በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ ከተማ ፅንፈኛው የአሸባሪ ቡድን ሸኔ ጥቅምት 1 እና 2 በንፁሃን ላይ በከፈተው ጥቃት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
ቡድኑ ከህውሃት የሽብረ ቡድን ጋር ህብረቱን ካረጋገጠ በኋላ በብሄር ብሄረሰቦች ላይ ትንኮሳ በማድረግ ግጭቶችም የብሄር መልክ እንዲይዙ እየሰራ ይገኛል ብለዋል የቢሮው ኃላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ።
ኃላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ሸኔ በአካባቢው ከሚንቀሳቀስ ሌላ የሽፍታ ቡድን ጋር በመተባበር በሀሮ ከተማ በከፈተው ጥቃት የ15 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የንብረት ውድመት እንዳደረሰ እንዲሁም 967 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ተጨማሪ የፀጥታ ሀይል ወደ ስፍራው በማሰማራት ወረዳውን እና ከተማውን የማረጋጋት ስራ እየሰራ ሁኔታውን የተቆጣጠረ ሲሆን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ እነዚህ ቡድኖች የብሄርን ሳይሆን የሶስተኛ ወገን ዓላማ እያስፈፀሙ በመሆኑ ህብረተሰቡ እኩይ ተግባራቸውን ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የመታገል እና ፀጥታውን የማስጠበቅ ስራውን እንዲያግዝ የቢሮ ኃላፊው ጠይቀዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሸባሪው ሸኔ እና የጥፋት አጋሮቹ በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ጥቃት የፈጸሙት ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት አስበው መሆኑን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የኮሙኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ጌታቸው ኢታና መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም አሸባሪው ሸኔ እና የጥፋት አጋሮቹ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ሆራ አዲስ የተባለች የገጠር ከተማ ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ጥቃት የፈጸሙትን የአሸባሪው ሸኔ አባላትን ለመደምሰስና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት። ረዳት ኮሚሽነር ጌታቸው እንደገለጹት፥ በዕለቱ ጸረ ሰላም ሀይሎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ብሔርን ከብሔር በማጋጨት አልመው ነው። የጥፋት ሀይሎቹ ላይ በተወሰደው እርምጃም የአሸባሪው ሸኔ አባላት ተገድለዋል።
በአሁኑ ወቅት የተፈናቀሉት ዜጎችም በኪረሙ ከተማ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸው፥ ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት አካባቢ ለመመለስም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። የክልሉ መንግስት አሸባሪው ሸኔ በዘላቂነት ለማጥፋት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
እንደ ረዳት ኮሚሸነሩ ገለጻ፤ በምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ በሚንቀሳቀሰው አሸባሪ ቡድን ላይ ጠንካራ እርምጃም ይወሰዳል።
በሌላ በኩል የተወሰኑ መገናኛ ብዙሃን የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ብሔር አባላት ሆነው ሳለ ተጎጂዎችን የአንድ ብሔር አባላት ማድረጉ ተገቢ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል። በቀጣይም መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛውን መረጃ ከተገቢ አካላት ማጣራት እንደሚኖርባቸውም ጠቁመዋል። በአካባቢው የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ሁሉ መሰዋዕትነት እየከፈሉ እንደሚገኙም መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ ኃላፊዎች ይህንን ቢሉም እውነታው ግን በመሞት አፋፍ ላይ ያለው ትህነግ የሚፈጽመው ሤራ እንደሆነ ይታመናል። በደርግ ዘመን ከትግራይ ወደ ወለጋ ሠፍረው የነበሩና አሁን ያካባቢውን ቋንቋና ባሕል ለምደው ያደጉ የትግራይ ተወላጆች ከሸኔ ጋር በመግጠም የሚፈጽሙት ግፍ እንደሆነ ከብዙዎች ሲነገር ይሰማል። እነዚህ በተለይ ከት ህነግ ጋር ቃል የተጋቡ ሸኔ ከት ህነግ ጋር ጥምረት ፈጥሮ አካባቢውን እንዲያሸብር ልዩ ተልዕኮ ሲሰጡ የኖሩ ናቸው። ትህነግም በሥልጣን በነበረ ወቅት ለችግር ጊዜ ብሎ ያስቀመጣቸውና እስካፍንጫቸው የታጠቁ እንደሆኑ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንደሚሉት “ዋና ጥያቄ ሆኖ መጠየቀ ያለበት ለምን ወለጋ? ለምንስ የተወሰነ ቦታ ብቻ? የሚለው ሊሆን ይገባል። ይህንን የሚጠይቅ የትኩረት አቅጣጫውን ሊያስተካክል ይችላል” ብለዋል።
እነዚህ የትህነግ ታጣቂዎች ዋንኛ ዓላማቸው “እሣትና ጭድ ናቸው፤ እኛ የቤት ሥራችንን ስላልሠራን ነው እንጂ አብረው መኖር የሚችሉ አይደሉም” በማለት ጌታቸው ረዳ የተናገረላቸውን አማራና ኦሮሞ ብሔረሰቦችን ማጋጨት ነው። ትህነግ ከሥልጣን ለመወገዱም ሆነ አሁን ላለበት የሽፍታ ደረጃ እንዲደርስ ያደረጉት የእነዚህ ሁለት ቡድኖች ጥምረት እንደሆነ ባደረገው ግምገማ ያመነበት ጉዳይ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ለሣንቲም ለቀማ የሚርመሰመሱ ኅሊናቢሶች ከወገናቸው ዕልቂት ይልቅ ከርሳቸውን የሚሞሉብትን ትርፍ ብቻ ስለሆነ የሚያስቡት “ኦሮሞ አማራን ገደለ” የሚል ዘገባ በማውጣት የትህነግን ዓላማ እያሳኩ ይገኛሉ በማለት አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
ጊዜው መሽቷል። ሰው አረመኔ ሆኗል። ባጭሩ ሃገር ለቀን ወጣን በሃገር ውስጥ ኖርን ሰላም የሌለን ሰላም የማንሰጥ ሆነናል። በየስፍራው የሚደረጉ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፎችን ለተመለከተ ከሃገር ውስጥ ሰው የቀረ አይመስልም። አንዳንድ እማ ልክ ሃገር ቤት እንዳለ ዘመድ አዝማድን እየቆጠረ ሲያስተዋውቅ እንዴ እነዚህ ሰዎች የዚሁ ሃገር ተወላጆች ናቸው እንዴ ያስብላል። በሊቢያ የኤርትራዊያን ስደተኞች ምጻት ከፍቷል። ሰሚ ግን የለም። የአረብ ሃገር ዋና አሸባሪ ሳውዲ በአሜሪካ እየተመራች በሊባኖች፤ በየመን፤ በሶሪያና በተለያዪ የአፍሪቃ ሃገሮች እሳት ታነዳለች። በሃገሯ የተጠለሉ በተለይም ሃበሻ የሆኑትን ሁሉ በግፍ ታስራለች፤ ታባርራለች። አውሮፓ፤ ሰሜን አሜሪካ፤ ላቲን አሜሪካ ቆዳው ጠቆር ያለውን ሁሉ ከድንበር እየመለሰ ነው። በፓላንድ ለረጅም ጊዜ የቆየ አንድ የስደተኞች ካምፕ በቅርቡ እንደሚዘጋ ወሬው ተናፍሷል። ባጭሩ የአለሙ የፓለቲካ አሰላለፍ በተሰባጠረ ቁጥር የድሆች እንባና የመከራ ጎዳናም ሰፊ እየሆነ መጥቷል።
የጨለማው አህጉር እያሉ ነጮች ወደሚጠሩት አፍሪቃ ስንመጣ ደግሞ በጎሳ፤ በዘር፤ በቋንቋና በሃይማኖት በመለያየት መገሻለጡ ቀጥሏል። የሚገርመው ሰው የራሱ ቤትና ማሳ ላይ እሳት ለኩሶ ኡኡ ድረሱልኝ የሚል እብድ ሆኗል። በሰሜን ሽዋ የተከመረ እህል እሳት የለኮሰው በዘሩ የሰከረ በሃይማኖት የተሸፈነ የእውራን ቡድን ነው። ሌላኛው ዘራፊና ቀማኛ ወያኔ ትግራይ በአፋርና በአማራ ክልል የሚሰራው የግፍ ክምር ያለ ሮኬት እርዳታ ሰማይ ይደርሳል። የሰው ልጅ በራሱ ሃገርና ህዝብ ላይ እንዲህ ያለ በደል ይፈጽማል ብሎ መገመት ጭራሽ አይቻልም። ግን እጻዋት፤ እንስሳትና የሰው ህይወትን ያለምንም ርህራሄ እያጠፉና የቆመን ነገር ሁሉ እየዘረፉ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ወደ ኦሮሞው አሸባሪ ድርጅት ስንመጣ ያው የተጋተው የወያኔን ጽዋ በመሆኑ ጭካኔው ጭራቃዊ ነው። በዚህ ሁሉ ጋጋታ ውስጥ መንግስት ይፎክራል፤ አማራው ይፎክራል፤ የተጎዳው ድረሱልኝ ይላል። በዚህ ሁሉ ያሻጥርና የድረሱልኝ ድምጽ መካከል ሟች ይሞታል፤ ዘራፊ ይዘርፋል፤ የሚፈናቀል ይፈናቀላል፤ የመንግስትም የማያቋርጥ መግለጫ ከክልል እስከ ቤተመንግስት ይንጋጋል። በዚህ ሁሉ አስረሽ ሚችው አማራ ጠል ሃይሎች አማራ የተባለን ከአራቱም ማዕዘን እያሳደድ ይገድላሉ፤ ያፈናቅላሉ፤ ይዘርፋሉ። ግን ህዝብ ደንዝዟል። በኑሮ ክብደት፤ በፈጠራ ትርክት፤ በኖራለሁ ተስፋ ሟችን ቀብሮ፤ ያለውን ወርውሮ የራሱን ሞት ከመጠበቅ በስተቀር በአደባባይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ አንድ ሆኖ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አልቻለም። ትላንት የኦሮሞ ደም የእኛ ደም ነው በማለት በአደባባይ ወጥተው የተፋለሙት እነዚያ አማሮች ዛሬ የእነርሱ ደም በየአቅጣጫው ሲፈስ ለምን የኦሮሞ ህዝብ ዝም አለ? መልሱ ቀላል ነው። በራሱ እንዳያስብ የፓለቲካ መሪ ነን የሚሉ ክፉዎች ጠፍንገው ስለያዙት ነው። የወያኔና የኦሮሞ ጽንፈኞች ጥምረት የሚያሳየው የጋራ ጠላታቸው አማራ መሆኑን ብቻ ነው። ግን ለምን? አማራ ምን አድርጎ ነው እንደዚህ ለዘመናት በሻቢያ፤ በወያኔና በኦሮሞ ሃይሎች የተጠቃው? መልሱ ቀላል ነው። ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራን መበተንና ማጥፋት ቀዳሚ አጀንዳቸው ሲሆን ሌላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማውደውም ነው። ከሞላ ጎደል እየተሳካላቸው ነው።
እስቲ ማን ይሙት በንፋስ የተበተኑ ድቄት ናቸው የተባሉት ወያኔዎች አፋርና ደ/ታቦር በር ድረስ ሲደርሱ የጦር ሃይሉ የት ነበር? ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር ጨረስናቸው ሲሉን የነበሩት ዛሬ በወሎ ህዝብ ላይ የሚያደርሱት ግፍ መፈጠርን ያስጠላል። ወረኞች በበዙበት፤ ለፍላፊ ብቻ በመድረክ ላይ በሚደሰኩርበት ሃገር ሰርቶ ማሳየት አይቻልም። አትለፍልፉ፤ ሙያ በልብ ነው። ሁሉም ነገር በኤሌክትሮኒክስ ግንኙነት አይሁን ይጠለፋል። ወረቀት ተጠቀሙ ሲባሉ አይሰሙም። ገና ምንም ሳይጀመር ወያኔ የጦሩን አሰላለፍና ከየት ወደ የት እንደሚሄድ ለይቶ ያውቃል። የሚያሳዝነው ለሃገር ብለው የተሰለፉ ወገኖች በአሻጥር እንዲመቱ መደረጉ ነው። ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚባለው እንዲህ ስለሆነ ነው።
በቅርብ ድሮ የወያኔ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮነን ከነበረ ሰው ጋር ስለ ሃገር ጉዳይ ስንጫወት እንዲህ አለኝ። እኛ ልክ እንደ ታልባን 20 ዓመትም ቢፈጅ ተዋግተን ወደ ስልጣን መመለሳችን አይቀሬ ነው። የሱዳንን ኮሪደር ካስከፈትን ደግሞ አንድ አመትም አይፈጅብንም አራት ኪሎ ለመመለስ በማለት ያው በሩቅና በቅርብ ካሉ ጭፍን ወያኔ አፍቃሪዎች ጋር የመከረውን ነገረኝ። እኔም አንተ እድሜህ ገፍቷል በዚህ እድሜ እንዴት እንዲህ ታስባለህ? ቢቻል የትግራይ ህዝብ ከዚህ አረንቋ ድርጅት የሚወጣበትን መንገድ መፈለግ ነበረብህ እንጂ ስለው ከት ብሎ ስቆ አረንቋ አልከን። አዎን ጭቃ ማለት ነው። የማይወጡበት ማጥ ስለው እረ አማርኛውን አውቃለሁ። ትግርኛውም ይቀራረባል ብቻ ተወው ራሴን ያመኛል። ሌላ ጫወታ አምጣ ብሎኝ ጫወታ ጠፍቶብን በዚሁ ተሰነባበትን። ሰው በዘሩ ካሰበ እንስሳ ነው። የሰው መለኪያው ሰውነቱ ነው። ግን ያቀርቶ ሌላ ዘፈን መቶ ይኸው ሁሉ የክልል ባንዲራውን እያውለበለበ አሸሸ ገዳሜ ይላል። አታድርስ ነው። የዛሬው ዜና ከትላንቱ፤ የትላንቱ ከዛሬ አመቱ አይለይም። ዛሬም ሞትና ግድያ መፈናቀል፤ የቤቶች መቃጠል የከብቶች መዘረፍ ዜና ነው። ይህ ግፍ ይገታ ይሆን?
የጠ/ሚሩ መንግስት በአጭር ጊዜ የደም መፋሰሱን ካላቆመ፤ የኑሮ ውድነቱን ካላስተካከለ፤ በዚህም በዚያም ለግድቡ፤ ለወታደሩ እያለ የሰራተኛውን ደሞዝ መዝረፉን፤ በየቤቱ እየተዞረ በርበሬ፤ ድቄት፤ ሽሮ ገለመሌ እየተባለ የሌለውን ህዝባችን ማራቁቱ፤ ለወታደር ሰንጋ የእርድ በግና ፍየል ሌላም አቅርቦት እያሉ የሌለውን ገበሬና ድሃ ማዋከቡ መቆም አለበት። ይህ አሰራር የደርግ አይነት አሰራር ነው። ሰው ሳይፈልግ የወር ደሞዙን መቀማት የለበትም። የወደደ ይስጥ ያልፈለገና አቅም የሌለው መክፈል የለበትም። ለማኝን ለማኝ ቢለምነው ድርሻው ፍርፋሪ ብቻ ነው። አሁን በክልል መንግስታትና በፌዴራል መንግስት በኩል ራሱ ረሃብተኛ የሆነን ህብረተሰብ አምጡ፤ አዋጡ እየተባለ ለከፋ ችግር ሰውን ማጋለጥ እብደት ነው። ለወታደሩ ድርቆሽና ቆሎ/ዳቦ ቆሎ ይዘጋጅ። ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመቋጨት ቁርጠኝነትና ስልት ይኑር። ካልሆነ የጠ/ሚሩ መንግስ አምስት አመት ቀርቶ አንድ ዓመትም ላይዘልቅ ይችላል።
ፓለቲካ ወልጋዳ ነው። የኢሳያስና የዶ/ር አብይ ፍቅር እንዲህ በርዶ ያ ሁሉ የቃላት ድርደራ ምንም አይነት ፍሬ ሳይሰጥ እንሆ አራተኛ አመቱን ሊይዝ ነው። አሁን እንሆ በኬኒያና በሶማሊያ ICJ (የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ፍ/ቤት) ለሱማሊያ የበለጠ ድርሻ መስጠቱ ለሱማሊያዊያን ድል ሊመስላቸው ይችላል። ግን አይደለም። ልክ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ባድሜን አስታኮ በተደረገው አፈራረድ ላይ እንደሆነው ሁሉ ለዘመናት የሚያፋልምን ነገር ነው የሚፈርድት። ልብ ላለው ግን ባድሜ ኤርትራ ሆነ ኢትዮጵያ ሰው ሰላም ኑሮ ሰርቶ እስከኖረ ድረስ ችግር የለውም ነበር። አሁን በኬኒያና በሱማሊያ የባህር ድርሻ ላይ የተፈረደው ፍርድም ቢሆን ለሱማሊያም ለኬኒያም ችግች የለውም። አዎን ነዳጅ ይኖርበታል የተባለ ቦታ ነው ተብሏል። ይሁና። አንድ ከአንድ መግዛት ይችል የለ። ግን ነጩ አለም እኛ ያለማቋረጥ እንድንላተም ስለሚሻ በዚህም በዚያም የቅኝ ግዛት ካርታን እያመጣ ይኽው ዛሬም ያባሉናል። ሰው ግን አሁንም ተኝቷል። የነቃውና በቁም የሚያንቀላፋው አፍሪቃን ለቆ በየስፍራው እየተሰደደ ነው። ጥያቄው የህዝባችን እንባ ዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት ሳይለይ መቼ ነው የሚቆመው? ሃበሻው የእህል ክምሩን፤ ቤቱን፤ ንብረቱን እሳት እየለኮሰ ተራብኩ፤ ተጠማሁ ማለቱ መቼ ነው የሚገታው? ማንም መገመት አይችልም። በቃኝ!
Miherete Tibebe says
በእሸት ያለው እየተጎበኘ የበሰለው ለድጋፍ የደረሰው ክምር ግን በጦረኛ እሳት ሲቃጠል ጥበቃ አይደረግለትም!የእርጥብ ቅልነትና የዘመን መዥገርነት ለጀግኖች አይመችም! በሸዋና ወለጋ የሰፈሩ ኦሮሚኛ ተናጋሪ ትህነጎችና የሸኔ ግፍም እያሚያባራው መቼ ነው!