ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ ከነበሩ አካውንቶች ውስጥ 49 በመቶ የሚሆኑት በዲጂታል ወያኔ ቡድን የተከፈቱ አካውንቶች ናቸው ተባለ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በወጣው መግለጫ 122,000 ሀሰተኛ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ ብሏል። ከእነዚህ የሀሰት መረጃ ከሚያሰራጩ አካውንቶች ውስጥ 49 በመቶ የሚሆኑት በዲጂታል ወያኔ ቡድን የተከፈቱ መሆናቸውን አጀንሲው ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም የህውሐት ቡድን በ2013 ዓ.ም ጦርነት በከፈተበት ህዳር ወር ብቻ 17,000 የሚሆኑ ሀሰተኛ የቲዊተር አካውንቶችም በዲጂታል ወያኔ ቡድን ተከፍተው ነበር ተብሏል።የኤጀንሲው የግልጽ ምንጭ መረጃ ኦፕሬሽን ማዕከል ኃላፊ የሆኑት አቶ አሸናፊ ኃይሉ በቡድኑ በተከፈቱ ሀሰተኛ አካውንቶች በአንድ ቀን ብቻ 25,000 የሚደርሱ መልዕክቶች በቲውተር ምህዳሩ ላይ ይሰራጩ እንደነበርም ተናግረዋል።
የህወሐት ቡድን እነዚህን ሁሉ ዘመቻዎች አድርጎ አልሳካ ሲለው ለሽብር ተግባር ተባባሪ ከሆኑ ሃገራት እገዛ በማግኘት እንዲሁም አስቀድመው አስርገዉ ያስገቧቸዉን ሰዎች በመጠቀም ከእውነታ ውጪ የሆኑ ዘገባዎችን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ኤጀንሲው እወቁት ብሏል።
ተዋቂዎቹ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችም ከጥፋት ቡድኑ ጋር የተያያዙ ወይም ለቡድኑ ይጠቅማሉ ያሏቸውን ይዘቶች በፕላትፎርማቸው ላይ እንዲኖሩ ወይም እንዲቆዩ ከመፍቀድ ባለፈ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ ለሌሎች አካላት በስፋት ያሰራጩላቸው (Suggest) ያደርጉላቸው እንደነበረም ሀላፊው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የሀገርን አንድነት ወይም ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ አካውንቶችን የመዝጋትና መረጃዎቻቸው እንዳይሰራጩ የማድረግ እንዲሁም አንዳንድ አካውንቶችን መረጃ እንዳይለጥፉ ከማድረግም ባለፈ ለተለያየ ጊዜ ሲዘጉ እንደነበር አቶ አሸናፊ አብራርተዋል። (ሸገር ኤፍኤም)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply