የዛሬው ጽሑፌ መነሻውና መድረሻው በዚህ ሳምንት አነጋጋሪ ስለነበረው የኡጋንዳ የፀረ ግብረ ሰዶም ሕግና አገራችን በንፅፅር የምትወስደውን ልምድ መቃኘት ነው፡፡
ኡጋንዳ ይህንን ሕግ በማውጣቷ ዓለም ተደንቋል፡፡ አፍሪካን ግን የሚደንቅ አይደለም፡፡ አገራችንንማ ሕጓን እንድታጠነክር ካልሆነ ግብረ ሰዶማዊነትን የሚታገስ ባህልም ሕግም ኖሯት አያውቅም፡፡ ዜናው እጅጉን የሳበው ምዕራባውያንን ነው፡፡ ኡጋንዳ እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች በአንድ ወቅት ቅኝ ገዥ ስለነበራት የድሮው አስተሳሰብ የተፀናወታቸው ወገኖች ተቃውሞውን አድምቀውት ሰንብተዋል፡፡ አገራችን በማንም ቅኝ ተገዝታ ባለማወቋ፣ ባህሏ የራሷ በመሆኑ ተቃዋሚዎች የመተቸቱን ሞራል የኡጋንዳን ያህል አያገኙትም፡፡ ከዓለም ጋር አንድ በሚያደርገን በተባበሩት መንግሥታትም ቢሆን አንድ የሆነ አቋም ባለመኖሩ፤ ቢኖርም በተዓቅቦ (Reservation) ስለምናልፈው አስቸጋሪነቱ ቅርብ አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉባዔ በተደጋጋሚ የሰዎቹን መብት በሕግ ዕውቅና እንድትሰጥ አገራችንን ቢጠይቋትም የማይሸረሸር የተቃውሞ አቋሟን አንፀባርቃለች፡፡
ፌብሩዋሪ 25 ቀን 2014 ከምሽቱ 5፡30 የቢቢሲ ጋዜጠኛዋ የኡጋንዳ ሕግ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረውን አሜሪካዊ ስለሕጉ ስታናግረው ያደመጠ የምዕራባውያኑ አካሄድ ሳይደንቀው አይቀርም፡፡ ጋዜጠኛዋ ሰዎቹ መብት የላቸውም? አንተ ጠርዝ የያዝክ አይመስልህም? አሜሪካዊ ሆነህ ሕጉን መደገፍህ አያሳፍርህም? እያለች ሰውዬውን ዝቅ ለማድረግ ብዙ ጥራለች፡፡ የፊቷ ሁኔታ እጅጉን የተቆጣ፣ ርስቱን ያጣ የአገሬ ገበሬ እንደሚናደደው ዓይነት ሆናለች፡፡ ሰውዬው በዝግታ ግብረ ሰዶም ኃጢአት ነው፡፡ ለጤና ጠንቅ ነው፡፡ ከአፍሪካዊ ባህል ጋር ይጋጫል ወዘተ እያለ ግልጹንና እውነታውን ነገራት። የኡጋንዳ ሕግ እንዲፀድቅ ሲሞግቱ የነበሩ ወገኖች ሕጉ ሲፀድቅ የኡጋንዳ ዕርዳታ ይቀንስ፣ ሕጉ ከሰብዓዊ መብት ጋር ይጋጫል፣ ኡጋንዳን ዘመናዊ እንዳትሆን ያደርጋታል በሚል ከጉዳዩ ጋር የማይያያዝና የማያሳምን አቋም ሲያንፀባርቁ ይስተዋላል፡፡ ይህ የምዕራባውያን አቋም የገረመው አንድ ምሁር “If we truly believe that Africans are human, we should also be able to understand that they can make their own decisions” በሚል ገልጾታል፡፡ ‹‹አፍሪካውያን ሰዎች መሆናቸውን ካመንን የራሳቸውን ውሳኔ እንደሚሰጡም ልንገነዘባቸው ይገባል፤›› እንደማለት ነው፡፡
የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የፀረ ግብረ ሰዶማዊ ሕጉን በፊርማቸው ሲያፀድቁ ግብረ ሰዶማውያኑን ‹ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ›፣ ‹አፀያፊ› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሕጉን በማፅደቅ ሒደት ምዕራባውያን በኡጋንዳ ጉዳይ በግልጽ ጣልቃ ለመግባት መሞከራቸውን በመግለጽ ‹‹አፍሪካውያን በሌሎች ላይ የራሳችንን አመለካከት አንጭንም›› በማለት የምዕራባውያኑ ድርጊት ‹ማኅበራዊ ኤምፔሪያሊዝም› መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዓለም ካሉ አገሮች አብዛኞቹ አገሮች የግብረ ሰዶማውያኑን ድርጊት የሚያወግዝና የሚቀጣ ሕግ ያላቸው ሲሆን፣ የአፍሪካ አገሮች የግብረ ሰዶማውያኑን ድርጊት ከሚቃወሙት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በቅርቡ እንኳን ከኡጋንዳ በፊት ናይጄሪያ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕግ በማውጣት ጋብቻ በተቃራኒ ጾታ ብቻ ካልተፈጸመ ሕገ ወጥ እንደሆነ፣ በግብረ ሰዶማዊነት በአንድም በሌላ የተሳተፈ፣ የተሰበሰበ እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ደንግጋለች፡፡ የአገራችን ሕግጋትም በተመሳሳይ መልኩ ግብረ ሰዶማዊነትን ወንጀል ያደረጉ ሲሆን፣ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ97 በመቶ በላይ ሕዝቡ ግብረ ሰዶማዊነት ጠንከር ባለ ሕግ ሕገወጥነቱ ሊደነገግ እንደሚገባ ያምናል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የሁሉም ቤተ እምነቶች ባደረጉት ስብሰባ ግብረ ሰዶማዊነት በአገሪቱ እንዳይስፋፋ በአንድነት እየሠሩ መሆናቸውንና እስከ ሞት ቅጣት በሚደርስ ቅጣት በወንጀል ሕጉ እንዲካተት መወትወታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ያም ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ግብረ ሰዶማዊነት በተለይ በአዲስ አበባ በአስደንጋጭ ፍጥነት በመስፋፋት ላይ ነው፡፡ ግብረ ሰዶማውያኑ ‹‹ሬንቦ›› የተባለ ማኅበር ማቋቋማቸው፣ ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ተማሪዎች ሳይቀሩ የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው፣ ዓለም አቀፍ የሕፃናት ዕርዳታ ድርጅቶች እንዳረጋገጡት በአዲስ አበባ ከሚፈጸሙት የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መካከል 22 በመቶ የሚደርሱት የተፈጸሙት በወንድ ላይ መሆኑ፣ ግብረ ሰዶማውያኑ በከተማይቱ የተለያዩ ቦታዎች እንደሚቃጠሩ ወዘተ በየመገናኛ ብዙኃኑ ተዘግቦ አንብበነዋል፡፡ የአገራችን ሕግ ድርጊቱን ከልካይ ቢሆንም ተግባራዊ አፈጻጸሙ የላላ በመሆኑ የኅብረተሰቡን ሞራላዊ አስተሳሰብ ለማስጠበቅ ጥቅም ላይ ሊውል አልቻለም፡፡ ከኡጋንዳ ሕግ አንፃር ከተመለከትነውም የአገራችን ሕግ ግልጽ፣ ዝርዝርና ምሉዕ ድንጋጌዎች አሉት ለማለት አያስደፍርም፡፡ በዚህ ጽሑፍ የኡጋንዳ ሕግን መነሻ በማድረግ የአገራችን ሕግ ያለበትን ክፍተት ለማሳየት ሙከራ እናደርጋለን፡፡
የኡጋንዳ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕግ
የሕጉ ረቂቅ ለመጀመርያ ጊዜ የቀረበው እ.ኤ.አ. መስከረም 25 ቀን 2009 ሲሆን፣ ባሃቲ የተባሉ የፓርላማ አባል ሕጉ እንዲቀረፅ ውትወታ በማድረግ ቀዳሚው ሰው ናቸው፡፡ በ1950 የወጣው የኡጋንዳ የወንጀል ሕግ ግብረ ሰዶማዊነት ወንጀል መሆኑን የሚደነግግ አንቀጽ አለው፡፡ የሕጉ ምዕራፍ 120 አንቀጽ 145 ከተፈጥሮ ውጭ የሚደረግ የወሲብ ግንኙነት ወንጀል መሆኑን በመደንገግ፣ በዕድሜ ልክ እስራት እንደሚያስቀጣ ገልጿል፡፡ ይህ ድንጋጌ ግብረ ሰዶምን ለመከልከል ያለመ ቢሆንም ግልጽነት የሚጐድለውና ዝርዝር ባለመሆኑ ለመፈጸም አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡ በ2009 የተረቀቀው ሕግ ግን አንድ ደረጃ አሳድጐታል፡፡ ሕጉ በዚህ ሰሞን ፀድቋል፡፡
የሕጉ አስፈላጊነት በመግቢያው ላይ በግልጽ ሠፍሯል፡፡ የሕጉ ዓላማ የኡጋንዳ ሕዝብን ባህል፣ ሕጋዊ፣ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ የቤተሰብ ዋጋን መጠበቅና ያልተገባ ወሲብ ነክ ባህልን በአገሪቱ ላይ የሚጭኑ አካላትን ተፅዕኖ ማስቀረት ነው፡፡ ሕጉ የግብረ ሰዶም ወንጀልን ግልጽ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ከተመሳሳይ ጾታ ጋር የወሲብ ግንኙነት መፈጸም ብቻ ሳይሆን ግብረ ሰዶምን ለመፈጸም በማሰብ መነካካትን ሳይቀር ወንጀል አድርጐታል፡፡ ግብረ ሰዶምን መፈጸም በዕድሜ ልክ እስራት ያስቀጣል፡፡ ወንጀሉን ለመፈጸም መሞከርም ከባድ ወንጀል ሲሆን ሰባት ዓመታት ያስቀጣል፡፡ ምዕራባውያኑን እጀጉን ያስቆጣው የሕጉ አንቀጽ 3(2) ሲሆን፣ የግብረሰዶም ወንጀልን የሚያከብዱ ሁኔታዎች ካሉ እስከሞት ቅጣት ድረስ እንደሚያስቀጣ መደንገጉ ነው፡፡ የሞት ቅጣቱ ከመጨረሻው የሕጉ ረቂቅ ላይ ወጥቷል፡፡
የግብረ ሰዶም ወንጀልን የሚያከብዱ የሚባሉት ሁኔታዎች ሰባት ናቸው፡፡ ወንጀሉ ሕፃናት ላይ ሲፈጸም፣ ፈጻሚው ኤችአይቪ ኤድስ በደሙ ውስጥ ካለ፣ ፈጻሚው የተጐጅው ወላጅ ወይም ሞግዚት ከሆነ፣ ወይም ሌላ በሕግ ወይም በውል በልጅ ላይ ሥልጣን ካለው፣ ተጐጅው አካል ጉዳተኛ ከሆነ፣ ፈጻሚው ከፍተኛ ኃይል በመጠቀም ወንጀሉን ከፈጸመው እንዲሁም ቀደም ሲል በተመሳሳይ ድርጊት ፍርድ ካለበት ወንጀሉ የሚከብድ ይሆናል፡፡ በከባድ የግብረ ሰዶም ወንጀል የተከሰሰ ሰው የኤችአይቪ ምርመራ እንዲያደርግ ይገደዳል፡፡ ከባድ የግብረ ሰዶም ወንጀል የሞከረም በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል፡፡ በወንጀሉ ተጐጅ የሆነ ሰው ሚስጥራዊነቱ ይጠበቃል፣ የመሰማት መብት አለው፣ የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲሁም የካሳ ክፍያ የሚያገኝበት ድንጋጌም ተቀርጿል፡፡
ሕጉ ድርጊቱን ያወቀ ሰው ለሚመለከተው አካል በ24 ሰዓት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርግ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ሪፖርት ካላደረገ እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ በድሮው የኡጋንዳ ሕግ ያልነበረ አዲስ የሕጉ ጭማሪ ግብረ ሰዶማዊነትን ስለማስተዋወቅና ማስፋፋት የተደነገገው ክፍል ነው፡፡ ማንም ሰው ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያሳይ ነገር (Material) ያመረተ፣ የሸጠ፣ የገዛ፣ በሚዲያ ያስተላለፈ፣ ያስፋፋ፣ ያተመ ወይም ግብረ ሰዶማዊነትን በገንዘብ ወይም በሐሳብ የረዳ ወይም የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረቱን ለድርጊቱ ማስፋፊያ ያዋለ፣ ግብረ ሰዶማዊነትን ለማሳየት ኢንተርኔትን፣ ፊልምና የሞባይል ስልክን የተጠቀመ ሁሉ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል፣ የገንዘብ ቅጣትም አለው፡፡
የአገራችን ሕግ ምን ይላል?
በ1997 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣው የወንጀል ሕግ ቀደም ሲል ከወጡት ሕጐችና የተጻፉ የአገራችን ሕጐች ታሪካዊ ምንጭ ከሆነው ከፍትሐ ነገሥት ጋር ተመሳሳይ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ በእርግጥ ፍትሐ ነገሥት ግብረ ሰዶምን የተመለከተ ግልጽ ድንጋጌ አልያዘም፡፡ ሆኖም ግብረ ሰዶምን የሚያወግዙ መሠረተ ሐሳቦችን አካትቷል፡፡ ጋብቻ በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መካከል ሊደረግ እንደሚገባና የጋብቻ ዋና ዓላማ ዘርን መተካት (Procreation) መሆኑን በአግባቡ ስለሚደነግግ ግብረ ሰዶም ቦታ የለውም፡፡ ፍትሐ ነገሥት እንኳን ግብረ ሰዶምን በተቃራኒ ጾታ መካከል ሊኖሩ ከሚችሉ ግንኙነቶች ቅምጥን ይከለከላል፡፡ ተቃራኒ ጾታ ጋር የሚመሠረት ግንኙነት ቢሆንም አራተኛ (ሦስት ጊዜ ፈትቶ አራተኛ) ማግባትንም ይከለክላል፡፡ ይህ ጠለቅ ያለ የሞራል ጥንቃቄ (Moral concern) ለግብረ ሰዶም ክልከላ ትክክለኛ መሠረት ነው፡፡ የ1949 የወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን ግን ከፍትሐ ነገሥት በተሻለ በግልጽ በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም መሰል ድርጊትን ወንጀል በማድረግ በአንቀጽ 600 ላይ ደንግጓል፡፡ መነሻው ለዘመናት የቆየ የኢትዮጵያውያን መልካም ባህልና የሞራል አስተሳሰብ መሆኑ አስረጂ አይፈልግም፡፡
በአሁኑ ወቅት ተፈጻሚነት ያለው የወንጀል ሕጋችንም በግብረ ሰዶም ላይ የፀና አቋም ይዟል፡፡ “ለተፈጥሮ ባህርይ ተቃራኒ የሆኑ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች” በሚል ርዕስ ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን አካቷል፡፡ ሕጉ “ግብረ ሰዶም” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስያሜ ከመጠቀም ባለፈ ግብረ ሰዶምንና ለንፅህና ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች በተመሳሳይ ጾታ ከተፈጸመ በወንጀል እንደሚያስቀጣ ደንግጓል፡፡ አንቀጽ 629 እንዲህ ይላል፡፡
“ማንም ሰው ከእርሱ ጋር አንድ ዓይነት ጾታ ካለው ከሌላ ሰው ጋር ግብረ ሰዶም ወይም ለንፅህና ክብር ወይም ለመልካም ፀባይ ተቃራኒ የሆነውን ሌላ ድርጊት የፈጸመ እንደሆነ በቀላል እስራት ይቀጣል፡፡”
የግብረ ሰዶም ወንጀል የሌላውን ሰው የገንዘብ ችግር ወይም የህሊና ሐዘን ወይም የዚህ ሰው አሳዳሪ፣ ሞግዚት፣ ጠባቂ፣ አስተማሪ፣ አሠሪ፣ ወይም ቀጣሪ በመሆኑ ያገኘውን ኃላፊነት፣ ሥልጣን፣ ወይም ችሎታ ያለአግባብ በመጠቀም ተፈጽሞ ከተገኘ ቅጣቱ ይከብዳል፡፡ እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ያስቀጣል፡፡ በተለይ ድርጊቱ የተፈጸመው በኃይል፣ በዛቻ፣ በማስገደድ፣ በተንኮል፣ በማታለል ከሆነ፣ ተበዳዩ/ዋ ከተሰቃየች ወይም እንዳለበት የሚያውቀውን የአባላዘር በሽታ ያስተላለፈበት (ያስተላለፈባት) እንደሆነ ወይም ተጐጂው/ዋ ከጭንቀት፣ ከኃፍረት ወይም ከተስፋ መቁረጥ የተነሳ ራሱን የገደለ እንደሆነ ቅጣቱ ከሦስት ዓመት እስከ 15 ዓመት ጽኑ እሥራት ሊደርስ ይችላል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው አካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ከሆነ ደግሞ እንደ ዕድሜያቸው ሁኔታ እስከ 20 ዓመት ጽኑ እሥራት ያስቀጣል፡፡
ከዚህ በላይ ከተገለጸው የወንጀል ሕጋችን ድንጋጌ የተወሰኑ መሠረታዊ ነጥቦችን መገንዘብ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ግብረ ሰዶም በወንድ (Homosexuals) ወይም በሴት (Lesbians) ቢፈጸም ወንጀል ሆኖ ያስቀጣል፡፡ በአንዳንድ አገሮች የወንዶች ተከልክሎ የሴቶች ግብረ ሰዶማዊነት በዝምታ የሚታለፍበት ሁኔታ በመኖሩ የእኛ አገር የሕግ ሽፋን በዚህ ረገድ ክፍተት የለበትም፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 631(2) “አንዲት ሴት ለአካለ መጠን ባልደረሰች ልጅ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት የፈጸመች እንደሆነ ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ትቀጣለች፤” በማለት በግልጽ ከመደንገጉ ባለፈ ሁሉም ድንጋጌዎች በሁለቱም የጾታ አንቀጽ መቀረፃቸው ይህን ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው በእኛ ሕግ ግብረ ሰዶም በግል (In private) ሆነ በአደባባይ (In public) ቢፈጸም ወንጀልነቱን አይለቅም፡፡ በሌሎች አገሮች በግል የሚፈጸም ግብረ ሰዶም ወንጀል የማይሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡ በእነዚህ አገሮች ሕግ የግለሰቦችን የግል ሁኔታ (Private Thoughts & Action) ዘልቆ መግባት የለበትም ከሚል መነሻ ግብረ ሰዶማዊነት በግል ሲፈጸም የማይቀጡበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሦስተኛው በእኛ ሕግ ግብረ ሰዶም በፈቃድም (Consensual) ሆነ በማስገደድ (Triad) ቢፈጸም ወንጀል ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች በማስገደድ ብቻ ወንጀል መሆኑን የሚደነግጉበት ሁኔታ አለ፡፡
ከላይ የጠቀስነው የሕጉ አንቀጽ 628 በጠቅላላ አነጋገር መግለጹ ወንጅሉን በፈቃድ ለፈጸሙ ሰዎች መከራከሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ በወንጀል ሕግ አስተምህሮ የተጐጅ ፈቃድ ለአጥፊው መከላከያ የሚሆነው በሕጉ በግልጽ ከተቀመጠ ወይም ወንጀሉ በፈቃድ ከተፈጸመ ወንጀልነቱን የሚያስቀር ክፍል ካለው ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በተቃራኒ ጾታ መካከል በፈቃድ የተፈጸመ የግብረ ሥጋ ግንኙነት “የተጐጅው” ፈቃድ የመደፈር ወንጀል ተጠርጣሪ መከላከያው ነው፡፡ አራተኛው ግብረ ሰዶምን ወንጀል ያደረገው ሕጋችን አመክንዮ ተፈጥሮ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ወንጀሉ የተደነገገበት ክፍል ርዕስ “ለተፈጥሮ ባህርይ ተቃራኒ የሆኑ የግብረ ሥጋ ግንኙነቶች”ን የሚመለከት በመሆኑ ክልከላው መሠረት የሚያደርገው ተፈጥሮን ስለመሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ሰው በተፈጥሮው ወንድና ሴት ሆኖ በመፈጠሩ ግብረ ሥጋ ግንኙነትም ከዚህ ውጭ ባለ ግንኙነት ከተፈጸመ ተፈጥሮአዊ አይሆንም፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሕግ ይደግፈናል ለሚሉ አንዳንድ አስተሳሰቦች ክፍተት ይዘጋል፡፡ የሰው ተፈጥሮ መቼም ስለማይቀየር ለወደፊቱም የወንጀል ሕጉ ቢሻሻል በግብረ ሰዶም ላይ የተያዘው አቋም ሊቀየር አይችልም፡፡
ንፅፅራዊ ምልከታ
የኡጋንዳና የኢትዮጵያን የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕግ ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፡፡ ሁለቱም ሕግጋት ግብረ ሰዶማዊነትን በሁሉም ዓይነት ቅርፅ ወንጀል ማድረጋቸው፣ ወንጀል ለማድረግ መነሻቸው ድርጊቱ ከተፈጥሮ ጋር መቃረኑ፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን የተሻለ የሚጠብቅ ወንጀሉን የሚያከብዱ ሁኔታዎችን መደንገጋቸው፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ዕውቅና መንፈጋቸው ወዘተ አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ ሕግጋቱን የሚያለያያቸውም ነጥቦች አሉ፡፡ የልዩነቱ ምንጮች በዋናነት (በአጠቃላይ) በሁለት ሊከፈል ይችላል፡፡ የመጀመርያው ኡጋንዳ የፀረ ግብረ ሰዶማዊነት ሕግን በልዩ ሕግ መደንገጓ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን የወንጀል ሕግ አካል ማድረጓ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የኡጋንዳ ሕግ ተግባራዊ ተሞክሮን መነሻ ያደረገ፣ ግብረ ሰዶማዊነትን በዘርፈ ብዙ መንገዶች ለመዋጋት ያለመ፣ እንዲሁም በጊዜ ደረጃ ቅርብ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ልዩ ሕግ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ግብረ ሰዶምን ወንጀለኛን ከመቅጣት ውጭ ድርጊቱን በተለያዩ መንገዶች ለመዋጋት የወጣ አይመስልም፤ ሕጉ በወጣበት ወቅትም (ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት) የአሁን ያህል ተግባራዊ ተሞክሮ በስፋት ባልነበረበት ወቅት በመሆኑ ምናባዊ መነሻው ከተግባራዊ መነሻው ያመዝናል፡፡
የኡጋንዳ ሕግ ልዩ ሕግ ከመሆኑ ጋር የሚነሱ ተያያዥ ነጥቦችን እናንሳ፡፡ የመጀመርያው ሕጉ የራሱ መግቢያ (Preamble) አለው፣ ይህም የሕጉን ዓላማ በግልጽ ለመገንዘብና ትርጉም ባስፈለገ ጊዜም የሕግ አውጭውን ሐሳብ ለመረዳት ይጠቅማል፡፡ የሕጉ መግቢያ በግልጽ እንደሚያስቀምጠው የሕጉ ዓላማ የኡጋንዳን ትውፊታዊ ቤተሰብ መጠበቅ ነው፡፡ የቤተሰብን ዋጋ የሚሸረሽር ውስጣዊና ውጫዊ ሥጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል አገራዊ ብቃት ማጠናከር፣ ተፈጥሮአዊ ያልሆነውን ግብረ ሰዶም ምሉዕ በሆነ የሕግ ማዕቀፍ በማስወገድ የኅብረተሰቡን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዋጋ ማስቀጠል፣ እንዲሁም የኡጋንዳን ሕፃናትና ወጣቶች ከወሲባዊ ጥቃት፣ ወጣ ካለ ያልተገባ ባህሪ፣ ያለ ቅድሚያ ምርመራ ከሚለቀቁ የቴክኖሎጂ መረጃዎች ለመጠበቅ መሆኑ በሕጉ መግቢያ ተቀምጧል፡፡ ሁለተኛው ነጥብ ግብረ ሰዶም ያመጣቸውን የጽንሰ ሐሳብ ትርጓሜዎች በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ይህ ሁሉንም የግብረ ሰዶም ዓይነቶችና የመፈጸሚያ መንገዶች ለመከልከል የሚረዳ ሲሆን፣ ሌሎች ሕግጋትን ለመጠቀም መብት እንዳላቸው እንዲያስቡ ለማድረግ (ዝግ ለማድረግ) ጠቃሚ ነው፡፡ ለአብነት የሕጉን አንቀጽ 18(2) ብንመለከት “Definitions of sexual orientation” “sexual rights “sexual minorities” “gender identity” shall not be used in any way to legitimatize homosexuality, gender identity disorders and related practices in Uganda” በማለት ግብረ ሰዶማውያን ድርጊታቸው የጾታ፣ የአመለካከት መብት፣ የጾታ ልዩነት፣ የወሲባዊ መብት መሆኑን በመግለጽ መከራከሪያ እንዳያደርጉ ሕጉ ዘግቶታል፡፡ ሌላው ሕጉ በተለየ አዋጅ መውጣቱ የበለጠ ዘርዘር እንዲል፣ ሥልጣን ያለውን ፍርድ ቤት በግልጽ ለማመልከት በአፈጻጸም የሚያጋጥሙትንም ችግሮች በደንብ (Regulation) የበለጠ ለማውጣት የሚያሻሽሉ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡
ሁለተኛው የልዩነት ምንጭ የኡጋንዳ ሕግ የግብረ ሰዶማውያንን ተግባራዊ ሁኔታ መነሻ በማድረግ የወጣ በመሆኑ ድርጊቱን ለመዋጋት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ደንግጓል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ እንሞክር፡፡
የመጀመሪያው የኡጋንዳ ሕግ ወንጀሉን ትርጉም ከመስጠትና ወንጀል ከማድረግ በተጨማሪ ወንጀሉን የማስፋፋትና የማስተዋወቅ ድርጊቶችን በመከልከል ወንጀል አድርጓል፡፡ የሕጉ አንቀጽ 13 ግብረ ሰዶማዊነትን በሚዲያ፣ በገንዘብ፣ ቤት በማከራየት፣ በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘዴዎች የመቀስቀስና የማስፋፋት ድርጊትን ሰባት ዓመት የሚደርስ ቅጣት በማስቀመጥ ከልክሏል፡፡ ይህ ወንጀሉ ወደተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳይደርስ የመከላከል ተልዕኮ ይኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ግብረ ሰዶም ማስፋፋትን በተለየ የሚገዛ ድንጋጌ የለውም፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም የሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት (ዝሙት አዳሪነት) የሚታይና ቀለል ባለ ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑ አይቀርም፡፡
ሁለተኛው ለግብረ ሰዶም የተቀመጠው ቅጣት በኡጋንዳ ሕግ ጠንካራ መሆኑ ላይ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ድንጋጌዎች ወንጀሉን ከሰባት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጡ ሆነው ተደንግገዋል፡፡ የአገራችን ሕግ ከፍተኛው ቅጣት 20 ዓመት ጽኑ እስራት መሆኑ በአንፃራዊነት ቅጣቱ ቀላል እንዲሆን አድርጐታል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት በኅብረት ያዘጋጁትን ጉባዔ ለተከታተለ ግን የወንጀሉን ቅጣት ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ኅብረተሰባዊ ምክንያት መኖሩን ይገምታል፡፡
ሦስተኛው ልዩነት የኡጋንዳ ሕግ ግብረ ሰዶማዊነት ተፈጽሞ ሲገኝ ሪፖርት እንዲደረግ ሪፖርት ያላደረገ ሰው ደግሞ ቅጣት እንደሚጠብቀው ደንግጓል፡፡ ሪፖርት የማድረግ ግዴታው በፈጻሚው ወይም በተጐጅው ላይ ሥልጣን ያለው ሰው (አሳዳጊ፣ ሞግዚት፣ ጠባቂ፣ አስተማሪ፣ አሠሪ ወይም ቀጣሪ) ላይ የተጣለ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ዋና ዓላማው በኅብረተሰቡ ውስጥ በኅቡዕ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ለመለየትና ለመቅጣት የሚያስችል በመሆኑ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡
አራተኛው ልዩነት የኡጋንዳ ሕግ የግብረ ሰዶም ወንጀል ሰለባ (ተጐጅ) ለሆነ ሰው የተለያየ ጥበቃ ማድረጉ ነው፡፡ ተጐጅው ማንነቱ አይገለጽም፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ በዝግ ችሎት ይታይለታል፣ እርሱ የመሰማት መብት አለው፣ ለደረሰበት የሥነ ልቦና፣ የአካልና የወሲብ ጉዳት ተመጣጣኝ ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ ይህ ድንጋጌ ተጐጅዎች ፍትሕ እንዲያገኙ፣ በሥነ ልቦና ታንፀው ጥሩ ዜጐች እንዲሆኑ የሚያስችል በመሆኑ አገራችንም ልትማርበት የምትችለው ድንጋጌ ነው፡፡
ሕጉን መከለስ ያስፈልግ ይሆን?
ሕግ በባህርይው ኅብረተሰብን የሚመራ፣ ካልሆነም ኅብረተሰብን የሚከተል ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለን ችግር ከራሱ ከኅብረተሰቡ በሚቀርብ መፍትሔ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ማስቻል በብዛት ተቀባይነት ያለው የሕግ አስተምህሮ ነው፡፡ ይህ ባህርይው ሕግ ለለውጥ የተመቻቸ (Flexible) እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ከግብረ ሰዶም አንፃር የአገራችን የወንጀል ሕግ ሲወጣ ችግሩ ሰፍቶ፣ ያስከተለው አሉታዊ ተፅዕኖ ገዝፎ የሚነገርበት አልነበረም፡፡ አልፎ አልፎ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን በሚስጥር የፍርድ ቤት መፍትሔ ይሰጥባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን እንደ ትናንት አይደለም፡፡ የግብረ ሰዶማውያን ቁጥር እየበዛ በሮችን እያንኳኳ እንደሚገኝ መገናኛ ብዙኃን ይዘግባሉ፡፡ የሕክምና ተቋማት የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ዜጐችን ማከም ቀጥለዋል፡፡ ግብረ ሰዶማውያኑ በድብቅ ማኅበር አቋቁመው፣ በአደባባይ ሲቀጣጠሩ መስተዋል ጀምሯል፡፡ መምህራን በተማሪዎቻቸው ላይ ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረው መቅረባቸውን ታዝበናል፡፡ ዳንኤል ክብረት የተባሉ የማኅበራዊ ጉዳይ ብሎገር በአዲስ አበባ ይፋ ያልሆነ ጥናትን መሠረት አድርገው በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች በሚማሩ 2,000 ተማሪዎች በተደረገ ጥናት 48 በመቶ የግብረ ሰዶማውያን ደጋፊ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአንድ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሴቶች የመኝታ ክፍል ውስጥ ከ130 በላይ የተለያዩ የሰው ሠራሽ የወሲብ መሣሪያዎች መገኘታቸውን ሰምተናል፡፡ ሌላም ብዙ ብዙ መረጃዎችን ማግኘት መስጠትም ይቻላል፡፡
ሁሉም የሚያሳየው ግን ችግሩ ሥር እየሰደደና ካልተቆጠጣርነው ትውልድን ብሎም አገርን የሚጐዳ መሆኑን ነው፡፡ የሁሉም ቤተ እምነቶችን ያስማማ ሀቅ በመሆኑ ሁሉም በአደባባይ ተወያይቶበታል፡፡ ከሕግ አንፃር ሊኖር የሚችለው ክፍተት ሁለት ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ጥንካሬ አንሶአቸዋል ወይም ያለውን ሕግ ለመፈጸም የማያስችሉ ክፍተቶች አሉ፡፡ የትኛው ክፍተት ሰፊ መሆኑን ማወቅ የሚቻለው ጥናት ከተደረገ ብቻ ነው፡፡ ችግሩ ሕጉ ካለመጠንከሩ ጋር ከሆነ የኡጋንዳ ተሞክሮ ጥሩ በመሆኑ ልምድ ወስዶ ጠንካራ ሕግ በማውጣት የአገራችንን ሕግ መከለስ ይጠበቅብን ይሆናል፡፡ ሕጉ ይከለስ ከተባለ ደግሞ ሥጋት ወይም እንቅፋት የሚሆኑ ተግዳሮቶች አይጠፉም፡፡ የግብረ ሰዶማውያኑ መብት አቀንቃኝ ምዕራባውያን ሕጉ ከሰብዓዊ መብት ጋር ይጋጫል፣ የምንሰጣችሁን ዕርዳታ እናቆማለን ወዘተ ሊሉ ይችላሉ፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ እንደ ኡጋንዳ ዓይነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ ነው፡፡ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን ለመጨረስ እንችል ዘንድ ፍቀዱልን በማለት ለውትወታቸው ጆሮአችንን ልንዘጋ ይገባል፡፡ እንዲህ ማድረግ መንግሥትን ሕዝባዊ ያደርገዋል፡፡ ቅኝ ተገዝቶ ለማያውቅ አገር ደግሞ ይህ የመከራከሪያ መስመር የሚከብድ አይሆንም፡፡ የሙሴቬኒ ቁርጠኝነት ሕጉን ካፀደቁ በኋላም ቀጥሏል፡፡ ጋዜጠኞች ሕጉ ከሰብዓዊ ሰነዶች ጋር አይጋጭምን ብለው ለጠየቋቸው ጥያቄ አለመጋጨቱን ከመግለጽ ባለፈ “Any law that appears to impose homosexuality on Ugandans could be changed-quipping that the constitution was made by “us” and not God; any document can be changed if it affects the existence of Ugandans and their cultural norms. Our existence is more important than (any) document” በማለት ከምዕራባውያን የሰብዓዊ መብት ትርጉም ጋር ቢጋጭ እንኳን ከሕዝብ ሞራልና ባህል ጋር እስካልተጋጨ አንቀበለውም ማለት ያስፈልጋል፡፡ የሚሆነውንም የማይሆነውንም ወደፊት እናየዋለን፡፡
(ምንጭ: ሪፖርተር፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡)
Leave a Reply