እድሜው አርባዎቹን ስለመሻገሩ ገጹ ይናገራል። በተፈጥሮ ያለው እርጋታ አዲስ አበባ ካጋጠመው ትንግርት ጋር ተዳምሮ አፍዞታል። ፊቱን ፈገግ የሚያደርገው ስለ አዲስ አበባ አራዳዎች ሲናገር በቻ ነው። ጨዋታውን የጀመረው በጫማ አሳማሪዎች ነበር። ጫማ አሳማሪዎች ደረጀ ወጥቶላቸዋል። “የታቀፉና ያልታቀፉ” ሁሉንም ገጠመኞቹን ሲያስረዳ “አዲስ አበባ እንደ ወበቅ ነች” ይላል። የወበቅ ጭንቀት የሚለቀው በደንብ ሲዘንብና አየሩን አፍኖ የያዘው ደመና ሲገፈፍ ነው። ወበቅ ለሱ በሽታ ነው።
ነዋሪነቱ አውሮጳ ሲሆን አዲስ አበባ የከረመበት ምክንያት ቤት ቢጤ ስላለው እሱኑ ሸጦ ለአንዴና ላልተወሰነ ጊዜ የሚወዳትን “ወበቃም” ከተማ ለመለየት ነው። ቦሌ ፒኮክ ቁጭ ብለን ስናውጋ ቀድሞ አደራ ያለኝ ፊቱ ማስታወሻ አውጥቼ የሚነግረኝን እንዳልጽፍ ነው። ለወትሮም ቢሆን ስለማላደረርገው ተስማማሁና አወጋን። አዲስ አበባን በቅጡ የሚያውቃት ወዳጄ ስለታቀፉና ሰላልታቀፉ ሊስትሮዎች የሰማውን አንቆረቆረልኝ።
ከፊት ለፊታችን መኪና ውስጥ ተቀምጠው የሚጎነጩትን እግረ መንገዴን እያየሁ ወሬውን ቀዳሁት። ያላስተዋልኩትን ጉዳይ ያወራልኝ ነበርና ገረመኝ። ጫማ አሳማሪዎች /ሊስትሮዎች/ አባል ናቸው። አባልነታቸው የእድር ወይም የስፖርት ማህበር አይደለም – የኢህአዴግ እንጂ!! የታቀፉ አባላት ሲሆኑ፣ ያልታቀፉት ጫማ እየጠረጉም ቢሆን ኢህአዴግ የማያምናቸውና አባሉ እንዲሆኑ ያልበቁ ናቸው። አሁን “ባለ ራዕዩ ሰውዬ ታወሱኝ” በደናቁርት መካከል ራሳቸውን ጠቢብ ያደረጉት “ጠቢብ” – “ … የኢህአዴግን አላማ እስካስፈጸመ ድረስ መሃይምም ቢሆን ሚኒስትር ይሆናል” ነበር ያሉት። ነፍስ ይማር አልኩና ረሳኋቸው። ህልም እልም እንዲሉ!!
ጥያቄው “መታቀፍና አለመታቀፍ” ምን ውጤት አስከተለ? የሚለው በመሆኑ ምላሹን ጠበኩ። የታቀፉና አንደኛ ደረጃ የሚባሉ ሊስትሮዎች ዋና መንገድ ላይ የመቀመጥና ጫማ የመጥረግ ልዩ መብት አላቸው። በዋና መንገድ ላይ ሆነው ይሸቅላሉ። ያልታቀፉ ዋና መንገድ ላይ ሆነው እንዳይሰሩ ይከለከላሉ። ጫማ ለመጥረግና አቧራ አቡንኖ ለመኖርም መድለዎ ይደረጋል። የገዢው ግምባር አባላት የሆኑት የጫማ አስዋቢዎች እንደ አቀማቸው የቤት ስራ የሚሰጣቸው ሲሆን አንዳንዴም “አዲስ አበባ ምን አለ?” ለሚለው የሚተነተን መረጃ ግብአት የሚሆን ተባራሪ ወሬ ይለቅማሉ። ብዙዎቹ ከደቡብ ክልል የመጡ ሲሆኑ “መሪያችን” እያሉ ማውራት ይቀናቸዋል። ቀደም ሲሉ በተሾመ ቶጋ ስም ይምሉ የነበሩ ሊስትሮዎች እንደነበሩ ስለማውቅ ዝርዝር ማብራሪያ ሳልጠይቅ ወደ ሌላው ጉዳይ ገባሁ።
ባህታ ቤተክርስቲያን ከባለቤቱ ጋር ሄዶ ያጋጠመውን እንዲህ አጫወተኝ። ባህታ መግቢያው ላይ ከተቀመጡት የኔ ቢጤዎች መካከል አንዷን እናት ያውቃቸው ነበርና ተጠጋቸው። ያለውን ሊያካፍል “የ50 ብር ዝርዝር አለዎት” ሲል ጠየቃቸው። “ምን አልክ ልጄ? እኛ እንዲህ ያለውን ብር ካየን ቆየን። እንደዚህ አይነቱን የሚቆጥሩት ናቸው እዚህ የጣሉን” አሉና አቀረቀሩ!! ምክንያቱን በውል ባያውቀውም ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ያውቃል። አዲስ አበባ እነዚህን የምጽዋት ደጅ ላይ ጥላ ወደ ላይ ትገነባለች፤ በዚህ የሚኮሩትም “አገር እያለማን ነው” በማለት ከበሮ ምቱ ይላሉ። አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ሰሞኑን ሲጠየቅ “ብዙ ግንዘብ ምን ያደርጋል” ሲል ከኑሮ ወለል በታች የሚንደባለሉ በበዙባት አገር ጥቂቶች ሰማይ መድረሳቸውን ቅድሚያ ሰጥቶ መናገሩ እዚህ ላይ እንዲጠቀስ ወደድኩ።
ነገርን ነገር ካነሳው የኬኒያው ታዋቂ ሯጭ ፖል ቴርጋት አገሩ የመመገቢያ ማዕከልና ትምህርት ቤት ክፍቶ ወገኖቹን መርዳት የጀመረው ገና ብዙ ገንዘብ ሳይቆጥር ነበር። ሃይሌ ገብረስላሴ ይህንን ማዕከል መጎብኘቱን የሚናገረው በኩራት ነው። ግን እሱ ለወገኖቹ ምን አበረከተ ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ የዘመናችን “ታላቁ ሰው” ፈይሳ ሌሊሳ የሰጠው መልስ ይሆናል። ለቪኦኤ ጋቢና ፕሮግራም “ሃይሌና ቀነኒሳ ብር አላቸው፤ ባሸነፉ ቁጥር ከቦሌ እስከ ስታዲየም እያጀበ ያሞገሳቸው ህዝብ ሲያልቅ፣ ሲጨፈጨፍ ዝም ማለታቸው ትክክል አይደለም” ሲል እሱ የዜግነቱን ድርሻ ከመወጣቱ ውጪ የጀግንነት ስሜት እንደማይሰማው በመግለጽ ነበር። የጸዳ ስብእና እንዳለው በሚያስታውቅ መልኩ ስለ አንድነትና ስለ መላው ኢትዮጵያ መዳን የሚናገረው ፈይሳ ሌሊሳ “እርስ በርስ በመባላት ከተለከፈው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘዋሪዎች መርዝ ይጠብቅህ፤ በተለይ ከዳያስፖራው” እያሉ የሚጸለዩለት ጥቂት አይደሉም።
ባህታ የተቀመጡን ደርባባ እናት በሌላ ቀን እንዳገኛቸው የወዳጄ ባለቤት ነግራኛለች። ግን ስንቱን በግል መደጎም ይቻላል? የአዲስ አበባ ወበቅ የሚያጥወለውለውና ደራሽ ዝናብ የሚያስመኘው እዚህ ላይ ነው። ወዳጄ በዚህ አላበቃም ራሱ ከውጭ የተላከ ሰላይ ስለመሆኑ ጥርጥር ውስጥ የጣለኝን መረጃ አሾለከለኝ። “ማታ ማታ ባጃጅ ተጠቅመህ ታውቃለህ” ሲል ጠየቀኝ በአሉታ ጭንቅላቴን አወዛወዝኩ። “ማታ ማታ አዲስ አበባ ዳርቻና ኦሮሚያ ኩታ ገጠም መንደሮችና ሰፈሮች ውስጥ የሚሰሩ ባጃጆች” አለና ድምጹን ቀነስ አድርጎ “ሰላዮች ናቸው” አለ … “ቤቴን ሸጬ ልሄድ ነው እኔ” ብሎ የሞተ ፈገግታ አሳየኝ። በቅጽበት ፊቱ ወየበበኝ። የሚተነፍስ ሬሳ መሰለኝ። አብዛኛው ህዝብ ከኑሮ ወለል ስር ወድቆ የሚተነፍስ ሬሳ መሆኑን አስታወስኩ። ደርግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ውስጥ ሱሪ ገዝተው የማያውቁት እናት ታሪክ ታወሰኝ። በሌላ በኩል ደግሞ ሰው ብርም እያለው መንፈሱ ሲሞት የሚተነፍስ ሬሳ እንደሚመስል ተረዳሁ። “ታሰረው የመኖር መብት የሌላቸውን ወገኖች ያሳዝናሉ። ሰው ሲጠበስ ሸተተኝ። ደም ያልጠገቡ የሰው ስጋ ጥብስ አማራቸው” ሲል ነበር የቂሊንጦን ጉዳይ የገለጸልኝ!! የአዲስ አበባን ወበቅ ንሮ መለኪያውን ሰብሮታል። አሁን የሙቀቱን መጠን የሚያነበው የለምና አብሮ መንፈር ነው … ቀጠለ። ደኅንነቶች!!
እያሳፈሩ ሰዉን ይጠቡታል። እንዳስፈላጊነቱ እነሱ እንዳደረሱት ከኋላ ታጣቂ ይልኩበታል። ቀን ቀን ሰዉ በቀላሉ ሰለሚለያቸው በባጃጅ አይሰልሉም። እስካሁን ከነሱ ጋር የተጣበቁት ዞሮ መግቢያቸውን ራሳቸው የዘጉ ካልሆኑ በስተቀር ዋናዎቹ ቁመናቸውና ገጻቸው ለስራው ባህሪ አይሆንም። እንደ ወዳጄ ገለጻ ኑሮ ቀኑንን ሙሉ ሲያሳድደው የሚውለውን ያልሞላለትን ህዝብ ይከታተሉታል። የዋጣቸው ፍርሃት ሰላም ስለነሳቸው ሁሉም እንደ እነሱ ሰላም ያጣ ይመስላቸዋል። ኑሮ ያመነዠገውን ህዝብ በስለላ ወጥረው ከኑሮ ጥርስ የተረፈውን ስነልቦናውን ያነከቱታል። ለዚህ ይመስላል አዲስ አበቤ መተማመን ተስኖታል።
ጨዋታው የገባቸው የአዲስ አበባ አራዶች፣ ፈገግታ አክለው የልባቸውን ይናገራሉ። “አካፍሉና፣ የት ትበሉታላችሁ? ያው መመለሳችሁ አይቀርም … ለማንኛውም አንዱን ቪላ በእናቴ ስም አድርገው” እያሉ ይፈትላሉ። ያላቸውን ንብረት እንደ ዋናው ተቆጣጣሪ ለክተውና መዝግበው የያዙት ይመስላሉ። ማን የትና ስንት አይነት ንብረት እንዳለው ያውቃሉ። አራዳ የሚያውቀው ሁሉ ህዝብ ያወቀው ነው። ይህ ሰው የሚያወራው መዓት ነው።
አዲስ አበባ የሚገነባው ቤት፣ የሚወጠነው ህንጻ፣ የሚፈሱት መኪኖች ይገርማሉ። ግን የውስን ሰዎች ናቸው። ለባለስልጣናት ሴት የሚያቀረቡና የሚቀረቡትም ያሽከረከራሉ። በማንነት ቀውስ እየዞረባቸው መኪና ሲያዞሩ የደላቸው ይመስላሉ። የጎልጉል ዘጋቢ የራሱም ትዝብቶች አሉት። አዎ!! አለመጣጣም ገዝፎ ወጥቷል። በየክልሉ የሚፈጸመው ግፍ መጠራቀሚያ ባህሩ አዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ መንፈሯ የሚደበቅ አይደለም። በሁሉም አቅጣጫ ወበቅ ነው። በወቀብ ላይ መስቀል አደባባይ ሰሞኑን ይደመራል። (የፊትለፊት ፎቶ:
)ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Cccc says
ደናቁርት