አቶ ዠ፣ ከ Fast Lane ዩኒቨርስቲ በተልዕኮ በአራት ወራት እድሜ የዶክትሬት ድግሪ የተጫነባቸው የክብር ዶክትሬት እንደሚጫንባቸው ጭምጭምታ ተሰማ። ጭምጭምታው ደግሞ ከሁነኛ ምንጮች ነው። በ“ተልዕኮ” ማለት ለ Fast Lane ዩኒቨርሲቲ ደብዳቤ መጻፍና ገንዘብ መላክ ነው ተብሎ ይታማል። ይህን ሃሜት እኔ ጭምጭታ ነው የሰማሁት። ጭምጭምታው ግን ከሁነኛ (አስተማማኝ) ሰው ነው።
አቶዠ፣ቀድሞ በደርግ ጊዜ መፈክር ጸሃፊ፣ በኋላም በኢሃዲግ ጊዜ ልማታዊ ጸሃፌ ተውኔት፣ቀድሞ የኢሃዲግ ፍቅር ቤት ሥራ አስቀማጭ፣ ይቅርታ ሥራ አስኪያጅ፣ በዩናይትድ ኔሽንስ የኢትዮጵያ ተወካይ፣ ለዩናይትድ ኔሽንስ ዋና ጸሃፊነት በራስ አነሳሽነት ተወዳዳሪ፣ ወዘተርፈ…ወዘተርፈ….ወዘተርፈ….እንዳልኩት የክብር ዶክትሬት እንደሚጫንባቸው ጭምጭምታ ተሰማ። ጭምጭምታው ደግሞ ከሁነኛ ምንጮች ነው።
ሆኖም ችግር ተፈጠረ። “እኔ ነኝ የምጭንባቸው፣ እኔ ነኝ የምጭንባቸው” የሚሉ ዩኒቨርስቲዎች ኢትዮጵያን ሞሏት። አንደኛው ዩኒቨርስቲ አንተ እንኳን ይቅርብህ ቢባልና ሊመከር ቢታሰብ “እኔ የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም ስለሌለኝ ነው?” በማለት ኩርፊያ ሁሉ ነካካው። ዋናው ችግር ግን ወዲህ ነው።
እንግዲህ አቶ ዠ መታወቂያቸው ላይ ብሄር በሚለው ሥር “አማራ” የሚል ተጽፏል። ሆኖም ግን አቶ ዠ የአባታቸው አባት አማራ፣ የአባታቸው እናት ደግሞ ኦሮሞ ሲሆኑ፣ የእናታቸው አባት ሲዳማ፣ የእናታቸው እናት ደግሞ ጉራጌ ነበሩ። በዚህ የተነሳ አራት ክልላዊ ዩኒቨርሲቲዎች “እኔ ነኝ የምጭንባቸው፣ እኔ ነኝ የምጭንባቸው” ሲሉ አታካራ ያዙ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ደግሞ አቶ ዠ ለኔ ነው የሚገቡት ሲል አታካራው ውስጥ ጥልቅ አለ። ምክንያት? “አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ክልላዊ አይደለም፣ ፌደራላዊ ነው፣ ብሄር ብሄረሰብን የሚያንጸባርቅ። አቶ ዠ የዚህ ተምሳሌት ናቸው። ብሄር ብሄረሰብን ያንጸባርቃሉና” ሲል ተሟገተ።
ሌላው ችግር ደግሞ አቶ ዠ በምን መስክ የክብር ዶክትሬት ይሰጣቸው የሚለው ነው። አቶ ዠ አብዛኛውን እድሜያቸውን መፈክር በመጻፍ ነው ያሳለፉት። ለምሳሌ በሥነ ጥበብ በኩል፣ በማህረሰብ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ “Doctor of Letters” የሚባል የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ይሰጣል። ለአቶ ዠ ታዲያ “Doctor of Slogan” የሚባል የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ይሰጥ? የክልልና የፌደራል ዩኒቨርሥቲዎች የአካዳሚክ ጉባኤዎች ራስ ምታት ሆኑ አቶ ዠ።
ይህንን ሲሰሙ የአቶ ዠ ባለቤት ወይዘሮ ዘ “በልጅህ በኩል ደግሞ ኤርትራዊ ነህና አሥመራ ዩኒቨርሲቲም ዶክትሬት ልጫንብህ እንዳይልህ” ሲሉ ተሳለቁ። የባለቤታቸው የወይዘሮ ዘ እናትና አባት ”ኤርትራዊ“ ናቸውና።
የግርጌ ማስታወሻ
ይህንን ሙግት አስመልክቶ አንዳንድ ሰዎች አስተያየታቸውን መሥጠት ያዙ። አዛብኞቹ አሥተያየት ሰጪዎች አስተያየታቸው ተመሳሳይ ቢሆንም አንዱ ግን ከሌሎች በመለየት ”የክብር ዶክትሬትነት ማዕረግ የተሰጠው ሰው ማዕረጉን ከስሙ አስቀድሞ በመለጠፍ ሊጠቀምበት ይችላል” ሲሉ ደመደሙ። መልሱ አጭር ነው። ይህ ድርጊት የተለመደ አይደለም። የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን የሰጠው ዩኒቨርስቲ ለሰጠው ሰው “ዶ/ር ዠ” ብሎ ሊጠራ፣ ሊጻጻፍ ይችላል፣ የተሰጣቸው ሰውዬ (ዠ) ግን እንዳይጠቀሙበት ይመከራሉ። ሌሎችም በዚያ እንዲጠሩዋቸው የተለመደና የሚደገፍ ተግባር አይደለም። የክብር ዶክትሬት ብለው የህይወት ታሪካቸው፣ የሥራ ልምዳቸው (CV and Resume) ላይ ሊጠቅሱት ይፈቀዳል።
“Honorary doctorates are listed as an honor or award on a resume, rather than part of education with earned academic degrees.” እንዲሉ። ይህንን መረጃ በመረጃ በሆነው በአሁኑ ዘመን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply