ለእኔ ለፈጣሪ በታች በጎ ለሚሰሩ የሰው ዘሮች በሙሉ የሚሰጥ ምስጋና ቃል ይስበኛል። ብዙ ጊዜ የመልካምና የበጎ ምግባር ፋና ወጊዎች ስራ ተመልክቸና መስጦኝ ለቀሪው አርአያ፣ ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ምንጭ ነው ብየ ካሰብኩና ካመንኩበት የምስክርነት ቃሌን የምሰጠው ምስጋና በማቅረብ ነው። ይህን ካልኩኝ ዘንዳ የዛሬ የእኔን ምስጋና በአስተዋሽ አመስጋኙ አይታክቴ ለፌስ ቡክ ወዳጀ Eduardo Byrono፣ ለወጣቷን ድምጻዊ ሃኒሻ ሰሎሞን ያላቋረጠ ድጋፍ አድርጎ ለውጤት ላበቃ ጋዜጠኛ ወዳጀ ለጋዜጠኛ ድልነሳው ጌታነህ እና ለድምጻዊ ሃኒሻ እጅ በመንሳት ምስጋና በማለዳ ወጌ ላቀርብ በቀኝ ጎኔ ተነስቻለሁ!
ዘመኑ ረቅቋል፣ ጊዜ ወስደን የምናዘጋጃቸውን ማናቸውም መረጃዎቸ በሰከንድ ልዩነት ከአንዱ ከአድማስ አድማስ መርጨት በቀለለበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚተላለፉ ያልረባቡ ዝባተሎ መረጃዎች እንዳሉ ሆኖ ለሰው ልጅ አስተሳሰብ እድገት ጠቀሜታ ጉልህ ሚና ያላቸው መረጃዎችም ይቀርባሉ። ስለ ሰው ልጅ ፍቅር፣ ሰላም፣ ህብረት፣ ሰብአዊነት ብሎም ስለምኖርባት አለምና ወረድ ሲልም ስለ ሃገር ሰፊና ጥልቀት ያለላቸው ምርመሮችና ጥናቶች እንማርባቸው ዘንድ በሰፊው የመረጃ መረቡ ይስተናገዳሉ። የታደሉት ብጹአን ተመራማሪዎች የምርምር ስራቸውን ሲያቀርቡ መረጃውን በማቅረብና በማሰራጨት የተሰማሩ ብጹአንም መረጃ መርጠውና አደረጃጅተው ወደ እኛ ያደርሱታል. . . ከፋናወጊወቹ የሃገር ልጆች አንዱ ደግሞ ወዳጀ ኤድዋርዶ ቡርኖ ነው …
ከፈረንጆች ተወስዶ በእኛ ሃገር ብዙም ያላዳበርነው ይህ የምስጋናና እውቅናን የመስጠት ይተበሃል አሁን አሁን በስልጡን ወጣትና ጎልማሳው ትውልድ አበረታች መንገድ እየያዘ ለመምጣቱ ኤድዋርዶ ጥሩ ምሳሌ ነው ባይ ነኝ።
ከወደ ምድረ አሜሪካን ሃገር ነዋሪ የሆነ የፊስቡክ ወዳጃ Eduardo Byrono የምናውቀውን ጸሃይ የሞቀውን እውነት፣ እያየነው የማናሰወተውለውን፣ ይዘነው የምንኮራ፣ የማንኮራበትን፣ ግን ጠቃሚውን ሁሉ ሳይታክት እየቃረመ የሚያቀርብልን ወንድም ነው። ወዳጀ ያልሄድንበትንና ረስተነው ዝም ያልነውን የእናት ኢትዮጵያና ህዝቧን ታሪክ አበጥሮ እያስተዋወቀ ያወያየናል። የቀደሙ የተረሱ መረጃዎችን ወደኛ አስፈንጥሮ ማንነትን አብሮን ይፈልጋል፣ ያፈላልጋል። የተደበቀውን ቆፍሮ ያወጣና እውቅናና ምስጋና እንድንሰጥ ያበረታታናል። ኤድዋርዶ እንዲህ እያለ የእናት ሃገር ኢትዮጵያን ባህሏንና ወጓን፣ ጀግኖቿንና ቅርሷን ያለ መታከት ያዘክራል! ምስጋና ለወዳጃችን Eduardo Byrono ይገባል!
ጋዜጠኛውና ድምጻዊዋ …
ወዳጀ ጋዜጠኛ ድልነሳው ጌታነህ ከማመስገኔ በፊት እንዳመሰግነው ምክንያት የሆነችኝ ድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን መስከረም በጠባ ማግስት በዋሽንግተን ዲሲ ስለምታደርገው የሙዚቃ ድግስ በጨረፍታ ከዚያም ስለ እኔ ሃኒሻ ግንኙነት ጥቂት ላንሳ ….
ተስረቅራቂ ግሩም ድምጽ ያላት ድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን በምድረ አሜሪካ የሙዚቃ ድግሷን የምታቀርብ ሲሆን የሙዚቃ ድግሱ አላማ በአፍሪቃ የሚደረገውን የመሬት ቅርምት የአፍሪቃን አህጉር ለእጅ አዙር አገዛ የሚዳርግ መሆኑን የአለም ህዝብ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ መሆኑንም ሰምቻለሁ። በታዋቂው አርቲስት በቦኖ በተዘጋጀው በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ሃኒሻ ግንባር ቀደም በመሆን ዝግጅትዋን ታቀርባለችም ተብሏል። በዚህ ዝግጅት ላይ “ተባበሪ አፍሪቃ!” የሚለው ዘፈኗ በመላ የእለቱ ተካፋይ አርቲስቶች በህብረት የሚዜመው በዋሽንግተን ዲሲ DAR- Constitution Hall በመጭው መስከረም 11 ወይም እአአ Sept 21 , 2014 ሲሆን የመድረኩ ጌጥ ድምጻዊት ሃኒሻን ማየት መታደል ነው።
ድምጻዊት ሃኒሻን የማውቃት ከወራት በፊት በሳውዲ ኢትዮጵያው ስደተኞች ላይ መጠነ ሰፊ ” ከሃገር ውጡልን !” የሳውዲዎች ወከባ በተከሰተበት ወቅት ነው።… ትውውቃችንም እንደ ዋዛ በፊስ ቡክ ጓደኝነት ጠነከረ። በስደተኛው ዙሪያ የማቀርባቸውን የማለዳ ወጎችን አልፎ አልፎ የምትከታተለው እህት በአሳዛኝ ታሪኮች መነካቷ አልቀረም። እናም መረጃውን ተመልክታ ዝም አላለችም። ሌላው ሁሉ ቢቀር በጅዳ ቆንስል ተጠልለው ለሚገኙ በርካታ እህቶች በግል የእርዳታ ድጋፏን ለማድረግ ቀን ተሌት ትወተውተኝ ገባች። ያም ሆኖ እርዳታውን ለማድረግ ተጠያቂነት ባለው ደረጃ የተደራጀ የእርዳታ ማሰባሰብ ባለመኖሩ ብዙም እንድትገፋበት አለመከርኳትም። ግፉአን ኢትዮጵያውያን ታመሙ እና ተጎሳቆለው በተለያዩ የሳውዲ አውራ ጎዳናዎች ወድቀው አገኛለሁ። ግፉአኑን ችግራቸውን “እህ” ብየ አደምጨ፣ ጠይቄና ፎቶ አንስቸ ላልሰሜ የስደትን አስከፊነት ለወገኔ፣ የመብቱን ጥሰት ጠባቂ ማጣት ለሚመለከታቸው አቀርበዋለሁ። ይህንን መረጃውን የምትከታተለው ሃኒሻ “ሌላ ማድረግ ባይቻለኝ በጠራራው ጸሃይ የውሃ መግዣ ካልለሰኩላቸው!” እያለች ለወገን ያላትን ድጋፍ ከሚገልጹልኝ ወገኖች መካከል በቀዳሚነት ስለምትሰለፍ ለድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን ታላቅ አክብሮት አለኝ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከሃኒሻ ጋር አልፎ አልፎ እየተገናኘን ከማህበራዊ ኑሮው እና አልፎም በጥበቡ ዙሪያ እናወጋለን!
ድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን በተለይ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ሁና አማርኛን በመጫወቷ የሚቀየሟት አልጠፉም። ያም ሁሉ በጽኑ ኢትዮጵያዊ ስሜት በሙዚቃ ሰላምን ፣ ፍቅርን አንድነትና ህብረትን መፍጠር ሃገረ ሎንደን የከተመችው የወጣቷ ድምጻዊት የሃኒሻ ሰለሞን ህልም ሆኖ ቀጥሏል!
የድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን ሰብዕናና ለሃገሯ ያላት የማይቆረፍድ ህልም እንዳከብራት አድርጎኛልና ስራዋን እከታተላለሁ አደንቃለሁ። ከድምጻዊት ሃኒሻ ጋር አልፎ አልፎ በቀጭኑ መስመር ስንገናኝ በምናደርገው ጭውውት ከአፏ የማይለየው የሙያ ባልደረባየ ጋዜጠኛ ድልነሳው ጌታነህ ነው! ሃኒሻ በስኬቷ ዙሪያ ደጋግማ ስትናገር “አባቴ ነው” የምትለው የሙዚቃ ስራዋን የሚያንቀሳቅስላት ጋዜጠኛ ድልነሳህ የተባለ ደልዳላ አለቃ አላት! ድምጻዊት ሃኒሻን “አባቴ ነው! ” ባያስባላትን ጋዜጠኛና የሙዚቃ ባለሙያ ወዳጀ በጎ የድጋፍ ስኬት ኮርቻለሁ!
… ጋዜጠኛ ድልነሳው ከሎንደን እኔ ከሳውዲ አረቢያ በዚህና በዚያ ጫፍ ለጀርመን ራዲዮ በዘጋቢነት አብረን ሰርተናል … ሁሉ ሆኖ ድልነሳውን በደንብ የማውቀው በሃኒሻ በኩል በሚደርሰኝ መረጃ ነው! እናም ዛሬ ለወዳጀ ምስጋና ላቅርብ!
ወዳጀ እና የሙያ አጋሬ ጋዜጠኛ ድልነሳው ሆይ! … የወጣቷ ድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን ስኬት የአንተ ያላሰለሰ ብርቱ ድጋፍ ውጤት መሆኑን ድምጻዊት ሃኒሻ ሰሎሞን የምስክርነት ቃል መሆኑን ሰምቸ እንዴት ዝም ልበል? በእርግጥም የሃኒሻ መጎምራት፣ የሃኒሻ ለዚህ መብቃት፣ የሃኒሻ ስኬት ከፈጣሪ በታች የአንተ ብርቱ ድጋፍ ነውና ልትመሰገን ይገባል! የኦሮሞ ባህሏን በኩራት ይዛ ከአማርኛና ከቀረው የሃገሯ የኢትዮጵያ ብሔር ቋንቋ ጋር በማቀንቀን አንድነታችን ለማጎልበት ለምትደክመውን ታዳጊ ወጣት ላደረግከውና ለምታደርገው ድጋፍ ውለታ መላሹ የላይኛው ጌታ እግዚአብሔር ነው፣ እሱ ይርዳህ! እኔም ለበጎ ምግባርህ አመሰግንሃለሁ!
በመጨረሻም ብርቱ ወዳጀ ድምጻዊት ሃኒሻ ሰለሞን አንችም በሰብዕናሽና በሃገር ወዳድነትሽ ኮርቸብሻለሁ!
አመሰግንሻለሁም! በመንገድሽ ሁሉ እግዚአብሔር ይከተልሽ! ቅን ሰው ነሽና ይቅናሽ!
ከአክብሮት ጋር …
ነቢዩ ሲራክ
Leave a Reply