወጊዎች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ ማልኮም ኤክስ እንደ ወንበዴና ወሮበላ ተደርጎ ታሪኩ ሲጎድፍ ወረቀት ላይ ፊርማቸውን ማስፈራቸው እንደ ታላቅ ውለታ ተቆጥሮ ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ ጆንሰን የባርነት አስወጋጅ “መሲህ” ተደርገው ይወደሳሉ – ያለ እኛ አይሆንላችሁም የማለት ያህል ነው – ከማንዴላ ጋር ዴክላርክ እንደሚጠቀሱት፡፡ ችግር ፈጣሪውም መፍትሄ አምጪውም – ተወቃሽም ተሞጋሽም – ነጮች ናቸው፡፡
ይህንን ጉዳይ ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም፡-
ከጌቶቻቸው በጥንቃቄ የተማሩት ህወሃቶችም እንደ ዓቅማቸው ደፋ ቀና ሲሉ፤ ሲውተረተሩ 25ዓመታት ቆይተዋል፡፡ ሲሻቸው እንደ ነጻ አውጪ፤ ሲሻቸው ደግሞ እንደ ቅኝ ገዢ እንደ አቅሚቲ ሁሉንም ለመሆን ወጉ አይቅርብኝ ሲሉ መታዘብ የሚችል ሁሉ ላለፉት ዓመታት ሲያስተውላቸው ሰንብቷል፡፡ ከበረሃ ወጥተው ስለ ልምላሜ፤ በትግል ስም ወደር የሌለው ግፍ ሲሰሩ ቆይተው ስለ ህግ የበላይነት፤ ፊደል በቅጡ ሳይቆጥሩ በድንቁርና ተሸብበው ስለ ዕድገትና ብልጽግና ስሌት፤ ቤተሰባቸውን እንኳን በቅጡ የመምራት ብቃት ያላሳዩ ምግባረ ብልሹዎች ስለ አገር አስተዳደር፤ ለረሃብተኛ የተላከ እህል ሸጠው በሰው ህይወት ላይ የቀለዱ አጭበርባሪዎች ስለ ግልጽነትና ተጠያቂነት፤ አገር ለመገነጣጠል በነጻ አውጪ ስም ሲነግዱ የኖሩ የበረሃ ወሮበሎች ስለ ሉዓላዊነት፣ ስለ ፌዴራላዊ አወቃቀር ከበሮ ሲደልቁ፤ … አይተናል! ሰምተናል! ታዝበናል! ህወሃቶች ሁሉንም እስኪበቃን አሳይተውናል፡፡
በማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ /ማገብት/ አዋላጅነት በሻዕቢያ የተደቀለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር /ህወሃት/ በነጻ አውጪ ስም አገር መግዛት በጀመረበት ጊዜ ለእርሱ የበረሃ ራዕይ የሚለውን፤ ለኢትዮጵያ ግን ትውልድ የሚጨርስ ነቀርሳ የሆነውን ችግር ተከለ፡፡ ራሱን መሪ አድርጎ በሾመው መለስ ለማኝነት በዓለም እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተባበሩት መንግሥታት ፊት ቀርቦ አገር እንድትገነጠል በይፋ ለመነ፤ ሰዎችን እንደ እህል በዘር ጆኒያ ሰፈረ፤ በሰላም አብሮ የኖረን ሕዝብ እርስበርሱ አጋጨ፣ ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸው አፈናቀለ፤ መሬት ነጠቀ፤ ዜጎችን አዋረደ፣ አሰረ፣ ገረፈ፣ አሰቃየ፣ ገደለ፣ ጨፈጨፈ፣ … በመላው ኢትዮጵያ የማይጠፋ እሳት ለኮሰ፤ አሁን እሳቱ ራሱን የሚበላበት ሰዓት ላይ ደረሰ! አሁን መግቢያ መውጫው ሲጠፋ እስካሁን ማንም ሰው ምንም ዓይነት ሃሳብ ሳያቀርብ የኖረ ይመስል በጻድቃን ህወሃቶች “የዕርቅና ተሃድሶ” ምልጃ መቅረቡ አስገርሞናል፡፡ ግን አንሰማም አንልም፡፡
በኢትዮጵያ የተከበሩ የሚባሉትን እንደ ሽምግልና ያሉትን ተቋማት ያለልክ ያዋረደው ህወሃት 25ዓመታት በየቦታው የለኮሰው እሳት ራሱን ሊበላው በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ “ዕርቅ፤ ሰላም፤ ፍቅር፤…” እያለ መሆኑ ከውስጥም ከውጭም እየተሰማ ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል ሰሞኑን የተለቀቀው የጻድቃን ገ/ትንሳኤ “የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች!” በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ጽሁፉ በቀድሞ የህወሃት መሃንዲስ የተጻፈ ከመሆኑ ሌላ በይዘት ይህ ነው የሚባል አዲስ ነገር መጠቆሙ አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም ስለ ሕገመንግስት የሚያወራው ክፍልና ከዚያ ጋር በተዛማጅ የቀረቡት ሃሳቦች ነገደ ጎበዜ የዛሬ 12ዓመት አካባቢ ባሳተሙት መጽሃፍ ላይ የጠቆሙትን ዋቢ ሳይጠቅስ የተጻፈ ነው ተብሎለታል፡፡
“የመፍትሔ ሃሳብ” ጠቋሚ ነው ባሉት ጽሁፍ ላይ ጻድቃን በርካታ ነገሮችን ለማስፈር ሞክረዋል፡፡ በአንድ ወገን ህወሃት በበረሃ ያደረገችውን ትግል እያሞገሱ በሌላ ደግሞ “የኢትዮጵያን ችግር በኢህአዴግ መዋቅሮች ታጥረን መፍታት አንችልም” በማለት እርስበርሱ የሚጣረስ ሃሳብ በማቅረብ ህወሃትን ትተው ኢህአዴግን እንደ አንድ ችግር ፈጣሪ ተቋም አድርገው አቅርበውታል፡፡ በአገሪቷ ላይ አለቅጥ የተንሰራፋው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ጉድለት፣ የአንድ ፓርቲ አምባገነንነት፣ … በመለስ አነጋገር “የመበስበስ” ውጤቶች መሆናቸውን ሆን ብለው የዘነጉት ይመስል አሁን ለሚታው ችግር ምንጭ አድርገው አትተዋል፡፡ ከዚህ ሌላ ህገመንግሥቱን “እናምልከው” የማለት ያህል ደጋግመው አወድሰውታል፡፡
ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ስማቸው “ጻድቃን” ባይሆን ኖሮ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎች በጽሁፋቸው ላይ ባሰፈሯቸው ሃሳቦች ይኼኔ ማዕከላዊ ገብተው www.freetsadkan.com የሚል እርሳቸውን የማስፈታት ዘመቻ ተጀምሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም ህወሃት አገዛዝ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ህገመንግሥታዊ መብታችን ይከበር፤ እንዲያውም ሌላ ጥያቄ የለንም ህወሃት/ኢህአዴግ ህገመንግሥቱን ብቻ ያክብርልን በማለት የጻፉ፣ የተናገሩ፣ ህዝብ ያደራጁ፣ የታገሉ፣ … እጅግ በርካታ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች ተሰውተዋል፤ ተረሽነዋል፤ ለስቃይ ተዳርገዋል፤ ከዚህ የተረፉት አብዛኛዎቹ ደግሞ “አሸባሪ” ተብለው እስር ቤት እየማቀቁ ነው፡፡ “ድምጻችን ይሰማ” በማለት ዘመቻ የጀመሩት ሙስሊሞች ቀዳሚ ጥያቄ ህገመንግሥቱ ይከበር እንደነበር እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡ ጻድቃን በተመሳሳይ ሲሉት ግን ከሽብር ወደ “ጽድቅ” ይቀየራል፤ ርኩሰቱ ይቀደሳል፡፡
የህወሃት “ጄኔራልነትን” ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንቱንም ጠቅልለው የያዙት ባለሃብቱ ጻድቃን ስለ ትግራ ተወላጆች በርካታ ሃሳቦችን አንስተዋል፡፡ እነ ሰየ አብርሃን ወደ ወኅኒ የወረወረው ህንፍሽፍሽ የኋላ ሰለባ የሆኑት ጻድቃን በዚህ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያተኮረው ንግግራቸው ስየ አብርሃ ከእስር በተለቀቁ ቀናት ውስጥ “በትግራይ ህዝብ ላይ ተስፋ አትቁረጡ” በማለት ቪኦኤ ላይ ያደረጉትን ተማጽንዖ የሚያስታውስ ሆኗል፡፡
በጽሁፉ ላይ ሌሎችን በርካታ ነጥቦችን እያነሱ ዝርዝር ትንታኔ መስጠት ይቻላል፡፡ ላሁኑ በዚሁ እናብቃና ሃሳባችንን እናቅርብ፡- የጻድቃን “የመፍትሄ ሃሳቦች” ጽሁፍ (የቃላት ግደፈቶቹን ሳናንሳ) ከዚህ በፊት በተደጋሚ በቅንነት ከቀረቡት ጋር ሊወዳደር የሚችል ባይሆንም እንደዓቅሚቲ የተሰነዘረና አዎንታዊ ሃሳብ ያነገበ በመሆኑ ሊጤን ይገባዋል እንላለን፡፡ ሁሉንም ነገር በጭፍን ከመቃወም ይልቅ ተቃዋሚ ኃይላት በጽሁፉ ላይ በመመርኮዝ ህወሃትን የመገዳደሪያ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይገባቸዋል ለማለት እንወዳለን፡፡
የጻድቃን ትንታኔ እና የመፍትሄ ሃሳብ በህንፍሽፍሹ ወቅት ክትባት ተሰጥቷቸው የደነዘዙትን፤ የተወገዱትን፤ የላሉትንና የመከኑት የቀድሞ ህወሃቶች በዕድሳትና በስልት ወደ መንበሩ ለመመለስ ይሁን ወይም ተምሬበታለሁ ከሚሉት በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ በኩል ከህወሃት አንጋሾች የተላከላቸው ይሁን በውል የታወቀ ነገር ባይኖርም መፍትሔዎቹን በቅንነትና በእውነተኛ መንፈስ ያቀረቧቸው ከሆኑ እንደ አንድ ቆራጥ ጄኔራል የመሪነቱን ቦታ በመጨበጥ ወደ ፍልሚያው በፊት አውራሪነት እንዲዘምቱ ሃሳብ እናቀርባለን፡፡ ይህ ሲሆን አመራሩን የሚደግፉ የሚበዙበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ፤ የእውነተኛ ለውጥ ተስፋ ይፈነጥቃሉ፡፡ ከዚህ ካለፈ ግን “ወታደር ሲጠግብ የፖለቲካ ተንታኝ ይሆናል” ከማስባል በላይ አይሆንምና ውጤቱ ክሽፈት ይሆናል እንላለን፡፡
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው፡፡
koster says
The fascists cheated Ethiopians for the last 23 years and now it is over either one has to accept slavery or dismantle these home grown fascists by all means possible. First and foremost they have to learn that they are not all bullet-proof and that there are Ethiopian heroes other than these “chinigafi”/aborted home grown fascists.
tesfai habte says
የኤርትራ ኦፊሻል ቋንቋ ትግርኛ እና ዓርብ ነው። ሻዕብያ መለት ብዓረብኛ ”ህዝባዊ” ወይም ”ህዝብ” መለት ነው። ሻዕብያ እንደሰድብ የምያዩት ኢትዮጵያውያን ወገኖች እስከ አሁን ኣልጠፉም። ምክንያቱ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርት ሁሉግዜ አመሪካን እና ምዕራባውያን አገሮች ዓረቦጭ ይጠላሉ በማለት ዶላርን ለማግኘት ለኤርትራ ተጋድሎ ዓረበኛ በማመሰል”ሻዕብያ” እያሉ ይጠራሉ። ጥሩ ነው። ህዝበዊ ግንባር ከ”ሻዕብያ” ህዝባዊ ኣብራክ የወጣ ወጣት የማይበገር ተጋይ ነው። ”ሻዕብያ” ህዝባዊ ”ህዝብ”። ለማይረዳው ስድብ፡ ለሚረዳው ጥሩ ስም!!!—–”ሻዕብያ” ህዝባዊ!!!—ሻዕብያ ለኢትዮጵያ አንድነት የማይቀየር ኣቋም የነበረው ድርጅት ነበር። አሁኑም!—-ኣመሪካን በኢትዮጵያ ገዢዎች ላይ በሚያደርገው የቀይ ባህርና አፍሪቃን የመግዛት ስልት ቅድመ ግንባር የሚያዩት የኢትዮጵያ ገዢዎች እና ባለስልጣንትም ነው። ለነዚህ ውሁዳን ቤተሰቦች፡ በዶላር ከያዝክ ሁሉምን ነገር መደርግ ትችላለህ በሚል ፈሊጥ፡ በአከባብያችን የከፋፍለህ ግዛ እና የመተራመስ፡ መግደል፡ ጦርነትን የማወጅ ድርጊትን ያካይዳሉ። ኢትዮጵያን ኮርያን፡ ኮንጎን፡ ሶማል፡ ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉት የውክልናን ውግያን እያሳተፉ ነው። ለመሪዎች ዶላር፡ እንደ ዛሪ ወያኔም ጎሰኛ፡ በምትሃተ-ነፍስ የተጠቃ መድሃኒት የሌለው ህመምተኛ፡ ንኡሳን ቤተሰብ በትግራይን ካፒታልስት (ኢፈርት) ይፈጥራሉ ነው። ”ሻዕብያ” የኤርትራ ህዝብ ግን ጭቁን ህዝብ ከባርነት ለመውጣት ወያኔ፡ ኦሮሞ፦– ሌሎች የኢትዮጵያን ድርችቶች የሞራል፡ ትጥቅ፡ ድጋፍን ይሰጥ ነበር። ኢሃዴግ ከተለያዩ ውግያዎች ብሻዕብያን የተማረኩ እና ሌሎች ድርጅቶችን እያደራጀ ለኢትዮጵያን አንድነት ድጋፍ ይሰጣችው ከነበሩ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ ነበር። ሁሉም ከጠባብ ብሄርተኝነት ኣግልሎ አንድን ኢትዮጵያን የሚያስብ ራእይን ያለው መንግስት እንዲመሰረት ፍላጎት ነበረው። አፍሪቃን በራሱ ለራሱ፡ ነጽነት ያለው መንግስት፡ ሃብት ተጠቅሞ፡ ዕድገት ብልጽግና ለመምጣት ተጋድሎ የፈጸመ ነበር።፡ ሻዕብያ የመኘው ኣልሆኖም። ነቀርሳን ካልተፈወሰ፡ ጤንነት የለም። እንደ ድሮው ወያኔ ስልጣን ተቆጣጥሮ፡ ከምእራቡ ሃገራት የሰይጣንን ኣክሊል ሰቅሎ፡ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠርኩ፡ ሃብትን ለመዝመት፡ ኤርትራ መውረር፡ ባድመ መቆጣጠር፡ የራሴ ህልም ይፈጥራለሁ አለ። ቅዠት የሆነ ህልም! የኢትዮጵያ ሃብት ተቆጣጥሮ፡ ያለውን የሌለውን ሃብት ዘምቶ ወደ ትግራይ ከኣጓጓዘ ብሃላ፡፡ ሰራዊቱን እና ሰኩሪቱን በኢጁ ስላለ፡ መሬትን ከአማራ፡ ወሎ፡ አፋር ቆርሶ ትግራይን ግዙፍ ሃገርን ለመገንባት ወሰነ። ይህ የሻዕብያና ሃጥያት ኣይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብም ሃጥያትም ኣይደለም። ይህ ወያኔ ቢላውን በእጁን አንገቱን እንደማረድ ይቆጠራል። ሁሉም ነገር ግዜው አለው። ክፉም ደጉም ከተጀመረ፡ ፍጻሜ አለው። በትግሉ ስቃይ፡ መከራ፡ ሞት፡ መውደም ስደት፡ መስዋእትነት፡ ያለ ነው። ሃላ ግን የሁሉም መድምደምያ ኣለው። የኤርትራ ህዝብ የተረሳ፡ የሞተ እየተባለ ስቀለድለትና ስለቀስለት እንደነበረ፡ ድልን ተቀናጀ። የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነቱ ከተጠናከረ፡ ድሉን የሱን መሆኑን ሁሉም የትግሉ አጋር እና ጠላትም ማዋቅ አለበት። ሁሉግዜ ድል የ”ሻዕብያ” የህዝብ ነውና።
በለው! says
“ሰዶ ማሳደድ ሲያምርህ ሀገርን በክልል ለውጥ ”
—–ይህ እንቁላል የሆነብን ሕገ መንግሥት ለዚህ ትውልድ ዕንቁ ከሆነበት የዶሮ እንቁላል የበለጠ አስጎመጀን !? ጄኔራሉ ብሔር ብሔረሰቦች እና
ሕዝቦች ብለው በእኛ የተፈጠራችሁ ለእኛ የምትኖሩ ያለ እኛ የምትበታተኑና የየምትጠፉ አለማለታቸው ብቻ ደህና ነው ።
—— ይህ መንቀሳቀስ እና መዘዋወርን በቅጡ ያለየውን፡ እራስን በራስ ማስተዳደርና የያዝኩት ሁሉ የእኔ፡ክልሌ ጨርቅ ቀለም የነከረ ሁሉ ትናንሽ ሀገር ከመሠረተ ሉዐላዊነት የት ነሽ ? ፭፻፵፯ ወንበሮች ለአንድ ንባብ ካጨበጨቡ ሌላው እንዴት ይደመጣል ? ብሔር ነገድ ጎሳ ዜግነት ነውን
—– ጀነራሎችን አትራፊ ነጋዴዎች ማለት የራስን ሀብትና ንብረት ይሽፍናል? የሠራዊቱ በኢኮኖሚ እራሱን ችሎ ማደሩ ክልላዊ ልዩ ዞን ይፈጥራል ብለው ይሆን ? የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ምን አለው ምንስ ያጣል ?”ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የምትከተል ሀገር አደለችም” ገለታው ዘለቀ ችግሮችን ተንትነውታል ሀገር ብሎ ክፍለ ሀገር እንጂ’ ክልል’ የከብቶች የግጦሽ መሬት ነው ። ሰንደቅ ዓላማ ፡ብሔራዊ መዝሙር ፡ዳር ድንበር ፡ በልማታዊ አርቲስቶች ጋዜጠኞች ካድሬዎች አድርባይ ምሁር ተብዬዎች እንደ ጥጋብ እና ርሃባቸው ሁኔታዎች መቀያየርና መጭበርበር የለባቸውም ።አራት ነጥብ ። ለፃድቃን የዘነበው የታጋይ ውጤት ሀብት ለድሉ ውጤት ናፋቂ ለዳያኖችም ያካፋላቸው ወቅቱ የየሚጠይቀውን የሚተገበር ለውጥ እንጂ የጫካ ማኒፌስቶ አለመሳካት ፡የህወአት እንፍሽፍሽ፡ የ፲፱፺፯ አብዮት ፡ ቱማታ ምን ዋጋ አለው ? ትግሬ ከሰሜን መሐል ሀገር ክልል(የአፓርታይድ መንደሮች ) ሊመሠርቱ ይችላሉ። ቆሻሻቸውን የሚጥሉበት ቦታ እንኳን ሕገማኒፌስቶው አይሰጣቸውም አዲስ አበባን ያየ የቋንቋና ብሔር ተኮር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ግብሩ ‘ሜንጫ’ ነው።
አለም says
ጎልጉል፤ ጻድቃን በህወሓት ብሎግ ሆርን አፌርስ ስለ ለጠፈው ጽሑፍ ትንሽ ልበል። ሁለቴ በጥንቃቄ አንብቤለታለሁ። በዝብዝቡ መንገላታት አያሻንም። በግልጽ ያስቀመጣቸውን እንመልከት። 1/ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ከጓደኞቼ ጋር ተመካክረን ነበር ብሎናል፣ ጓደኞቹ እነማን እንደሆኑ ግልጽ ነው 2/ ስለኢትዮጵያ የነገረን የማናውቀውን አይደለም፤ ህወሓትን አሳጥቶ መጻፉ ለአንዳንዶች አስገራሚ መስሎ ይታይ ይሆናል። ጉዳዩ ግን፣ ህወሓት በራሱ ሊለው የማይችለውን ተመካክረው እያለላቸው ነው 3/ ምርጫ ይኑር፣ የምርጫ ውጤት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን ብሎአል 4/ የርሱ ሃብት ማካበት በራሱ ጥረት እንደሆነ ሊያሳምነን ሞክሯል 5/ ስዬን ጠቅሷል 6/ የኢትዮጵያን ሠራዊት በትኖ የህወሓትን መተካቱን በወቅቱ “National defense and economic development”ብሎ ያቀረበውን ሰነድ ቆንጽሎ ሙሉውን ሰነድ ሊደብቀን ሞክሯል 7/ ዛቻ ብጤም አሰምቷል፤ ካለዚያ ደም በደም እንሆናለን ብሎ። ድምዳሜዬ? 1/ የህወሓት አካሄድ እንደማያዋጣ ተረድቷል፤ ስዬ እንደሞከረው [ትዝ ይልሃል? አንዴ እስር ቤቱ ኦሮምኛ ይናገራል ያላትን?] 2/ ደቡብ ሱዳን ላይ ለአሜሪካኖች ዓላማ አስተባባሪ ሆኖ እየሠራ ነው፤ ስዬ ምዕራብ አፍሪካ ላይ። 3/ ህወሓት ከመለስ ሞት በኋላ መስማማት ስላልቻሉ ኃ/ማርያምን አስቀምጠው ካብ ለካብ እየተያዩ ነው፤ “ኮሌክቲቭ ሊደርሽፕ” በሚል ማጭበርበሪያ ኃ/ማርያምን ደብረጽዮን፣ በረከት፣ አባይ፣ ብርሃነ ገ/ክ ገንዘቡን ሥልጣኑን ተቀራምተውታል፤ አንዱ ችግር ይኸው ነው። አሜሪካኖች የችግሩን መጠን ያውቁታል፤ አታላይነቱ ስለገባቸው የመለስ መወገድ እረፍት ሆኗቸው ነበር፣ አሁን ደግሞ የዋለለ ጉዳይ እንዲቀጥል አይፈልጉም። ህወሓት ሶማሌን፣ ደቡብ ሱዳንን በኢትዮጵያውያን ደም እየነገደ አመቻችቶላቸዋል። ይህን ነገር መፍትሔ ስጡ እያላቸው ነው። የወገኖቻችን ደም መፍሰስ ምንም ያልመሰለው ለዚህ ነው። በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ጉዳይ ኢትዮጵያ ወንበር ያገኘችው በአሜሪካና በእንግሊዝ እርዳታ ነው። አሁን የሚፈለገው ጻድቃን [ወይም ስዬ] እንደ ታዳጊ ቀርቦ የአሜሪካኖችን ዓላማ ያስፈጽማል፤ በዚያውም የህወሓትን የበላይነት ይታደጋል ማለት ነው። ፕሮፌሰር መሳይ ይህን እንዴት እንዳልተረዳው ገርሞኛል። በናይጄሪያ ያደረጉት ይህንኑ ነው፤ ጆናታን ጉድለክ በጄኔራል ሙሐመዱ ቡሃሪ የተተካው በአሜሪካኖች እርዳታ ቦኮሃራምን ለመዋጋር በሚል ነው። ብዙ ሌላ ሐተታ በማቅረብ እንዳላሰለች ጉዳዩን ለማስረዳት የቀረበው በቂ ይመስለኛል። [በነገራችን ላይ የህወሓት ብሎግ ሆርን አፌርስ በእንግሊዝኛ የተረጎሙት ለህወሓት አመቻችተው ነው፤ ጊዜ ካገኛችሁ ትርጉሙን ከአማርኛው ቅጂ ጋር አስተያዩ። አሁንማ የጻድቅቃንን ኢንተርቪው እያሰሙን ነው። ፐብሊክ ሪሌሽንስ ነው ነገሩ፤ ለምርጫ ውድድሩ ፓርቲ ሳይኖር ተጀምሯል!]። ሌላ የሚያሣስበው የነዶ/ር ብርሃኑ መወላገድ ነው፤ ከጻድቃን ባላነሰ ለአገራችን መቅሠፍት ናቸው የሚል ግንዛቤ ላይ ደርሻለሁ። ብትፈቅዱ ይህን አስተያየቴን አትሙልኝ። እኔም ለአገሬ ማሰቤ ነውና፣ ሌሎች ይስሙትና የሚመስላቸውን ግንዛቤ ይውሰዱ። አመሰግናለሁ።