“የዜግነትና የሰውነት መሰረታዊ መብቶች በተከበሩ ጊዜ ሌሎች መብቶች ሁሉ ይከበራሉ” የሚል ዋና መርህ ያለው በወጣት አመራሮች የተገነባው ሰማያዊ ፓርቲ ገበሬው ነጻ እስካልወጣ ድረስ ችጋር ከኢትዮጵያ ምድር ሊጠፋ እንደማይችል አሳሰበ። የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌታነህ በፓርቲያቸው ድረገጽ ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ ኢህአዴግ ታላቅ ገድል አድርጎ የወሰደውን የጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት አስመልክቶ “ላይመለስ የሄደ ሰው ነበር፤ ባዶ ቦታ ነበር። ምክትሉ ተተኩ” ሲሉ የስልጣን ሽግግር አለመካሄዱን ጠቁመዋል። የዛሬ መቶ ዓመት የተደረገውን የስልጣን ስያሜ የተሻለ ነበር ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመሰረቱ መነሳት ያለበት ከግለሰብ መብት ላይ መሆን እንዳለበት እናምናለን” በማለት ለግለሰብ መብት መከበር ያላቸውን ጽኑ እምነት ኢንጂነር ይልቃል ጌታነህ “ሰው ከመብላትና ከመጠጣት ባለፈ በሰውነቱ ሊጠይቃቸውና ሊመልሳቸው የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች” እንዳሉ በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ባስተላለፉት መልዕክት ተናገረዋል።
ፓርቲያቸው ከሚያምንባቸው መሰረረታዊ ጉዳዮች መካከል የመሬት ባለቤትነት ዋናው መሆኑንን ያመለከቱት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንብር “… ገበሬው ከካድሬና ከመንግሥት ጭሰኝነት ነፃ ከሆነ እምቅ አቅሙን አውጥቶ በመጠቀም መሬቱን የመጠበቅና የመንከባከብ፣ የማልማትና በባንክ የማስያዝ፣ እንዲሁም የማውረስ፣ የመሸጥና የመለወጥ መብት ይኖሩታል” የሚል የጸና እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።
ለፌዴራል አወቃቀር ኢትዮጵያ በታሪኳ እንግዳ አለመሆኗን ያመለከቱት ኢንጂነር ይልቃል አሁን እንደሚባለው በጐሣ ከረጢት ውስጥ ያሉ ጎሳዎች ተስማምተው አገሪቷን ገና እንደ አዲስ እየፈጠሯት እንደሆነ የሚያስመስለው አቀራረብ ትልቅ ስህተት እንደሆነ አመልክተዋል። “ታሪክን በመፈልሰፍ አንድ ጐሣና አንድ ጐሣ እንደተዋጉ የሚያስመስለው አቀራረብም በፍፁም የተሳሳተና አውዳሚ ነው፡፡ መንግሥት ከመንግሥት፣ የአካባቢው አገዛዝ ከአካባቢው አገዛዝ ተጣልተው ያውቃሉ እንጂ አንድ ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ ጋር በታሪክ ለዚያውም በታቀደ ሁኔታ ጎሣን መሠረት አድርጎ የተደረገ የፖለቲካ ትግል በአገራችን ውስጥ የለም፡፡ ይሄ ከቅርብ ጊዜ በኋላ በጥራዝ ነጠቅነት ሣር-ቅጠሉ ኮሙኒስት በነበረበት ከ66ቱ አብዮት ጋር ተያይዞ እንደወረደ ስለተቀበልነው የመጣ ነገር እንጂ የአገራችንን እውነተኛ ገፅታ የሚያሳይ አይደለም ብለን እናምናለን” በማለት በብሄር ብሄረሰቦች መፈቃቀድ አዲስ ኢትዮጵያ ስለመገንባቷ አጥብቆ የሚናገረውን የኢህአዴግን ቅስቀሳና ትምህርት ነቀፈዋል።
በተወሳሰበ የሞራል ቀውስ እንዲገባ ስለተደረገው የወጣቱ ክፍል ተጠይቀው “ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው። በራሱ በምርጫው ያደረገውም አይደል” ካሉ በኋላ ወጣቱ “… ሽንፈቱ ዘላቂ እንዳይሆን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ወደ አሸናፊነት ለመውጣት ሁልጊዜ ተሸንፌያለሁ በቃ! ብሎ አለመቅረት አንዱ ወሳኝ የመፍትሄ ጉዞ ነው፡፡ ከዛ ባለፈ ደግሞ የህይወት መርህ መመዘኛውን ወይም የሞራል እሴት መሠረቱን /Value-Judgment/ መቀየር ነው፡፡ ሰው አካል አለው፣ አእምሮ አለው፣ መንፈስ አለው፡፡ ለአካሉ ነው የሚመገበው፡፡ ይህ የእንስሳነት ባህሪያችን ነው፡፡ እኛን ከእንስሳት የለየን ሰውነታችን በሞራል መመዘኛ ስለሌሎች ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ይህም ነው የሰውነት ልዩ ባህሪያችን፡፡ ስለዚህ ስለሌሎች ማሰብ፣ ኢ-ፍትሃዊነትን አለመቀበል፣ አለመስረቅ የሞራል መርሆዎቻችንና የሰውነት መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ ሰው ስንባል አምላክ ሲፈጥረን ይሄ አብሮ የተሰጠን ነገር ነው፡፡ በመሆኑም አምላክ የሰጠኝን ሰውነቴን አላዋርደውም ይበል ወጣቱ! ስጋዬ ብቻውን አልተፈጠረም። አካልም፣ አእምሮም፣ መንፈስም አንድ ላይ ያለኝ ነኝ ሊል ይገባዋል፡፡ ስለዚህ የአእምሮዬን የመንፈሴንና የሰውነቴን ባህርይ ትቼ በእንስሳነቴ ብቻ አልኖርም ብሎ ቆራጥ አቋም መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ያ በሆነ ጊዜ ከውድቀታችንም ለመቃናት ራሳችንንም ተጠያቂ ለማድረግ ዕድል ይሰጠናል” ብለዋል ሙሉው ቃለ ምልልስ እዚህ ላይ ይገኛል።
Leave a Reply