
ብዙ ሰዎች በተደጋገሚ ብሩ በመለወጡ በቀጥታ ኢኮኖሚው ላይ የሚመጣውን ጥቅም ንገረን ብለው ጠይቀውኛል! ብር በመለወጡ የሚገኙት የአጭር ግዜ እና የረጅም ግዜ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች የሚከተሉት ናቸው!
የአጭር ግዜ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች፡- በሀገራችን ከ113ቢሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ከፋይናንስ ገበያው ቁጥጥር ውጪ አለ! ስለዚህ የገንዘብ ለውጡ ይህንን ገንዘብ ወደ ብሄራዊ ባንክ የመለወጥ እድል ይፈጥራል!
ለምሳሌ፡- ምንጩ ያልታወቀ በመሆኑ ወደ ባንክ ሳይመጣ ከሚበላሸው፤ ከሀገር ውጪ በጎረቤት ሀገር በመሸሹ ከማይመለሰው፤ የመቀየሪያ ወቅቱ ከሚያልፍበት፤ በጎርፍ፤ በቃጠሎ፤ ወዘተ ከወደመው ውጪ 100 ቢሊዮን ብር እንኳን ወደ ህጋዊ የባንክ ስርዓት ቢመጣ ከፍተኛ ገንዘብ ከገበያ የመሰብሰብ እድል ስለሚፈጠር የዋጋ ንረት በሚታይ መልኩ የመቀነስ አቅም ይኖረዋል!
ምንጩ ያልታወቀ፤ በሙስና የ ተገኘ፤ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ከፍተኛ ገንዘብ በገበያ በድርጅቶች እና በሰዎች እጅ እንደሚገኝ ይታወቃል! ስለዚህ የተቀመጠውን የጥሬ ገንዘብ ገደብ (1.5 ሚሊዮን ብር ለማለት ነው!) እና ከ5 ሺህ ብር በላይ በባለቤቶች እንዲቀመጥ የሚያዘውን መመሪያ ተከትሎ ህገወጦችን ለመለየት እድል ይፈጥራል፡፡
ለምሳሌ፡- በህገወጥ መንገድ ሃብት ያከማቸ ሰው ወይም ድርጅት ህጋዊ ከሆኑት ሰዎች ተገቢ ያልሆነ Advantage እንደወሰደ ግልጽ ነው! ስለዚህ የብሩ መቀየር የተለየ እድል ያገኙ ሰዎችን በተወሰነ መልኩ ለመቆጣጠር ያሰችላል፡፡
የረጅም ግዜ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች፡- ኢትዮጲያ ውስጥ በባንክ ቤቶ ች ያለው የቁጠባ መጠን ማነስ እና ባንኮች ለባለሃብቶች የሚያቀርቡት የብድር መጠን ማነስ የታወቀ ጉዳይ ነው! ስለዚህ ለምሳሌ 100 ቢሊዮኑ ቢሰበሰብ እና የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ገደቡን ተከትሎ 80 ቢሊዮኑ በባንኮች ቢቀመጥ ተጨማሪ ቁጠባ እና ተጨማሪ የብድር አቅርቦት እንዲገኝ ያደርጋል፡፡
ለምሳሌ፡- መንግስት ባወጣዊ አዲስ መመሪያ መሰረት የግል ባንኮች የመንግስትን የግምጃ ቤት ሰነድ የመግዛት እድል ተፈጥሮላቸዋል! ስለዚህ መንግስት ወደ ፊት ለሚያስበው የበጀት ጉድለትን በሀገር ውስጥ የመሙላት ፍላጎት ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ ሊያገለግለው ይችላል፡፡
ገንዘቦች በመሰብሰባቸው እና በግል ባን ኮች ውስጥ በመቀመጣቸው የሚቀርበው ብድር የግል ሴክተሩን በማነቃቃት ተጨማሪ ምርት እንዲመረት፤ ተጨማሪ ሰራተኛ እንዲቀጠር፤ ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች አድገው የውጪ ምንዛሬ ግኝት እንዲያድግ፤ የሀገር ውስጥ አምራቾች ተበረታተው ከውጪ የሚገቡትን የመተካት አቅም የሚፈጥሩ ከሆነ የውጪ ምንዛሬ እንዲቆጠብ፤ ወዘተ የማድረግ አቅም ይኖረዋል፡፡
ነገር ግን ብር መለወጡ ብቻውን ስር ነቀል ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም! ምክንያቱም ዋጋ ንረት፤ ስራ አጥነት፤ የውጪ ምንዛሬ ክምችት ማነስ፤ የበጀት ጉድለት፤ ዝቅተኛ ምርት እና ምርታማነት መኖር፤ የንግድ ሚዛን መዛባት፤ ወዘተ በገንዘብ ምክንያት ብቻ የመጡም አይደሉም በገንዘብ ምክንያት ብቻም የሚፈቱ አይደሉም! ሌሎች ፖሊሲዎች እና ስራዎች በተጨማሪነት መሰራታቸው ግድ ነው።
©The Ethiopian Economist View
Leave a Reply