በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ የተለያዩ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች እና ሰነዶች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው 32 ቀበሌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውሰጥ ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት በተደረገ ፍተሻ የጦር መሳሪያዎች እና ሰነዶች መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ላይ ጥናት በማድረግና የፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ በማውጣት በተደረገ ብርበራ 85 የክላሽን-ኮቭ እና የሽጉጥ ጥይቶች፣ 3 ሽጉጦች ፣ 2 ሳንጃዎች እና 1 የእጅ ቦንብ መያዙን ነው ፖሊስ የገለፀው፡፡
በተጨማሪም 10 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እና በርካታ ፓስፖርቶችን ጨምሮ የትምህርት ማስረጃዎች በግለሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ መገኘታቸውን ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ዳይሬክቶሬት መረጃው መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቡ በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የተሰማራና በሃገራችን አሁን ያለውን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ለዚሁ ህገ-ወጥ ድርጊት መሸሸጊያ ባዘጋጀው ከጣውላ የተሰራ ሳጥን ውስጥ የጦር መሳሪያዎቹን ደብቆ ለማዘዋወር በዝግጅት ላይ እያለ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply