ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ማስጠንቀቂያ መስጠቱን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
መንግሥት ዓርብ ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳሰታወቀው፣ የተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ የሆነው ተቋም፣ የኢትዮጵያን ሕግ ያላከበረ ድርጊት በተደጋጋሚ እየፈጸመ ከመሆኑም በላይ፣ በትግራይ ክልል ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያዛባ መግለጫ እያወጣ መሆኑን በመግለጽ ለተቋሙ ማስጠንቀቂያ ጽፏል፡፡
“በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ድርጅት የትግራይ መከላከያ ኃይል በማለት በሚያወጣው መግለጫ በተደጋጋሚ ጊዜ እየጠቀሰ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ የሚያወጣው መረጃ የተዛባና ሕገወጥ የተባለውን ኃይል የሚያበረታታ ነው” በማለት ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አስጠንቅቋል።
ተቋሙ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት ከሚያበላሹ ድርጊቶቹ እንዲታቀብና የእርማት ዕርምጃዎችን እንዲወሰድ፣ ለተቋሙ በደብዳቤ ማሳወቁንም መግለጫው አመልክቷል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ በአየር ትራንስፖርት ማቅረብ ለሚፈልጉ አካላት የበረራ ፈቃድ መሰጠት መጀመሩን መንግሥት ያሳወቀ ሲሆን፣ ይህም ደንብና አሠራርን ተከትሎ እንደሚከናወን ገልጿል።
በዚሁ መሠረት ማንኛውም የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅት አውሮፕላን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጭኖ ሲመጣ በቀጥታ ማረፍ ያለበት አዲስ አበባ እንደሚሆንና ዕርዳታውን ወደ ክልሉ ካደረሰ በኋላም ተመልሶ አዲስ አበባ ማረፍ እንዳለበት አስታውቋል፡፡
በመሆኑም አዲስ አበባ ሳያርፍ በቀጥታ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረግ በረራ እንደማይኖር፣ ከትግራይ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሳይመለስ በቀጥታ ከኢትዮጵያ የአየር ክልል መውጣት እንደማይቻል አስታውቋል።
ከሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ወደ ትግራይ ክልል የአየር በረራ ፈቃድ መስጠት መጀመሩን ያስታወቀው መንግሥት፣ እስካሁን ወደ ክልሉ በረራ ለማድረግ የጠየቀው የዓለም የምግብ ድርጅት የዕርዳታ ሠራተኞችን ለማጓጓዝ መሆኑን አስታውቋል።
በትግራይ ክልል ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች፣ ከሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ክልሉ መንቀሳቀስ መጀመራቸውንም መንግሥት አስታውቋል።
በዚህም መሠረት በዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች አማካይነት ከ40 የሚበልጡ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰብዓዊ ዕርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ መንቀሳቀሳቸውን ገልጿል። (ሪፖርተር)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply