- ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከዓለም 150ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች!
- አገሪቱ የነፃ–ሚዲያ ባለቤት የምትሆነው በህወሓት መቃብር ላይ ነው!
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ድጋፍንም ሆነ ተቃውሞን ምክንያታዊ በሆኑ ነገሮች መግለጽ የሚችልና ፖለቲካዊ ንቃት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ትግል፤ ካለ ነፃ ፕሬስ ተዋፅኦ ስሙር ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ገዥው ኃይል የግሉ ፕሬስ ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና አሳታፊነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር የራሱን በጎ ሚና እና አበርክቶ እንዲወጣ ምቹ የሥራ ምህዳር ከመፍጠር ይልቅ በትዕግስት አልባ ባህሪው የተነሳ በነፃ ፕሬሱ ላይ የተለየ ሃሳብና የፖለቲካ አመለካከት በተንፀባረቀ ቁጥር በመደንበር ሚዲያዎቹን በመዝጋት፣ በግልፅ የተደነገገውን ህግ በህብዑም ሆነ በግላጭ ሲንደው ታይቷል፡፡
በውጤቱም፤ በየዓመቱ የዓለም አገራት የጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ይዞታን እየገመገመ ደረጃ በማውጣት የሚታወቀው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በፕሬስ ነፃነት ኢትዮጵያን ከ180 የዓለም አገራት በ150ኛ ደረጃ አስቀምጧታል፡፡ በገዥው ኃይል ጫና ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች የመፃፍ ነፃነትን በመንፈግ እንደ ኤርትራ፣ ሶሪያ ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ማይናማር (በርማ)፣ . . . ካሉ አገራት ጋር ሥሟ የሚጠራ አፋኝ አገር እንደሆነች የፕሬሱ ጠበቃ የሆኑ ድርጅቶች በየጊዜው ከሚያወጡት ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡
ጋዜጠኞች በፃፉት ፅሁፍና በህትመት ውጤቶቻቸው በተስተናገዱ ፅሁፎች ብቻ ተከሰው እስራትና የገንዘብ ቅጣት የሚፈረድባቸው አገር የህወሓቷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ለነፃ ጋዜጠኞች የተመቸች አገር አልሆነችም፡፡ ስደት ወይም እስር የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች ዕጣ ፈንታ ነው፡፡
ህወሓት ባሳለፈው ረዥም የትጥቅ ትግል፣ ሚዲያ ከፕሮፓጋንዳ አኳያ ለትግሉ የነበረውን አስተዋፆ በድምፀ – ወያኔ በኩል ተረድቶታል፡፡ የህትመት ውጤቶችን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በተመለከተ ደግሞ በነ “ታጠቅ”፣ “ወይን” በኩል የፕሮፓጋንዳን ዋጋ አስተውሏል፡፡ ድርጅቱ በተፈጥሯዊ ባህሪው ብቸኛ የአገሪቷ አዳኝ መሆኑን በበዛ “እርግጠኝነት” ያምናል፡፡ ከዚህ ስሁት አመኔታው ተነስቶ ከርሱ ውጪ የሚቀርቡ ሃሳቦችም ሆነ ይህንን የተለየ ሃሳብ ይዘው የሚከራከሩትንና የሚሞግቱትን ነፃ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት በተለያዩ ጫናዎች ከገበያ እንዲወጡ አልያም በ“ህግ” ሽፋን መጨፍለቅ የሩብ ክፍለ ዘመን ተሞክሮው ገላጭ ማሳያ ነው፡፡ ይህ “እኔ ብቻ የእውነት ባለቤት ነኝ” ርዕዮተ ዓለማዊ በሽታ፣ ጉልበት ብቸኛ አማራጭ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በዚህ አፄ – በጉልበቱ ባህሪው ህዝባዊ አደባባዩን ጭር አድርጎታል፡፡ የነፃ – ፕሬሱ አፈና የማህበራዊ ድረ – ገፆችን የአመፃ መንገድ ቢወልድበትም ቅሉ፡፡
ህወሓት መራሹ ገዥ ኃይል ከምርጫ 97 በኋላ ነፃውን ፕሬስ ለማፈን ሁለት አዋጆችን በማውጣት ለአፈናው መሳሪያነት ሳያሳልስ ተጠቀሟል፡፡ የመጀመሪያው አዋጅ “ተሻሽሏል” በሚል የወጣው የፕሬስ አዋጅ መሆኑ ይነሳል፡፡ ይህ አዋጅ የአገዛዙ የግራ ጥፍር የሆኑ የጋዜጣ ባለቤቶች (አማረ አረጋዊንና መሰሎቹን ልብ ይሏል) “አስደሳች” ሲሉ ያወደሷቸው አንቀፆች ግራ እንዳጋቡን እያስታወስን፤ ቅጣቶችን በተመለከተ ያስቀመጣቸው የህግ ማዕቀፎች ክፋት አከል ናቸው፡፡ አዋጁ እንደሚለው ለአነስተኛ የሥም ማጥፋት ክስ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ድረስ የገንዘብ ቅጣት እርከን አስቀምጧል (ተከሳሹ ጋዜጠኛ ቅጣቱን መክፈል ካልቻለ ወደ እስር ይቀየራል) በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የቅጣት ህግ ጠጥቶ በማሽከርከር የሰው ህይወት ያጠፋ አሽከርካሪ በስም ማጥፋት ተከሶ ከሚቀጣው ጋዜጠኛ በእጥፍ ያነሰ የገንዘብ ቅጣት ነው የሚወሰንበት፡፡
ይሄ አዋጅ አንድ የክፋት ዓላማ አለው፡፡ እሱም የነፃውን ፕሬስ አባላት በቅጣት ሥም የገቢ አቅም ማሽመድመድ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ተጨማሪ የነፃ ፕሬሱን የገቢ አቅም ማዳከሚያ መንገድ ደግሞ “የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መንፈግ” የሚል ይሆናል፡፡ በመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም. በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተፃፈ የሚነገርለት “የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግል እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ” በሚለው ሰነዱ፤ ጉዳዩን እንዲህ ሲል ያብራራል “ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ተቋሞች በተለይም የመንግስት ድርጅቶች እና ልማታዊ ባለሃብቶች ማስታወቂያቸውን ለሥርዓቱ አደጋ በሚሆኑ የሚዲያ ተቋሞች ላይ ማውጣታቸውን” እንዲተው ሰነዱ ያሳስባል፡፡ “ዜጎችም በሂደት ሥርዓቱን ለአደጋ የሚጥል ሚዲያ መጠቀም በራሳቸው ላይ እባብ መጠምጠም መሆኑን ተገንዝበው” ሚዲያዎቹን ከመጠቀም (ከመግዛት) እንዲቆጠቡ ያዝዛል፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ በሽታ የሚመራው ህወሓት/ኢህአዴግ ከላይ ከተጠቀሰው የፕሬስ አዋጅ በተጨማሪ ብዙ ዜጎችን ወደ ቃሊቲ ለመወርወር ጥቅም ላይ ያዋለውን “የፀረ- ሽብርተኝነት ህግ” በመጠቀም የነፃውን ፕሬስ ቤተሰቦች ለማጥቃት ረዥም ርቀት ተጉዟል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ያሻውን የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማቸውን በፈቀደው ጊዜ የፈለገውን ያህል የሐሰት ክስ በመዘርዘር ጋዜጠኞቹን ማሰርና የሚዲያ ተቋማቱን መዝጋት የአገዛዝ መለያ ባህሪው ነው፡፡ በእስካሁኑ ተሞክሮውም “ህገ – መንግስቱን በኃይል ለመናድ፣ በመንግስት ላይ የሀሰት ወሬ በማውራት ህዝቡ እምነት እንዲያጣ ማድረግ” እና “ከሽብር ቡድኖች ጋር ተባብሮ መስራት” የሚሉ ዋጋ አልባና ፍሬ ከርስኪ ነገሮችን በመደርደር “ክስ” ብሎ የሚዲያ ተቋማቱን ዘግቷል፡፡ ጋዜጠኞቹን አስሯል፡፡ እንዲሰደዱ ገፍቷል፡፡
አሁን በአገሪቱ ላይ ካሉት የህትመት ሚዲያዎች ውስጥ ሞጋች የሆኑ የነፃው ፕሬስ ውጤቶች አደባባዩ ላይ ተቀብረዋል፡፡ “አለን” የሚሉትም በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎችና ገዥውን ኃይል በነቃፊ – ደጋፊ አሰላለፍ የወገኑ ተለጣፊ የህትመት ውጤቶች ናቸው፡፡ የህወሓቱ ቋሚ ዘብ አማረ አረጋዊ “ሪፖርተር” ልፋጭ ዜናዎችና ሚዛናቸውን የሳቱ ከንቱ ፖለቲካዊ “ትንተናዎች”፤ የ“አዲስ አድማስ” በፍርሃት የተሸበቡ የፖለቲካ ዜናዎች፣ በተረት የታጨቁ “ርዕሰ አንቀፆች”፤ የጠቅላይ ኢኮኖሚ በዝባዡ አላሙዲን ዜና መዋዕል የሚፃፍበት “ሰንደቅ” ጋዜጣ፤ የኮሪደር ሃሜት የሚያስተናግደው “ፎርቹን” ጋዜጣ፤ የዝነኛ አርቲስቶችን ውሎና አዳር እየዘገቡ ገንዘብ የሚለቃቅሙ የፀጉር ቤት መፅሔቶች፤ . . . አገሪቱ አሁን ካለችበት አገራዊ ቅርቃር አኳያ የህትመት ውጤቶቻቸው ይዘት በህዝብ ደም ላይ እንደመረማመድ ያለ ድፍረት ነው፡፡ አገር ውልቅልቋ እየወጣ ወደ ርስ በርስ ጦርነት እየተጠጋን ባለበት ሁኔታ አቀርቅሮ የማስታወቂያ ገንዘብ መሰብሰብ ምን የሚሉት ብኩንነት እንደሆነ እንደዜጋ አይገባንም፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያ ቀዳሚ ተግዳሮት ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ አቻቻይና አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት አገራዊ አውድ፤ በሙያው መርህ ላይ በመቆም ከኢኮኖሚ እና ባህል ተኮር ከሆኑ አገራዊ ክስተቶች አንፃር የሚመጡ ማነቆዎችን በመሻገር ሙያዊ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል፡፡
እውነታው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አቻቻይ ሳይሆን “የእኔን እውነት ብቻ ተቀበል” የሚል ጨፍላቂ ፖለቲካዊ አገዛዝ በመስፈኑ የጋዜጠኝነት ጉዳይ የህዝብን የመረጃ ጥማት ማርካት ብቻ ሳይሆን አፋኙን ገዥ ኃይል የሚገዘግዝ መንገድን መምረጥና በፅናት መሞገት ምርጫ የሌለው የሙያው መንገድ ነው፡፡ በርግጥም አገር እየፈረሰች ባለችበት ሁኔታ ስለሙያው መርህ ማሰብ የበዛ አገራዊ ዝንጉነትና አድርባይነት ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚያድገውም ሆነ የሚበለፅገው አገር ስትሰነብት ነው፡፡ አገር በብተና ውስጥ ሁና የሙያውን መርህ በሚዛናዊ ዘገባ ልተርጉም ማለት ዘበት ነው፡፡
የዘንድሮው የፕሬስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ባለበት በዚህ ሳምንት እንኳ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር እየማቀቁ ያሉ ጋዜጠኞች ከደርዘን በላይ ናቸው፡፡ ሞጋቾቹ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ውብሸት ታየ፣ ጌታቸው ወርቁ፣ ኤልያስ ገብሩ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ዘላለም ወርቅአገኘሁ (ጦማሪ)፣ ደርሴማ ሶሪ፣ ካሊድ መሐመድ፣፣ . . . ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ በእስር እየማቀቁ ያሉ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
አሳፋሪ በሆነ የ“ክስ” አቀራረብ በ“ሽብር ወንጀል” የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበት፤ ቃሊቲ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በተከታታይ ዓመት አራት ጊዜ “የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጀግና” ሽልማት ተቀዳጅቷል፡፡ የነፃውን ፕሬስ ሞጋችነትና የተደበቀውን ፈልፍሎ የማውጣት ባህሪውን በተለየ ፅናት በማሳደግ የምናውቀው እስክንድር ነጋ፤ ለአቻዎቹም ሆነ ለተከታዮቹ የሙያው ሰዎች ‹የእስክንድር ሞዴል› ልንለው የሚቻለን የፅናት መንገድ አስተምሯል፡፡ ፈለጉን የተከተሉ የሙያው ሰዎች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው ስደት አልያም እስር መሆኑን ስንታዘበው የኖርነው እውነት ነው፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከህወሓት/ኢህአዴግ የልማት ፕሮፓጋንዳ ጀርባ ያሉ ሐቆችን በተጠየቃዊ አጀንዳዎች ተንትነው የሚያቀርቡ የነፃው ፕሬስ ውጤቶች በገበያው ላይ እንዲኖሩ አይፈለግም፡፡ የፕሬስ ተሟጋችነት ሚና አስፈላጊነቱ የማይካድ ቢሆንም፣ ግራ ዘመሙ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለ ትችትና ነቀፌታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚዲያ ህግ መሰረት የአገሪቱን ዜጎች ከአንድ ሚዲያ ብቻ መረጃ እንዲያገኙ የመጠርነፍ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ህወሓት ከአናሳ ዘውግ የመውጣቱ እውነታ ተጭኖት ያለቅጥ ከለጠጠው የዘውግ ፖለቲካው በተጨማሪ ህብረተሰቡን በመደብና በአመለካከት “ጠላት”፣ “አጋር” እያለ እንደከፋፈለው ሁሉ በነፃ – ፕሬስ ላይም ይህን ብያኔ ገቢር በማድረጉ፣ ድርጅቱ በሥልጣን እስካለ ድረስ ሞጋችነት የሚንፀባረቅባቸው የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን ማየት የማይታሰብ ሆኗል፡፡
የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች መከራ ህወሓት/ኢህአዴግ እስካለ ድረስ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ አገዛዙ ሥልጣኑን ካፀናባቸው የአፈና ግብሮቹ አንዱ ነፃውን ፕሬስ የማፈንና የመጨፍለቅ መንገድ ተጠቃሽ እኩይ ድርጊቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎች የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች “ህወሓት/ኢህአዴግ በነፃው ፕሬስ መቃብር ላይ ቁሟል” ሲሉ የሚከሱት በርግጥም አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ አገሪቱ የነፃ – ሚዲያ ባለቤት መሆን የምትችለውም ሆነ የህዝብ የመረጃ ጥማት የሚረካው የትግራይ እንክርዳድ በሆነው ህወሓትና ከአምሳያው አሳንሶ የፈጠራቸው ተለጣፊ የግንባሩ አባል ድርጅቶች መቃብር ላይ ነው፡፡
የዓለም የፕሬስ ቀንን ስናስብ ስደት ወይም እስር ዕጣ ፈንታቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ቤተሰቦችን ማስታወሱ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለከፈሉት ዋጋ እንደዜጋ ባለዕዳ መሆናችንንም አንዘነጋውም!! (Photo: HRW እና ጎልጉል)
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው፡፡
Leave a Reply