• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ከፍተኛ ዋጋ ያለው የሊዝ መብት በተጭበረበረ መንገድ በማሸጥ የተጠረጠሩ ባልና ሚስት ታሰሩ

August 15, 2013 06:41 am by Editor Leave a Comment

ፈጽመዋል በተባሉት በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአታላይነት፣ በከባድ እምነት ማጉደል፣ በሰነድ ማጥፋትና ሐሰተኛ ምስክርነት መስጠት ወንጀል የተጠረጠሩት ባልና ሚስት፣ አቶ ጌታቸው ጣሰውና ወይዘሮ ሸዋነሽ መንግሥቱ፣ እንዲሁም የቅርብ ዝምድና እንዳላቸው የሚገለጸው አቶ ዘውዱ ክንፈና አቶ ወንድአፍራሽ ፍቅሩ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የሊዝ መብት፣ በተጭበረበረ መንገድ እንዲሸጥ አድርገዋል በሚል ታሠሩ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋል በተባሉባቸው ድርጊቶች ስድስት ክሶች የተመሠረቱባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ሲሆን፣ የፈጸሙት ወንጀል በዝምድና በተሳሰረ መንገድና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ከልክሏቸው፣ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ብይን ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋል የተባሉባቸው የወንጀል ድርጊቶችን በሚመለከት ክስ ያቀረበባቸው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸውና አቶ ጌታቸውና ወይዘሮ ሸዋነሽ ካልተያዘውና ቃለ ሥላሴ በላይ ከሚባለው አባሪያቸው ጋር በመሆን፣ ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘትና ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የፍርድ ባለዕዳ በሆኑት አቶ ድልአርጋቸው በላይ ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡

የፍርድ ባለመብት ኢትዮሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የአቶ ድልአርጋቸው ይዞታ የሆነውንና ከባንቢስ ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው መንገድ የመካነ ኢየሱስ ዋና መሥሪያ ቤት አካባቢ በሚገኘው 543 ካሬ ሜትር ቦታ የሐራጅ ጨረታ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡

ተከሳሾቹ ሕጋዊ ተጫራቾች በመምሰል ለጊዜው ካልተያዘው ቃለ ሥላሴ በላይ ጋር በመመሳጠር በጨረታው ይሳተፋሉ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በዝምድናና በጥቅም በመተሳሰር ወደ ጨረታው የገቡትና የፍርድ ባለዕዳ የሆኑት አቶ ድልአርጋቸው፣ የሊዝ ይዞታቸው ከሆነው 543 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ማግኘት የሚገባቸውን ትክክለኛ የሽያጭ ዋጋ ለማፈንና ለመገደብ አስበው መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ባልና ሚስት እያንዳንዳቸው 264,169 ብር ከ50 ሣንቲም ከተለያዩ የባንክ ሒሳቦች በሲፒኦ በማሠራት፣ እንዲሁም አሰፋ በየነ የተባለ የአቶ ቃለ ሥላሴ ጓደኛ ተመሳሳይ ሒሳብ በሲፒኦ በማሠራት፣ ከፍርድ ባለመብት ኢትዮሩት ኢንተርናሽናል፣ ካልተያዘው ተጠርጣሪ ቃለ ሥላሴ የባንክ ሒሳብ፣ ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ኡራኤል ቅርንጫፍ፣ በማውጣትና ለፌዴራል ፍርድ ቤቱ ፍርድ አፈጻጸም መምርያ የጨረታውን መነሻ ዋጋ አንድ አራተኛውን ማስያዛቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የመሬቱ ዋጋ ከሚገመተው በላይ እንዳይሄድ ጨረታውን በማፈንና በመገደብ፣ የጨረታ መነሻ ዋጋ 1,056,07 ብር እንዳይዘል በማድረግ፣ በ1,065,000 ብር ጨረታውን አቶ ቃለ ሥላሴ እንዳሸነፈ በማስመሰል፣ የሊዝ ባለመብቱ አቶ ድልአርጋቸው በላይ በአግባቡ ቢሸጡት ኖሮ ሊያገኙ የሚችሉትን 5,949,766 ብር እንዲያጡ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡ የፍርድ ባለዕዳ የተባሉት አቶ ድልአርጋቸው፣ ያልተያዘው ተጠርጣሪ አቶ ቃለ ሥላሴ ወንድም ሲሆኑ፣ ከባላቸው ጋር የማታለል ተግባር ፈጽመዋል የተባሉት ወይዘሮ ሸዋነሽ ደግሞ የአቶ ቃለ ሥላሴ እህት መሆናቸውን፣ የመያዣ ትዕዛዝ ሁለት ጊዜ የወጣበትና በወንጀል ተሳታፊነቱ የተጠረጠረው አቶ ዘውዱ ክንፉ ደግሞ የወይዘሮ ሸዋነሽ የቅርብ ዘመድ መሆኑን፣ አቶ ወንዳፍራሽ ፍቅሩ ደግሞ የአቶ ድልአርጋቸው በላይ ወኪል የነበረ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ባላቸው የዝምድናና የጥቅም ትስስር አቶ ወንዳፍራሽ ፍቅሩ የአቶ ድልአርጋቸው ወኪል ሆነው በሚሠሩበት ጊዜ፣ ውክልናቸውን ተጠቅመው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር 1,474 ካሬ ሜትር የሊዝ ውል ፈጽመዋል፡፡ አቶ ድልአርጋቸው የፍርድ ባለዕዳ የሆኑበትን 543 ካሬ ሜትር ብቻ ፍርድ ቤት በሐራጅ እንዲሸጥ ወስኖና የሐራጅ ሽያጩን ካከናወነ በኋላ፣ በጨረታ መሳተፍ የማይገባቸው ወይዘሮ ሽዋነሽ ተሳትፈው 543 ካሬ ሜትሩን ያልተያዘው ቃለ ሥላሴ በላይ አሸናፊ ሆኖ ሲረከብ፣ ለጨረታ የቀረበው ቦታ ስፋት 543 ካሬ ሜትር ብቻ መሆኑን እያወቀ፣ የአቶ ድልአርጋቸው ንብረት የሆነውን ትርፍ 931 ካሬ ሜትር ቦታ ጨምሮ በመፈረም ተቀላቅሎ እንዲወሰድ ማድረጉን ክሱ ይተነትናል፡፡

ሌላው ተጠርጣሪና በቁጥጥር ሥር ባለመዋሉ ሁለት ጊዜ የመያዣ ትዕዛዝ የወጣበት አቶ ዘውዱ ክንፈ አርአያ ሲሆኑ፣ የፍርድ ባለዕዳ ናቸው የተባሉት አቶ ድልአርጋቸው በላይ ንብረት የሆነ ሬንጅሮቨር መኪና የሐራጅ ሽያጭ ላይ ተጠርጣሪዎቹ ሕጋዊ ተጫራቾች በመምሰል፣ አቶ ድልአርጋቸው ከመኪናው ጨረታ ሊያገኙ የሚችሉትን ትክክለኛ የጨረታ ዋጋ እንዳያገኙ ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ይህም የሆነው ተጠርጣሪው የጨረታ ዋጋውን ለመገደብና ለማፈን በማሰብ ለራሱ፣ መሐመድ ያሲንና ተወልደ አሰፋ ለተባሉ ግለሰቦች ለእያንዳንዳቸው በተለያዩ ሲፒኦ የተሠራ 60 ሺሕ ብር፣ በእጅ ጽሑፍ በመጻፍና አስመስሎ በመፈረም ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ኡራኤል ቅርንጫፍ በማውጣት ለፍርድ አፈጻጸም መምርያ የጨረታ መነሻ ዋጋ ማስገባቱን ክሱ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም አቶ ድልአርጋቸው በአግባቡ ቢሸጥ ሊያገኙት የሚችሉትን 471,911 ብር 44 ሣንቲም እንዲያጡ ያደረጉት፣ መኪናውን በ275 ሺሕ ብር የተሸጠ በማስመሰልና በማታለል ከመሆኑም ሌላ፣ ከቀናት በኋላ መኪናውን አቶ ቃለ ሥላሴ እንዲወስዱት መደረጉን ክሱ ይጠቁማል፡፡

አቶ ድልአርጋቸው የተባሉት የግል ተበዳይ በተጠርጣሪና ወኪላቸው በነበረው አቶ ወንድአፍራሽ ፍቅሩ የደረሰባቸው ተጨማሪ በደል፣ የተበዳዩ ንብረት በሆነው ልደታ ሼል ዴፖ ተቀጥሮ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሠራ የነዳጅና የዘይት ዲስፓች፣ የነዳጅ፣ የመኪና እጥበትና የካፊቴሪያ ገቢ ደረሰኞችና የባንክ ስቴትመንቶችና የሠራተኞች ፔሮል ለድርጅቱ ገቢ ሳያደርጉ፣ ሰነዶች እንዲጠፉ በማድረግ መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተጠርጣሪው ከተለያዩ የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች በተለያዩ ቀናት በድምሩ 250 ሺሕ ብር ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅሙ ማዋሉንና እምነት ማጉደሉንም ክሱ አካቷል፡፡

የአቶ ድልአርጋቸው እናት የቁም ኑዛዜ እንዳደረጉ በማስመሰል ካልተያዘው ተጠርጣሪ ቃለ ሥላሴ ጋር በመሆን ሕጋዊ ኑዛዜ ማድረጋቸውን እንዲመሰክሩ፣ ሌሎች ምስክሮችን በማዘጋጀት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት አቅርበው በማፀደቅ፣ አቶ ድልአርጋቸው እናታቸው ከፍተኛ ባለድርሻ ከሆኑበት ድል ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሊያገኙት ከነበረው የአክሲዮን ድርሻ እንዳያገኙ ማድረጉን፣ በዓቃቤ ሕግ የተመሠረቱ ስድስት ክሶች ያብራራሉ፡፡

የክሶቹን ጭብጥና ዝርዝር የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ከልክሎ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ብይን ሲሰጥ፣ ተጠርጠሪዎቹ ‹‹የዋስትና መብታችን ሊከበር ይገባል›› በማለት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው ነበር፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ መዝገቡን እንዳልመረመረው ገልጾ፣ ‹‹ዋስትና ሊፈቀድላቸው ይገባል ወይስ አይገባም›› በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለነሐሴ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የግል ተበዳይ አቶ ድልአርጋቸው በላይና የወንድማቸው አቶ ቃለ ሥላሴ በላይ የፍርድ ቤት ጉዳይ የተጀመረው ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ቢሆንም፣ ለፍርድ ቤት ክርክር ያበቃቸው ዝርዝር ጉዳይ የተጀመረው ከአሥር ዓመታት በፊት መሆኑን ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ አቶ ድልአርጋቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ በዜግነት አሜሪካዊ ናቸው፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት የአባታቸው ልጅ የሆነውን አቶ ቃለ ሥላሴ በላይን ወደ አሜሪካ ለመውሰድ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ ወቅቱ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትየጵያውያን በአገራቸው ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉ ይነገራቸዋል፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀድሞ የደኅንነት መሥሪያ ቤት በአሁኑ የመካነ ኢየሱስ ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ በሊዝ ቦታ ይወስዳሉ፡፡

በወሰዱት ቦታ ላይ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ይገነባሉ፡፡ ሕንፃውን ሲገነቡ ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሦስት ሚሊዮን ብር ከመበደራቸው ውጪ፣ ቀሪውን በራሳቸው ወጪ መገንባታቸውንና ማጠናቀቃቸውን የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ አቶ ድልአርጋቸው ሕንፃውን ‹‹ድል ሀውስ›› የሚል ስያሜ ከሰጡት በኋላ ወዲያው ለኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ ያከራዩታል፡፡ አቶ ድልአርጋቸው በመቀጠል ያቋቋሙት ድርጅት ድል ኢንተርናሽናል የሚባል ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱን ሲያቋቁሙ እናታቸው ወይዘሮ አየሁሽ ከበደ 87 በመቶ፣ ወንድማቸው አቶ ቃለ ሥላሴ በላይ አሥር በመቶና ራሳቸው ሦስት በመቶ ድርሻ ይዘው መሆኑንም የድርጅቱ መመሥረቻ ሰነድ ያስረዳል፡፡

በሦስት ሰዎች የተቋቋመው ድል ኢንተርናሽናል ድርጅት በዋነኝነት የሚሠራው በደቡብ ክልል ቦንጋ በወሰደው 250 ሔክታር መሬት ላይ ቡና ማልማት መሆኑም በሰነድ ተገልጿል፡፡ በወቅቱ በተለይ ለቡና ልማቱ ገንዘብ የሚያስፈልገው ድል ኢንተርናሽናል፣ የገንዘብ ብድር የሚያገኘው አቶ ድልአርጋቸው ቀደም ብለው ከገዙት ልደታ ሼል መሆኑን አቶ ድልአርጋቸው ከሰጡት መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በወሩ መጨረሻ ላይ ብድራቸውን ለሼል ነዳጅ ማደያ ኩባንያ እንደሚመልሱም ተናግረዋል፡፡

እህትማማች ኩባንያዎች በመሆናቸው መበዳደርም እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ የድርጅቶቹ የበላይ ኃላፊ አቶ ቃለ ሥላሴ ሲሆን፣ አቶ ድልአርጋቸው ቀደም ባሉት ዓመታት በጥበቃ ሠራተኝነት ቀጥረውት በኋላ የሼል ሥራ አስኪያጅ ያደረጉትና የሒሳብ ሥራውን የሚሠራው ወኪላቸው የነበረው አቶ ወንድአፍራሽ መሆኑን አቶ ድልአርጋቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ድልአርጋቸው በ1992 ዓ.ም. የጀመራቸው ከአዕምሮ ጋር የተገናኘ ሕመማቸው በ1994 እና በ1995 ዓ.ም. እየባሰባቸው በመሄዱ፣ ወንድማቸው አቶ ቃለ ሥላሴ ‹‹ንብረቱን ለመቆጣጠር ሁሉም ነገር በእኔ ስም ቢዞር ይሻላል›› ሲላቸው ‹‹ጠበቃዬን አነጋግረው›› ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠበቃቸው አቶ ሽመልስ ሞገስ ከአቶ ቃለ ሥላሴ ጋር በመመሳጠር አቶ ድልአርጋቸው የአቶ ቃለ ሥላሴ ዕዳ እንዳለባቸው የሚያስመስል የሐሰት ደብዳቤ በማዘጋጀት በፋክስ ሲልኩላቸው እሳቸው በወቅቱ ሕመም ላይ ስለነበሩ ሐኪማቸው ፈርመው ደብዳቤውን እንደመለሱላቸው አብራርተዋል፡፡

አቶ ቃለ ሥላሴ፣ አቶ ድልአርጋቸው በ1992 ዓ.ም. መታመማቸውን ሲያውቁ፣ በ1993 ዓ.ም. የድል ኢንተርናሽናል ድርጅት ከፍተኛ ባለድርሻና የአቶ ድልአርጋቸው እናት የሆኑት ወይዘሮ አየሁሽ ከበደ በቁም ኑዛዜ እንዳወረሷቸው በማስመሰል፣ የአቶ ድልአርጋቸው ተወካይ አቶ ወንድአፍራሽን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን በማስመስከር፣ በውልና ማስረጃ በፀደቀ ኑዛዜ አቶ ድልአርጋቸው ከእናታቸው ውርስ እንዲነቀሉ ማድረጋቸውንም ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ የአቶ ድልአርጋቸው ጠበቃ ከአቶ ቃለ ሥላሴ ጋር በመመሳጠር ፋክስ ያደረጉትን ደብዳቤና የእሳቸው ሐኪም ከዚያ የሰጡትን ምላሽ ይዘው ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ ‹‹አቶ ድልአድርጋቸው አራት ሚሊዮን ብር ዕዳ አለበት›› በማለት አቶ ቃለ ሥላሴ ክስ ሲመሠርት የእሳቸው ጠበቃ ደግሞ እውነት መሆኑን በማረጋገጣቸው፣ ፍርድ ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲከፍሉ ውሳኔ መስጠቱን ሰነዶች ያብራራሉ፡፡ ቀጥለው አፈጻጸም በመክፈት ንብረትነቱ የአቶ ድልአርጋቸው የሆነው ‹‹ድል ሀውስ›› ሕንፃ በሐራጅ እንዲሸጥ በፍርድ ቤት ያስወስናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የአቶ ድልአርጋቸው ጠበቃ ‹‹ወንድማማቾች በመሆናቸውና አቶ ድልአርጋቸው ሌላም ዕዳ ስላለባቸው ሕንፃውን አቶ ቃለ ሥላሴ ይረከቡ›› በማለታቸው ሕንፃውን እንዲረከቡ መደረጋቸውን የፍርድ ቤት ውሳኔው ያብራራል፡፡ በወቅቱ ሕንፃው በዓመት 2.2 ሚሊዮን ብር እንደሚከራይ ታውቋል፡፡

የሕንፃው ጉዳይ እንደተጠናቀቀ የአቶ ድልአርጋቸው ብቸኛ እናት ወይዘሮ አየሁሽ ከበደ በ1997 ዓ.ም. ሲሞቱ፣ አቶ ቃለ ሥላሴ ቀደም ብሎ በ1993 ዓ.ም. በቁም አውርሰውኛል በሚል የያዘውን ሰነድ፣ ማንንም ወራሽ ሳይጠራ እንዲፀድቅ በማድረግና አቶ ድልአርጋቸውን ከውርስ በመንቀል፣ የግል ንብረቱ መሆኑን ማረጋገጡን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡ በዚያን ወቅት በድል ኢንተርናሽናል ሥር የተጀመረው የቦንጋ ቡና እርሻ አፍርቶ ቡና ይለቀም እንደነበር አቶ ድልአርጋቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ ድልአርጋቸው እናታቸውን ‹‹ምን ነክቷት እኔን ከውርስ ነቀለችኝ?›› በማለት ከራሳቸው ጋር ሲሟገቱ (በወቅቱ እየተሻላቸው ነበር) አቶ ቃለ ሥላሴ የድርጅቱን 99 በመቶ ድርሻ በራሱ፣ አንድ በመቶ ደግሞ ሸዋነሽ ለምትባለው እህቱ በመስጠት፣ ድል ኢንተርናሽናል የሚለውን ድርጅት ስሙን ‹‹ኢትዮሩት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በማለት ቀይሮ የግሉ ማድረጉን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

አቶ ድልአርጋቸው በ2003 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ በመሆናቸው ስለእናታቸው ውርስ ማጣራት ይጀምራሉ፡፡ ከሕግ አማካሪዎች ጋር ሲነጋገሩ፣ ‹‹ሕንፃህ የተወሰደው አላግባብ ነው፡፡ ጠበቃህ ያስወሰደብህ ሕንፃውን ብቻ ሳይሆን የእናትህን ድርጅትም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ጠበቃህ ሆኖ ከውርስ ሊያስነቅልህ አይገባም ነበር፤›› ሲሏቸው፣ አቶ ድልአርጋቸው ጉዳዩን ይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያና ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር መሄዳቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ አቶ ድልአርጋቸው ጠበቃቸው ከውርስ ስለመነቀላቸው ይርጋ ሳያግደው ሊነግራቸው ይገባ እንደነበር ለሁለቱም ተቋማት በመግለጽ ሲከሱት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ባደረገው ማጣራት ጠበቃቸው አቶ ሽመልስ ሞገስ ከእሳቸው ባላንጣ (ከወንድማቸው) ጋር መመሳጠሩን፣ ለሁለቱም ውል ፈጽሞ መገኘቱን አጣርቶ እውነት ሆኖ ስላገኘው አሥር ሺሕ ብር ቀጥቶታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ይርጋ እንደሚያግደው ነግሯቸው ግን ስላወራረሱ በውልና ማስረጃ ፀድቋል ስለተባለው ሰነድ ግለሰቦቹ ቀርበው እንዲያስረዱ እንዲጠሩ ማድረጉም ተገልጿል፡፡

በውርስ ወቅት የተገኙ ሦስቱ ምስክር ናቸው የተባሉት (በኑዛዜው) ተጠርተው ሲጠየቁ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ሲናገሩ፣ የአቶ ድልአርጋቸው ወኪል አቶ ወንድአፍራሽ ግን ፍርድ ቤት ቀርቦ ‹‹ሰምቻለሁ እንጂ አላየሁም›› ብሎ በመዋሸቱ ውርሱ በወንጀል የተደረገ በመሆኑ ይርጋ ስለማያግደው፣ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ፋይል ሊከፍቱ መቻላቸው በሰነዱ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን እነ ቃለ ሥላሴ ለከተማው ሰበር ሰሚ ምድብ ችሎት ይግባኝ በማለት ‹‹ሊከፈት አይገባም›› ሲያስብሉ፣ አቶ ድልአርጋቸው ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ‹‹የሕግ ስህተት ተፈጽሟል›› በማለት በማመልከታቸው፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ተቀብሎ ጉዳዩን ለመስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጥሮታል፡፡

እነ ቃለ ሥላሴ የአቶ ድልአርጋቸውን እናትና የእሳቸውን ድርሻ ከድል ኢንተርናሽናል ላይ መንቀላቸውና መውረሳቸው ጉዳይ በቀጣይ የሚታወቅ ሲሆን፣ ድል ሀውስን በፍርድ ቤት ከወረሱ በኋላ ቃል ሀውስ ብለው በራሳቸው ቢይዙትም፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለአቶ ድልአርጋቸው እንዲመለስ ወስኖ ነበር፡፡ እነ ቃለ ሥላሴ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሲሉ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዝገቡን መርምሮ የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመሻር ለእነ ቃለ ሥላሴ በመስከረም ወር 2004 ዓ.ም. ቢወሰንላቸውም፣ አቶ ድልአርጋቸው የሕግ ስህተት መፈጽሙን በመግለጽ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ሲያቀርቡ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሌለው ሥልጣንና መዝገቡን በደንብ ሳይመረምር የሰጠውን ውሳኔ በመተቸት፣ በደንብ መርምሮ እንዲወስን መዝገቡን ለሥር ፍርድ ቤት በመመለስ ለመስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Law Tagged With: Right Column - Primary Sidebar

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “የእኔን ልጆችና የልጅ ልጆች (22ቱንም) የቀበርኩት እኔ ነኝ” አቶ መሀመድ የሱፍ ከምዕራብ ወለጋ June 28, 2022 01:07 pm
  • የገዳ ሥርዓት እና የኦሮሞ ገዢ መደብ June 20, 2022 11:34 pm
  • “የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው” ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል June 12, 2022 07:09 pm
  • የሰሜን ምዕራብ ዕዝና የአማራ ልዩ ኃይል ተከዜ ክፍለ ጦር ዕውቅናና ሽልማት ተሰጣቸው June 12, 2022 06:21 pm
  • ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታቶችን በተገቢው በመጠቀም ዘላቂ እርቅና ሰላምን ማምጣት ይቻላል June 12, 2022 05:40 pm
  • የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በገረጂና በቀበና ያስገነባቸውን የመኖሪያ አፓርትመንቶች አስመረቀ June 12, 2022 05:35 pm
  • በኦነግ ሸኔ ፈርሶ የነበረውና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት ጀመረ June 10, 2022 09:13 am
  • ጃዋር በዳውድ ኢብሣ ቀይ መስመር ተሰመረለት June 8, 2022 12:59 pm
  • ወልቃይት: ቢመረንም ለመዋጥና ራሳችንን ለመመልከት እንሞክር June 8, 2022 11:53 am
  • እብድ ይሻለዋል እንጂ አይድንም፤ ሐጂ ጃዋር አሁን ለምን ብቅ አለ? June 8, 2022 05:59 am
  • ሕዝብ ድምፅ የነፈጋቸው “ፓርቲዎች” የሽግግር መንግሥት ይቋቋም አሉ June 7, 2022 01:11 am
  • “አድጌ እንደናንተ መሆን እፈልጋለሁ” June 5, 2022 06:58 pm
  • በሳምንት ለ100 ያህል ሕሙማን አገልግሎት የሚሰጥ የኩላሊት ዕጥበት ማዕከል ሥራ ጀመረ May 30, 2022 02:20 am
  • የጥቁር አንበሳ ዕጩ መኮንኖች (ካዴቶች) ተመረቁ May 29, 2022 04:01 pm
  • “ኢትዮጵያን መንካት አይቻልም!!” በሚል ቁጭት ነው እየሠራን ያለነው May 29, 2022 01:04 pm
  • “ከሞፈርና ቀንበር ወደ ትራክተር” በሚል መርህ ለአማራ ገበሬዎች የግብርና ሜካናይዜሽን ተሰጠ May 29, 2022 02:02 am
  • ኢትዮ 360 “የወያኔ፣ የጁንታ ሚዲያ ነው” – ባለከዘራው ጄኔራል May 27, 2022 02:51 am
  • “እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ የሚያጣሉን ፖለቲከኞች ናቸው” የአማራ ወዳጃቸውን አደራ ቤት የመለሱ የቅማንት ተወላጅ May 27, 2022 01:40 am
  • ትግራይን አገር እናደርጋለን፤ “በውይይት እና በጦርነት” ሁሉንም ጉዳይ እንቋጫለን – የወንበዴው መሪ ደብረጽዮን May 26, 2022 09:18 am
  • “ሁለቱ የምዕራብ ዕዝ ተዋጊ ዶክተሮች” May 26, 2022 08:19 am
  • ወደ ትህነግ ሊተላለፍ የነበረ አምስት ሚሊዮን ብር ከ20 ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ May 25, 2022 01:57 am
  • የጦርነቱ ስትራቴጂያዊ እውነታዎች May 19, 2022 09:37 am
  • በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የዓለም ባንክ May 16, 2022 10:22 am
  • በአዲስ አበባ 1 ሺህ 98 የብሬን እና 2 ሺህ 162 የክላሽ ጥይት ተያዘ May 16, 2022 10:10 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2022 · Goolgule