ከፍጥነት ወሰን በላይ በመንዳት የሚደርሰውን የትራፊክ ጉዳት ለመቀነስ በተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲገጠም መወሰኑን ተከትሎ፣ በፌደራል መንግሥት ፈቃድና የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው አቅራቢዎች ለኦሮሚያ ክልል እንዳያቀርቡ የገበያ ገደብ እንደተጣለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
በዚሁ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የመሰረቱት “ኢትዮ መላ የተሸከርካሪዎች ፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አስመጥቶ መግጠም ዘርፍ ማኅበር” ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፣ በኦሮሚያ ክልል 17 ሺሕ ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ እንዲገጠምላቸው ተወስኖ ከሕግ አግባብ ውጪ ለአንድ ግለብ ተስጥቶ ሌሎቹ በነጻ ገበያ እንዳይሳተፉ ተከልክለዋል ብሏል።
የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ በክልሉ የሚገኙ የተሽከርካሪ ባለንብረት ማኅበራት፣ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ከአንድ ግለሰብ ጋር ውል ገብተው እንዲያስገጥሙ ትዕዛዝ በመስጠት ውል እንዲገቡ አድርጓል ተብሏል። ቢሮው ማኅበራቱ ከአንድ ግለሰብ ጋር ውል እንዲገቡ የተደረጉት ዋጋውን ጭምር በመወሰን በማስፈራራት መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል።
ከማስፈራሪያዎች መካከል ከተባለው ግለሰብ የፍጥነት መገደቢያ የማታስገጠሙ ከሆነ ወይም ከሌላ አቅራቢ የምታስገጡሙ ከሆኑ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አትሆኑም የሚል እንደሚገኝበትም ማኅበሩ ጠቁሟል።
የቢሮው ውሳኔ በዘርፉ የተሰማሩ የማኅበሩ አባላት በሕግ የሰጣቸውን በነጻ ገበያ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ መብት፣ እንዲሁም የተሽከርካሪ ባለንብረቶቹ በነጻ ገበያ በጥራትና ዋጋ አወዳደረው የመግዛት ዕድላቸውን የነፈገ መሆኑን ማኅበሩ ገልጿል።
ማኅበሩ ግለሰቡ ያሰረው ውል እንዲቋረጥና አባላቱ በነጻ ገበያ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለፌደራልና ኦሮሚያ ክልል ጸረ ሙስና ኮሚሽን እና ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ቅሬታ ለማስገባት ደብዳቤ አዘጋጅቻለሁ ብሏል።
የቴክኖሎጂ አቅራቢዎቹ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የተረጋገጠ ጂፒኤስ የተገጠመለት የፍጥነት መገደቢያ ቴክኖሎጂ፣ መንግሥት በፈቀደላቸው የቀረጥ ነጻ ዕድል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አስገብተው የገበያ ዕድሉ በመታገዱ እየከሰሩ መሆኑም ተነግሯል። (አዲስ ማለዳ)
Leave a Reply