ባለፈው “በሪሞት ኮንትሮል ትግል ማካሄድ …” በሚል በጫጫርኩት መደምደሚያ ላይ ስለነጸነት ጉዳይ ያለችኝን ይዤ እመለሳለሁ ብየ ነበርና ተመልሻለሁ። ከዚያ ቀደም ብዬ ግን ከርዕሱ ጋር ያልተያያዘ አንድ ዳሰስ ላደርገው የፈለግሁት ድንገተኛ ስላጋጠመኝ ጣልቃ አስገብቼዋለሁ። ጉዳይ “ሐገራዊ እርቅ” የሚሉት ነገር ነው። ይህ ጥያቄ በድርጅቶችም በግለሰቦችም እየተነሳ ይገኛል። በቅርቡም ዶ/ር አክሎግ ቢራራ “አገርን እንደ እናት ያለመቀበል አደጋ እና ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት” በሚል ባቀረቡት 6 ገጽ ጽሁፍ ውስጥ በመደምደሚያው ላይ ይህንኑ የአገራዊ ዕርቅ ጥያቄ እንደሚከተለው አስቀምጠውታል፡-
“ምን መፍትሄ አለ? ይሔን ጽሁፍ ለማጠቃለል፤ አፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ በዘር ጥላቻ የተመረዘች አገር ነበረች። የጥቁሩን ሕዝብ በጭካኔ ትጨፈጭፍ፤ ታስር፤ ታጉርና ታሳድድ ነበር። ለብዙ አስርት ዓመታት የደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ፤ ለጥቂት ነጮች አይተውት የማያውቁት ገቢና የድሎት ኑሮ ከማመቻቸቱ ባሻገር ለማምረት፤ ለብዙሃኑ የጥቁር ሕዝብ የስራ እድል ለመፍጠር ያልቻለበት ዋና ምክንያት የስርዓቱ ትኩረት ሕዝብን አፍኖና ቀጥቅጦ በመግዛት ላይ ስለሆነ ነው። በጥቂት ነጮች የበላይነት ይተዳደር የነበረው ስርዓት ለስለላ፤ ለአፈናና ሌላ የሚያወጣው ኃብት ብዙ ፋብሪካዎች ሊያሰራና የስራ እድል ሊፈጥር ይችል ነበር። ኔልሰን ማንዴላ አፈናውና ግድያው የማያዋጣ መሆኑን ካሳሰቡ በኋላ አማራጭ አቅርበው የስርዓት ለውጥ አምጥተው ነበር። ይኼም አማራጭ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዲሞክራሳዊ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ነበር። አስተዋይ የሆኑት የደቡብ አፍሪካ መሪዎችና አባቶች፤ በተለይ ማንዴላና ዴስሞንድ ቱቱ ለሃገራቸውና ለሕዝባቸው በመቆርቆር ስርዓቱ ከስሩ መለወጥና እንደገና መመስረት አለበት የሚል መርህ ተከተሉ። ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም እንዲካሄድ አድርገው የሰላም መሰረት ጣሉ። ዛሬ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ገዢውን ፓርቲ፤ ሁሉንም የፖለቲካና የማህበረሰብ ስብስቦችና ተቋሞች፤ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች፤ እውቅና ያላቸው ግለሰቦች የሚያካትት የብሄራዊ መግባባት፤ ውይይት፤ የፖለቲካ ድርድር፤ እርቅና ሰላም ጉባኤና ስብሰባ ማካሄድ ነው።” (ስርዝ የኔ)
የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በሰው ልጆች ላይ ባደረሰው በደልና በሕዝብ መካከል ያሳደረውን ቂምና በቀል ቀርፎ የሕዝብን አንድነት በማረጋገጥ፤ የደቡብ አፍሪካን ህዝብ ለሰላምና መረጋጋት፤ የተጠናከረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት የወሰደው የሃገራዊ ዕርቅ መፍትሄ የወያኔው የአፓርታይድ ስርዓትም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን በደልና በሕዝብ መካከል ባለፉት 25 ዓመታት የዘራውን ቂም በቀል አሽሮ ወደተረጋጋችና የህዝብ አንድነት ብሎም ፍቅር የሰፈነባት ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመመስረት፤ ለተመሳሳይ በሽታ ተመሳሳይ መድሃኒት – የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ በሽታ የተፈወሰበት ለወያኔው አፓረታይድ በሽታ መፈወሻ – ይሆናል ብለው ዶ/ር አክሎግ ያመላከቱት አቅጣጫ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የተቃኘ ስለሆነ፤ ጥበብ የተሞላበት አካሄድ ነው። ጎሽ የሚያሰኝ ነው።
ከዚያ በተረፈ ግን፤ ዶ/ር አክሎግ ያላነሱት ሃቅ የደቡብ አፍሪካ የእርቅ ኮሚሺን መቼ እንደተቋቋመና ማንስ እንዳ ቋቋመው ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ በደፈናው ኢትዮጵያ ውስጥ ሃገራዊ እርቅ አሁን አስፈላጊ ነው ለሚለው ሃሳባቸው መደገፊያ አድርጎ ማቅረቡ ፋይዳ የሚኖረው አይመስለኝም።
ዶ/ር አክሎግ “ዛሬ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ገዢውን ፓርቲ፤ ሁሉንም የፖለቲካና የማህበረሰብ ስብስቦችና ተቋሞች፤ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች፤ እውቅና ያላቸው ግለሰቦች የሚያካትት የብሄራዊ መግባባት፤ ውይይት፤ የፖለቲካ ድርድር፤ እርቅና ሰላም ጉባኤና ስብሰባ ማካሄድ ነው።” ሲሉን፤ በጎ አሳቢነታቸውን ባልጠራጠርም፤ የደረደሯቸው የተሳታፊ አካላት ስብጥርና የሚሳተፉባቸው የጉዳይ ዓይነቶች፤ ከደቡብ አፍሪካው የዕርቅ ኮሚሽን ተግባር ጋር በምንም፤ በምንም የሚያገኛኘው ነገር የለም። ነገሩ ፍየል ወደዚህ ቅዝምዝም ወደዚያ ይመስላል።
የደቡብ አፍሪካ የእርቅ ኮሚሽን የተቋቋመው በ1989 ዓ.ም የተጀመረው የአፓርታይድ ስርዓት መወገድ ሂደት በእንደ አኤንሲ የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ህጋዊነትን በማግኝት፤ በእነማንዴላ ከስር መፈታትና፤ በመንግስቱና በኤንሲ መካከል ተደርሶ ወደዴሞክራሲ በተደረገ ሰላማዊ ሽግግር ብዙ ሪፎርሞች ተደርገው፤ በ1994 ዓ.ም. የመጀመሪያው ጥቁሮቹ የተካፈሉበት ምርጫ ተካሂዶ፤ ማንዴላ የሃገሩ ፕሬዚዴንት ሆነው ከተመረጡ፤ ደቡብ አፍሪካ የተረጋጋ ስርዓትና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታዎች ከሰፈኑባት በሁዋላ፤ ምንም እንኳን የእርቅ ኮሚሽኑን ጥያቄ ቀደም ሲል በ1994 በሁለት ታዋቂ ሰዎች የተጀመረ ቢሆንም፤ ኮሚሽኑ የተቋቋመውና ሕልውናውን ያገኘው በ1996ዓ.ም. በፕሬዝዳንቱ በራሳቸው ትዕዛዝ ነው። ለማሰሪያ ያህል ወዶም ሆኖ ተገድዶ የአፓርታይዱ ስርዓት ከተንበረከከ በዃላ ነው።
ስለሆነም እንግዲህ ዛሬ ሃገራዊ እርቅ በኢትዮጵያ ያስፈልጋል በማለት በተለይም ዛሬውኑ የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ለሚደረገው ጥሪ፤ ሐገራዊ እርቅ ስለማስፈለጉ ብቻ ሳይሆን፤ እንጥፍጣፊም ቢሆን እንኳን የወያኔ ስርዓት ሃገራዊ ዕርቅን ለማስጀመር የሚሰጠው አመቺ ሁኔታ አለ የሚባለውን በግልጽ በማመላከት ጭምር መሆን ይኖርበታል። ያ ካልሆነ ግን በወያኔ ላይ ከያቅጣጫው የሚሰነዘሩትን የህዝብ ቁጣዎች አቅጣጫ በማሳት ለስርዓቱ ፋታ በማስገኘት ታውቆም ሆነ፤ ሳይታወቅ የሚደረግ ጥፋት መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ስለሃገራዊ እርቅ አስፈላጊነት ካሁን ቀደም በጁን ወር 2015 ገደማ አሸብር የተባሉ ሰው በጻፉት እንዲህ ሲሉ ይጀምራሉ፤- “… ዕርቅ በኢትዮጵያ ስል ሌላ ምንም ሳይሆን፤ ከዘረኛው የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (TPLF) የባርነት አገዛዝ ነጻ ወጥታ በምትመሰረተው ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማለቴ መሆኑን ግንዛቤ እንዲያዝልኝ አሳስባለሁ።” ይሉና በመቀጠል፤ በሚከተሉት፤- “1ኛ/ ስለ ሀገራዊ ዕርቅ አስፈላጊነት፤- 2ኛ/ የዘረኛው የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር (TPLF) አካሄድ፤ 3ኛ/ በቁጥር 2 የተጠቃቀሱትና የሌሎችም መሰል ሂደቶች ዕድል፤- 4ኛ/ የሃገራዊ እርቁ ቦታ ዩዳይ፤- 5ኛ/ የዚህ የአገራዊ ዕርቅ ጥያቄ ባሁኑ ጊዜ ስለመነሳቱ፤-” የጻፉትን እንድታነቡ ልጋብዛችሁ፤
ወደዋናው ርዕስ – ወደነጻነቱ ጉዳይ ተሻግሬአለሁ፤- የነጻነቱን ጉዳይ እንዳነሳ ምክንያት የሆነኝ ባለፈው ጽሁፌ እንደጠቆምኩት በሃገር ቤት ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ” ቢደረግ ወያኔን እናሸንፈው ነበር የሚሉት ትረካቸው ማርኮኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፤
ሆነናም ታዲያ፤ እንዴት ነው አንድ ምርጫ ነጻ ሊሆን የሚችለው? ምንስ መደረግ አለበት? የሚለው ጥያቄ ከፊቴ ስለተደቀነ፤ ተቃዋሚዎቹ የሚሰጡት መልስ እንደለ ስሻ፤ ያገነሁት መልስ የምርጫ ቦርድ፤ ሚዲያ፤ ፍርድ ቤት፤ ታዛቢ፤ ቆጣሪ ወዘተ… ነጻ መሆን አለባቸው የሚል ነው። አሁንም እንደገና እነዚህ ተቋማትስ እንዴት ነው ነጻ የሚሆኑት የሚለው ጥያቄ መልስ ጠየቀኝ፤ ለነሱ መልስ ሳሰላስል፤ ሳላስበው ለመሆኑ ምርጫ ምንድነው? ወሚለው ጥያቄ ላይ ተሻገርኩና ሁሉንም እርግፍ አድርጌ ትቼ አትኩሮቴን በሱ ላይ አደረግሁ። ምርጫ ድርጊት ነው። ድርጊት ደግሞ አድራጊ አለው። የምርጫ አድራጊ ማነው? ሰው ነው። አንድ ሰው ከብዙ ነገሮች መካከል አንዱን የምፈልገው ነው ብሎ ሲጠቁም ያ የተጠቆመ ነገር የሱ ምርጫ ነው ተብሎ ይቀመጥለታል። ከዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ ይህ ምርጫ የተደረው በመራጬ ፍላጎት ነው ወይስ ተገዶ የመረጠው? የሚለው ነው። አንድ የተለመደ ምሳሌ፤- ዘራፊ ተዘራፊ ቤት ገብቶ ባለቤት አንገት ላይ ጩቤ ገትሮ ከህይወትህ ወይም ከገንዘብህ ቢለው ተዘራፊው በእርግጥ ምርጫ አለው። ከሁለቱ አንዱን ብቻ እንዲመርጥ የተደረገው ግን ተገድዶ ነው። ነጻ ቢሆን የሚመርጠው ህይወቱንም ገንዘቡንም ነበር፤ ከሁለት አንዱን ብቻ እንዲመርጥ ስለተገደደ አንዱን ይመርጣል፤ ነጻ ምርጫ ለማድረግ ከፈለገ የግድ ያንን ዘራፊ አስቀድሞ ከፊቱ ማስወገድና ነጻ መሆን አለበት ማለት ነው። የፓርላማ ምርጫ ጉዳይም የኸው ነው። አንዱ ሌላውን ሰው መምረጥ ፍላጎት አለው። ይህንን ፍላጎቱን ለማሟላት ይመዘገባል፤ በምርጫ ዕለት በቦታው ተገኝቶ ድምጹን ይሰጣል፤ ይህ የወሰደው እርምጃ በራሱ የተወሰ እንጂ በሌላ በማንም ጫና ያልተደረገ መሆኑ መረጋገጥ አለብ ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ ከምርጫው ጋር ወደተያያዙት ከላይ የዘረዘርናቸው ተቋማት ውስጥ የሚንቀሳአሱና ያሚያንቀሳቅሱ ሰዎች በድርጊታቸው ላይ ከማንም ተጽዕኖ የጸዱና ለሚወስዱት ማንኛውም ውሳኔ ተገዠነታቸው ለህሊናቸው ብቻ የሆኑ መሆናቸው የተረጋገጠ መሆን አለበ ማለት ነው።
ይሁንምና፤ ዛሬ በሃገራች ላይ በሰፈነው የወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ስር በምትገኘው ኢትዮጵያ የሚደረግ ምርጫ ነጻ ሊሆን እንደማይችል እስካሁን በተገኘው ተሞክሮ፤ ተረጋግጧል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የግለሰቦች ነጻነት/መብት ያለተረጋገጠ መሆኑ ስለሆነ፤ ወደምርጫ ከመግባት በፊት መረጋገጥ ያለበት መራጭ የሚሰጠው ድምጽ በእርግጥ በነጻነት የሚሰጥ መሆኑን ማረጋገጥ ግድ ይላልና መራጮች ከሁሉ አስቀድሞ በነጻ የመምረጥ መብታቸው እንዲረጋገጥላቸው ትግል ማካሄድ አለባቸው ማለት ነው። ይህም ማለት ባጠቃላይ ሕብረተሰቡ ነጻ ምርጫ ለማካሄድ ለሚያስችል ነጻነት ትግል ማድረግ አለበት ማለት ነው።
ታዲያም ለነጻነት የተደረጉ ትግሎች ታሪክ እንደሚያመለክተው የሚከፈል ዋጋ አለው። ይህ ዋጋ ያነሰ ወይም የበዛ ነው ብሎ ከወዲሁ የሚወሰን አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ አገር ላይ የሰፈነው ጨቋኝ ሥርዓት በታጋዮቹ ላይ በሚሰነዝረው ጨካኝ ክንድና ያንን የሚመጥን የተቃውሞ ሃይል በመኖር ወይም ባለመኖር የሚወሰን የሆነውን ያህል፤ በተጨባጩ በሃገራችን የወያኔውን ስርዓት ለመቋቋም የሚደረግ የነጻነት ትግል የሚያስከፍለው ከባድ ዋጋ የመኖሩ ጉዳይ ላይ ለማስመር ብዙ ማውጣት ማውረድን የሚጠይቅ አይደለም።
ለነጸነተ ትግል ዋናና ወሳኙ ጉዳይ፤ ሰዎች ለሰብአዊ መብት ረገጣ በመጋለጥ ለውርደትና ለጥቃት ተዳርገው፤ የበደል ተሸካሚ ሆኖ መኖራቸውን የረጋገጡና፤ ይህንንም በደል አሜን ብሎ ተሸክሞ ለመጓዝ ትከሻቸው ያልደነደነና ለነጻነት የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል የሚያስችለውን ጽናትና ብርታትን ሰንቀው መነሳት ግድ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ነው።
እነዚህ የነጻነት ታጋዮችን መኖርም ለመገንዘብ፤ እንደሚደበደቡ፤ እንደሚታሰሩ፤ እንደሚገረፉ፤ አልፎም የጥይት አራት እንደሚሆኑ እያወቁ፤ ከእቅፍ ያልወረዱ ህጻናት ልጆቻቸውን ታቅፈው፤ ስለነጻነታቸው ጩኸታቸውን ለማሰማት የተፈቀደና ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ ብለው ሳያማርጡ፤ ለሰልፍ የሚወጡ፤ ለልጄ የሚወረስ አንዲት ዛኒጋባ ሳልቀልስ፤ ብለው ሳይሆን፤ ለልጄ እኔ ዛሬ የምኖረውን የባርነት ኑሮ ሳይሆን ነጻነትን አውርሼ አልፋለሁ ብለው የቆርጡ፤ እምቢ ባዮች፤ ብሶታቸው አይሎ እሳት ሆኖ ያቃጠላቸው፤ ልጅ፤ ሚስት፤ ባል፤ ሳይሉ ዱር ቤቴ ብለው ነፍጥ አንግበው ጨቋኛቸውን ለመግጠም ወደበረሃ ያቀኑ፤ ከልጆቻቸው የወተት መግዣ ላይ ቀንሰው ለነዚህ በረኸኞች ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብሉ ሁሉ የነጻነት ዋጋ ከፋዮች ናቸው።
“መልክ ስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤቴ እማራለሁ” አለች እንደተባለው፤ ለነጻነት ስለሚከፈል ከባድ ዋጋ ብዙ ርቀን ሳንሄድ ዛሬ በዳዮቻችን ናቸው ከምንላቸው ወያኔዎቸ ወንድመቻችን መማር እንችላለን፤ ነጻ ምርጫ ለማካሄድ መጀመሪያ መራጭ ነጻ መሆን አለበት ባልነው ቆይተን ስናየው፤ እነዚህ ከትግራይ ኢትዮጵያውያን እናቶችና ከትግራይ ኢትዮጵያውያን አባቶች አብራክ የተከፈሉና የዘውጋቸው ነጻነት ተቆርቋሪ ይሆኑ ዘንድ አምላክ መርጦ የፈጠራቸው ወንደሞቻችን፤ የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር በሚል ተቧድነው፤ ዛሬ የምናያትን ኢትዮጵያ ከካርታ አቀማመጧ ጀምሮ፤ ሕዝቧም አንዱ ዘውግ ሌላውን በጎረጥ እንዲያይ፤ በጋርዮሽ መተያት ቢታሰብም የነሱን በጎ ፈቃድ በቅድሚያ ያገኘ መሆኑ ሲተረጋገጥ – የዘውጎች ከየቦታው ተሰባስበው በየዓመቱ አብሮ መጨፈርን ልብ ይሏል – በነሱ አዛዥና አናዛዥነት፤ እነሱ በቀደዱለት መስመር ብቻ የሚሄድ፤ ከዚያ እዛነፋለሁ ቢል ግን ውርድ ከራሴ በማለት፤ በመደብደብ፤ በማሰር፤ ካስፈለገም እስከወዲያኛው እንዲሰናበት በማድረግ፤ አስፈራርተውና አንቀጥቅጠው የመግዛት፤ የሃገሪቱን ሃብት ከዚህ ተመለስ የሚላቸው ሳይኖር፤ የመዝረፍ ወዘተ… የመሳሰሉ ፍላጎቶች ስለነበራቸው፤ እነዚህ ፍላጎቶች ተሟልተው ለማየት የሚያስችላቸውን ነጻነት ለመጎናጸፍ ከላይ ለነጻነት የሚከፈሉ ዋጋዎች ብዬ የዘረዘርኳቸውንና ሌሎችም መስዋዕትነቶች ከፍለዋል። ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ ተርበዋል ተጠምተዋል፤ ተሰደዋል፤ ሞተዋል ገለዋል፤ አስገድለዋል፤ ለምነዋል፤ ታርዘዋል፤ ተበርደዋል፤ ከስተዋል ጠቁረዋል፤ ትዳራቸውን በትነዋል፤ ትዳር ሳይመሰርቱም ዘር ሳይተኩም አልፈዋል፤ ወዘተ… እንበልና መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ ግን የተገኘው ውጤት ተካፋዮች ሁሉም እንደማይሆኑ፤ እንዳልሆኑ፤ ሊሆኑም እንደማይችሉ፤ የድሉ ተጠቃሚ ከሕይወት የተረፈውና ከዚያ የሚቀጥለው ትውልድ ብቻ እንደሚሆን ሳያስቡ እንደላደረጉት መሆኑን ነው። ይህ ትረካ ከትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ፍላጎትና ያ ፍላጎት በስራ ተፈጻሚ ሆኖ እንዲታይ ለማየት ስለተደረገ መስዋዕትነት ነው።
የኛስ ፍላጎት ምንድነው? ከሁሉ አስቀድሞ የህግ የበላይነት የሰፈናባት፤ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግለሰብ መብቱ የተከበረባት፤ በዘሩ፤ በእምነቱ፤ በቋንቋው፤ በጾታው፤ አድልኦ የማይደረግበት፤ የመሰብሰብ፤ የመደራጀት፤ ከቦታ ኦታ የመንቀሳቀስ፤ የመናገር፤ የመጻፍ፤ መሪዎችን የመምረጥ ወዘተ … ነጻነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ማየት ነው። የዚች ዓይነቷ ኢትዮጵያ ማለት ታዲያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሆነች አገር ነች ማለት ነው። ምናልባት አሁን ከትከሻችን አውርደን ለመጣል የምንፈልገው የባርነት አገዛዝ ባለቤት የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ለሁሉም የምንላት ኢትዮጵያ ውስጥ ብን ብሎ የሚጠፋ የሚመስላቸው ሰዎች ካሉ፤ ተሳስተዋል። በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር፤ የሚባልን ነገር ዓይኔን አላይም የሚል ካለ፤ ዓይኑን መጨፈን ይችላል። ባለፈው ጽሁፌ “በሪሞት ኮንትሮል….” እንዳስቀመጥኩት፤ ዴሚክራቲክ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ የሚነሱ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ ማለቴን አስታውሳለሁ። የትግሬ ሕዝብን ነጻነት ግንባርን መባረር የምንፈልገው ከተጣበቀበት ሥልጣን አካባቢ ነው። መጣበቅ የሚለውን ቃል የቀለብኩት ከጠቅላይ ሚነሰትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አንደበት ሲወረወር አግኝቼ ነው። ቃሉ አስበው የወረወሩት ይሆን ወይም ባርቆባቸው ለጊዜው ይሄ ነው ለማለት እቸገራለሁ።
ያም ሆነ ይህ፤ ለነጻነቱ ትግል የሚከፈለው መስዋዕትነት ሕይወትን እስከማጣትም እንደሚደርስ ስናስብ፤ የሚፈስ ደም ዋጋ እንዲኖረው የማድረግ ሃላፊነትን አለመርሳት፤ ስለሚጠበቀው ውጤት አዎንታዊነት እርግጠኛ መሆን፤ ሁሉም ነገር ባፍጢም በሚደፋ ፍጥነት ይሳከል ብሎ ማሰብን ማረቅ! በ66 አብዮት ዘመን ከሚገባ በላይ ደም ፈስሶአል ይባላል፤ ያ ደም በይፈስ ኖሮ፤ ዛሬ የምናየውን ሸጋ ነገር አናይም ነበር የሚያሰኝ አኩሪ ቅርስ ጥሎ ሳይሆን፤ አሳዛኝ በሆነ ውጤት የመጠናቀቁ ግንዛቤ እንዳለን ባምንም፤ ያ ዘመን ግን፤ የእብደት ዘመን ስለነበረ የደም መፋሰሱ አስፈላጊነት ታስቦበት፤ ግራ ቀኙ ታይቶ የተካሄደ ስላልነበር፤ የማይሆነው አልነበረም የሆነው። ዛሬ ግን አስቦና መክሮ የመስራት ዕድል መኖሩን አለመዘንጋት።
እስከዚህ ያልኩት እንደለ ሆኖ ታዲያ፤ አሁንም እኮ እየተደረገ ያለው ትግል የነጻነት ትግል ነው ስራ አልፈታንም የሚሉ እነደሚኖሩም እርግጠኛ ነኝ። እርግጥ ነው ለነጻት የሚታገሉ አሉ! የኔ ሃሳብ የሚያዘመው ወደነሱ አይደለም። እነሱን በርቱ ነው የምላቸው። ሃሳቤ የሚቃኘው የሰላማዊ ታጋዮች ነን የምንለውንና የነጻነት ታጋይ አስመስለን እራሳችንን ለማቅረብ የሚዳዳንን ነው። ያሁኑ ሰላማዊ ታጋዮች ከምናደርገው ብዙ ጊዜ ከምናጠፋባቸው ጉደዮች ውስጥ አንድ ምሳሌ ላንሳ፤- ጊዜ የማይለውጠው 11 በመቶ የወያኔ ኢኮኖሚ እድገትን ይዘን አድጓል አላደገም፤ በሚል እንደትልቅ ጉዳይ አድርገን እየተወዘወዝን ነው መሽቶ የሚነጋው። የነጻነት ታጋይ እንዲህ ያለ ጣጣ ውስጥ አይገባም። አንድ የነጻነት ታጋይ የዚህ ዓይነቱን ጉዳይ የሚያየው ባሪያ ከጌታው አምልጦ ሊጠፋ እየተዘጋጀ እያለ ዘንደሮ የጌታዬ ማሳ በደንብ ታርሶላቸው ይሆን ብሎ እንደሚጠይቅ አድረጎ እንደሆነ ማንኛችንም የምንስተው አይመስለኝም። ኢኮኖሚው አድጎ ሰማይ ይጥቀስ፤ ሌላ ሌላውም የሚያድግ ነገር ሁሉ አድጎ አገር መሬቱን ያልብሰው። ያለነጻት ምን ፋይዳ አለው?
ማሳረጊያ፤ ከወያኔ ወንድሞቻችን መስዋዕትነት ትምህርት ቀስመን፤ እነሱ ለተጠቀሙበት ግብ ዓይነት ሳይሆን እኛ ለምንፈልገው ግብ የማዋል ጥበቡ ይኑረን፤ በከፈሉት መስዋዕትነት ካገኙት ትርፍ ጋር በምንም መመዘኛ ሊወዳደር በማይችል ሁኔታ ከደረሰባቸው ከፍተኛ “የኢትዮጵያን ሕዘብ ፍቅር የማጣት” ኪሳራ እግዜሩም አላሁም ይሰውሩን፤
በሰላማዊ እምቢተኝነትም ሆነ፤
በአመጻዊ ምት!
በነጻነቱ ትግል ወደፊት!
____________________________________________________________________________________
ማስታወሻ ለአንባቢዎች፤
በጃንዋሪ 2016 መጀመሪያ ላይ “የማስተባበር ጥሪ” ለሚከተሉት ሁለት ሰፊ ስብስቦች አስተላልፌ ነበር።
- Peoples Alliance for Freedom & Democracy (PAFD)
- United Movement for Salvation of Ethiopia through Democracy (UMSED)
ሁለቱንም በድጋሚም ጠይቄ ያማራም የኦሮሞም ሳይሉ ቀርተዋል። እንድታውቁት የሆነው ሆኖ ጥሪውን ያነበባችሁና ሃሳቡን ደግፋችሁ እንዲሳካ በጎ ምኞታችሁን ሌሎችም ስብስቦች እንዲታከሉበት ፍላጎታችሁንና ከዚያም አልፎ አስፈላጊ ለሆነ ትብብርም ዝግጁ መሆናችሁን ለገለጻችሁልኝ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
ተንኮል ከጀርባው ያለበት ነው፤ ደርሰንበታል በማለት ስጋታችሁን ለገለጸችሁም፤ አንተ ለመሆኑ ማን ሆነህ ነው ሰብሳቢ የሆንከው? ለመሆኑ እንዴት ሃብት ቢተርፍህ ነው? ላላችሁትም አክብሮት አለኝ።
tassat@t-online.de
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply