… ለመሆኑ ከየት መጣን?…. ወዴት እንሄዳለን? …እንዴትስ እንኑር? የሚሉትን የፈላስፋውን ጥያቄ ስናነሳ፣ ግሪክ አገር አቴን ከተማ የዓለም ፈላስፋዎች ሰሞኑን ተሰብስበው “ስለ ዓለም ሁኔታ ይነጋገራሉ” ብለን አልገመትንም ነበር።
እኛ በዚህ እትማችን ሰለ ዓለም ሳይሆን ስለ እኛው ስለ ራሳችን ችግር ነው አንዳንድ ነገሮቸን አንስተን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብትን መለስ ብለን ለመመልከት የተነሳነው።
“…እንዴት እንኑር? ” የሚለው ጥያቄ ሲሰነዘር የሚያስቆጣቸው ሰዎች እንደሌሉ ተስፋ እናደርጋለን።
አንደንድ ጊዜ ከረጅም መላ-ምትና ግራ ከሚያጋቡ ጠማማ ጽንሰ-ሓሳቦች፣ ከቲዎሪ ዎች ይልቅ ቀላልና ጥሩ ጥያቄ ማቅረብ ፣ሌላውም ጎረቤት አገር ሆነ ራቅ ያሉ ሰዎች “እነሱስ እንዴት ይኖራሉ ?”ብሎ እራስን መጠየቅ ከብዙ ድካምና መነከራተት ያድናል።
ግን ደግሞ ወደፊት ዘልቃችሁ እንደምታነቡት ፣ እንደዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት በደንብ ከአልተወያዩበት የአርባና የሃምሳ አመት መከራ ውስጥ አንድን ሕዝብ ከቶ አገሪቱን ያተረማምሳል። እንኳን እኛ “እንዴት እንኑር ?” ብለን ከሩሲያ በተዋስነው ትምህርት “በቀላሉ ነጻ ልንወጣ” ቀርቶ ራሺያ እራሱዋ ከገባችበት ማጥ ለመውጣት ከሰባ አመት በላይ ፈጅቶበታል ።
“…እንዴት እንኑር? ወዴት እንሄዳለን? ከየት መጣን ” የሚለው ጥያቄ የፈላስፋዎች ጥያቄ -ወረድ ብለችሁ እንደምታዩት- ብቻ አይደለም። ግን አንድ ክፍል ከሌላው በልጦ፣ የግንባር ቀደምነት ቦታውን ይዞ “…እኔ ያልኩት ከአልሆነ፣ ሞቼ እገኛለሁ፣ አለበለዚያ ዋ! አንተ ከአልተቀበልክ፣ እኔ አንተን እገደልሃለሁ…” የሚል የምሁር ክፍል አለ። እሱ ነው እንግዲህ የእኛ የዛሬው እትማችን አርዕስት።
ምሁሩ በጅምላ ሲታይ በሕብረተሰቡ ውስጥ ጥቂት አይደለም። እነሱም በተለያዩ መስኮች ውስጥ ተሰማርተው እራሳቸውንም ሕብረተሰቡንም፣ አገሪቱንም ቤተሰቦቻቸውን በአእምሮ ሥራቸውና ችሎታቸው ይረዳሉ ። ግን ከእነሱ አንዱ ክፍል -ቀጥሩ ትንሽ ቢሆነም- በጩኸቱ፣ በክርክሩ፣ በጽሑፉ፣ ግርግር በመፍጠሩ፣ በክሱ፣ በብዕሩና በምላሱ፣ በመቀስቀስና በማደረጀት ችሎታው፣ በአፍዝ አደንግዝነቱ…ጠቅላላውን መድረክ በመያዝ ችሎታው ማንም የሚደርስበት የለም። እሱም “አቫንጋርዱ የሙያ አብዮተኛ ” የሚባለው ትንሽ ክፍል ነው።
ይህ ክፍል (ፖለቲካ ምንድነው ? በሚለው መጣጥፍ ላይ አንሰተናል) ለሠራውና ለሚሰራው ሥራ ኃላፊነትና ተጠያቂነት እማይሳማው ነው። በዚህም ከሌሎች ሕግ አክባሪ ፖለቲከኞች ፍጹም ይለያል።
ኃላፊነት መቀበል ምንድነው? በአጭሩ “ሁሉን ነገር ማድረግ ስችል ለምን አላደርገውም “ብሎ መነሳት ነው። ሃምሳ ሚሊዮን፣ ሰባ ና ሰማኒያና ከዚያም አልፎ ዘጠና ሚሊዮን በሚኖርበት አገር፣ አምስትም ሚሊዮን ይሁኑ “….ጥቂት ሰወች ተሰባስበው እኛ ለአንተና ለአንቺ፣ እንዲያውም ለሁላችሁም የአሰብነው የአኗኗር ዘይቤ ወይም ሥርዕት ይህ ነው፣ ወደዳችሁት ጠላችሁት ተቀበሉት፣ ከዚያ ወጭ ትንሽ ትንፍሽ ብትሉ…” ተብሎ ፖለቲካ የሚሰራበት ዘመን ከምሥራቁ ዲክታተሮች ጋር አብሮ አልፎአል። ይህ ጊዜም አክትሞአል።
የአሁኑ እትም አተኩሮ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በእሲያ በሥራቅ አውሮፓም ጭምር ፣አንድ የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ እንዴት በጥቂት ምሁሮች አመካኚነት እንዴት ተስፋፍቶ እንደመጣና “የሰውን” ልብና አእምሮ ፣የእራሳቸውንም “የፈጣሪዎቹና የተከታዮቸንም ” መንፈስ ይዞ እነሱን እንዴት “አገልጋይ ባሪያቸው” እንዳደረጋቸው ከብዙ በጥቂቱ ለማሰየት ነው።
እገረ መንገዳችንን “እኛ ማነን!” የሚለውን ስለ አሜሪካን ክሬዶ ፣…አሜሪካንን አሜሪካ ስለ አደረገው ፣ መንፈስ፣ እሱ ጸሓፊው ሳሙኤል ሐንቲንግተን “እስፐሪት” ቀደም ሲል የጻፈውን መጽሓፍ ተመልክትን አጠር ያለ ግርፋትና ክትበት ሰጥተናል።
እንዴት እንኖራለን? እንዴት አብረን እንኑር ? እናውቃለን አወዛጋቢ ጥያቄ ነው። ግን በዘጠና ሚሊዮን ሕዝብ መካከል “ኢሚንት የማይሞሉ የፖለቲካ ሰዎችም አጉል ቲዎሪ አንግበው፣ እኛ ያለነው ብቻ…” እያሉ መከራ ከሚያሳዩ ጠለቅ ያለ፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ ነገር በያቀርቡልን ደግ ነው። ያ ቲዎሪ እኮ የ19ኛው ክፍለ-ዘመን ትምህርት ነው። ከእዚያ በላይ ይህን ቲዎሪ የሚያራምዱት ከጠቅላላው የአገሪቱ ምሁሮች፣ በሌላ መስክ ላይ ከተሰማሩት ከእነሱ ጋር ሲነጻጸሩ፣ እንደዚሁ ትንሽ ናቸው።ይህንንም ማወቅ ያስፈልጋል።
ተሽከርካሪ ጎማ ገና ዱሮ ጥንት በተፈጠረበት ዓለም –አውሮፓያኖች፣ ወርቅማ ጊዜህን አዲስ ታይቶና ተሰምቶ ተሞክሮ ፣ የማይታወቅ አዲስ ተሽከርካሪ ጎማ እፈጥራለሁ ብለህ ጊዜህንም ጉልበትህንም አትጨርሰው ይላሉ። ይህም ማለት በአጭሩ አዲስ የሕብረተስብ ሞዴል፣ በዓለም ላይ ታይቶም ተሰምቶም የማይታውቅ እፈጥራለሁ ብሎ መድከም ከንቱ ነው። ያው የምናውቀው የዲምክራሲና የታወቀው የፓርላማ ሥርዓት፣ ነጻው ሕብረተሰብ ይሻለናል።
የነገሮች ሁሉ እምብርት ደግሞ፣ ወዳጄ ! ነጻ ሐሳብ፣ በነጻ-ፕሬስ ላይ ማራመድ ነው። ከሁሉም አቅጣጫ ነገሮችን ሰርስረን “እንዴት እንኑር?” ለሚለው ጥያቄ በየጊዜው መልስ እንሰጣለን።
(የ”ለአእምሮ መጽሔት” ዋና አዘጋጁ ይልማ ኃይለ ሚካኤል)
Leave a Reply