“ባለፉት 50 ዓመታት የተከሰቱት ጦርነቶች የተጀመሩት ሚዲያው ባስተጋባው ውሸት መሆኑን ደርሼበታለሁ” ጁሊያን አሳንዥ፤ የዊኪሊክስ መሥራች።
የአገራችን ሚዲያ አውታሮች በተለይም የግሉ ሚዲያ የሚባሉትና በ1997 ምርጫ ወቅት የነበሩት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲቀጭጭ፣ የሃሳብ ልዩነት እንዳያድግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ጉያ ሥር ገብተው የፈጸሙት ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው። ለቀጣዩ ትውልድ መማሪያ ይሆን ዘንድ በወጉ ተጠንቶና ተሰንዶ ሊቀመጥ ይገባል።
ምክንያቱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲከሰት ያየነው ፖለቲካው ወይም ፓርቲዎች ሚዲያውን አጀንዳ እያስያዙ ሲመሩት ይቆዩና በኋላ ፖለቲከኞቹ እርስበርስ ሽኩቻ ውስጥ ሲወድቁ የሚፈልጉትን ለማጥቃት ወይም በሐሰት ለመወንጀልና ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት ሲሉ ለሚዲያ ባለቤቶቹ ባሪያና ተገዢ በመሆን እነርሱ ሚዲያውን መምራት ሲገባቸው በሚዲያው በመመራትና አሽከርና ባሪያ ሲሆኑ ነው። ከዚያ ሚዲያው ወይም “ጋዜጠኞች” የተባሉት የሚቀርጹላቸውን አጀንዳ ማስፈጸም የፖለቲከኞቹ ዋንኛ ተግባር ይሆናል።
የ1997ቱ ምርጫ ወቅት “ጋዜጠኞች” ናቸው ዛሬም በየሚዲያው በጋራና በተናጠል አገሪቱን እያመሱ ያሉት። ኢንተርኔት ከመስፋፋቱና ዩትዩብ ከመታወቁ በፊት ባለው ዘመን እንደ ዮሴፍ ያሉ የመቃብር ቦታዎች በመሄድ ከመቃብር ላይ ፎቶ እየነቀሉ የፈጠራ ታሪክና ዜና ሲሠሩና ሳንቲም ሲለቅሙ የነበሩትን ጨምሮ “ፓርላማ እንዳትገቡ” በሚል ልዩ ተልዕኮ የ1997ቱን ሕዝብ ዋጋ የከፍለበትን ምርጫ በዜሮ ያባዙ ነጻው ሚዲያ የሚባለው ባልደረቦች ናቸው።
በ1997ቱ ምርጫ ቅንጅት አሸንፎ ፓርቲዎቹ ፓርላማ ስለመግባት ጣይቱ ሆቴል ተነጋግረውና ወስነው ሳለ በቀጣይ በነበሩት ቀናት “ዋ! ፓርላማ ትገቡና” የሚል በፊት ገጻቸው ላይ የማስጠንቀቂያና የማስፈራሪያ ዘገባ ሲያወጡ ከነበሩት መካከል የእስክንድር ነጋ “ሚኒሊክ” እና “አስኳል” ጋዜጦች ተጠቃሾች ናቸው። ለዚህ ነው ይህ ሊጠናና በይፋ ለሕዝብ ያለ አንዳች ፍርሃት ሊቀርብ የሚገባው ጉዳይ ነው በማለት ማሳሰቢያም ተማጽንዖም ለማቅረብ የወደድነው።
ዛሬ ላይ በአብዛኛው ሚዲያ ንግድ፣ የወር ገቢ፣ እንጀራ፣ ወዘተ እየሆነ መጥቷል። በሕዝብ ስቃይ፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደትና እንግልት የሚነግድ ሚዲያ፣ ብሔራዊ ጥቅምና የፖለቲካ ልዩነትን ቀላቅሎ አገራቸው ላይ የባዕድና አጀንዳ የሚረጩ የሚዲያ ውጤዎች ጉዳይ ሰፊ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ እናምናለን።
እነዚህ ሚዲያ ተብለው የሚጠሩት ለፍልፈው ሲጨርሱና ለመለፍለፍ ሲዘጋጁ “በሉ እንግዲህ አገልግሎቴን የምትደግፉ በፔይፓል፣ በቀጥታ በባንክ፣ በዜል (Zelle)፣ በካሽአፕ (CashApp)፣ …ጣል፣ ጣል አድርጉ፣ … በሱፐር ቻት፣ በሱፐር ስቲከር፣ … ይህንን ሚዲያ ደግፉ” በሚል የጠዘቀጠ ልመና ላይ የተሰማሩ ሚዲያዎች ራሳቸውንም ከልመና በማላቀቅ ሠርተው እንዲበሉ ተማፅዕኗችንን እናቀርባለን። መረጃ በማቅረብ ስም እንደማትነጥፍ የፈረንጅ ላም ብሩን የሚያልቡትን አድማጭና ተመልካች “ቤተሰብ” እያሉ መሸንገላቸው ሌላው መጠቀስ ያለበት ጸያፍ ተግባራቸው ነው። ይህን የምንለው ግብዝ ሆነን ሳይሆን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 11+ ዓመታት ያለ ምንም ማስታወቂያ አንዲት ሳንቲም ከማንም ሳይወስድ ሥራውን እየሠራ መሆኑን ለመግለጽ ጭምር ነው።
ወደ ተነሳንበት አጀንዳ ስንመለስ በዳያስፖራ የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚቃኙና በአንድ ቦይ እንዲፈስ ከሚያደርጉ ወሳኝ አካላት መካከል መሽቶ ሲነጋ ጎራ እየለየ የሚሰነጠቁት ሚዲያዎች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በሚዲያው ላይ ቀን ተሌት የሚታዩት ግለሰቦች አጀንዳ በመስጠትና መረጃን በሚፈልጉት አቅጣጫ እንዲፈስ በማድረግ ከአገሩ ተለይቶ በርቀት የሚገኘውን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ሲንጡት ይታያሉ።
ሲጀምሩ “አንድነትን መሠረት ያደረግን ነን፣ ኢትዮጵያዊ ነን፣ የምንሰብከው፣ የምንቆመው ለኢትዮጵያዊነት ነው” በሚል ይምላሉ፣ ሲቀጥሉም “ከየትኛውም ሃይማኖት፣ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ቡድን የወገንን ሳንሆን በነጻነት ለሕዝባችን መረጃ የምናቀርብ ነን” ይላሉ። ሳይውል ሳያድር በተግባር ሲከፈቱ የአንድ ጎጥ፣ ፖለቲካ ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ግለሰቦችና የባዕዳን ኃይላት አጀንዳ ተሸካሚና አከፋፋይ መሆናቸው ይገለጣል። ይህን ለማረጋገጥ ነብይ መሆንም ሆነ የጠለቀ ጥናት ማካሄድ አያስፈልግም። መለስ ብሎ ከራሳቸው አንደበት የወጣውን ምስክርነታቸውን ማየት በቂ ነው።
የተበጣጠሰው ኢሳት እንደማሳያ
ለምሳሌ ያህል በዋናነት ማሳያ የሚሆነው፣ በትህነግ አገዛዝ ዘመን የነበረውን ጭቆና ለመታገል ከተቋቋሙት የሚዲያ አውታሮች መካከል የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ገደማ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትዎርክ ወይም (Ethiopian Television Network (ETN)) ነው። ይህንን ተቋም ከመሠረቱት መካከል በግምባር ቀደምትነት የሚታወቀው ታማኝ በየነ ሲሆን ሌሎችም አብረውት ሲሠሩ ቆይተዋል።
ይህ የበርካታዎችን ተስፋ ዕውን ያደረገ ሚዲያ ገና እንደ ተቋቋመ መናጥ ሲጀምር ድጋፍና መዋጮ ሲያደርጉ የነበሩ ወገኖችን ማሳሰብ ጀመረ። አንዱ ችግሩ ያለ ዕቅድ የ24 ሰዓት ፕሮግራም መጀመሩ ሲሆን የአየር ሰዓቱን ክፍተት ለመሙላት የፕሮግራም ድርቅ ወዲያው ሲመታው ከብጥስጣሽ የዜና መረጃና የታማኝ በየነ ከተለያዩ ዐውዶች ባለሥልጣናት የሚናገሩትን በመቆራረጥ እንዲመቸው አድርጎ ሰዎችን የሚያሳጣ ሙያዊ ልምሻ ያለበት ፕሮግራም ከማሰራጨት በስተቀር በርካታውን ሰዓት በዘፈንና ፕሮግራም በመደጋገም ነበር የሚሞላው።
ከዚህ ሌላ ታማኝ በየነ የወያኔ መራር ተቃዋሚና ተቺ ሆኖ ቢቀርብም ከወያኔ ጋር አብሮ ተወዳጅቶ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት አገራችንን ሲያፈርስ የነበረው ሼህ መሃመድ አላሙዲን የቅርብ አፍቃሪና ተሟጋች መሆኑ ብዙዎችን አልዋጥላቸው ያለ ጉዳይ ነበር፤ የተከፈተውንም ሚዲያ ጎድቶታል። እርሱም በተደጋጋሚ ሲጠየቅ “ከእጃቸው በልቻለሁ” ማለቱን ተከትሎ “ታዲያ ከወያኔ እጅ የበሉት ወያኔን መደገፋቸው ለምን ያስወቅሳቸዋል?” የሚል ጥያቄ አስነስቶ አልፏል። ይህ አሁንም ምላሽ ያላገኘና የታማኝን ታማኝነትና ማንነት ፍንትው አድርጎ የሚሳይ መረጃ ነው።
ይህ በዕውር ድንበርና በተራ ሽለላ ያለ ዕውቀት ሲነዳ የነበረውና ኪስ ያደለበው የታማኝ ሩጫ ወዲያው ዕጣ ፋንታው በፍጥነት ከአየር መውረድ፣ መጥፋት፣ … መሆኑ ዕውን እየሆነ ሲመጣ ብዙዎች የፍርሃት ቆፈን ይዟቸው ድምጻቸውን በአደባባይ ማሰማት ጀመሩ። ጫጫታው ቢበዛም አሸዋ ላይ እንደታነጸ ሕንጻ ብዙም ሳይቆይ የበርካታዎችን ገንዘብና ተስፋ ይዞ ሚዲያው ተሰናበተ።
የታማኝ ስንበትና የሚዲያው ቀብር ሲጠናቀቅ “የአገር ፍቅር አንገበገበን፣ የትህነግ ጭቆና መረረን” ያሉ ሰዎች “ተሰባሰብን” አሉና የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ወይም ኢሳት (ESAT) የሚባል ሚዲያ ከፈቱ። ወቅቱ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2010ዓም ነበር። ኢሳት ከነታማኝ ETN ትምህርት ወስዶ የጀመረ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢናገርም ይህም የመዘጋት ዕጣ ይደርስበታል ብለው ሥጋት የያዛቸው ወገኖች “እባካችሁን እንዳትዘጉት፣ የሚቸግራችሁን ንገሩን፣ ዓቅማችን በፈቀደ እንደግፋችኋን፣ ተስፋችንን አታጨልሙት፣ የማትቀጥሉ ከሆነ አትጀምሩ፣ …” የተሰኙ አስተያየቶችን ከያቅጣጫው ማሰማት ጀመሩ።
ኢሳት ሲጀመር የቦርድ አባላት የነበሩት ፕሮፌሰር አል ማርያም (ዓለማየሁ ገብረማርያም) የቦርዱ ሊቀመንበር፣ የቀድሞ የትህነግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ግደይ ዘረዓጽዮን ምክትል፤ ሜሮን አሐዱ ሳቡሬ ጸሐፊ፤ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ምክትል ጸሐፊ፤ አበበ በለው አፈቀላጤ፣ አባላት ደግሞ – ታማኝ በየነ፣ ሼክሲፒር ፈይሣ፣ አበበ ገላው፣ ሙሉጌታ ሉሌ (አሁን በሕይወት የሌሉ)፣ ሉሊት መስፍን፣ ዶ/ር አዚዝ መሐመድ፣ ዳኛ ፍሬሕይወት ሳሙኤል እና ነዓምን ዘለቀ ነበሩ።
ከጅምሩ ከነጻ ሚዲያነት ይልቅ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለመተግበር ኢሳት ገብተው የነበሩ፤ ሚዲያውን በራሳቸው አቅጣጫ የዓላማቸው ማስፈጸሚያ ማድረግ ሲጀምሩ እንደ ታማኝ በየነ ኢቲኤን ኢሳትም መናጥ ጀመረ። ሲቋቋም የትህነግ ሰዎችንም እንኳን ቢሆን አቅርቦ ለመሞገት ዓላማ አድርጎ የተነሳው ኢሳት “በኢሳት ሚዲያ በወያኔ ላይ የሚሠራው ፕሮፓጋንዳ የተለሳለሰ ነው፣ ኃይለ ቃላትን በመጠቀም ትህነግን ማውገዝ እና ሲብስም መሳደብ” እንደሚገባ በተለይ በእነ ነአምን ዘለቀ በኩል የከረረ አቋም ተያዘ።
ከሙያም፣ ከሥነ ምግባርም አኳያ ሁኔታው ያልጣማቸው እነ ፕሮፌሰር አል ማርያም ከተወሰኑ ስብሰባዎችና ክርክሮች በኋላ ድምጻቸውን አጥፍተው ከኢሳት እብስ አሉ። ውሎ ሳያድርም ኢሳት የግንቦት ሰባት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ልሳን ሆነ። ለአብነትም ያህል የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት ነዓምን ዘለቀና በኋላም ቢሆን አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲሁም የግንቦት ሰባት የሙሉ ጊዜ ደጋፊዎች የነበሩት ታማኝ በየነና አበበ ገላው የኢሳት አመራር መሆናቸው ሚዲያው የግንቦት ሰባት ንብረት ለመሆኑ አንድ ማረጋገጫ ነው። ውሎ አድሮም ግንቦት ሰባት ወያኔን ለመጣል “ከሰይጣንም ጋር ቢሆን እንሠራለን” በሚለው አቋሙ ኢሳት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ግብጽ ዕርዳታና ድጎማ እስከመቀበል እንዲደርስ አደረገው።
በበርካታ ብልሹ አሠራርና ሽኩቻ እየተወዛገበ እንደምንም እስከ ለውጡ የዘለቀው ኢሳት የለውጡ አካባቢ የመጀመሪያ የሚባለው የክፍፍል ምች መታው። ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አገር ቤት ሲገባ፣ መሣሪያ አስነግቦ ፎቶ እያነሳ በመለጠፍ ለማስታወቂያ ሥራ ይጠቀምባቸው የነበሩ እነ ዘመነ ካሤ ከኤርትራም ሆነ ከግብጽ የሚላከው የግንቦት ሰባት ፈንድ በመቋረጡ ምክንያት ሥራ ፈት ሆኑ፤ ጠብሽ መታቸው። በተመሳሳይ ኢሳት አገር ቤት ከገባ እና የለውጡ ደጋፊ ከሆነ በኋላ በቀጣይ ባለው ዓመት “የአሠራር ለውጥ አድርጌአለሁ” በሚል ወደ 10 የሚጠጉ ሠራተኞቹን አሰናበተ።
ከኢሳት ማህጻን የተወለደው ኢትዮ 360 እና ይዞት የደራው ገበያ
ኢሳት የአሠራር ለውጥ ሲያደርግ፣ በወቅቱ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢሳት ኃላፊ ተደርጎ ሲሾምና እነዚህ 10 ሠራተኞች ከኢሳት ሲለቅቁ በዋነኝነት ምክንያት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሳትን እንዳፈረሱት፣ ለዚህም ተግባር የቀድሞ የኢሳት እና የግንቦት ሰባት ኃላፊዎች እንደተባበሯቸው፣ በመንግሥት ላይ የሰላ ሒስ ማቅረብ በመጀመራቸው ከሥራ ሊባረሩ እንደቻሉ እንጂ ኢሳት እንደሚለው የበጀት ዕጥረት ዋንኛው ምክንያት እንዳልሆነ በሚዲያ ወጥተው ተናገሩ። በወቅቱ ከኢሳት የተባረሩትና የለቀቁት: ምናላቸው ስማቸው፣ ሃብታሙ አያሌው፣ ጌታቸው አብዲ፣ ልዩ ጸጋዬ፣ ኢየሩሳሌም ተክለጻዲቅ (የምናላቸው ሚስት)፣ ኤርሚያስ ለገሠ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ተወልደ በየነ (የርዕዮት ባል) እና ሌሎች የቴክኒክ ሰዎች ይገኙበታል።
ከኢሳት የለቀቁት በአንድነት ተሰባሰቡና ኢትዮ 360 የሚባል የዩትዩብ ሚዲያ አዋለዱ። ከዚህ በፊት ኢሳት የነበረው አበበ ገላው ከኢሳት ቀድሞ የለቀቀ ቢሆንም በኢሳት ባልደረባነት ስም ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የክብር አቀባበልና መስተንግዶ ተደርጎለት ነበር (አበበ ከለቀቀ የቆየ ቢሆንም ከኢሳት ባልደረቦች ጋር አብሮ ለመሄድ በብርቱ ለምኖ እንደተሳካለት የቅርብ ወዳጆቹ ይመሰክራሉ)። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መጠቀስ የሚገባው የኢሳት ባልደረቦች ኢትዮጵያ “የድል” አቀባበል የተደረገላቸው ብቻ ሳይሆን ውሎ አበል እየተከፈላቸው ከመሰንበት ባለፈ ከመንግሥትም ዳጎስ ያለ ጥቅማጥቅም ተለግሶላቸው ነበር።
የዚያን ጊዜ ከኢሳት የለቀቀው አበበ ብቻ ሳይሆን ኔዘርላንድስ የሚገኘው ደረጀ ሃብተወልድ “በራሴ” በሚለው ምክንያት ከኢሳት ለቅቆ ነበር። እርሱም ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ጀግኖ ተመልሶ መምጣቱ ይታወሳል። ከኢሳት ከለቀቀ በኋላ “ዜና ትዩብ (በኋላ ደሬ ኒውስ)” የሚባል እዚያው ኔዘርላንድስ ከሞቀ ጓዳው ተቀምጦ “ጋዜጠኝነት እንዲህ ከሆነ ባፍንጫዬ…” የሚያስብል፤ ሙያውን በቀን ሁለቴ እየሰቀለ እየቀበረ ነው። ለነገሩ እሱ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሁሉም ስሙን ተሸክመው የሚሸቅጡ እንጂ የሙያና የሙያው ሥነምግባር ጉዳይ ከተነሳ “ዜሮ በዜሮ” የሚለውን ዘፈን ከማስታወስ በቀር ዝርዝር ጉዳይ እንኳን አንስቶ ለማስረዳት የሚበቃ ሽራፊ ፍሬ የላቸውም።
በዚህ መልኩ መከፋፈል የጀመረው ኢሳት ከቀደምት ሠራተኞቹ ሲሳይ አጌናን፣ መሳይ መኮንን፣ ፋሲል የኔዓለምን፣ እንዲሁም ጴጥሮስ መስፍን፣ ግዛው ለገሰ፣ ወንድምአገኝ ጋሹና ሌሎች ሠራተኞች በመሆን ኢሳትን በአሜሪካ ሲያስቀጥሉ የአገርቤቱ ኢሳት በሳባ አታሮ አመራር ቀጠለ። ሳባ ከዲሲ ኢሳትን አጅባ አዲስ አበባ ያለው ቢሮ መሪ ከሆነች በኋላ በውስጥ በተነሳ ሽኩቻ ለራሷ ደሞዝ፣ ጥቅማ ጥቅምና አስፈላጊ ያለቻቸውን ክፍያዎች በመክፈል ወደ ዲሲ ተመለሰች። ዛሬ ላይ ቦሌ ወሎ ሰፈር ግድም የሪል ስቴት ነጋዴ ሆናለች። አንዳርጋቸው ጽጌ የተተካው በሳባ አታሮ እግር መሆኑ ነው።
ከኢሳት ማህጸን ተገፍተን ተወለድን ብለው የተደራጁት የኢትዮ 360 ፊት አውራሪዎች ወዲያውኑ ተፈጥሯቸው የሆነው የመከፋፈል ምች አጠናገራቸው። ምቹ ባልና ሚስቱ ተወልደ በየነ እና ርዕዮት ዓለሙ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን እንዲጠቀሙ አደረጋቸው። በዚሁ መብታቸው የመገንጠል አዋጅ አውጀው ከኢትዮ 360 ተለዩ። የራሳቸው “ምንጊዜም” የሚባል ዩትዩብ ከፍተው “አገልግሎታችን በዚህ እና በነዚህ የክፍያ መንገዶች ደግፉ፣ ጎፈንድ አድርጉ፣ ላይክ እና ሰብስክራይብ አድርጉ፣ በሱፐር ስቲከር ሸልሙን” በማለት ድጋፍ መለመን ጀመሩ። ከኤርሚያስ ለገሰ ጋር ዓይንና ናጫ የሆነው ምናላቸው ስማቸውም ከጎጃም ባለሃብቶች በተደረገለት ድጋፍ “ጊዮን ሚዲያ” የሚባል ዩትዩብ ከፍቶ ባለቤቱ ኢየሩሳሌም ተክለጻድቅ ካለችበት 360 በመልቀቅ እሱም የሕዝብ ድምጽ ሆኛለሁና “አገልግሎቴን” በዚህ መንገድ ደግፉ በሚል በየፕሮግራሙ ይለምን ገባ።
በአሜሪካው ኢሳትና በኢትዮጵያው ኢሳት መካከል የተለያዩ አለመግባባቶች ከጅምሩ የነበሩ ቢሆንም በተለይ የአሜሪካው ኢሳት ውስጥ ያሉት በመንግሥት ላይ ባላቸው የአመለካከት መለያየት ክፍፍል ውስጥ ገቡ። ይህም እነ ሲሳይ አጌና አሜሪካ ተቀምጠው ኢሳት የሚለውን ስም መጠቀም ወደማይችሉበት ደረጃ ሲያደርሳቸው ከኢሳት ተገንጥለው EMS (Ethiopian Media Services) የሚባል ሚዲያ ከፈቱ። የአገርቤቱም “ኢሳት ኢትዮጵያ” በመባል ቀጠለ። እነሱም “አዲስ ነን” በሚል ወዲያው በአዋጅ የተለመደውን “የሳይበር ልመና” ጀመሩ።
በሌላ ወገን ኢትዮ 360 በመንግሥት ላይ በመረጃ የተደገፈም ያልተደገፈም የሚዲያ ዘመቻውን ተያያዘው። ኤርሚያስ ለገሠ በአንድ ወቅት “በ360 ከሚቀርቡት አምስት የዜና ዘገባዎች ሦስቱ እዚያው ስቱዲዮ ውስጥ የሚፈበረኩ ናቸው” እንዳለው ሚዲያው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን አጧጧፈው። በተለይ ፖለቲካን ከሃይማኖት ጋር በማጋባት የዶ/ር ዐቢይን አስተዳደር ከፖለቲካም ሆነ ከሃይማኖት (ፕሮቴስታንትን በመቃመው) ከፍተኛ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ኢትዮ 360 ሲሠራ ቆይቶ በኤርሚያስና በሃብታሙ መካከል ቀድሞ ጀምሮ የነበረው የመናናቅ ቁርሾ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ኤርሚያስ ከ360 እንዲለቅቅ ሆነ።
ነገሮችን በካድሬ የሤራ ስልት እየሰነጣጠቀና በሦስትና በአራት ወይም በአምስት እየከፋፈለ “የሚተነትነው” ኤርሚያስ በአብዛኛው ሃብታሙን የዕውቀት ድርቀት የመታው ነው በሚል የሚንቀው ሲሆን ብዙ ጊዜ ሃብታሙ በሚሰጠው ትንታኔ ላይ ሲያሾፍና ሲያላግጥ አልፎም ንቀት ሲያሳይ እንደነበር አብረው የሠሯቸው ፕሮግራሞች ምስክር ናቸው። ከዚህ ሌላ ኤርሚያስ ለኢትዮ 360 የዩትዩብ ገቢ ዋናው ምንጭ እርሱ የሚሰጠው ትንታኔ በመሆኑ ከገቢው የአንበሳውን ድርሻ ማግኘት እንዳለበት መናገሩና ይህም ለክፍፍሉ ሌላ ምክንያት እንደሆነ ብዙዎች የሚመሰክሩት ነው። አፍቃሪ ትህነግ የሆነው ኤርሚያስ ከወጣ በኋላ የኢትዮ 360 የዩትዩብ ተመልካች በአስደንጋጭ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ እንደ አንድ ማሳያ ይጠቀሳል።
ወዲያውም ኤርሚያስ ከኢትዮ 360 ከለቀቀ በኋላ “ኮምፓስ” የሚባል የዩትዩብ የማውሪያ መስመር ከፈተ። የኤርሚያስ መሰናበት 360ን ለቅቆ ለሄደው ምናላቸው ስማቸው ዳግም ትንሳኤ ሆነለት። ኤርሚያስና ምናላቸው በአንድ ቢሮ ውስጥ በዳይና ተበዳይ ሆነው መክረማቸው ለዚህ አጀንዳ ባይመችም ከሞራል አንጻር ማሳያ ስለሆነ ወረፍ አድርጎ ማለፉ አግባብ ይሆናል።
ከኢሳት ማህጸን የወጣው ሌላው EMS – የመሳይ መኮንን “ጫማ” ሰቀላ
ከኢሳት የተገነጠለው የእነ ሲሳይ አጌና ቡድን EMS እንዲሁ በፖለቲካና በጥቅም ጉዳይ መናጨት የጀመረው ገና የዳዴ እርምጃውን ሳይጨርስ ነው። በውጤቱም ጽንፍ በወጡና ዕለት ዕለት በደፈናው የፖለቲካ እርግማን ላይ ባተኮሩት “ተንታኞች” እና “ሚዛን እንጠብቅ” በሚለው ሲሳይ አጌና መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ይፋ ሆነ።
በሲሳይ በኩል በተቻለ ነገሮችን ከስሜት ይልቅ በኢትዮጵያዊነትና ሚዛናዊነት እንይ የሚለው አስተሳሰብ ያልተስማማው መሳይ መኮንን ከEMS ለቀቀ። እንደወጣም “ጫማ ሰቅያለሁ፤ ፎጣ ወርውሬያለሁ፤ ወደ ሚዲያ አልመለሰም” በማለት የደጋፊዎችን ልብ ለማራራትና ተመልሶ ለመምጣት ራሱን ሲያመቻች ከቆየ በኋላ “ብዙዎች ባደረጉልኝ ጥሪና በአገራችን ላይ እየደረሰ ባለው ግፍ ዝም ብዬ መቀመጥ ስላልቻልኩ” ብሎ ፈጣን የጎፈንድ ሚ አካውንት በማዘጋጀት “አንከር ሚዲያ” የሚባል ዩትዩብ ከፍቶ እውነትን ይጨፈላልቅ ጀመር። ያለ አንዳች ሃፍረት የሐሰት ወሬ መፈብረኪያ ቱቦ ከፍቶ ኪሱን እያደለበ ከኪሱ እያወጣ በሚያወራው ወሬ ከአስመራ አመራር የሚቀበሉትን ጌቶቹን ጮቤ ማስረገጥ ጀመረ። ከአንድ ወር በፊት የምኒልክ ሃውልት ሊፈርስ ነው ብሎ የሠራው በሬ ወለደ ዓይነት ወሬ እንደ ማሳያ የሚጠቀስ ነው። ከሁሉ የሚያሳዝነው ለዚህ ዘገባው ይቅርታ አለመጠየቁ ብቻ ሳይሆን እስካሁንም ከዩትዩቡ ሳያወርደው ሳንቲም እየለቀመበት መሆኑ ነው።
በቀጣይም ሲሳይ እና እነ ግዛው በየቀኑ በሚደረገው ዕለታዊ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የሆነ መቃቃር የሚያደርስ ሙግት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲሳይ ብቸኛ መሆኑን ተመልክቶ EMSን ለፋሲል፣ ለግዛው፣ … በመተው የራሱን “ሉዓላዊ” የሚባል ሚዲያ ከፍቶ እየሠራ ይገኛል።
ከኢሳት ከለቀቀ በርካታ ጊዜያት ያሳለፈው አበበ ገላው ወደ አገር ቤት የክብር አቀባበል እንዲደረግለት ኢሳትን በመለመን አብሮ ከተጓዘ በኋላ ጥቂት ነገሮች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ከመጻፍ ሌላ የግል ሥራውን በሥፋት የመሥራቱን ጉዳይ ነበር ቀዳሚ ያደረገው። ሆኖም እንደ ኢሳት ያለ ሌላ አዲስ ሚዲያ እንደሚቋቋም በተደረገው ስምምነት እርሱም ከማን አንሼ ዩትዩብ ማውሪያ ቱቦ ከፈተ። ስሙንም “የኢትዮ ቮይስ ኔትዎርክ EVN” በማለት ጠራው።
ጠቅላዩ ሥልጣን እንደተቆናጠጡ ከዳያስፖራው ጋር ለመነጋገር ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ በመጡ ጊዜ ለጣዖት እንደሚሰገድ በደረቱ ለጥ ብሎ እግራቸው ላይ የወደቀው ታማኝ በየነ የራሱ “ታማኝ ሾው” የሚባል ዩትዩብ አለው። በዚህ ቱቦ የሚቆራረጠውን እየቆራረጠ፤ የሚከተፈውን እየከተፈ ዓቅሙ በፈቀደ የተለያዩ ቁርጥራጭ ቪዲዮዎችን ቀጣጥሎ ይፖስታል። እርሱም ከኢሳት ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጦ አውርቶ ማደሩን የተያያዘው ቀደም ብሎ ነበር። አዲስ በተቋቋመው ቲቪ (ኢሳን) ተደፍቶ ከሰገደላቸው ጠቅላዩ ጀምሮ የብልጽግና ሰዎችን ንግግር ከዚህ በፊት ያደርግ እንደነበረው እየቆረጠና እየቀጠለ ለማቅረብ የወሬ ጠብመንጃውን ወልውሏል።
የጎጃም ዕዝ – የጎንደር ዕዝ – የሸዋ … የፖለቲካና የሚዲያ አሰላለፍ
ኢሳት ተበጣጥሶ እዚህ ከደረሰ በኋላ ሁሉም እንደጋላቢያቸው አሳብና ዕቅድ ማስፈጸሚያ ያመች ዘንድ የተለያዩ ሚዲያዎችን እንዴት እንደከፈቱ ካየን ቀጣዩ የሚዲያ አሰላለፍ ምን ሊሆን እንደሚችል ማመላከቱ አግባብ ይሆናል።
ከላይ ከኢሳት መበጣጠስ በኋላ የራሳቸውን ፕሮፓጋንዳ ማፍሰሻ ቱቦ (ዩትዩብ) የከፈቱት በቅርቡ ተነጋግረውና ተማምለው አዲስ ሚዲያ ከፍተዋል። ሚዲያውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ኔትዎርክ (ኢሳን/ESAN) ብለውታል። በዚህ ሚዲያ ተሳታፊ የሆኑትና የራሳቸውን የወሬ ቱቦ ይዘው የመጡት የአበበ ገላው “ኢቪኤን”፣ የደረጀ ሃብተወልድ “ደሬ ኒውስ”፣ የመሳይ መኮንን “አንከር”፣ የመታሰቢያ ቀጸላ “ምናለሽ መቲ”፣ የታማኝ በየነ “ታማኝ ሾው” እና እነ ግዛው የሚመሩት “ኢኤምኤስ” ናቸው። እነሱም ገና ከመጀመራቸው “ይህንን የሕዝብ ድምጽ የሆነ ሚዲያ ደግፉ” ብለው የጎፈንድሚ የልመና ኮሮጆ ከፍተዋል። በነገራችን ላይ ጎፈንድሚ ላይ ሕዝብ ይሰጣል ቢባልም ሚዲያ እንዲከፈት የሚፈልጉ ባዕዳንና ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ግለሰቦችና አገራት ስማቸውን ደብቀው (Anonymous) በማለት ወይም በሃሰተኛ ስም የሚሰጡ መሆናቸው በመረጃ የሚናገሩ ጥቂቶች አይደሉም። ለነዚህ ወገኖች በቀጥታ ድጎማ ከማድረግ ይህ የጎፈንድሚ አካሄድ በጣም ይመቻቸዋል፤ ተቀባዮቹንም “እኛ ከማንም ምንም የማንቀበል በሕዝብ ድጋፍ ብቻ የምንቀሳቀስ ነን” ብለው እንዲመጻደቁ ይረዳቸዋል።
አሁን ላይ ፖለቲካውን በዋናነት የሚዘውረው ሚዲያ (ኢሳን) የሚመራው በአንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ (አባቱ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ለጣሊያን ያደሩ ባንዳ ነበሩ)፣ በነዓምን ዘለቀ፣ በትሪፕል ኤ (AAA) ወይም (Amhara Association of America) ሆነው በዋናነት ይጠቀሳሉ። በአማራ ክልል ያለው የነፍጥ ትግል አደረጃጀት እንደየ አካባቢው ስለሚለያይ እነዚህ ግለሰቦችና ቡድን/ቡድኖች የተለያዩትን አደረጃጀቶች በሥራቸው ለማድረግ ርብርቡ ቀጥሏል። ለዚሁ ዓላማቸው ሚዲያ መቀራመት ደግሞ ቁልፍ ነው።
በዚሁ ሃቅ መሠረት እስክንድርን ነጋን የአገር ውስጥ መሪ፤ የውጪውን ደግሞ ሻለቃ ዳዊት ያደረገው ቡድን 360ን በዋናነት ሲጠቀም ቆይቷል። አሁን ላይ አንዳርጋቸው ከሻለቃ ዳዊት ጋር አብሮ እየሠራ ቢሆንም ኢትዮ 360 አንዳርጋቸውን እጅግ በከፋ ደረጃ ሲሰድበውና ሲያበሻቅጠው ስለነበር አሰላለፉ እንዲቀየር ይፈልጋሉ። በዚሁ መነሻ ሃብታሙ አያሌው ሎንዶን ድረስ በመሄድ ከአንዳርጋቸው ጋር ተመካክረው ተመልሷል፤ አንዳንዶች ሃብታሙ ብቻውን መቅረቱን በማየት “የአስገቡኝ” ማመልከቻ ነው ያቀረበው ይላሉ።
በወያኔ ግፍ ደረሰብኝ ብሎ ጋቢ ተከናንቦ ፎቶ በመልቀቅ የበርካታዎችን ልብ ያራራውና ኪሳቸው እንዲከፈት ያደረው ሃብታሙ በቀጣይ ወደ አውሮጳ ጉዞ እንደሚያደርግም ይጠበቃል። የጉዞው ዋና ዓላማ አገር ለማፍረስ እንዴት አብረን እንሥራ ቢሆንም ተንገዋሎ የቀረው ሃብታሙ የ“አስታውሱኝ አትርሱኝ፤ አስገቡኝ” ልመና የሚያደርግበትም ነው ተብሏል። ይህ ልመና በአውሮጳ የሚኖሩትን የቀድሞ ኢሳት ባልደረቦቹን አሁን ኢሳን የተባለውን ሚዲያ የከፈቱትን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘመነ ትህነግ/ወያኔ አንዳርጋቸው ጽጌ አስመራ ይዞት ከሄደው ታማኙ መሳይ መኮንን ጋር እስካሁን በዋናነት ስለሚሠራ በሚዲያው ቁጥጥር ላይ የበላይነት ያላቸው ይመስላሉ። አሁን ላይ ደግሞ የጎጃሙ “ፋኖ” ዕዝ እነ ሃብታሙን በግልጽ በማሰናበቱና በማውገዙ ሃብታሙ ጭንቅ ውስጥ ገብቷል። ለዚህም ይመስላል “የጎንደር ዕዝ ተመሥርቷል” በሚል በስፋት እየሠራ ያለው። ለጎጃሙ ዕዝ ተገዳዳሪ የመረጃ ኃይል በመሆን በጎንደር ዕዝ ስም የሚዲያ/የመረጃ ባለቤትነት ያለው መሆኑን ለማሳየት ይመስላል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን ጎንደር ላይ አዲስ ተቋቋመ የሚባለው ዕዝ እነ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአስመራው ሻዕቢያ ጋር በመሆን ያደራጁት በመሆኑ ሃብታሙ ሳይወድ በግዱ እዚህ አሰላለፍ ውስጥ እንዲገባ እያደረገው ነው።
የእነ ሻለቃ ዳዊት ሴል አራማጅና አዝማች የሆነው እስክንድር ነጋ ከጎጃም መባረሩ፣ ዝናቡ ይመራዋል የሚባለው የጎጃም ዕዝ እነ ሃብታሙን ማሰናበቱና ጎጃምን በተመለከተ በ360 ላይ ምንም መረጃ እንደማይሰጡ ካስታወቁ በኋላ አዲስ የተሰማው ወሬ ዘመነ ካሴ የሚመራው ኃይልም በተመሳሳይ ከእነ ሃብታሙ ጋር የመቆራረጡ ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ ዝናቡና ዘመነ አንድ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑንን ተከትሎ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” እንዲሉ ሁለቱም ከ360 ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲበጥሱ ኤርሚያስ ለገሰ ከ360 መውጣቱን ተከትሎ ወደ 360 ተመልሶ የነበረው ምናላቸው ስማቸው የራሱን ሚዲያ ይዞ እንዲወጣ ትሪፕል ኤዎች (AAA) አቋም ወስደዋል። በተሰጠው መመሪያ መሠረትም ምናላቸው ከ360 መልቀቁን በይፋ አስታውቋል።
የጎጃም ባለሃብቶች ከጀርባው እንዳሉ የሚነገርለት ይህ ቡድን (AAA) በትህነግ ዘመን ሃብት ያፈራና ጎንደር ለትህነግ ባሳየው የመረረ አመለካከት ሲታሽ ከትሕነግ ጋር አብረው የነበሩ እንደሆኑ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። እነዚህ ኃይሎች “ብልጽግናን አብረን እንዋጋው” በሚል አሜሪካ ሆነው ከትህነግ ጋር ግንባር ስለመግጠምም እየተወያዩ እንደሆነ መረጃዎች አሉ። ለዚህ ከትህነግ ጋር ለሚደረግ ትብብር መደራደሪያና መማማያው ደግሞ ወልቃይት ሲሆን፣ ይህን የተረዳው የወልቃይት ጠገዴ አስተዳደር ከመከላከያ ጋር በመሆን በእያንዳንዱ ቀበሌ ሚሊሻ፣ ፖሊስና ማንኛውንም ኃይል በይፋ እያሰለጠነ መሆኑን አስታውቋል።
ከጎጃም የሚወጡ መረጃዎች ለምናላቸው ስማቸው ብቻ እንደሚሰጠው፣ የመነሻ ድጋፍም እንደሚደረግለት (ስም ሳይጠቅሱ ጎፈንድሚ ላይ ዕርዳታ የሚያደርጉትን እያሰብን)፣ ማንኛውንም የድጋፍ መስመሮች እሱ ብቻውን እንደሚያስተዳድር ቃል ተገብቶለት ከ360 እንዲወጣ ሲጋበዝ ጎን ለጎን የተሰማው ዜና ሸዋ ያለው እንቅስቃሴ መሪ “የማንንም ድጋፍ አንፈልግም፤ 360 ከራሳችን ላይ ውረድ” በሚል ሃብታሙ አያሌው “ተሼ” እያለ የሚጠራው አመራር የሰጠው ጥብቅ ማሳሰቢያ ነው።
ተሼ “እፈሩ” ሲል የሸዋው ኃይል የማንንም ድጋፍ እንደማይፈልግ ለነሃብታሙ አስታውቋል። የእነ ሃብታሙ ክንፍ የሆነው እስክንድር ከጎጃም ሲባረር መሽጎበታል ከተባለበት ሸዋ ይህ ዜና መውጣቱ ያስደነገጠው ሃብታሙ 360 ላይ “ለዜና አይሆንም፣ ትግሉን ያበላሻል ብለን እንጂ ስንቱን ዕንቁ እንደረሸንህ …” እያለ ተሼን ሲዘልፍ ተሰምቷል። በዚህ መነሻ 360ን የሸዋውና የጎጃሙ ኃይል ከማንኛውም መረጃ አቅበውታል፤ ቆልፈውበታል። ይህም 360ን በመረጃ ድርቅ ውስጥ ከማስገባት ባለፈ የግድ በአንዱ የሚዲያ መስመር መሰለፍ እንዳለበት እያስገደደው መጥቷል። የሃብታሙ የሎንዶን ጉዞና በቀጣይም ወደ አውሮጳ የሚያደርገው ጉብኝት ከዚህ አንጻር የሚታይ እንዲሆን አድርጎታል።
ይህ የሃብታሙ አካሄድ ግን አማትቦ ጀምሮ በስድብ የሚጨርሰውን፤ በራሱ አንደበት ጤነኛ እንዳልሆነ የሚናገረውን ዘመድኩን በቀለን ያላስደሰተው መሆኑን በቅርቡ ባወጣቸው መረጃዎች ላይ ጠቋሚ ፍንጮች ሰጥቷል። የዘመድኩንን ድጋፍ ማጣት ለሃብታሙ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ 360 ውስጥ የቀሩትን ጥቂት ሰዎች ለተጨማሪ አሜባዊ ክፍፍል ይዳርጋቸዋል ተብሎ ይገመታል።
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ያለው ሃብታሙ “ሲፋጅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ በእጄ” እንዲሉ “የዐቢይ አሽከር” እያለ አንዳርጋቸው ጽጌን ሲቀጠቅጥ እንዳልነበር በሰሜን በኩል “የጎንደር ዕዝ” በሚል እነ አንዳርጋቸው ያደራጁትን ኃይል ለመቀላቀል ተገድዷል። ማንኛውም ጎጃም ነክ መረጃ ለምናላቸው ብቻ የሚደርስ ከሆነና የሸዋው ቡድን “አትድረስብን” በማለቱ ለሃብታሙ ጎንደርን መያዝ የኅልውና ጉዳይ ሆኖበታል። ለዚህም ይመስላል ረጅም ርቀት በመሄድ አምርሮ ከሚጠላው አንዳርጋቸው ጋር አብሮ ለመሥራት “የአስገቡኝ” ማመልከቻ እየበተነ የሚገኘው።
ይህ መነሻ ምክንያቱ ከሆነ የሚዲያው አሰላለፍ በዚሁ ዐውድ ይቃኛል። ጎን ለጎም ክፍፍሉ ከምን የመነጨ ነው የሚል ጥያቄ በስፋት እየተነሳ ነው። ሚዲያው በዚህ አሰላለፍ ከሄደ አንዳርጋቸው የሚመራውና እነ መሳይ አቋቋምን ያሉት ኢሳን ከኤርትራ ጋር በአንድ የሚወግን ሲሆን በሌላ ደግሞ የጎጃሙ ክንፍ አፈቀላጤ የሆነው ምናላቸው አንድ ኃይል ሆኖ ከኢሳን ጋር በኅብረት ሊሠራ ይችላል ወይም አስቀድሞ በጎጃም ባለሃብቶች ለብቻው እንዲወጣ የተደረገበት ምክንያት ስላለ የነአንዳርጋቸውን ኃይል የሚገዳደር ሆኖ ክፍፍሉን የሚያሰፋ ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ነፍጥ ያነሳው ኃይል እንደታሰበው እየተንቀሳቀሰ አይደለም። አንድ ወጥ ዓላማና ግብ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ተከፋፍሎ ሲናጥ ከርሟል። “በምድር ላይ እኔ እና እስክንድር ብቻ ብንቀር አንነጣጠልም፤ እኔና እስክንድር በፍጹም ይህ ምድር ሊበጥሰው የማይችል የመንፈስ አንድነት አለን፤ በምድር ላይ እስክንድርና እኔ ብንቀር አንጣላም፤ ትግሉን ወደ አንድ እናመጣዋለን” እያለ ሲምል ሲገዘት የነበረው ዘመነ ካሤ “እስክንድር ካደኝ” በማለት በዚያው አፉ ሲረግመው እየተሰማ ነው። እንመራዋለን ያሉት ኃይልም በኢህአፓ ዘመን በ”ቸ” እና “ሸ” (እናቸንፋለን እና እናሸንፋለን) ልዩነት ጠመንጃ የተማዘዘውን የዚያን ትውልድ ሌጋሲ በመድገም እነሱም “ግምባር” እና “ኃይል” በሚል መከፋፈላቸው ከተሰማ ቆይተዋል።
ይህ ክፍፍልም እያደገ መጥቶ መሣሪያ እስከ መማዘዝ ያደረሳቸው በመሆኑ “በተለያዩ ቦታዎች የሚገኘው ኃይል በአንድ ዕዝ ሥር ይመራ” የሚለውን የብዙዎችን ምኞትና ሕልም ቅዠት አድርጎታል። ይህም ለነአንዳርጋቸው ጥሩ ዕድል ከፍቶላቸዋል። ከሻዕቢያ ኃያል ጋር ሆነው ሃብታሙ ተመሠረተ ያለውን የጎንደሩን ዕዝ ከነሱ ጋር በማስተባበር የጎጃሙ ኃይል ከጎንደር ጋር ካለው ታሪካዊ ልዩነት ታክሎበት ብቻውን እንዲቀር ይሆናል። የሸዋውና የወሎው ኃይሎች በየፊናቸው እንደሆኑ ቀድሞ ከራሳቸው አንደበት የተሰማ ነው። ይህ የኃይል አሰላለፍ ከነ ዘመነ ጎጃም ተተፍቶ ሸዋ የተደበቀውን እስክንድርን ነጋን ወደ አንዱ የቡድን አባት እንዲገባ ያስገድደዋል። በተለይም ሻለቃ ዳዊት ከነአንዳርጋቸው ጋር በጥምረት መሥራቱ እስክንድርን ወደዚው እንዲገባ ሊያደርገው ይችላል። አልገባም ካለ ግን ብቻውን ቀርቶ ይከስማል።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ከመንግሥት የተሰጠውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ እጁን እየሰጠ ያለው ሠራዊት ቁጥሩ ቀላል አይደለም፤ ይህ በመንግሥት ሚዲያ የሚሰጥ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን እነ 360ም ያመኑበት ነው። እጃቸውን የሰጡትንም ስማቸውን እየጠሩ “ከሃዲ፣ ባንዳ፣ …” እያሉ ኮንነዋቸዋል። በየቦታው በታጣቂው ኃይል ላይ እየደረሰ ያለው ሽንፈትም “በ15 ቀን አራትኪሎ” ብሎ የብዙዎችን ልብ ያማለለው እንቅስቃሴን ክፉኛ አዳክሞታል። ይህ እርስበርስ ከተፈጠረው መከፋፈል ጋር ተዳምሮ የኃይል አሰላለፉን ብቻ ሳይሆን የነፍጡን እንቅስቃሴ አከርካሪውን የመታ ተግባር ሆኗል። በተለይ ደግሞ ነፍጥ አንጋቢዎቹ በቡድን ተከፋፍለው የተጋደሉና ደም የተቃቡ በመሆናቸው በክልሉ ካለው የጥቁር ደምና የአቋጥሬ ባሕል አኳያ ይቅር ተባብለው ወደ ኅብረት የመምጣታቸውን ተስፋ በእጅጉ አጨልሞታል።
በአንዳርጋቸው አጋፋሪነት የተመሠረተው የዩትዩብ ስብስብ ወይም ኢሳን ይህንን የተመሰቃቀለ ፖለቲካ የማቅናትና ወደራሱ የመጠምዘዝ ከባድ ኃላፊነት ወድቆበታል። ፖለቲካውን መዘወር ከመጀመሩ በፊት ግን የራሱን ኃይል ማጠናከርና መዋጥ የሚችለውን ሚዲያ (ዩትዩብ) በተቻለው ፍጥነትና ብርታት መዋጥ አለበት። ስለዚህ ሃብታሙ እንደ ሌሎቹ የራሱን ዳቦ 360ን ይዞ ወደዚህ ማኅበር ከገባ ቀሪዎቹ ምናላቸው፣ ኤርሚያስና ባልና ሚስቱ እነ ርዕዮት ይሆናሉ።
አሁን ያሉት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አፍቃሪ ትሕነግ የሆነው ኤርሚያስ ከነቴዎድሮስ ጸጋዬ (ርዕዮት ሚዲያ) ጋር ዕጣ ክፍሉን ካደረገ ቆይቷል፤ ፍርድ ቤት የሞገተው አበበ ገላው የሚመራውን ሚዲያ የአበበ ታዛዥ ሆኖ መሥራቱ ለኤርሚያስ የማይዋጥለት ነው። ምናላቸው ወደ ኢሳን ስብስብ ለመግባት በቅድሚያ ከድርጎ ሰፋሪዎቹ የጎጃም ባለሃብቶች ፈቃድ ማግኘት ወይም መቆራረጥ አለበት። ያለ ፈቃዳቸው መለያየቱ እጅግ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለው ይሆናል። ከአገር የተባረረበትን ምክንያት አድርጎ የሚያቀርበውን የስኳር ፋብሪካ ምሥረታ ጉዳይ በተያያዘ ብዙ ሰነድ የሚያወጣበት ስለሚሆን ያለ ባለሃብቶቹ ይሁንታ እንቅስቃሴው የተገደበ ነው። ባልና ሚስቱ ርዕዮትና ተወልደ (ተቦርነ) ደግሞ ዳግም መጠቀሚያ ላለመሆን የወሰኑ በመሆኑ ከኑሯቸው ጋር የተቆራኘ ሌላ አሳማኝ ምክንያት ካልተሰጣቸው በስተቀር ተመልሶ በዚህ ስብስብ ውስጥ የመታቀፍ ፍላጎት የላቸውም። እምቢታቸው ግን ተመልካች አሳጥቶ የመክሰም አደጋ ውስጥ ስለሚከታቸው ምናልባት ፍራቻው ወደ ኅብረቱ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።
የኢሳት ውልድ የሆነው አዲሱ የዩትዩብ ጥምረት ኢሳን፤ ልክ እንደ አባቱ ካሁኑ የመከፋፈል ምልክቶች እየታዩበት ነው። የመጀመሪያ ተብሎ በተለቀቀውና መታሰቢያ ቀጸላ እያጋፈረች ደረጀ ሃብተወልድ፣ አበበ ገላውና መሳይ መኮንን በተካፈሉበት ውይይት ላይ ደረጀ መለስ ዜናዊን እና ዐቢይ አሕመድን “አንቱ” እያለ ሲጠራ መሳይና አበበ ግን “አንተ” ከማለት ባለፈ ወደ ስድብ በሚወስድ ቃል ሲጠሯቸው ተሰምተዋል። ደረጀ ባብዛኛው ከዶ/ር ዐቢይ ጋር በፊት ለመሥራት መፈለጉን በማመን በግልጽ ይናገራል፤ በአነጋገሩም የጨዋነት ሥነምግባር ለማሳየት ይሞክራል። በአንጻሩ መሳይና አበበ ግን ስድብ ቀረሽ ቃላትን በመጠቀም እጅግ ሲያጥላሉና ሲነቅፉ ተሰምተዋል። በደረጀ በኩል ያለው መለሳለስ በኢሳን ዘንድ ተቀባይነት የማግኘቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። ኢሳትም የገጠመው ተመሳሳይ ችግር እንደነበር ከላይ ጠቅሰናል። ይህ አካሄድ ደረጀን የአቋም ለውጥ እንዲያደርግ ይገፋዋል ወይም “እንደ እናንተ አልወርድም” ብሎ በጠዋቱ ከኢሳን እንዲለይ ያደርገዋል።
ሌላው ልክ ትሕነግ እንደመሠረተውና የፌዴራሊስቶች ግምባር እንደሚባለው ስብስብ ተጠራርተው ኢሳንን የከፈቱ እያንዳንዳቸው ለኢሳን ያላቸው አበርክቶ በጣም የተለያየ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ እጅግ በርካታ ተመልካችና ተከታይ ያለው ደረጀ ነው። መሳይ ቀጥሎ ሲሆን ሌሎቹም ከዚያ የሚከተሉ ናቸው። የዩትዩብ ገቢ ደግሞ በተመልካች ቁጥር የሚወሰን በመሆኑ የደረጀ ተመልካቾች ኢሳንን በመመልከታቸው የሚያስገቡት ከፍተኛ ገቢ እጅግ ጥቂት ካላቸው የማኅበሩ አባላት እኩል የገቢ ክፍፍል ሊደረግላቸው አይገባም የሚል የፍትሐዊነት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ይህም ልክ ኤርሚያስን ከ360 እንዲወጣ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ሁሉ ለኢሳን ስብስብ አባላትም ትልቅ ፈተና ይሆናል። ሆኖም ስጋቱ ለማንም እጅግ የሚያስፈራ አይደለም። ምክንያቱም ኢሳን ቢፈርስ እንኳን ሁሉም ይዞ የመጣውን ዳቦ (ዩትዩብ ቻናል) ይዞ ስለሚመለስ የሚላስ የሚቀመስ አያጣም።
ዕድሜ ጠገቦቹ የቀድሞ የኢሳት ሰዎች ቪዲዮ ከታፊው ታማኝን ይዘው ይህንን ሁሉ የሚዲያ ተግዳሮት ከተቋቋሙ በኋላ ነው ፖለቲካውን መዘወርና ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚጀምሩት። ለዐሥርተ ዓመታት በ“ሚዲያ” ላይ በመታየት ከመሰልቸታቸው ባለፈ አዲስ አቀራረብ ይዘው አለመምጣታቸው አሁን ላይ እነርሱም ዕድሜያቸው ገፍቶ እንደ ታማኝ ያለውን ከአንዳርጋቸው ጋር ይዘው ብቅ ማለታቸው የዝንጀሮውን ብሒል ያስታወሳቸው እንዲህ ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፤ “ዝንጀሮ የሚሞተው በወጣትነቱ የዘለለውን ገደል በስተርጅና ሊዘልለው ሲሞክር ነው”።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Haile says
የሐሰቱ ፕሮፓጋንዳ መጀመሪያ ሲጀምር መነሻው ግብፅ ነበር የጀመረችው። የእስራኤልና በአረብ አገሮች መካከል የስድስቱ ቀን ጦርነት ከመጀመሩ በፉት ግብፅ በወታደራዊ መስክ ያላት ብቃት የጦር መሳሪያቸው ታንኮቹ አሮጌ ከመሆናቸው የተነሳ ፣ኤልኮፕተርና የጦር አውሮፕላን ብዙ ጥገና የሚያስፈልጋቸዎና የጦር ሃይሉ የውጊያ ብቃቱ ደካማ ነው ተብሎ እንዲፃፍ ቨለንደን ሚዲያዎች በምዕራቡ ዓለም እንዲለቀቅ ተደረገ። ይህ ዜና ለእስራኤል መዘናጋት አንዱ ምክንያት ነበረ። ከ1976 ጀምሮ ሕወኣት /የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ፓለቲካውን የጀመረው በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነበር። ሕወኣት መንግስትም ሆኖ የኢትዮጵያንና የትግራይን ሕዝብ የገዛው በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው መንኛውም ጦርነት፣ረሃብ፣በሽታና ለሕዝቦች ሕይወት መጥፋት መንስሔውጨየምዕራቡ ዓለም የፕሮጋጋንዳ ማሽን የነበረው CNN, BBC, Associated Press, Amenity International , Human Right watch, etc…. ከአገራችን የፕሮፓጋንዳ ማሽን ከሆኑት በአሜሪካና በኢትዮጵያ የሚገኙ የሬዲዮ፣የቴሌቪዥን፣የዩቲዩብ፣የፌስቡክና የትውተር ሐሰተኛ የወሬ ቋቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳዮሆን በዓለም ዘዙሪያ ለተፈጠሩት፣ማንኛውም ቀውሶች ተጠያቂ መሆናቸው ግልፅ ነው። ሕዝብ ለሕዝብ፣አማኝ ከአማኝ ጋር፣ሃይማኖት ከሃይማኖት ጋር ፣ ዘር ከዘር ጋር፣ ጎሳ ከጎሳ ጋር፣ክልል ከክልል ጋር በመሬት እንዲገዳደል ተደርጎኣል። ለለፉት 50 አመታት በኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው የኢኮኖሚ፣፣የፓለቲካና የማዕበራዊ ቀውሶች መባባስ የዜና ማሰራጫ ድርጅቶች፣የሶሻል ሚዲያዎች ፣ጋዜጦች፣ድራማና ቪዲዮዎች 70% ሲወስዱ፣20% በውጭም በአገርም ያሉ የፓለቲካ ፓርቲዎችና 10% ደግሞ ገዢው መንግስት ሃለፊነት ነበረባቸው። በአሁኑ ሰዓት ግን በየመንደሩጨእንደ እንጉዳይ የሚፈላው የሶሻል ሚዲያ ከቁጥጥር ውጭ በመውጣቱ ሕዝብም፣መንግስትም፣የዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ግራ በመጋባት ላይ ናቸው። በለፉት አምስት አመታት መንግስት በቂ የሆነ ነው ባይባልም አንዳንድ ማሻሻያ ቢያደርግም የሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ዋና ተዋንያን ሚዲያዎች ላይ ማድረግ የሚገባው ሕጋዊ የሆነ እርምጃ በአገርም ሆነ በውጭ እጅግ ደካማ ነው። የዲሞክራሲ መብቶች መፈቀድ ለአገር፣ለሕዝብ፣ለልማት፣ለሰላም፣ለሰብዓዊ መብትና ለፍትሕ መከበር ሲባል የሚሰጥ መብት ሲሆን አንዳንዶች የዲሞክራሲ መብቱን በተቃራኒው በመጠቀም ስርዓተ አልበኝነትንና ሕገወጥ ሴራዎችን ለመፈፀም እየቸጠቀሙበት ነው። ሐሰተኛ የሶሻል ሚዲያዎች አንድ ቀን ትክክለኛ የሆነ ፍርዳቸውን የሚቀበሉበት ግዜ ሩቅ አይደለም።
Tesfa says
ከግጭት በፊትም ሆነ በጦርነት ጊዜ የመጀመሪያዋ ሟች እውነት ራሷ ናት። የእኛውን ሃገር የፓለቲካ ስንክ ሳር የበለጠ የሚያጠላልፈው ከነገር በፊት ቀድመን በወሬ ስለምንፈታ ነው። ታዲያ ሜዳ ሰጠ ተብሎ በቅሎ እንደ ፈረስ አይጋለብምና አሁን ላይ የወሬው ብዛቱ የጥራቱን አይነት አያሳይም። ይህችንም ያችንም እየለቃቀሙና እየጨማመሩ በየድህረ ገጽና በሌሎችም ሶሻል ሚዲያ ላይ በማሰራጨት የዪቱቭ ሽርፍራፊ ሳንቲም ሰብሳቢዎችና የግድ ውደድኝ በማለት የሚማጸኑት ሁሉ ጊዜ ያመጣው አስረሽ ምችውና ፍሬፈርስኪዎች ናቸው። ለዚህ ነው የሆነውን ሁሉ እንዳለ መጋቱ መልካም አይደለም የምንለው።
በተደጋጋሚ እንዳልኩት የሃገራችን ችግር እኛው ራሳችን ነን። ልክ ነው እኛው በከፈትነው በር ሌሎችም በመግባት በልዪ ልዪ ስልት እርስ በእርሳችን እንድንገዳደል ሰርተዋል እየሰሩም ይገኛሉ። በሃበሻው የጊዜ መስፈሪያ በ 1953 በታህሳስ ግርግር ምክንያት ታስረው የነበሩት ኮ/ሌ እምሩ ወንዴ እንደገና በደርግ ጊዜም ታስረው በድምሩ ከእድሜአቸው ላይ 27 ዓመቱን በእሰር አሳልፈውታል። ከዚያ የተረፈው ጊዜአቸው ደግሞ በስደትና በመንከራተት ያለፈ ነው። አሁን በህይወት የሌሉት እኝህ የሃገሪቱ ውድ ልጅ እንደምሳሌ ተጠቀሱ እንጂ ሌሎችም ሲገድሉና ሲያስገድሉ፤ ሲዘርፉና ሲያዘርፉ፤ ሲሸሹና ተይዘው እንበለ ፍርድ ሲገደሉ የዛሬው የዘርና የጎሳ የክልል ፓለቲካ ላይ ደርሰናል። ምድሪቱ ለእርሷ የሚያስብላትንና የሚያሳስቧትን ለይታ ማየት ከተሳናት ቆይቷል። ከማሰር፤ በግዞት ከማባረር፤ ከመግደል የተለዬ ሌላ ሃሳብ ማመንጨት እስካልቻልን ድረስ መገዳደላችን ይቀጥላል።
ጊዜ ቆሞ ማንንም አይጠብቅም። አሁን በአማራና በኦሮሚያ ያለው ግጭት የህዝብን ሰላም የሚቀማ፡ ረሃብና ጠኔው እንዲበረታ፤ መማር ያለባቸው ልጆች ጊዜአቸው በከንቱ እንዲያልፍ የሚያደርግ የፓለቲካ እሰጣ ገባ ነው። መንግስትም ሆነ ተፋላሚ ሃይሎች ቆም ብለው ያላዪት እንድ ነገር አለ። ወያኔ ብረት እየሳለ፤ ሰው እያሰለጠነ፤ የውጭ ሃይሎችን እርዳታ እየሰበሰበና የፓለቲካ ሽርክናውን ከውጭና ከውስጥ ሃይሎች ጋር እያጠናከረ እንደሆነ ነው። ወያኔ ሶስት ነገሮችን አይወድም። የአማራ ህዝብን፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያንና የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ። ለንገሩ አሁን ያሉትስ የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች መቼ ከወያኔ ይለዪና።
የትዝታ ፈለግ በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እውቁ ኢትዮጵያዊ የጋሞ ሰው አቶ አሰፋ ጫቦ የሻቢያንና የወያኔን ሽርክናና የነጩን ዓለም ክፋት በማጣመር በተለምዶ የደርግ ሰራዊት እየተባለ የሚጠራው የኢትዮጵያ ሰራዊት ወያኔ ሲበትነው ልክ አለመሆኑን ሲቃወም ወያኔዎች እንዳሾፉበት በትዝታ ያወሳል። የዲያስፓራ ፓለቲካ የስማ በለው ፓለቲካ ነው። በዚህም በዚያም ወሬውን እያናፈሱና እየተናፈሱ ድንገት ሃገር ሰላም ሲሆንና ነገሮች ሲቀየሩ ደግሞ ከረባት ቀይረው ብቅ በማለት ስልጣን ይፈልጋሉ። ድሮም አሁንም ወደፊትም የሚሆነው ይህ ነው። መሪዎቻችን ያለፈውን እያክፋፉ የራሳቸውን ህልምና የቀን ቅዥት እየለፈፉ እነርሱም እንደ ቀደሟቸው ሁሉ ምንም ሳያሳኩ ሳያስቡት ይሸኛሉ። የፓለቲካ አዙሪት እንዲህ ነው። መገዳደል፤ እስር፤ የክልል ፓለቲካ፤ የሃይማኖት ሽኩቻ፤ የዘርና የቋንቋ ፍትጊያ እስካልቆመ ድረስ የሃበሻዋ ምድር ሰላም አይኖራትም። የፓለቲካን ውስልትና ለማወቅ ከፈለክ የአብይና የእድሜ ልክ የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ መሪ የነበራቸውን የጫጉላ ጊዜ አሁን በቅርቡ የፈንቅልን በዓል ሲያከበር ተሳዳቢና ፎካሪ ህጻኑን እየሰማ ሲፍነከነክና በመጨረሻ ልጅን አቅፎ ሲታይ እውነትም እነዚህ ሰዎች ካበድ ቆይተዋል ያሰኛል። የሚያሳዝነው በዓሉ በተከበረበት ስፍራ በጦርነቱ የተጎዱት ህንጻዎችና መንገዶች እንኳ ከ 30 ዓመት በህዋላ አልተጠገኑም። ጉራውም ፉከራውም ግን ቀይ ባህር የእኛ ነው ለማንም አንሰጥም ነው። አይ መስጠትማ ይሰጣል። ራሺያ፤ ቻይና ሌሎችም አሰፍስፈውና ለዚህ ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ታላቅ አቀባበል በሃገራቸው ላይ ያደረጉት ለዚህ ነው። ዓለም ሳይታሰብ ወደ ሁለት ጎራ ዳግመኛ እየተከፈለች በመሆኑ ነገርዬው አይቀሬ ነው። ግን ኢትዮጵያ በምጽዋና በአሰብ የእርዳታ እህል እንኳ ማስገባት አትችልም። ታዲያ ለእኛ ይታዘናል? አረመኔዎች ነን እኮ!
በመጨረሻም የስም ለውጥ የይዘት ለውጥን አያመጣም። መጽሃፉም ቄሱም ያው ነው። የፈጠራ ወሬ ማናፈስ። ትንሹን አጋኖ ማውራት። እስቲ ሰው መልሰ ብሎ የወያኔን የጦርነት ወሬ ይመልከት? ስንት ብርጌድ ተደመሰሰ? ስንቱ ተማረከ? ሰነፎችና የፓለቲካ መሰሪዎች የዛሬን እንጂ ታሪክን አያዪም። ለዚህ ነው ከዘመናት በፊት ታምራት ሞላ እንዲህ ብሎ የዘፈነው።
ከመቃብር ጀርባ ስምን የሚያስጠራ
ከሌለ ቁም ነገር አኩሪ ታሪክ ስራ
ምንድነው ትርጉሙ ነበረ መባሉ
እየኖሩ ማለፍ ቁም ነገር ሳይሰሩ። ሌላኛው ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ አቶ ከበደ ሚካኤል
ዓይን የለውምና የሰነፍ ልመና
ወደ አምላክ ሲጸልይ ማታ በልቦና
መንገድ ሳይመታኝ ባቧራ በጭቃ
አድርገኝ ይለዋል ለሃገሬ እንድበቃ
እንጦጦ ተኝቼ ሃረር እንድነቃ
እውነት ነው የዓለም ግጭትና ጦርነቶች ሁሉ ለተመራመረ በፈጠራ ዜና የተቀጣጠሉ ናቸው። የዲያስፓራው ፓለቲካም ሊመረመር፤ ሊፈተሽና በእውነት ላይ ተመርኩዞ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽና ድጋፍ መሆን ከቻለ መልካም ነው። የሚያስፈራው ለሃገርና ለወገን የሰሩ መስሏቸው የጥፋትና የአፍራሽ ሃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚዎች እንዳይሆኑ ነው።