ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሰላም ስምምነት ከፈፀሙና ሁለቱ መሪዎች በየአገራቱ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ከመንግሥት አልፎ በሕዝብ ደረጃ በርካታ ለውጦችን አምጥቶዋል። ይህንን ተከትሎ ኢሳያስ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ደረጃ የአማራን ብሔራዊ ክልልን እንደሚጎበኙ ተገልጾዋል። ኤርትራን ከትግራ ጋር እንድታብር ለሚመኛትና በኢሳያስ አጠራር የህወሓት “ጥምብ አንሣዎች” ይህ ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራና ውርደት ነው ተብሏል።
ፋና ባሰራጨው ዜና ላይ እንደተገለጸው “የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሚመሩት ልኡክ በአስመራ ይገኛል። በቆይታቸውም አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ ከአቶ የማነ ገብረአብ ጋር የኤርትራውያንንና የኢትዮጵያውያንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ላይ መወያየታቸውን አስታውቀዋል” ብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ “እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ አማራ ክልል እንዲሚመጣ ከስምምነት መድረሳቸውም” አቶ ንጉሡ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ኤርትራ ሄደው በነበሩበት ወቅት ከኤርትራ ጋር የመጀመሪያውን የወዳጅነት እግርኳስ ጨዋታ ለማድረግ የጠየቀው የአማራ ክልል ፌዴሬሽን ጥያቄው ወዲያውኑ ተመልሶለታል።የሤራና ተራ የሽቅድምድም ፖለቲካ የሚጫወተው የወንበዴው ቡድን ህወሓት በቀጣይ የትግራይ ክልል ጨዋታ እንዲያደርግ የጠየቀ መሆኑ በወቅቱ የተዘገበ ጉዳይ ነበር።
ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር የቀጥታ ግንኙነት በማድረጋቸው ታላቅ የፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ የገባው ህወሓት ለኤርትራ የምንቀርበው እኛ ነን፤ በደምም የተሳሰርነው እኛ ነን ከማለት አልፎ “የኤርትራ ልጆች! አማራ ባህራችሁን ይፈልጋል፤ እኛ ትግራዮች ግን የምንፈልገው ፍቅራችሁን ነው” እስከማለት የደረሰ መሆኑ አይዘነጋም።
በመቀጠልም ኢሳያስን ለማባበል እና ኤርትራውያንን ወገናዊ ለማድረግ የኤርትራ ቲቪ ወደ ትግራይ መጥቶ እንዲዘግብ ህወሓት ያቀረበው ጥያቄ ኢሳያስና መንግሥታቸው ከህወሓት ጋር የጎንዮሽ ግንኙነት እንደያማያደርጉ በመግለጽ ጥሪውን ውድቅ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ህወሓትን የፈጠሩትና ማንነቱን የሚውቁት ኢሳያስ አሁን ባለንበት ወቅት ህወሓትን አጥብቀው ይጸየፉታል፤ የወንበዴ ቡድኑንም መሪዎች እጅግ ይንቋቸዋል። ከዚህ አንጻር ህወሓት የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ ጠላት መሆኑን ኢሳያስ በውል ያውቃሉ። (በዚህ ጉዳይ ላይ ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ያቀናበረው ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል)።
ኢሳያስ አፈወርቂ እኤአ ሰኔ 20 (ሰኔ 13) ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ እየተከሰተ ስላለው ለውጥ ካደነቁ በኋላ በዋንኛነት የንግግራቸው ትኩረት የነበረው “መርዘኛ፣ በጣም አደገኛ፣ (ተንኮለኛና ምቀኛ) ስለሆነው የህወሓት ሌጋሲ” ነበር። ሲቀጥሉም የህወሓት “ጥምብ አንሣዎች” ሥልጣናቸውን እንዳጡ ሲያውቁ በመደናገጥ “አዎንታዊውን ለውጥ ለማጨናገፍ” ይህም በሁለቱ አገራትና በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚሠሩ ንግግራቸውን ሊያደምጥ ለተሰበሰበው ሕዝባቸው በግልጽ ተናግረው ነበር። ይህንን ካሉ በኋላ ነበር ከዶ/ር ዐቢይ ጋር የሰላም ግንኙነቱን መስመር ማስያዝ የጀመሩት።
በዚህ ዓይነት የለውጥ ሂደት ላይ የሚገኙት የሻዕቢያ መሪዎች እየወሰዱ ያሉት እርምጃ ህወሓትን ትልቅ ኪሳራና ውርደት ውስጥ ቢከተውም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ለዓመታት ሲመኘው የኖረው ሐቅ ነው በማለት ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ ግለሰብ ይናገራሉ። ይህ የማይገባው ህወሓት ግን አሁንም የጥላቻ ፖለቲካውን ለመተግበር ከላይ ታች ደፋ ቀና ይላል፤ ባይሳካለትም ሙከራውን ይቀጥላል፤ ሁሉንም የሚያደርገው ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ስም ስለሆነ እንዳንዱ የትግራይ ሕዝብ ይህንን የህወሓት መሠሪነት አጥብቆ በመቃወም ዶ/ር ዐቢይ እንዳሉት “አንቅሮ ሊተፋቸው” ይገባል። ሕዝብ የተፋው ህወሓት ከነወንበዴ መሪዎቹ ወደ መቃብር መግባቱ የማይቀር ይሆናል በማለት አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል።
ማስተካከያ – የማነ ገብረአብ ተናገሩት ብለን የጠቀስነው ህወሃት በEritrea Press ስም በከፈተው ማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ ሆኖ ስላገኘነው ከይቅርታ ጋር መረጃውን አንስተነዋል። ከአንባቢዎቻችን በውስጥ መስመር በደረሰን መረጃ መሰረት ከታላቅ ይቅርታ ጋር ማስተካከያ አድርገናል። በEritrean Press ስም የተከፈቱት ሁለቱም የማኅበራዊ ድረገጾች (አንዱ እውነተኛ የኤርትራ ፕሬስ ሲሆን ሌላኛውና አነስተኛ ተከታይ ያለው የህወሓት የሳይበር አርበኞች የከፈቱት መሆኑ ይታወቃል) አወዛጋቢ ሆነው መቆየታቸውን ብናስታውስም ይህንን መረጃ ግን በወቅቱ በፋይል ክምችታችን ውስጥ አስቀምጠነው ስለነበር በመዘንጋት እንደትክክለኛ መረጃ አውጥተን ልንጠቀምበት ችለናል። ለስህተቱ ሙሉ ኃላፊነት እንወስዳለን።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
Biniam says
እርማት ይደረግ፡
“የማነ ገብረአብ” ተናገሩት ተብሎ ” Eritrean Press ” የተባለው በቅርብ በወያነ የተገነባ ወብ-ሳይት በመጥቀስ አማካሪው አቶ የማነ ገብረአብ ያልተናገሩት ነውር የሐሰት ወሬ ተቅሳቹ እንደ source መጠቀማቹ ትክክል አይደለም። ወያነ “Eritrean Press ” የሚባል እውነተኛው የኤርትራ ወብ-ሳይት ስም በመጠቀም አካውንት መፍጠሩ እና ይህን የሚያጋልጥ በ ሶሻል ሚድያ ተሰረጭተዋል። ለተጨማሪ
Be Aware Of Fake ‘Eritrean Press’ Accounts on facebook https://twitter.com/EriLoveer/status/1020405837418967040
Editor says
Biniam
ለአስተያየቱ እናመሰግናለን። ከእርስዎና ከሌሎች በውስጥ መስመር በደረሰን መረጃ መሰረት ከታላቅ ይቅርታ ጋር ማስተካከያ አድርገናል። በEritrean Press ስም የተከፈቱት ሁለቱም የማኅበራዊ ድረገጾች (አንዱ እውነተኛ የኤርትራ ፕሬስ ሲሆን ሌላኛውና አነስተኛ ተከታይ ያለው የህወሓት የሳይበር አርበኞች የከፈቱት መሆኑ ይታወቃል) አወዛጋቢ ሆነው መቆየታቸውን ብናስታውስም ይህንን መረጃ ግን በወቅቱ በፋይል ክምችታችን ውስጥ አስቀምጠነው ስለነበር በመዘንጋት እንደትክክለኛ መረጃ አውጥተን ልንጠቀምበት ችለናል።
ለስህተቱ ሙሉ ኃላፊነት እንወስዳለን።
ከታላቅ ምስጋና ጋር
የጎልጉል አርታኢ
Tesfa says
አወናባጅ ሃይሎች ዛሬም በመልካም ነገር ላይ ጥላሸት መቀባትና ህዝባችንን መከፋፈል ቋሚ ተግባራቸው ነው። የኤርትራው መሪ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር መጎብኘት ዳንኪራ አያስመታም። ሃገሩ ነው። ችግሩ ሰልፋችን ሁሉ የአስረሽ ምቺው ሆነና አቋቋማችን ተንጋደደ። የምናስበውና የምንተነፍስበት ጭንቅላትና ሳንባ በፓለቲካና በዘር ዙሪያ የተገጠመልን በመሆኑ የተከታይ ተከታይ ሆነን እንሆ አንድ የሚያረጉንን ነገር እያፈረስን በሚያራርቁን ላይ እሳቱ ቦግ ብሎ እንዲነድ ነዳጅ ስናቀርብ ቆይተናል። ይህ ጊዜ ማንም ያላተረፈበት የኪሳራ ዘመን እንደነበር አቶ ኢሳይያስ በግልጽ አስቀምጠውታል።
አሁን በኢትዮጵያና በኤርትራ የተደረሰው ስምምነት የውጭ ሃይል ያልገባበት፤ በሁለት መሪዎች መካከል የተፈጸመ ተግባር ነው። ይህ ራሱ ህዝባችንን ሊያኮራ ይገባል። የራስን ችግር በራስ መፍታት። ይህ ግን በዘራቸውና በጥቅማቸው ለሰከሩ አይታያቸውም። ልምዳቸው እየቀሙ እየገደሉ እያሰሩ መኖር ነውና! ይህንም አጥፊ ስራቸውን ለማበራከት በእየ ድህረ – ገጽ የፈጠራ ወሬ መንዛታቸው አንሶ መሳይ ድህረ – ገጾችንም በማቅረብ ህዝባችንን ለማወናበድ የሚያደርጉት ሴራ ዛሬም አልተገታም። የጎጥ ፓለቲከኞች ዛሬም አካኪ ዘራፍ ከማለት አላለፉም። ሃገርና አፍሪቃ አቀፍ እይታ ኑሮአቸው አያውቅም። በነጻነት ስም ባርነትን፤ በህዝብ ስም ንግድን የለመድ እኔ አውቅላችሁሃለሁ የሚሉ ጎጠኞች ዛሬ ወድቀው በመፈራገጥ ላይ ናቸው። ለበደልና ለግፍ ማብቂያ አለው። የእናንተ ቀን ለማክተሙ ምስክር አያሻም። ህዝባችን ወደ ነበረበት የግፍ ዓመታት ላይመለስ ቆርጦ ተነስቷል። ለፕሬዝደንት ኢሳያስም መልካም ጉዞና የጉብኝት ጊዜ እንዲሆንላቸው ከወዲሁ እመኛለሁ።