ኦባማ በአፍሪካ ኅብረት ያደረገው ንግግር ብዙ ጥያቄዎችን መልሷል፤ የኦባማ ጉብኝት ያስከተለው ጫጫታ ሁሉ መልስ አገኘ፤ የሰው ልጆች በመሀከላቸው ምንም ዓይነት የአድልዎ ልዩነት ሳይደረግባቸው በሰውነታቸው ብቻ በተፈጥሮ ያገኙትን ክብራቸውንና ሞገሣቸውን አስከብረው መኖር እንዳለባቸው በአጽንኦት ተናገረ፤ ዛሬ የአሜሪካኑ ፕሬዚደንት ያደረገው ንግግር ከፕሬዚደንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ እስከ ፖሊሶች፣ መርማሪዎችና አዛዦቻቸው፣ እስከጦር ኃይሉና አዛዦቻቸው፣ አስከዓቃብያነ ሕግና ዳኞች፣ እስከወህኒ ቤት ጠባቂዎችና አዛዦች በየሥልጣን ተዋረዱ ላይ ሆነው የኢትዮጵያውያንን የሰውነትና የዜግነት እኩልነት አፈራርሰው በጎሣ መሠረት ላይ ሊበታትኑት የሚሞክሩትን በኃይለኛ ቃላት ከመሬት በታች ከቶአቸዋል፤ ማሰብና ማስተዋል የጎደለው፣ ከአፍንጫ የራቀ አመለካከት የሌለበት፣ አገርን የሚያጠፋ፣ ከሰውነት ጎዳና የሚያወጣ የድንቁርና መንገድ መሆኑን ገልጧል፡፡
ኦባማ የኢትዮጵያን ገዢዎች ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ገዢዎች በሙሉ አላግጦባቸዋል፤ በሥልጣን ላይ ሙጭጭ በማለታቸው፣ በሙስናቸው፣ በአፈናቸው፣ ልክ ልካቸውን ሲነግራቸው እፍረታቸውን ውጠው ያጨበጭቡለት ነበር፤ የአፍሪካ ገዢዎች ሕጉን እንደፈለጉ የሚጠመዝዙትን መሳቂያ አድርጓቸዋል፤ በአዳራሹ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች የኦባማን ንግግር በማድነቅ በጭብጨባና በጩኸት ይገልጹ ነበር፤ ለወግ ብቻ የሚደረግ ምርጫ የዴሞክራሲ መግለጫ አይሆንም አለ፤ ዴሞክራሲ ነጻና ትክክለኛ ምርጫን፣ ሀሳብን በነጻነት መግለጽን፣ በነጻነት መደራጀትንና መሰብሰብን ያካትታል፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድረጅቶችን ማገድና መገደብ ለዴሞክራሲ እንቅፋትና ለእድገት ጸር ነው፡፡
አገዛዞች ነጻነትን በማፈናቸው ሁለት ዋና ዋና የማኅበረሰብ ዓምዶችን ማለትም ደኅንነትንና ሰላምን ያጣሉ፤ ሰላምና ደኅንነት ሰጠፋ ማኅበረሰቡ የጉልበተኞች መጫወቻ ሆኖ ይደናበራል፤ ይህ አደገኛ ጉዞ ነው፤ መልካም አስተዳደር ከሰፈነ ሽብርተኛነት የሚበቅልበት መሬት አያገኝም፤ ሰዎች ሁሉ በሰውነታቸውና በዜግነታቸው እኩልነት ሰብአዊ መብቶቻቸው ሁሉ ከተከበሩላቸው ወደኃይል እርምጃ የሚወስደውን መንገድ የሚከተሉበት ምክንያት የለም፤ እድገት የነጻነትና የዴሞክራሲ ውጤት ነው፤ ነጻነት የሰው ልጆች ሁሉ ዓላማ ነው፡፡
ማንም ቢሆን ከሕግ በታችና ለሕግ ተገዢ መሆን አለበት፤ ሕገ መንግሥቱን ለእሱ እንደሚበጀው እያደረገ በመተርጎም በሥልጣን ላይ መቆየት አይቻልም፤ ሊፈቀድም አይገባም፤ በአጠቃላይ አባማ በአፍሪካ ኅብረት በአደረገው ንግግር የአፍሪካ ገዢዎችን ሁሉ ቁስላቸውን በአልኮል ሲያጥብላቸው እየለበለባቸው ተመልክተውታል፤ አዳምጠውታል፤ አንዳንዶቹም እያፈሩ አጨብጭበውለታል፡፡
የዚህ ንግግር የመጨረሻው ግብ ያልገባቸው የአፍሪካ ገዢዎች ክፉ ነገር ይጠብቃቸዋል፤ በሽብርተኛነት መነገድ መልኩን ሊለውጥ ነው፤ ካላወቁበት የማያውቁት ሽብር ቤታቸውን ይጠርግላቸዋል!
ሐምሌ/2007
በለው ! says
>>> የአፍሪካ መሪዎች በአሜሪካው ጥቁሩ መሪ በነጩ ቤት ከተጋበዙ በኋላ የነበሩበትንም ያሉበትንም ዘንግተው ፎቶአቸውን አየለጠፉ ሲፈነድቁ ከርመዋል። ተራቸው ደርሶ ጥቁሩን መሪ በጥቁር ምድር ቻይና በሰራው ቤት ጋበዙት…”የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ” ነዋ! ጠርታችሁ እየሳቃችሁና እያጨበጨባችሁ ስለተሰደባችሁ በጣም ደስ ብሎናል እንኳን ደስ አላችሁ። ወ/ሮ ዊንዲ ሸርማን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አለ.. ምርጫው ፍትሃዊና እንደቀድሞው ሁሉ የተሳካ ይሆናል ሲሉ የኢህአዴግ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር አቶ ቴዎድሮስ አደሃኖም በሳቅ ታፍነው ሽምቅቅ አሉ። ለምን? ከውሸታሙም በላይ ዋሾው ሲያሳምረው ደንግጠው…ከኦባማ ጉብኝት በኋላም ቴዎድሮስ አድሃኖም ሃፍረትና ድንጋጤያቸው ትክክል እንደነበር ተረድተው ስሐተቶችን አምነው መቀበል ጀምረዋል ሆድአደር ካላሰናከላቸው ይበርቱ። ወ/ሮ ሱሳን ራይዝ ደግሞ “ በቅርቡ ኢህአዴግ በመቶ ደምፅ የተመረጠ መንግስት ብለው… በመቶ ደምፅ መመረጥ ዲሞክራሲ ነውን? ሲባሉ አዎን! በመቶ ደምፅ ብለው በምርጫው ሳቁበት ”የዓለም ሕዝብም ሳቀ እኛም ተሳቀቅን…. ኦቦ ባራክ ሁሴን” የኢትዮጵያ መንግስት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የመጣ ነው” አሉት… ሁለት ውሸታም አማካሪዎቻቸውን ላለማሳፈር እሳቸውም በዲሞክራሲ ያልተመረጠ መንግስትን አልጎበኘሁም ለማለት ነበር። በእርግጥ ዲሞክራሲ ምርጫ ነው? በኢህአዴግ አባባል “ምርጫ ሂደቱ ብቻ በቂ ነው”ሲል ፮ሚሊየን አባላት አለኝ የሚለው ኢህአዴግ ፩ ለ ፭ ጥርነፋ የታፈኑ ሚሊየኖች አሉ። ምርጫው ከ፴፭ ሚሊየን አስከ ፴፰ነጥብ ፭ሚ ሕዝብ ተሳትፏል ይላሉ በእርግጥ ይህ ቁጥር እንዴት ተዘበራረቀ? ተመዝጋቢው ቀድሞ ከታወቀ የምርጫ ወረቀትስ እንዴት አነሰ? የትግራይ ልጆች በኤትርትራውያን ስደታኛ ሥም ከሀገር ሲሰደዱ ኤርትራውያን በትግራይ ልጆች ሥም ምርጫ ገብተውስ እንደሆነ? በመለስ ግዜ አመራር በቡድን ነበር በኀይለመለስ በኅብረት አደለምን!? ወጣም ወረደ ኦባማ ዋሽንግተን ነጩ ቤት ተቀምጦም ይሁን አዲስአባባ አፍሪካ ኅብረት ቻይና ሰራሽ አዳራሽ ቆመው ተናገሩ አልተናገሩ ገዢው፣ አውራ ፓርቲ፣ የኀያላን ሀገሮችን ትዕዛዝ እስካከበረና ጥቅማቸውን በድሃ ልጅ ደምና አጥንት እስካስከበረ ድረስ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ልማታዊ፣ እያሉ በፓርቲውና በሕገመንግስቱ ከለላ ጃፓን የደረሰችብት የዕድገት ደረጃ እስኪደርስ ሁሉም በአንድ የፖለቲካ ጥላ ሥር አጠቃሎ እንዲቀጥል ይደረጋል። ኀይሌ አሜሪካ ከእኛ የምትፈልገው አለ እኛም የምንጠይቃቸውን ያደርጉልናል ሲሉ ነበር። በመሠረቱ ሁሴን ኦባማ እንዳሉት አሜሪካም ሙስና አለ ካሉ ህወአት አባላትም እሥርና ግድያም አሜሪካንም አለ እንደሚሉን ማን በነገራቸው። የእያንዳንዱ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ፓርቲ አባል ክስ የሚመሰረትበት አሸባሪ ህግ አንቀፆችን አጠጋግቶ ከ፲ እስከ ዕድሜ ልክ የሚያስፈርጀውን የሚጽፉ የህግ ተማሪዎች (ዐቃቢ ሕግ) ባለሙያ ሳይሆኑ የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪዎች እንደሆኑ አልተረዱልንም!። ሕግን ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ኮርጀን በእስታሊን በሌኒን በቦልሸቪክና ሞኖቪክ ገሎ ማለፍ ሥርዓት የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ሙስና መር ኢኮኖሚ ሲፈጠር ከታጋዩ ይልቅ ጥቅማጥቅመኛው አድርባዩ፣ አውርቶ አደሩ ሠላም፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ እንዳይኖር እሳት ሲጭር ይኖራል…
“አገዛዞች ነጻነትን በማፈናቸው ሁለት ዋና ዋና የማኅበረሰብ ዓምዶችን ማለትም ደኅንነትንና ሰላምን ያጣሉ፤ ሰላምና ደኅንነት ሲጠፋ ማኅበረሰቡ የጉልበተኞች መጫወቻ ሆኖ ይደናበራል፤ ይህ አደገኛ ጉዞ ነው፤ መልካም አስተዳደር ከሰፈነ ሽብርተኛነት የሚበቅልበት መሬት አያገኝም፤ ሰዎች ሁሉ በሰውነታቸውና በዜግነታቸው እኩልነት ሰብአዊ መብቶቻቸው ሁሉ ከተከበሩላቸው ወደኃይል እርምጃ የሚወስደውን መንገድ የሚከተሉበት ምክንያት የለም፤ ዕድገት የነጻነትና የዴሞክራሲ ውጤት ነው፤ ነጻነት የሰው ልጆች ሁሉ ዓላማ ነው፡፡ -ይህ ሳይሆን ሲቀር ነው ሰዶ ማሳደድ የሚጀምረው ። ኦቦ ሁሴን ባራክ በቤታችን መጥተው እያሳሳቁ ከሚተርቡን ከሚያፌዙብን ከሚሳቅብን ከምንሳቀቅ እዚያው ሆነው እርስ በእርሳችን በተደማመጥን በተራረምን መልካም ነበር። አሁንማ ሰድበው ለሰዳቢ ሰጡን መልካም የ፲፰ ወር ቆይታ በነጩ ቤት ይሁንላቸው እኛም ጥንቷዊቷ የምርጥ ዘርና የሰው ልጅ መገኛ የጥቁር ቤታችን ኢትዮጵያ በሠላም ለዘለዓለም በክብር ትኑር!! ሠላም ለሁሉም በቸር ይግጠመን