‹‹መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም፡፡›› ሕገ መንግስት አንቀጽ 11 ንዕስ አንቀፅ 3፡፡
‹‹ማንኛውም ሰው የማሰብ፤ የሕሊና እና የሃይማኖት ነጻነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይመኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡›› ሕገ መንግስት አንቀጽ 27 ንዕሱ አንቀፅ 1፡፡
‹‹ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነጻነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ ማስገደድ ወይም መከልከል አይቻልም፡፡›› ሕገ መንግስት አንቀጽ 27 ንዕስ አንቀፅ 3 ፡፡
የሙስሊሞች ጥያቄ
1ኛ. በስልጣን ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች ያለምርጫ የመጡና ህዝቡን የማይወክሉ በመሆናቸው ህዝቡ በነፃ ፍላጎቱ፤ በገለልተኛ አስመራጮች እና በመስጂድ ደረጃ በሚመርጡ አመራሮች ይተኩልን፡፡
2ኛ. አህባሽ የተባለው እምነት እንደ ማንኛውም እምነት እራሱን ችሎ የመንቀሳቀስ መብት ይኖረዋል እንጂ በሙስሊሙ መስጂዶችና መዋቅር ውስጥ በግድ እንዲጫን ሊደረግ አይገባውም ፡፡
3ኛ. አወሊያ የህዝብ ንብረት እንደመሆኑ መጠን እራሱን በአግባቡ ማስተዳደር ለማይችለው መጅሊስ መሰጠት የሌለበት ሲሆን ህዝብ በሚመርጣቸው የቦርድ አባላት ይተዳደር ፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች ለመንግስት ለማድረስና መፍትሄ ለማፈላለግ ደግሞ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በራሱ ፍቃድ 17 አባላት ያላቸውን ተወካዮች (ከሃገር ሽማግሌዎች፤ ከሃይማኖት ኣዋቂዎች፤ ከምሁራን እና ከሰባኪያን) ጥቆማውን በመቀበል እና ከመላ ሃገሪቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የተፈረሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የድጋፍ ፊርማዎችን በማስረጃነት በመያዝ እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች ብቻ በመያዝ ምላሽ ለማፈላለግ ከላይ ታች ሲሉ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሜቴዎች ስምንት ወራት አለፉ፡፡ በሂደቱ ከክፍለ ከተማ እስከ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ሁሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ድረስ እነዚህን ጥያቄዎች በመተንተን በተለያየ ግዜ አቅርበዋል ውጤቱ ግን አራተኛ ጥያቄ ወለደ እሱም፡-
4ኛ. ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ለመንግስት ለማድረስና መፍትሄ ለማፈላለግ ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን በመወጣታቸው ለእስር የተዳረጉ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሜቴዎች ይፈቱ ፤የሚል ነው፡፡
ሆኖም በምድር ላይ የሚከናወኑ ነገሮች ሁሉ ፖለቲካዊ እንድምታ አላቸው ከሚል የተቆነጠረ ሃሳብ በመነሳት ምክንያቲዊ እና ወቅታዊ ነገሮችን ግምት ውስጥ ሳያስገብ ተቃራኒን ሃሳብ ለማሸነፍ ወይም ድጋፍ ለማግኘት ተብሎ መሰረታዊ የህግ ስእተት እና ፖለቲካዊ ወለምታ ከመዳረግ በፊት በመግቢያነት የተጠቀሱት የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎችና የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ጎን ለጎን በማስተያየት የተሻለ ሃሳብ እስኪገኝ ድረስ ለድምዳሜ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
በመሆኑም ከላይ የተገለጹት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ የመብት ጥያቄዎች ናቸው መብት ደግሞ ከህግ የሚመነጭ ሲሆን የህግ ጥያቄ መጠየቅ በራሱ ፖለቲካዊ ጥያቄ መሆን አይችልም፤የፖለቲካ ጥያቄ መሆን የሚችለው እስላማዊ መንግስት እናቋቁም ወይም ፖለቲካዊ ሥልጣን ይኑረን እና የመሳሰሉት ከሙስሊሙ ማህበረሰብ የተነሱ ሃሳቦች እና በዚህ ምክንያት የደረሰ ጉዳትና እስራት ቢኖር ሂደቱ ፖለቲካዊ ነው ብሎ በመደምድም በጉዳዩ ላይ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት አቋም መያዝ ይቻላል ግን እውነታው የመብት እንጂ ፖለቲካዊ ጥያቄ አለመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪ እነዚህ ግልፅ የመብት ጥያቄዎች በሃይል በመጠምዘዝ ፖለቲካዊ ይዘት ለማላበስ በመንግስት የሚደረገው ጥረት ለማንም ግልፅ ቢሆንም የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎች ንፁህ የመብት ጥያቄ ነው፤የፖለቲካ ጥያቄ ነው ለማስባል ተራ አሉባልታ ለማጠናከር ተደጋጋሚ በእውነት ላይ ያልተመሰረተ ዘጋቢ ፊልም በኢቲቪ በማቅረብ ያልተሳካ ጥረት ተደርጓል፤ በቀጣይም ይበልጥ ተጠናክሮ የህዝብን አንድነትን ሊንዱ በሚችሉ መልኩ ተቀነባብሮ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
ይሁን እንጂ ከሃይማኖታዊ መቻቻል ባለፍ ሃይማኖታዊ መከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኝነትን ባዳበር ህዝብ መካከል አንዳችም አስፈሪ ነገር እንደማይኖር ይገመታል፤ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የሙስሊሙ ማህበረስብ ጥያቄ ከእምነት ነፃነት መብት የመነጨ ጥያቄ መሆኑን በመረዳት የሌላ እምነት ተከታይ ለሙስሊም ማህበረሰብ ጥያቄ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያለሆነ ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል ይህ ደግሞ የመንግስትን አፍራሽ ተልኮ ያጋለጠ ነው፡፡
በመሆኑም የሙስሊሞች ጥያቄ ከህገ መንግስቱ ጋራ ሲመሳከር ሙሉ በሙሉ የመብት ጥያቄ ነው ለዚህም ነው ከአንድ ዓመት ከ 6 ወር በላይ ‹‹ ፍትህ ፍትህ ፍትህ ፍትህ………. ›› ሲሉ የከረሙት መንግስት ደግሞ በተቃሪኒው ‹‹ የሃይማኖት አክራሪነት ለማስፋፋት እና ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የሚጥሩ ›› በማለት እየወነጀላቸው ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የሙስሊሞች ጥያቄ ሃይማኖታዊ ጥያቄ ነው ፡፡
ስለሆነም የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ እና የመንግስት ተሳትፎ በማስተያየት ጥያቄው ሃይማኖታዊ እንጂ ፖለቲካዊ ላለመሆኑ እነዚህን ማስረጃዎችን መመልከት ተገቢ ናቸው፡-
1ኛ. መንግስት በቀጥታ እጁን በማስገባ የመጅሊስ ምርጫ በቀበሌ እና በመንግስት ካድሪዎች እንዲካሄድ አድርጓል፡፡የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ደግሞ የመጅሊስ ምርጫ በተቻለ ፍጥነት እና በገለልተኛ አስመራጭ አማካኝነት ምርጫ መካሄድ የሚኖርበት ሲሆን ጉዳዩም ሃይማኖታዊ እንጂ ፖለቲካዊ ባለመሆኑ በመስጂድ ሊካሄድ ይገባዋል፡፡
2ኛ. አህባሽ የተባለው እምነት ሸኽ አብደላ አልሃረሪ በሚባሉ የሚመራ እምነት በመንግስት ልዩ ድጋፍ ተደርጎለት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ በወኑት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም አማካኝነት ሃምሌ 2003 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ይህንን አመለካከት በሃገራችን ለማስፋፋት እንዴት ብንሰራ ይሻላል በሚል መንግስት ለረጅም ግዜ ሲመክር ቆይቷል›› በማለት በሰጡት ሰፊ ጋዜጣዊ መግለጫ የአህባሽ እምነት ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ከመኖሩ ባለፈም አስተምህሮቱን መንግስት ለማስፋፋት ፍላጎት እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ደግሞ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ሃይማኖትም በመንግስት ጣልቃ አይገባም፡፡ የሚለውን ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ተጥሷል በተጨማሪ አህባሽ የተባለው እምነት እንደ ማንኛውም እምነት እራሱን ችሎ የመንቀሳቀስ መብት ይኖረዋል እንጂ በሙስሊሙ መስጂዶችና መዋቅር ውስጥ በግድ እንዲጫን ሊደረግ አይገባውም ፡፡
3ኛ. አስተዳደራዊ የሆነ ጥያቄ ሲሆን እሱም አወሊያ ት/ት የህዝብ ንብረት እንደመሆኑ መጠን እራሱን በአግባቡ ማስተዳደር ለማይችለው መጅሊስ መሰጠት የለበትም ህዝብ በሚመርጣቸው የቦርድ አባላት ይተዳደር የሚለው የህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄ ነው ፡፡ ይህን ጥያቄ በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል አንድም መጅሊሱ የሙስሊሙ ማህበረስብ ውክልና እንደሌለው ሁለተኛ ደግሞ የአወሊያ ት/ት አስተዳደር ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ካስፈለገ የተለያዩ መመዘኛዎችን መሰረት በማድረግ ህዝብ በሚመርጣቸው የቦርድ አባላት ይተዳደር የሚል ነው፡፡
4ኛ. ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮችን ለመግለፅ እና ለችግሮቹሁ መፍትሔ ለማፈላለግ የተመረጡ የኮሜቴ አባላት ከመንግስት ተወካዬች ጋር በተደጋጋሚ በመገናኘት ጥያቄው ሃይማኖታዊ መሆኑ እና መፍትሔም ሊገኝለት የሚችለው ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ ብቻ መሆኑን ሲያስረዱ ሰንብተዋል፤ መንግስትም በጉዳዩ ላይ ከኮሜቴ አባላት ጋር ሲደራደር ቆይቷል፡፡ይሁን እንጂ መንግስት በስተመጨረሻ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ተልካሻ አስተሳሰብ በመነሳት የኮሜቴ አባላትን በሽብርተኝነት ስም ከሶ ለእስር ዳረጋቸው፡፡
ይሁን እንጂ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ሲመረመር በየትኛውም መመዘኛ የሃይመኖት ነፃነት መብት ጥያቄ ነው ፤ በመንግስት በኩል ደግሞ እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ አካሄድ ነው ለዚህም ነው ጥያቄችን ሃይማኖታዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም በማለት ከመናገር እና ከመፃፍ ባለፈም ሰላማዊ በሆነ መንግድ በተለያ ቦታና ጊዜ ድምፃቸውን ሲያሰሙ የከረሙት፡፡ የነገሩ አካሄድ እንዲ በሆነበት ሁኔታ የሙስሊሞች ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው በማለት ከፖለቲካ ፓርቲ መገለጹ ከስእተትም በላይ ስእተት ነው፤ ነገ ደግሞ ከችግሩ ለመላቀቅ በአቻነት አብረን እንስራ ወደሚል ጥያቄ እንዳያመራ ያሰጋል ፡፡ ነግር ግን በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶች እንዲከበሩ አደርጋለው ለዚህም ድጋፋቹሁን ስጡኝ ብሎ የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎ መታገል እና ጥያቄ ማቅረብ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠበቅ ተግባር ነው ፡፡
Leave a Reply