* አቶ በእግዚአብሔርና አቶ ምሕረተአብ ተጨማሪ ጊዜ ተጠየቀባቸው
* ሦስት የባለሥልጣኑ ሠራተኞች በነፃ ተሰናበቱ
* የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ስምንት የክስ መዝገቦች አቅርቧል
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በከባድ የሙስና ወንጀል ተሳትፎ በጠረጠራቸውና ከሦስት ወራት በላይ በእስር ላይ ባቆያቸው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ክስ መመሥረቱን፣ ለፍርድ ቤት ቢያሳውቅም፣ ተጠርጣሪዎቹ መከሰሳቸውን የሚያሳይ ክስ እንዳልደረሳቸውና የሕግ ሥርዓትን ያልተከተለ መሆኑን በመግለጽ ክሱን ተቃወሙ፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራውን አጠናቆ ለኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን፣ ጊዜ ቀጠሮውን ሲከታተል ለነበረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት መግለጹ ተዘግቦ ነበር፡፡ በዕለቱ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ መረከቡን ለችሎቱ በማረጋገጥ የክስ መመሥረቻ ጊዜ 15 ቀናት እንዲሰጠው ጠይቆ 13 ቀናት እንደተፈቀደለት ይታወሳል፡፡ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ መመሥረት የነበረበት ነሐሴ 13 ቀን 2005 ዓ.ም ቢሆንም፣ “ከመርማሪ ቡድኑ የደረሰኝ የምርመራ ግኝት ያልተሟላ በመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ 38 ሐ መሠረት አሟልተህና የኦዲት ሪፖርቱንም አካተህ እንድታመጣ፤” ብሎኛል በማለት መርማሪ ቡድኑ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2005 ዓ.ም ለተረኛ ችሎቱ ካሳወቀ በኋላ፣ በዓቃቤ ሕግ የታዘዘውን የምርመራ ሥራ ለማከናወን 14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ተረኛ ችሎቱ “የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ይፈቀድ ወይም አይፈቀድ የሚለውን አከራክሮ ለመወሰን መዝገቡን ወደ ኋላ ሄጄ መመርመር አለብኝ፡፡ ነገር ግን ባለኝ አጭር ጊዜ ውስጥ ልመረምር አልቻልኩም፡፡ በመሆኑም ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ችሎት ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ሥራ ስለሚጀምር አከራክሮ ብይን ይሰጥበታል፡፡ እስከዚያው ድረስ ያለው ጊዜ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ላይ ታሳቢ ይሆናል፤” በማለት ለነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ቀጥሮ ነበር፡፡
ከሰባት ቀናት በኋላ ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም መደበኛ ችሎቱ ተሰይሞ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ቀደም ብሎ በጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ላይ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር አወያይቶ ብይን እንደሚሰጥ ሲጠበቅ፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ችሎት ቀርቦ ጉዳዩን ሲከታተለው ለነበረው ችሎት ክስ መመሥረቱንና በሌላ ችሎት እንደሚታዩ ገለጸ፡፡ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ክስ ከተመሠረተባቸው በዕለቱ ማለትም ነሐሴ 23 ቀን 2005 ዓ.ም ክሱ እንዲነበብላቸውና የደንበኞቻቸው የመብት ጉዳይ እንዲታይላቸው፣ ወይም ያለውን ሁኔታ አውቀውት እንዲሄዱ ጉዳዩን ሲከታተል ለነበረው ችሎት አቤቱታ አቅርበውታል፡፡ ችሎቱ ክሱን አንብቦና ቀጠሮ ሰጥቶ የጊዜ ቀጠሮ ፋይሉን ለመዝጋት እንዲያመቸው የክስ መዝገቡ እንዲቀርብ ጠይቋል፡፡
ክሱ ከሰዓት በኋላ እንደሚቀርብ ለችሎቱ የተነገረ ቢሆንም፣ ሳይቀርብ በመቅረቱ ችሎቱ ስለተጠርጣሪዎቹ ምንም ሳይል ተጠርጣሪዎቹ ባሉበት ቆይተው ለነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲቀርቡ አዟል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች፣ “ደንበኞቻችን መብታቸው ታልፎ ያለምንም ምክንያትና ከሕጉ ሥነ ሥርዓት ውጭ እንዴት ባሉበት ይቆዩ ይባላል፤” በማለት ጥያቄ ሲያነሱ፣ ለነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ቀርበው ክሱ እንደሚነበብላቸው በመግለጽ የዕለቱ ችሎት ሲጠናቀቅ ሁሉም በሁኔታው ግራ በመጋባት ተመልሰዋል፡፡
የጊዜ ቀጠሮ ሲሰጥ የከረመው ችሎት ክስ ተመሥርቶባቸዋል የተባሉትን ተጠርጣሪዎች ለነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ከመቅጠሩና መዝገቡን ከመዘጋቱ በፊት በእነጥጋቡ ግደይ ምርመራ መዝገብ የነበሩት የባለሥልጣኑ ሠራተኞች አቶ ምሳሌ ወልደሥላሴ፣ ንጉሤ ክብረት እንዲሁም በእነ አምባው ሰገድ አብርሃ የምርመራ መዝገብ አቶ ጌታቸው አጐናፍር በነፃ መሰናበታቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ እንዳስታወቀው ገልጿል፡፡ በሌላ የምርመራ መዝገብ ደግሞ በአቶ ምሕረተአብ አብርሃ፣ በአቶ በእግዚአብሄር አለበልና በአቶ ፍፁም ገብረ መድኅን ላይ ምርመራ እንደሚቀረው የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን መግለጹንና የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁንም ችሎቱ አስታውቋል፡፡
አብረው ተጠርጥረው የታሰሩት ጥቂቶቹ በነፃና በዋስ ሲለቀቁ፣ በቀሪዎቹ 45 ተጠርጣሪዎች ላይ ደግሞ ክስ መመሥረቱ ሲነገር፣ በእሳቸው ላይ ቀሪ ምርመራ መኖሩ ተገልጾ 14 ቀናት የተጠየቀባቸው አርክቴክት በእግዚአብሔር ለችሎቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ “እኔ የዶክትሬት ተማሪ ነኝ፤ ደላላ አይደለሁም፡፡ 104 ቀናት ታስሪያለሁ፡፡ በከተማው ውስጥ የሚታዩትን አብዛኞቹን ሕንፃዎች የገነባሁት እኔ ነኝ፡፡ ብዙ ኩባንያዎችንም አቋቁሜያለሁ፡፡ ድርጅቶቼም ተመርምረዋል፡፡ ልማታዊ ነኝ እኔ ምን ልሁን? በዋስ ልውጣና ትምህርቴን ልከታተል፤” በማለት ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ ሌላው በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሲሠሩ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በማከማቸትና በሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው ታስረው የነበሩ አቶ ሙሴ ጋሻው የተጠረጠሩበት የወንጀል ጉዳይ ወደ ኦሮሚያ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተዘዋውሮ እንዲታይ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ነሐሴ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ክስ ተመሥርቶባቸዋል የተባሉት አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዎርጊስን ጨምሮ 45 ተጠርጣሪዎች ችሎት የቀረቡ ቢሆንም፣ ዳኞች ስላልተሟሉ ክሱ ሳይነበብላቸውና ሳይሰጣቸው ቀርቷል፡፡
በአጠቃላይ በ45 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱን የኮሚሽኑ ተወካይ ጽሕፈት ቤት ቀርቦ አስረድቷል፡፡
በጽሕፈት ቤት ተጠርጣሪዎቹን በማስቀረብ ጊዜ ቀጠሮ ብቻ የሰጡት ዳኛ አቶ አቦሃይ ጓዴ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹን ተጠርጣሪዎች ለጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም በመቅጠር እስከዚያው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ አዘዋል፡፡ ሁለት መዝገቦችን ደግሞ ለጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥረዋል፡፡
በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ቁጥር 434 መሠረት በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚካሄደው ምርመራ መጠናቀቅ ሲገባው፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 38ሐን በመጥቀስ ወደ መርማሪ ቡድኑ መመለሱ፣ ተገቢ አለመሆኑን የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ከመግለጻቸውም በተጨማሪ፣ ዓቃቤ ሕግ ክስ ማቅረቡን ከገለጸ ክሱ ተነቦላቸው በመብቶቻቸው ላይ ከተከራከሩ በኋላ ብይን መስጠት ተገቢና የሕጉ አሠራር ቢሆንም፣ በደንበኞቻቸው ላይ የተፈጸመው ግን ያላግባብና ከፕሮሲጀሩ ውጭ በመሆኑ አግባብ አለመሆኑን ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ ጠበቆቹ ክሱ ለደንበኞቻቸው እንዲደርሳቸው ችሎቱን ሲጠይቁ፣ ፍርድ ቤቱ ከኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ጋር ተነጋግሮ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲደርሳቸው እንደሚያደርግ በመግለጽ ችሎቱ አብቅቷል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሠረተባቸው 45 ተጠርጣሪዎች መካከል አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ከተማ ከበደ፣ አቶ ስማቸው ከበደ፣ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፣ ኮሎኔል ሃይማኖት ተስፋዬ፣ አቶ ያዴሳ ሚደቅሳ፣ አቶ እሸቱ ግረፍ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ጥሩነህ በርታ ይገኙበታል፡፡ የኦዲት ምርመራ ያላጠናቀቁ በፖሊስ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ታዟል፡፡
Leave a Reply