ከሁለት ሳምንታት በፊት በ9-11-2006ዓ.ም. አንድ የፋክት መጽሔት ደንበኛ የሰፈር ሰው አንድ ጸሐፊ በፋክት መጽሔት ላይ አንድ ጽሑፌን መነሻ አድርጎ ያልኩትንም ያላልኩትንም እየቀላቀለ አብጠልጥሎኝ ኖሮ ይሄ ቁጭት ፈጥሮባቸው ስለነበር ባገኙኝ ጊዜ “ባይ ባይ ምንም የለም ለምንድን ነው መልስ የማትሰጠው?” ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ለማን? ስል መለስኩላቸው ፋክት መጽሔት ላይ ስምህን ላጠፋው ሰው ነዋ! አሉኝ፤ ማን ነው ስሜን ያጠፋው? ስላቸው እንዴ! አላየኸውም ማለት ነው? አንዱ እኮ ጻፈብህ አሉኝና ወደ ቤታቸው ገብተው መጽሔቱን ይዘው መጡ ያሉትን ጽሑፍ አነበብኩት ልክ ወያኔ ዜጎችን “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ” እያለ እንደሚያሸማቅቀው ሁሉ ይሄም ሰው እኔን “ባረጀውና ባፈጀው መንገድ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚታገል ሰው፣ የብሔረሰቦችን እኩልነት የማይቀበል” ምንትስ እያለ እንደ ወያኔ በፈጠራ ክስ ያብጠለጥላል፡፡
እዛው እያለሁ ከፋክቶች ለአንደኛቸው ስልክ ደወልኩላቸውና ከሰላምታ መለዋወጥ በኋላ ርእሱን ጠቅሸ እያነበብኩት ነበር መልስ ልሰጠው እፈልጋለሁ ስለው “እስካሁን አላየኸውም ነበር?” ሲለኝ አዎ አሁንም ሰው ነው ያመለከተኝ ስለው “አሀ አይ መልስ መስጠቱ ግን ቢቀርብህ ይሻላል ያንን በመጻፍህ ተከሰስክ፣ በዋስ ነው የወጠኸው፤ አሁን ደግሞ ብትጽፍ የኦሮሞ ጠላት እንደሆንክ ሊያስቆጥርህ ይችላል” የሚል ምክር ይሰጠኝ ጀመር፡፡ እኔም ከራሴ አፍልቄ የተናገርኩት ነገር እንደሌለ፣ ዋቢ መጻሕፍት እንዳሉ፣ እንዲህ ብለው ለሚያስቡ ዋቢ መጻሕፍቱን ለእነርሱ መግለጽ ስለሚኖርብኝና የጠፋውን ስሜን ማደስ ስላለብኝ እጽፋለሁ ተባባልንና ጽሑፉን ለመስጠት ተቀጣጥረን ተለያየን፡፡
ከፋክቶች ጋር ያለኝ ቅርበት ያን ያህል ነው፡፡ የፍትሕ ጋዜጣ ፈቃድ እንደተሰረዘባቸው አቁሞ የነበረን “አዲስ ታይምስ” የተባለን መጽሔት ገዝተው ወደ መጽሔት ኅትመት እንደተቀላቀሉ “የአማርኛ ፊደላት ይቀነሱ የለም አይቀነሱም” በሚል ክርክር ዙሪያና በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በወቅቱ የነበረውን “ከስደተኛው ሲኖዶስ ጋራ የነበረውን የእርቅ ሒደትና የፓትርያርክ ምርጫ” የተመለከቱ ሁለት ጽሑፎችን ሰጥቻቸው አትመውት ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ መጀመሪያ የሰጠኋቸውን ጽሑፍ እንዳተሙት አርትኦት ሲሠሩ አጉል ቦታ ላይ ቆርጠውት ስለነበር ከፍቶኝ ሔጀ “ለምን ቆረጣቹህት?” ስል ጠየኳቸው ስለረዘመ ነው ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ታዲያ ቢረዝም ከሀተታው ላይ ይቆረጣል እንጅ የመከራከሪያ ነጥብ (Argument) እንዴት ትቆርጣላቹህ? ብየ ሳላውቀው በቁጣ ተናግሬያቸው ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ሁለተኛውን ጽሑፍ ሰጥቻቸው እሱም እንዲሁ በአርትኦት ላይ ስሕተት ተሠርቶ ስለነበርና እኔንም ስላስተቸኝ ሔጀ እነዚህን ቃላት ለምን ቀየራቹሀቸው? እንዲህ ማለት እንዲህ ነው ይሄ ደግሞ እንዲህ ማለት ነው ይሄም እንዲህ ማለት ነው እንደዚህ ሲባል ግን እንዲህ ማለት ስለሆነ ስሕተት ነው ስለሆነም አስተቸኝ ብየ ተናገርኳቸው፡፡ ሳላውቀው በቁጣ ተናገርኩ መሰለኝ ከፋቸውና “እርማቱን ጻፍና በቀጣዩ እትም ላይ ይወጣልሀል” አሉኝ፡፡ እኔም አይ ይሄንን ያህል እንኳን ማሳጣት አይኖርብኝም ብየ ተውኩት፡፡ እነሱም ብዙ አልቆዩ አሁንም ፈቃዳቸውን ሰረዙባቸው፡፡
ፋክትን አገኙና ፋክትን ማሳተም ከጀመሩ በኋላ አንድ ጽሑፍ ሰጠኋቸው፡፡ ጽሑፉ አገዛዙ የሀገራችንንና የሕዝቧን ክብር ሉዓላዊነትና ሁለንተና የምትወክለዋን ሰንደቅ ጨርቅ በማለት ለሰንደቃችን ያለውን አሳፋሪ የወረደ ግምት ቦታና አመለካከት በመግለጥ በባንዳዊ ተፈጥሮው እንዳላጣጣለ ሁሉ “የሰንደቅ ዓላማ ቀን” ብሎ መሀሉ ላይ የራሱን ባዕድ ምልክት የለጠፈበትን ሰንደቅ በዓል አከብራለሁ እያለ ሕዝብን ለመደለል እያከበረ በመሆኑ የዘንድሮውን ሊያከብር በተዘጋጀበት ወቅት “ሰንደቃችን ከየት መጣ ማንስ አጠፋው” በሚል እርስ የጻፍኩትን ጽሑፍ ሰጠኋቸው፡፡ በሰዓቱ ሳያወጡት ቀሩ ከዚያም በኋላ ባይ አያወጡትም ስልክ ስደውል አያነሡም ከዚያ በኋላ አይ አንተ አስቀድመህ ብትሰጠንም ለዚያ ሳምንት የሚሆነውን አስቀድመን ጨርሰን ስለነበረና ከዚያ በኋላም ወቅቱ አልፏል ብለን ነው የተውነው አሉኝ፡፡ እኔም አይ በቃ ቁጣዬ አሳቅቋቸው ይሆናል ብየ ተውኳቸው፡፡
አሁን ይሄ ጉዳይ ሲያጋጥመኝ ነው እንደሌሎቹ ለእኔ መልስ ብለው እንደጻፉት “እርባና ቢስ” ነው ብየ ንቄ እንድተወው የማያስችሉ ጽሑፉ ላይ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ስለተንጸባረቀበት፣ ያላልኩትን አልክ ስለተባልኩና ስም ማጥፋት ስለተፈጸመብኝ ነበር ያንን ለማስተካከል በዚያው መጽሔት ላይ ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ፈልጌ የነበረው፡፡ ምንም ምክንያት መጥቀስ አልቻሉም ዝም ብለው ብቻ ጽሑፉት ማስተናገድ አልፈለጉም፡፡ ለነገሩ ከሁኔታዎች የተረዳሁት ነገር ስለነበረ እኔም ያትሙታል ብየ ተስፋ አላደረኩም ነበር፡፡
ፋክቶቹ ይሄንን ጽሑፍ ማስተናገድ ያልፈለጉበት ምክንያት በጣም ግልጽ ነው፡፡ በዕንቁና በሎሚ መጽሔቶች ላይ የደረሰባቸውን ፈተናና የከፈሉትንና እየከፈሉት ያለውን ዋጋ መክፈል ስለማይፈልጉና ችግሩ አንዳይደርስባቸው ስለሚፈሩ ነው፡፡ ነገር ግን “እውነትን እናገለግላለን ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የቆምን ነን” ሲባል የግድ የሚከፈል ዋጋ እንዳለና ቢመርም እንኳ ለመክፈል መዘጋጀት ግድ እንደሆነ መረዳት ግድ ይላል፡፡ “ይሄንን ጽሑፍ ብናስተናግድ እንደ ዕንቁ እንደ ሎሚ መጽሔቶች እንደ ከያኔ (አርቲስት) ቴዎድሮስ ካሳሁን በእነ እከሌ ጥርስ እንገባለን ጥቅማችንም ይጎዳል” በሚል ሒሳብ እነሱን ሊያስከፋ ይችላል ያሉትን ጽሑፍ አለማስተናገድና እነሱን ያስደስታል ያሉትን የእነ አቶ ወርቁ ዓይነቱን ጽሑፍ ደግሞ ማስተናገድ ይሄ “ስለ እውነት ስንል በተደጋጋሚ ኅትመቶቻችን እየታገዱምን ፈቃዳችን እየተሰረዘብን እየታሰርን ዋጋ ከፍለናል” ከሚሉ ወገኖች ፈጽሞ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ይሄ መንጠብ ነው፣ ይሄ እጅ መስጠት ነው፣ ይሄ አጋርነት ነው፡፡
ሁሉም የብዙኃን መገናኛ ቢሆኑ በሥራዎቻቸው የሀገራችንንና የሕዝቧን ህልውናና ጥቅም ለማስጠበቅ መጣራቸውን እርግጠኛ ይሁኑ እንጅ ይሄንን ወይም ያንን በማድረጋቸው አፍንጫውን የሚነፋ ወይም የሚከፋ ቢኖር የሱ ጉዳይ በፍጹም ሊጨንቃቸው አይገባም፡፡ ምክንያቱም መሆኑን ባንፈልገውም ለጠላት ጥቅም ያደሩ ወገኖች እዚህ ሀገራችን ውስጥ መኖራቸው እርግጥ ነውና፡፡ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ካለን የሀገራችንን እሴቶች ማስጠበቅ ከጥቃት መከላከልና እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሁሉ የጋራ አስተሳሰብ መግባባት መያዝ ከቶውንም አንችልም፡፡የሕዝብ የብዙኃን መገኛኛ ነን የሚሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የጸናና ቁርጠኛ አቋም መያዝ ካልቻሉ ሥራ መሥራት፣ የዜግነት ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውንም መወጣት ጨርሶ እንደማይችሉ ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ለዘብተኛ አቋም ተይዞ እንዴት ነው የሀገርንና የሕዝቧን እሴቶች ከጥቃትና ከጥፋት መጠበቅ መከላከል የሚቻለው? ሁሉም ማለት በሚያስችለኝ ደረጃ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የብዙኃን መገናኛዎቻችን ለሚዛናዊነት ባላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ የሀገርንና የሕዝቧን ህልውናና ጥቅም ለአደጋ የሚዳርጉ ጉዳዮችን ሲያስተናግዱ ታዝቤያለሁ፡፡ ፋክት መጽሔት በምንም መመዘኛ ቢሆን እንደ አቶ ወርቁ ያሉ ጽሑፎችን ማስተናገድ አይኖርባቸውም ነበር የሚል የጸና አቋም አለኝ፡፡ “ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብትና ነጻነት” ሲባል ያለ አንዳች ገደብ የታሰበው ሁሉ ይጻፋል ይስተናገዳል ማለት አይደለም፡፡ ገደብ ልክ አጥር የማይታለፍ መስመር አለው፡፡ ገደቡ “የሀገራችንንና የሕዝቧን ጥቅምና ህልውና አደጋ ላይ በማይትልበት ክበብ ወይም ለአደጋ ከመዳረግ በመለስ” እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይሄማ ከሆነ በድራማዎች ሳይቀር አንድን ብሔረሰብ በሌላው ላይ ለማነሣሣት፣ ሀገሪቱን ለመበታተን ከሚያሴረው ከወያኔና ከብዙኃን መገናኛዎቹ በምን ተለዩ? ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ የዚህች ሀገር የአደጋ ሥጋት ወያኔ ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ የቻሉትን ያህል እየሠሩ ያሉና ቀን የሚጠብቁ ሌሎችም የጥፋት ኃይሎች አሉ፡፡ የአቶ ወርቁ ጽሑፍ የሚያገለግለው ከእነዚያ ውስጥ አንዱን ነው፡፡
አሁን ፋክቶች ሊያስተናግዱት ያልፈለጉትን ለአቶ ወርቁ ምላሽ ጽፌው የነበረውን የመልስ ጽሑፍ እንድታነቡ ልተዋቹህ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
አህያውንፈርተውዳውላውን
በዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 113 ላይ “የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሠቢያ ሐውልቶች የእነማንና ለእነ ማንስ ናቸው?” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ መጻፌ ይታወሳል፡፡ የዚያ ጽሑፍ ዋነኛ ርእሰ ጉዳዩ ባይሆንም የኦሮሞዎችን አመጣት አንሥቶ ዋቢ የሆኑትን መጻሕፍት ግን ሳይጠቅስ በመቅረቱ “በእንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ እንዴት ሊሆን ይችላል ብለው እንዳሰቡ ባይገባኝም” ከተለያዬ አቅጣጫ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የኔ የፈጠራ ወሬ እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡት አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ፋክትን ጨምሮ በተለያዩ የኅትመት የብዙኃን መገናኛዎች የተለያዩ ጸሐፍያን መልስ ብለው ያሉትን ጽፈዋል፡፡ እኔ ዋቢ መጻሕፍቶችን አለመጥቀሴ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ነውና ይሄንን የማያውቅ የለም ከሚል ግምት ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን እንደተረዳሁት ግምቴ የተሳሳተ ነበር፡፡ የመረጃ እጥረት እንዲኖርበትና የተወናበደ እንዲሁም የፈጠራ ታሪክ የተጋተና እየተጋተ ያለ ትውልድ መኖሩን ጨርሶ ዘንግቸው ነበር፡፡
መልስ ያሉትን ከጻፉት ውስጥ በዚሁ መጽሔት ቅጽ 2 ቁ. 53 ሰኔ 2006ዓ.ም. ላይ አቶ ወርቁ ፈረደ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ወርቁ እኔን “ባረጀውና ባፈጀው መንገድ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚታገል ሰው ይመስላል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ባረጀውና ባፈጀው መንገድ የሚታገሉ ሰዎች በሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በእኩልነት መርሕ ላይ ይገንባ ሲባሉ አይዋጥላቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው ብለው የሚያውጁበት አንደበታቸው መጤና ነባር ብለው ይሸነሽኑታል፡፡ ይሄንን ተከትሎ የሚመጣው ድምዳሜ መጤው የነባሮችን ያህል መብት ሊኖረው አይችልም የሚል መሆኑ ግልጽ ነው” በማለት ከሞላ ጎደል ባልወጣኝ ነገር ላይ ከምናባቸው አፍልቀው ሊከሱኝ ሞክረዋል፡፡ በጣም ያዘንኩት ግን ስለእኩልነትና መብት ጉዳይ ግልጽ አቋሜን በቀጣዩ እትም ላይ “ዕንቁ ቅጽ 6 ቁጥር 114 መጋቢት 2006 ዓ.ም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የመገንጠል ጥያቄን ማንሣት ይቻላልን?” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ እንደገለጽኩ እያወቁ ሆን ብለው በሐሰተኛ ክስ ለመወንጀል በመሞከራቸው ነው፡፡ ያሳዝናል በቀል መሆኑ ነው?
በዚያው እሳቸው በጠቀሱት ጽሑፌ ላይም ቢሆን ተቆርጦ ቀርቶ ነው እንጅ ለብሔረሰቦች እኩልነትና ፍትሕ የመታገሉን ተገቢነትና አስፈላጊነት ጠቅሻለሁ፡፡ ጽሑፉ በመካነ-ድር ላይም ተለቆ ነበርና ማንም ሰው ያልተቆረጠውን ጽሑፍ በዚህ ይዝ (link) ገብቶ ሊመለከተው ይችላል፡፡ https://www.goolgule.com/accusation
እኔ ለነገሩ የዚህ ወይም የዚያ ብሔረሰብ አባል ናቸው ተብለው የሚጠቁ የሚገለሉ ሰዎች አሉና “ብሔረሰቦች ወይም የእከሌ ብሔረሰብ” እላለሁ እንጅ የትኛውም ብሔረሰብ አለ ብየ አላምንም፡፡ እዚያው ላይም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተዋሐደና የተዋለደ በደም የተሳሰረ በመሆኑ እንዱን ብሔረሰብ ከሌላው ነጥሎ ማውጣት አይቻልም ብየ ገልጫለሁ፡፡
አቶ ወርቁ በዚያ ጽሑፋቸው ላይ አስቂኝና ሸፍጥ ያዘለ አደገኛና የጥፋት ኃይሎችን አንድ እርምጃ ወደፊት ለመሳብ የሞከረ አዲስ ሐሳብ አንጸባርቀዋል፡፡ የተስተዋለ ግን አልመሰለኝም፡፡ አቶ ወርቁ “በወቅቱ “ኦሮሚያ” ተብሎ አይታወቅ እንጅ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጆች የሚኖሩበት ከሞላ ጎደል ግልጽ የሆነ ድንበር ያለው ሀገር ነበረ” ብለዋል፡፡ ለዚህም መረጃ ይሉና “ዳግማዊ ምኒልክ ወደ ውጪ ሀገራት የሚልኳቸውን ደብዳቤዎች የሚጀምሩት “ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ሸዋ ወከፋ ወሐረር ወአድያሚሀ ለብሔረ ኦሮሞ” ማለታቸው ነው፡፡ ይሄም ከውጪ ሀገር መንገደኞች ምስክርነት ጋር የተጣጣመ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዙ ቆንሲል ዋልተር ፕላውደን ለጉዞ ማስታወሻው የሰጠው ርእስ ጉዞ በሐበሻና በኦሮሞ ሀገር የሚል ነው” ይላሉ አቶ ወርቁ፡፡ አቶ ወርቁ ያልገባቸው ነገር ቢኖር ይህ ምን ማለት መሆኑንና መቸ መባሉን ነው፡፡ ዳግማዊ ምኒሊክ የኢትዮጵያ ንጉሥ ከሆኑ በኋላ ዐፄ ከተባሉ በኋላ “ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ወብሔረ ከፋ ወብሔረ ኦሮሞ ወብሔረ ሐረሪ” ብለው ቢሆን ኖሮ እነዚህ የኦሮሞ የከፋ የሐረሪ ተብለው የተገለጹት ሀገሮች አቶ ወርቁ ሊሉ እንደፈለጉት ሁሉ እራሳቸውን የቻሉ ነፃ ሐገሮች ናቸው ለማለት በተመቸ ነበር፡፡ ነገር ግን ዐፄ ምንሊክ እነኝህን ደብዳቤዎች የጻፏቸው ዐፄ ሳይሆኑ በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ስር ከነበሩት ከወሎው ንጉሥ ሚካኤል፣ ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ጋራ የሸዋ ንጉሥ ሆነው ሲኖሩ በኋላ ላይ ከሸዋ በተጨማሪ የተጠቀሱትን አካባቢዎች በመጨመራቸው ምክንያት በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ስር ሆነው ይታወቁበት ከነበረው ከሸዋ ባሻገር የእነዚህም ግዛቶች ገዥ ሆኛለሁ ለማለት ይጽፏቸው የነበሩ ደብዳቤዎች ናቸው እንጅ አቶ ወርቁ ለማለት እንደፈለጉት የኦሮሞ ሀገር የታወቀ ድንበር ያለው፣ እራሱን የቻለ፣ የተለየ ሀገር ስለነበረ አይደለም፡፡ ተገጓዡ ዋልተርም በራሱ ግንዛቤ የዝርያ መደብን ለማመልከት እንጅ “የኦሮሞ ሀገር” ብሎ የገለጸው ቦታ የኢትዮጵያ ግዛት አይደለም ሊል ፈልጎ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ አቶ ወርቁ “አቢሲኒያ” የምትባል ቃልን መርጦ ያመጣበትም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ይህችን ቃል እነማን የተሳሳተ ትርጉምና አጠቃቀም ሰጥተውት ለምን ጉዳይ እየተጠቀሙበት እንዳሉ ይታወቃል፡፡
አቶ ወርቁ በገለጹት ዐውድ “ድንበር” የምትል ቃል የተጠቀሙት ቃሉን የመጠቀሙ ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ ስላልገባቸው ስለማያውቁ አይመስለኝም፡፡ እንደዛ ከሆነ ባይጽፉ ይመረጣል፡፡ ጽሑፉ ግን ግልጽ ነው “ድንበር” የምትለዋን ቃል የተጠቀሙት ትርጉሟን ዐውቀውት ሊደብቁት ያልቻሉትን ወይም ያልፈለጉትን ዓላማ ሲጠቁሙን ነው፡፡ አቶ ወርቁ ለመሆኑ “ድንበር” ያሉት ነገር መቸ? ማን? ከማን ጋራ? የት ድረስ? የተካለለው ነው?
አቶ ወርቁ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው የዛሬ መቶ ዓመታት(በዐፄ ምንሊክ ዘመን) አይደለም፡፡ አቶ ወርቁ የኦሮሞ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ስለ ነበረው አስተዋጽኦ ለመዘርዘር ሲሞክሩ ከመቶ ዓመታት ያለፈ ታሪክ ለምን ሊጠቅሱ እንዳልፈለጉ ገብቶኛል፡፡ ስለማያውቁ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ ምክንያቱም ቢያንስ እኔን ለመክሰስና ለመውቀስ በተጠቀሙበት ጽሑፌ ላይ የጠቀስኩትን ማለትም ቱርኮች ምጽዋንና አካባቢውን ወረው ይዘው በነበሩበት ወቅትና የባሕረ ምድር (የኤርትራ) ገዢ ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅም ከቱርኮች ጋራ ተሻርኮ በዐፄ ሠርፀ ድንግል ላይ በሸፈተባቸው ጊዜ የኦሮሞ ተወላጆች ከዐፄው ጋር በ1571ዓ.ም. ወደ ባሕረ ምድር (ኤርትራ) ዘምተው ለሀገራቸው ያስመዘገቡትን ድል መጥቀስ ይችሉ ነበርና፡፡ ነገር ግን አቶ ወርቁ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደ የጥፋት ኃይሎች ሁሉ በመቶ ዓመታት ስለሚገድቡ ነው ከመቶ ዓመታት ያለፈ ምሳሌ ሊጠቅሱ ያልፈለጉት፡፡ ኢትዮጵያን የሚያውቅና በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ሰው ይሄንን አቶ ወርቁ ያሉትን አይልም አያምንምም፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ከነበራት ሰፊ ግዛት አኳያ አይደለም እዚህ እምብርቷ ቀርቶ ሱማሌና ሱዳን የሚባሉ ሀገራት ከአካሏ ተቆርጠው ሌሎች ሀገራት መፈጠራቸውን ስናወራ የምናወራው የቅርብ ጊዜን የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው፡፡ እናም “ኦሮሞ የሚኖርበት ራሱን የቻለ ድንበር ያለው ሀገር ነበረ” ብሎ ማለት ምን ያህል ኢግብረገባዊ (ኢሞራላዊ) ጠባብ የጥፋትና የጠላትነት ተልእኮን ያነገበ ፀረ ኢትዮጵያ የክህደት አስተሳሰብ እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው፡፡
ወደ ተከሰስኩበት ጽሑፍና ወደ ዋቢ መጻሕፍቶቸ ስመለስ የተሟላ የኢትዮጵያን ታሪክ በቅጽ በመክፈልም ቢሆን ለመጻፍ የሞከሩት ጸሐፍት ሁሉም ማለት ይቻላል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሁን ኢትዮጵያ ብለን ከምናውቃት ውጭ መግባቱን ይስማማሉ ያረጋግጣሉም፡፡ ከእነኝህ የታሪክ ጸሐፍት ሰሎሞን ደሬሳ “የኢትዮጵያ ታሪክ በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን” ፣ ተክለጻድቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ልብነ ድንድል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ” ፣ አለቃ ታዬ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ” ፣ አባ ባሕሪ “ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ባተቱበት መጽሐፋቸው” ፣ ቅንጭብጫቢም ቢሆን የበላይ ግደይ “አክሱም” ሌሎችም የኦሮሞ ሕዝብ ከውጭ መግባቱን መምጣቱን ይናገራሉ የሚለያዩት የገባበትን ዘመንና የመጣበትን ቦታ ነው፡፡ ግማሹ የእንግሊዝ ሱማሌ (ሶማሌ ላንድ) ነው ሲል ግማሹ ከማዳጋስካር ነው ይላሉ፡፡ ዘመኑንም ግማሹ በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን በቦረና በኩል ነው ሲል ግማሹ ደግሞ እንደ ሰሎሞን ደሬሳ ያሉቱ “ከታማኝና ጥልቅ መረዳት ካላቸው አባ ገዳዎች ጠይቀን ተረዳን” እንደሚሉት በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከቤናዲር (ሱማሌ) ተነሥቶ የዋቢንና የገናሌን ወንዝ ተከትሎ ወደ ወላቡና ዙሪያው ገባና ከረጅም ዘመን በኋላ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ አናሳ ጎሳዎችንም እየዋጠ (ወደ ኦሮሞነት እየለወጠ) አሁን ያለበትን ቦታ ሊይዝ ቻለ ይላሉ፡፡ የእነዚህ ጸሐፍት መጻሕፍትና ዋቢ መጻሕፍቶቻቸው ለባዕዳኑም ሆነ በየ ዩኒቨርስቲው (መካነ ትምህርቱ) ላሉ የሀገራችንን ታሪክ ለሚያጠኑ የታሪክ ጸሐፍትና አጥኝዎች ብቸኛ የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡
እኔ የተቀበልኩትና የሚመስለኝም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቱርክና በዓረቦች ጦር የተረዳው የግራኝ መሐመድን ወረራ ተከትሎ ወረራው የፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በቦረና በኩል ገቡ የሚለውን ነው፡፡ ብዙዎቹ ታሪክ ጸሐፍቱን ጨምሮ ይሄንኛውን መላምት ሲያስተባብሉ ከዛጉዌው ሥርዎ መንግሥት ከጠጠውድም ጊዜ ጀምሮ ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም “ጋላ” በሚል ሥያሜ ሳይሆን በሌላ የነገድ ስም ነበሩ፡፡ ለዚህም ማረጋገጫው በአንዳንድ ነገሥታት ዜና መዋዕሎችና ክብረ ነገሥት ላይ በገድላትም ጭምር የኦሮሞ ስም ያላቸው እንደ ቱሉ፣ ላሎ አዛዥ ጫላ ያሉ ግለሰቦች ተጠቅሰው መገኘታቸው ነው ይላሉ፡፡
ነገር ግን እነዚህ ግለሰቦችም ሆኑ ሌሎች በዚያ ዘመን ሊገኙ የቻሉት እንደሚታወቀው የኦሮሞ ብሔረሰብ ከማዳስካር ወደ ሞዛምቢክ ከዚያ ታንዛኒያ ከዚያ ኬንያ መጥተው ኬንያን (ኬኛ) የኛ ብለው ስም አውጥተው ለረጅም ዘመናት እስከ 16ኛው መቶ ክ/ዘመን እዚያ ቆይተዋል፡፡ እዚያ በነበሩበት ጊዜ መነሻቸውን ኬንያ እያደረጉ በተለያዩ ዘመናት ተደጋጋሚ ጥቃት ይፈጽሙ አደጋ ይጥሉና ይዋጉ ስለነበር እንዲህ ዓይነት ጥቃት ይፈጽሙ በነበረበት ጊዜ በመከላከል እርምጃ ተማርከው የሚቀሩ የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ፡፡ እነዚያ የተጠቀሱት ከዐፄ ልብነ ድንግል በፊት ነበሩ የተባሉት የኦሮሞ ተወላጆች በእነዚያ ዘመናት ከኬኛ (ኬንያ) እየተነሡ ለዝርፊያና ለወረራ መጥተው ተማርከው ከቀሩት አንዳንዶቹ ናቸው እንጂ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልክ አሁን ኢትዮጵያ ብለን በምንጠራት ቦታ አሁን ያለበትን ሥፍራ ይዞ የነበረ ሆኖ አይደለም፡፡ እነ አዛዥ ጫላም ለዚያ ሹመት ሊበቁ የቻሉት ጠላት ሆነው ከጦርነት ዐውድ የተማረኩ ቢሆኑም ከዚያ በኋላ ባሳዩት በታማኝነታቸውና በአገልግሎታቸው ብቃት ልክ ዐፄ ምኒልክ ማርከው ካመጧቸው በኋላ እነ ፊት አውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን እነ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነብሶን ሹመት ሰጥተው ለክብር እንዳበቋቸው ሁሉ ያኔም እንደዚሁ ይደረግ ስለነበር ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን ኩሻዊ የሆነ ነገድ ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ እንደ አገው፣ ቅማንት ያሉ ቀደምት ነገደ ኢትዮጵያ ጥንትም ነበሩ ዛሬም አሉ፡፡ ከአራት ሽህ ዓመታት በፊት በሀገራችን የነበረውን ከሰብታህ እስከ ኢጶሪ ያሉ 22 ነገሥታት ያሳለፈው የኩሽ ሥርዎ መንግሥት ባለቤቶችም ናቸው፡፡ ከእነሱም በፊት ማለትም ነገደ ሴም ካም ያፌት ከመፈጠራቸው በፊትም የአዳም ልጅ ኦሪ ወይም አራም (ሲነበብ ይጠብቃል) ከዓለም መፈጠር 970 ዓመት በኋላ መንግሥቱን መሥርቶ ከትውልዱ 21 ነገሥታት ነግሠው ለ1286 ዓመት ያህል እስከ የጥፋት ውኃ ድረስ ገዝተዋል ይላል፡፡
ወደ ነጥባችን ስንመለስ አንድ የባዕድ ጸሐፊ በእርግጥ የተጠቀሰው ማስተካከያ ያስፈልገዋል “የመጀመሪያ ወረራ” የሚለው ትክክል አይደለም Krapfs ይመስለኛል 1480 ዓ.ም. “‐‐ Oromo, The first mention of the name “Galla” in The Abyssinian History of the Kings (“Tarika Negest”) is attributed to 1480 A.D. During the reign of Iskander, the Oromo made their first invasion into Abyssinian land and destroyed the monastery of Atones Maryam.” ብሎ ጽፏል፡፡ የዚህን ተመሳሳይ ወረራ እያደረጉ ገዳማትን አብያተ ክርስቲያናትን ያወድሙ ያቃጥሉ ይዘርፉ ሕዝብ ይጨፈጭፉ ነበር፡፡ በኋላም ላይ ከግራኝ መሐመድ ወረራ በኋላ በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ በቦረና በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው መኖር ከጀመሩም በኋላ ሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት መቀመጫውን በማዛወሩ እዚያም በኦሮሞዎቹ ከመጠቃት ባያድነውም መቀመጫውን ከሸዋ ወደ ጎንደር ያዛወረበት ምክንያትም ይሄው ነበር፡፡ እናም ያለው ነገር ይሄው ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን በዘመኑ የነበረውን ታሪክ እንደታሪክነቱ ለማሳወቅ ያህል የሚነገር እንጅ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በዚህ ዘመን ብሔረሰብን እየጠሩ እከሌ የተባለው መጤ ነው እከሌ ነባር ነው ማለት አይቻልም ይሄ ያለፈ ታሪክ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ በጊዜ ሒደትና በታሪካዊ ክስተት አንደኛው ከሌላኛው ጋራ ተዋሕደው ተዋልደው ወቶላቸዋልና፡፡ እናም በዚያ ጽሑፍ ላይ እንዲህ በግልጽ የሚታየውን በራሱ ጊዜ የተፈጠረውን የአንድ ደም የአንድ ሥጋነትን እውነት በመካድ “ኢትዮጵያዊያን አይደለንም የሚል ካለ ግን መጣሁበት ወደ ሚለው የመሔድ መብቱ የተጠበቀ ነው ምርጫው የራሱ ነው፤ እንገነጥላለን ማለት ግን አይቻልም! የማንን ሀገር ነው የሚገነጥለው?” ነበር ያልኩት፡፡
እንግዲህ ይሄንን ነበር ለመግለጽ የሞከርኩት ፈጥሬ ያወራሁት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ይሄንንም ስናገር እኔ የመጀመሪያው ሰው አይደለሁም ሙቱ ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊም በሽግግሩ ወቅት “መጤዎች ናቹህ ከማዳጋስካር ነው የመጣቹህት አርፋቹህ ተቀመጡ” ብለዋቸው ነበር፡፡ አቶ በለስ ሲናገሩ ዋጥ አድርገው የተቀመጡ ሰዎች አምሳሉ አለ ብለው በአንድ ተራ ግለሰብ ላይ እንዲህ ዓይነት ማዕበል ማስነሣት ምን ይባላል? እኔን እንደብሶትና ቁጭት መተንፈሻ አድርገውኝ ነው? ወይስ “አህያውን ፈርተው ዳውላውን” እንደተባለው ነው ነገሩ?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Leave a Reply