ሕዝባዊ ቁጣ ያንቀጠቀጠው ህወሃት/ኢህአዴግ በተለምዶ “የሰፈር ጉልበተኛ” የሚባሉ ወጣቶችን ለስለላ ስራ እየመለመለ እንደሆነ ተሰማ። ጥያቄውን ተቀብለው በየሰፈሩ ያሉትን የለውጥ አራማጆች ለመሰለል ፈቃደኛ ያልሆኑ እንደሚታሰሩ ለማወቅ ተችሏል። ከታሰሩት መካከል ከማዕከላዊ የተሰወረው ወጣት ጉዳይ በጥበቃ የተሰማሩትን ችግር ውስጥ ከቷቸዋል። አዲሱ ምልመላ የቀበሌ የስለላ መዋቅር መሰበሩን አመላካች እንደሆነ ተጠቁሟል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ዋቢዎቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ኢህአዴግ ቀደም ሲል “አደገኛ ቦዘኔ” ሲላቸው የነበረውን ወጣቶች ለስለላ ተግባር እየመለመለ ነው። የሚመለመሉት በሰፈር ውስጥ በተደባዳቢነት፣ በጉልበተኛነት የሚታወቁ ናቸው። በየሰፈሩ በተለምዶ “ጉልቤ” የሚባሉትን ወጣቶች የሚመለምሉት የህወሃት ሰዎች ናቸው። አመላመሉ በድንገት ከሚያዘወትሩበት ቦታ ወይም ከመንገድ አለያም ከተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች የሚፈለጉትን “ጉልቤዎች” በማደን ነው።
በየሰፈሩ ኢህአዴግን የሚቃወሙ፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን የሚከታተሉና የሚደግፉ፣ እንዲሁም በህቡዕ የድርጅት አባላት በመሆን ተቃውሞዎችን የሚያደራጁ ሰዎችን እንዲሰልሉ የሚመለመሉት ወጣቶች ጠቀም ያለ ክፍያ አላቸው። ቀደም ሲልም ስራ የማይሰሩ ናቸው።
ለጥንቃቄ ሲባል ስሙና አድራሻው እንዲሁም የደህንነት ኃይሎች የት እንደተገናኙት ይፋ ያላደረገው ዘጋቢያቸን ከአንድ ፑል መጫወቻ ቤት ስለተመለመለውና ፈቃደኛ ባለመሆኑ ስለታሰረው ወጣት መጨረሻ አትቷል። ወጣቱ ፑል እየተጫወተ ሳለ ሁለት ሰዎች መጥተው አብረውት ይጫወታሉ። ከዛም ሲወጣ እያሳሳቁ ሻይ አብሯቸው እንዲጠጣ ይጠይቁታል። በድንገት አንድ መኪና ትመጣና አስገብተውት ይጓዛሉ። አንድ አመቺ ቦታ ይዘው ስለመጡበት ጉዳይ ያስረዱታል።
ይህ በሰፈሩ ኃይለኛ የሚባል ወጣት በምንም ዓይነት ሰላይ እንደማይሆንና ጥያቄውን ሊቀበል እንደማይችል ይነግራቸዋል። ከብዙ ንትርክ በኋላ ጉዳዩ ባለመስማማት ሲቋጭ እስረኛ መሆኑ ይነገረውና ወደ ማዕከላዊ ይወስዱታል። ፈቃደኛ ባለመሆኑ ይታሰራል። ቤተሰቦቹና የትዳር ጓደኛው የት እንደገባ ለማወቅ ቢባዝኑም ሊያገኙት አልቻሉም። ሶስት ቀን ሙሉ ፈለገውት ሊያገኙት አልቻሉም። በአራተኛ ቀን ማዕከላዊ ይሄዳሉ። እዛም ስሙን ጠቅሰው ቢጠይቁ እንደሌለ ተነገራቸው።
ተስፋ የቆረጡት ቤተሰቦች ማዕከላዊን ለቀው ሲወጡ አንድ የሚያውቃቸው ሰው ከመካከላቸው አንዱን ጠርቶ ለማንም እንዳይናገር በማስጠንቀቅ የሚፈለገው ወጣት እዚያው ማዕከላዊ እንደሚገኝ ሹክ ይላቸዋል።
እንደመረጃው ምንጮች ከሆነ ወጣቱ ቀደም ሲል ፌደራል ፖሊስ የነበረና “በቃኝ” በማለት የለቀቀ ነው። በሰፈሩ የሚፈራና ጉልበታም ሲሆን ለነገሮች ቅርብ የሆነ ልበ ሙሉ እንደሆነ የሚያውቁት ይናገራሉ። ይህ ወጣት በአምስተኛው ቀን ከማዕከላዊ እስር ቤት ይሰወራል። ወጣቱ እንዴትና በምን በኩል እንደተሰወረ የመረጃው አቀባዮች ዝርዝር ባይናገሩም፣ የማዕከላዊ እስር ቤቱ አባል የሆነ እንዳመለከተው ወጣቱ የተሰወረው እርምጃ ተወስዶበት ወይም እክል ገጥሞት ሳይሆን አምልጦ ነው።
ቀደም ሲል የሥራ ባለደረቦቹ የነበሩ በጥበቃ ሥራ ላይ ማዕከላዊ አግኝቷቸው ሲያጫውቱት እንደነበር የጎልጉል ዘጋቢ አረጋግጧል። ይህ ወጣት በእነሱ እርዳታ ያምልጥ ወይም በራሱ ስልት ይሰወር ግን ለማወቅ አልተቻለም። ከወጣቱ መጥፋት ጋር በተያያዘ የታሰሩ የጥበቃ ሰራተኞች እንዳሉ ግን ለማወቅ ተችሏል። ወጣቱ ለጊዜው በትክክል ስሙ ወደማይጠቀስ ሌላ አገር ሸሽቷል።
በተመሳሳይ ከየሰፈሩ “ጉልቤ” የሚባሉ ሥራ ፈላጊዎችና የራሳቸውን የገቢ ምንጭ ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ ለስለላ ስራ መመልመላቸውን የጎልጉል ዘጋቢ አረጋግጧል። አንዳንዶቹም “ቢዚ ነው” እያሉ እንደሚቀለዱ ከጓደኞቻቸው እንደሰማ ዘግቧል። ከቄራ የተመለመለ “ጉልቤ” ጫት ቤት ለሚቀርቡት እንዴት እንደተመለመለና እነማን አብረውት እንደሚሰሩ መንገሩን ስፍራው ድረስ በመሄድ አረጋግጧል።
ከአንዳንድ ተመልማዮች እንደተሰማው ከሆነ ኢህአዴግ በቀበሌ መዋቅሩ እንደቀድሞው መረጃ አይጎርፍለትም። የቀበሌ አደረጃጀቶች በከፍተኛ ደረጃ ለደህንነቱ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል እንደነበር አይዘነጋም። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ የቀበሌ መዋቀሩና ጥርነፋው ተሰብሮበታል ወይም በመረጃ ፍሰት ድርቅ ገብቶበታል።
ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ዙሪያ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ሆነው ማታ ማታ የሚሰሩት የህወሃት የደህንነት ሰዎች እንደሆኑ፣ ቀን ቀን ግን በመልክ ስለሚለዩ ለመስራት እንደማይችሉ መዘገባችን ይታወሳል። በተያያዘ ዜና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞችና ሰፈሮች በማታ ለመንቀሳቀስ እንደሚፈሩ ታውቋል። ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ሰንዳፋና አካባቢው፣ ወደ ቃሊቲና አቃቂ እንዲሁም ሱሉልታ የሚሄዱ ሰዎች ሳይመሽ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ሲራወጡ ይታያሉ። ለዚህም ምክንያቱ ፍርሃቻ ነው። ዘጋቢያችን እንዳለው አዲስ አበባ ሰላም ብትመስልም ፍርሃት ውጧታል። የንግድ እንቀስቃሴዎች ተዳክመዋል። ወደ አገር ውስጥ የሚመጡ እቃዎች እጥረት በስፋት ይታያል። የዶላር ፈላጊና አቅራቢዎችም የአገዛዙ ሰዎች ናቸው። (ፎቶ: ለማሳያ የቀረበ)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Tesfa says
ከ 97 ምርጫ በህዋላ ሰውየውና ጓደኞቹ በወያኔ ታፍሰው የሆነ ሥፍራ ይታሰራሉ። ሴትና ወንድ ተለይቶ በአንዲት ጠባብና ጨለማ ክፍል ይታጎራሉ። በማግሥቱ አንድ ወንድና አንዲት ወጣት እስረኞች ወንድ እወንዶቹ ጋ ሴትዋ ደግሞ ሴቶቹ ክፍል ውስጥ ተወርውረው ይገባሉ። ወጣት ሴትዋ ገና ያልበሰለች ለግላጋ ወጣት መሆኑዋን ከፊትዋና ራስዋን ለማሳመር ከተቀባቸው የቀለምና የጥፍር ጠጉር መረዳት ይቻላል። በምን ታሰርሽ? አላወኩም። ጊዜ እየቆየ ሲሄድ እስራትዋ በሚስጥር የተያዘ የስለላ ሥራ መሆኑ ይደረስበታል። እስረኞች ሰብሰብ ሲሉ በአማርኛ፤ በትግርኛና በኦሮሞኛ የተቀላጠፈችው ይህች ወጣት ጠጋ ትላቸዋለች። ሰውም ከቅልጥፍናዋ የተነሳ አቀረባት። ለጸሃይ ጥዋት ሲወጡ አንድ ወጣት እስረኛ ጋር አይን ላይን ይተያያሉ። አያውቃትም አታውቀውም። በዓይን ብቻ የተግባቡበት የጋራ ቋንቋ ነበራቸው። የፍቅር ቋንቋ። የመቅጽፈት። ውስጥዋን ወረራት። እኔም ውስጤ ባላወኩት መዓበል ተመታ ይለኛል ወዳጄ። ከረጅም ጊዜ እሥራት በህዋላ ተፈላልገው ይገናኛሉ። እርሱዋም እስር ቤት የነበረቸው በሰላይነት ሥራ እንጂ ታስራ እንዳልነበር ትነግረዋለች። እሱም በቶሎ ታዲያ እንደትሰልይ ለላኩሽ ምን ምን ነገርሻቸው ይላታል። ምንም። ካርታና ገበጣ ሲጫወቱ ነው የሚውሉት አልኳቸው። እንደምታውቀው እዛ ቤት የነበሩ ሁሉ ተፈትተዋል። አንቺ እንደዛ ዓይነት ስቃይ ውስጥ የገባሽው ምን ቢከፍሉሽ ነው? ክፍያ ነበረው። ግን ክፍያው ሳይሆን እምቢኝ ለማለት ምርጫ አልነበረኝም። እምቢታ ሞትም ሊያመጣ ስለሚችል ትምህርቴን አቁሜ የታሳሪ ሰላይ ሆንኩ በማለት አጫውታው አሁን ባለቤቷ የሆነው ሰው ለእኔ አጫወተኝ።
ወያኔ መርዝ ያበላል። በመኪና ገጭቶ ገድሎ በስህተት ነው ይላል። በዘርና በጎሳ ሰውን አጋጭቶ አስታራቂ ሆኖ ይቀርባል። የሥራና የትምህርት መስኮችን ለራሱ ብቻ ያመቻቻል። በጠቅላላው አድራጎታቸው ሁሉ እንደ ጣሊያኑ የማፊያ ቡድን እንጂ መንግሥታዊ ጸባይ የላቸውም። በመሰረቱ ሊስትሮዎችን፤ የሰፈር አባወራዎችን፤ ሴተኛና ወንድ አዳሪዎችን፤ ለማኞችን ለስለላ እንደሚጠቀም ጠንቅቀን እናውቃለን። ሰው በአምስት መደራጀቱም ከዛው ጋር አብሮ የሚታይ ነገር ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ መሪ የሌላት ሃገር ናት። መቀሌ ላይ አባይ ወልድ አሻፈረኝ ሲል፤ የስለላ መረቡ ሃላፊ ጌታቸውና ወታደሩ ሳሞራ ተፋጠዋል። በዚህ መካከል ካድሬውና አብሮ አዳሪው ህግ አልባ ይገላል፤ ይዘርፋል፤ ያስራል፤ ይሰውራል። ጠ/ሚሩ የበይ ተመልካች፤ ለቆመና ለሞተ ማላዘኛ ማሲንቆ ናቸው። ምንም ስልጣን ኑሮአቸው አያውቅም። ሊኖራቸውም አይችልም። የወያኔ አሻንጉሊት የፓለቲካ ማስተባበያ ናቸው። ስለሆነም አሁን ወያኔ በሰሜን ገበሬዎች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከፍቶ ህዝብ እየጨረሰ እያለ በመሃል ሃገር ዝምታው ከምርጫ ሳይሆን ሞትን በመፍራት ነው። ወያኔ ቦዘኔዎችን ደስ ሲለው ሰላይ፤ ሲከፋው ሌባ ብሎ መግደልና ማሰር የነበረ ነው። ወያኔ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ የክፍያ ሰላዮች አሉት። የአቶ አንዳርጋቸው መያዝም በዚሁ የስለላ መረብ እርዳታ የተቀነባበረ ድርጊት ነው።