በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ብሄራዊ ምርጫ የተጀመረው እንደ ኣውሮፓውያን ኣቆጣጠር በ1957 በዓጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲሆን በ1955 የወጣውን ህገ -መንግስት መሰረት ያደረገ ንጉሱንና የላይኛውን ቤት ወይም ሴነቱን የማይመለከት ነገር ግን የተወካዮች ምክር ቤት ኣባላትን መምረጥ ተጀምሮ ነበር። እማኞች ሲነግሩን ምርጫውና ቆጠራው ግን ሃቀኛ ነበር ኣሉ። ታዲያ ንጉሱ በነበሩበት ዘመን የነበሩት ምርጫዎች ጅማሪያቸው መልካም ቢሆንም ዓለም በማህበራዊ ለውጥ ላይ በነበረችበት በመጨረሻው ሰዓት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ህገ-መንግስታዊ ሞናርኪ ቀይሮ የፖለቲካውን ስልጣንና የህዝቡን ተሳትፎ ማስፋት ስላልተቻለ ወታደራዊ ደርግ ኣብዮቱን ኣንግቦ ብቅ ኣለ።
ደርግ ወታደራዊ መንግስት ስልጣን ከያዘ በኋላ የሶሻሊዝም ርእዮት ተከታይ ነኝ በማለቱ በየማህበራቱ የሚደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ከዚያው ከኣንድ ምንጭ የሚቀዱትን የሶሻሊዝም ጓዶች መምረጥ ሆነ ምርጫ ማለት። ደርግ ኣብዩቱ ማለት ሞቱ ነበር። ይህ የሚሞትለት ምርጫ ደግሞ የሁሉም መሆን ኣለበት ብሎ ያምናል። በግድ ሁሉም ሰው ለኣብዮቱ መገዛት ኣለበት።የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ይህን የሚሳሳለትን ኣብዮት ያፈርሳል ብሎ ስለሚያምን ኣብዩቱ እንዳይቀለበስ ስለሚፈራ ምርጫ በኣስተሳሰብ(ideology) ና ፖሊሲ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ምን ኣልባትም በግለሰቦች ስብእና ላይ ያተኮረ እንዲሆን ኣደረገው ። በዚህ ምክንያት በደርግ ዘመን የመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ስላልነበረ ምርጫዎች ተካሄዱ ማለት ኣይቻልም።
ዓለም ወደ ዴሞክራሲ በጣም በተዘረጋችበት፣ ብዙ ኣገራት ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በጣም ባደጉበት ጊዜ ወደ ስልጣን የመጣው ወያኔ መራሽ የኢህዓዴግ መንግስት ደግሞ ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ጀምሮ ላለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት ኣራት ምርጫዎች የተደረጉ ሲሆን ኣምስተኛው ምርጫ የፊታችን ግንቦት ወር ላይ ይካሄዳል። ያለፉትን ኣራት ምርጫዎች ስናይ ሁሉም ዓለም ኣቀፍ ደረጃቸውን ያልጠበቁ በሚል የተከሰሱ፣ በተለይም የ1997ቱ ምርጫ የህዝብ ቅስም የሰበረ፣ ስብራቱም እስካሁን ያላገገመበት ሁኔታ በስፋት ይታያል።
እነዚህ ኣራት ያለፉ ምርጫዎች ስለምን እክል የበዛባቸውና በጣም የሚታሙ ሆኑ? ከመሰረቱ የምርጫ ችግር ኣለ ማለት ነው? ኣሁን ለኣምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ምርጫስ በምን ይለያል? በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ከባቢ ኣለ ወይ? ተስፋ እናድርግ ወይ? ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ መሰረታዊ ነገሮች ምን ምን ናቸው? በነዚህ መስፈርቶች ሲመዘን በውኑ ምርጫ በኢትዮጵያ ኣለ ለመባል ያስችላል ወይ? የሚሉትን የመወያያ ኣሳቦች ኣውራጅ ኣድርገን ጥቂት ብንወያይ ደስ ይለኛል።
በውኑ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ይታሰባል ወይ? ብለን ኣጥብቀን ስንወያይ በመጀመሪያ ምርጫን ለማካሄድ ምን ምን መሰረታዊ ጉዳዮች መሟላት ኣለባቸው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ኣንድ ሁለት ተብሎ በግልጽ መቀመጥ ኣለበት ብየ ኣመንኩ። ከዚያም ከነዚያ መስፈርቶች ኣንጻር የኢትዮጵያን ሁኔታ መገምገሙ ችግሩን በግልጽ ያሳያል ከሚል እምነት ነው። በዚህ መሰረት ዋና ዋና የምርጫ ምሰሶና ማገር ያልኳቸውን 8 ጉዳዮች እነሆ
ለኣገርኣቀፍምርጫብቁየሚያደርጉጉዳዮች
1. እምነት
2. ዋስትና
3.ብሄራዊ ማንነት
4. ታዛቢ
5. የተቋማት ነጻነት
6. ኮንስትቲየንሲ
7. የፖለቲካ ለሂቁና ፓርቲዎች
8. ካምፔን
እንግዲህ በኢትዮጵያ ተፈላጊ ለውጥ ከምርጫ ሳጥን ስበን እናወጣለን ለምንል ወገኖች እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች በተናጠል እየመዘዝን በተግባር መኖር ኣለመኖራቸውን ማረጋገጥ ኣለብን::በጣም በኣጭር በኣጭሩ እንቃኛቸው። ኣንባቢም በነዚህ መመዘኛዎች የራሱን መረጃና መረዳት ያክልበታና ከኔ በተሻለ ያብራራዋል ብየ ኣምናለሁ።
1. እምነት
ከዚህ እንነሳ። ምክንያቱም ወደ ምርጫ ለመሄድ ከሁሉም የሚቀድመው ይሄ ነውና። በራሱ በምርጫ ላይ ሊኖር ስለሚገባ “እምነት” ስናወራ በተለይ በታሪክ ኣጋጣሚ ወደ ስልጣን የመጣው መንግስት በምርጫ ላይ ያለው የእምነት ደረጃ በዚህ መንግስት ደጋሽነት የሚዘጋጁ ምርጫዎችን ሃቀኝነት እንድንመዝንበት የሚያደርግ ዋና መስፈርት ነው። በዚህ መሰረት ወያኔ ኢህዓዴግ በምርጫ ላይ ከልቡ ያምናል ወይ? እንደ ኣንድ ዋና መሰረታዊ የዴሞክራሲ መገለጫ ያየዋል ወይ? ብለን እንጠይቅ::
በመሰረቱ የህወሃት ኢህዓዴግን እምነት ለመለካት እያንዳንዱን ኣባል ቃለ መጠይቅ ማደርግ ኣይጠበቅብንም። የዚህን ገዢ ፓርቲ ርእዮት ጠጋ ብሎ ማየቱ ገዢው ፓርቲ በምርጫ ላይ ያለውን እምነት ቁልጭ ኣድርጎ ይነግረናል።
ከታሪክ እንደተረዳነው በማሌሊት ጡጦ ጠብቶ ያደገው ህወሃት ሁዋላ ላይ ደግሞ የካፒታሊዝም ስርዓት ኣራማጅ ነኝ ብሎ ጥቂት ከቆየ በሁዋላ የልጅነት ጊዜው እንደገና ትዝ ብሎት ወደ ኣብዮታዊ ዴሞክራትነት ተመልሷል። የፈለገውን ርእዮት እየቀያየረ እንዲኖር ያደረገው ከመነሻው የርእዮት ጉዳይ ሳይሆን ሌሎች ቁሳዊ ጉዳዮች ያማለሉት ስብስብ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ርእዮት ኣለው ከተባለ ያለው ወቅታዊ ርእዮት ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው።
የኣብዮታዊ ዴሞክራሲ ኣስተምህሮ ደግሞ የኣንድ ፓርቲ ስቴትነትን የሚያበረታታ፣ ኣንድ ፓርቲ ስልጣን ላይ በመቆየቱና መንግስት በገበያ ጣልቃ በመግባቱ ኣገር ያድጋል የሚል ፍልስፍና ያለው ነው።ከሊብራል ዴሞክራሲ የተለየ ሲሆን በቡድን መብት ላይ የሚብከነከን ነው። “የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ” የጎላበት፣ ከግለሰቦች ጉዳይ ይልቅ የብሄር ጉዳይ በህሊናው ጎልቶ የሚታይበት ድርጅት ነው። በኣንጻሩ የምርጫ ፍልስፍና መነሻ ደግሞ ኣንድ ሰው ለኣንድ ድምጽ “one man one vote” በሚል መርህ የሚመራ ለሊብራል ኣስተሳሰብ የሚቀርብ ነው።
ኣብዩተኞች በሰፊው ህዝብ ስምና በብሄር ስም ስለሚሰክሩ የግለሰቦች ምርጫም ሆነ መብት ብዙ ኣይታያቸውም። በመድብለ ፓርቲ ስርዓትና ምርጫ ላይ ያላቸው መሰረታዊ እምነት በጣም ዝቅተኛ ነው የሚሆነው። በነጻ ሚዲያ ላይ ያላቸው እምነት ከሚገባው በላይ ዝቅተኛ ነው ። ስለዚህ ከርእዮት፣ ከፖለቲካዊ እምነት የተነሳ ህወሃት ኢህዓዴግ የምርጫ እምነቱ ወደ ዜሮ የተጠጋ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ይህን መንግስት “ልማታዊ መንግስት” የሚባለው ዘመናዊ ስም የሚያስደስተው ሲሆን ሃብት በኣንድ ኣካባቢ ተጠራቅሞ እየደለበ ቢቆይ፣ ኣንድ ፓርቲ ለብዙ ዓመት ቢገዛ ጥሩ ነው፣ የሚል ፍልስፍና ስላለው “ምርጫን” ኣደናቃፊ፣ ቀውስ ቀስቃሽ ኣድርጎ ሊያየው ይችላል።
በቅርቡ እንኩዋን ለሚመጣው ምርጫ ኣዲስ ኣበባ ከተማ ውስጥ ምርጫ ቦርድ የጣለው እጣ ምን ያህል በምርጫ ላይ እያላገጡ እንደሆነ፣ ምርጫ የግብር ይውጣው የሸክም ስራ እንደሆነባቸው ያሳያል። እውነተኛው የምርጫ እምነት ውስጣቸው ቢኖር እጣ የሚለው ጉዳይ ኣይመጣም ነበር። ዜናው ሲሰማ ብዙ ሰው እንደሚስቅ፣ ሳቁን ሲጨርስ እንደሚናደድ ኣስብ ነበር። የሆነ ሆኖ የምናያቸው ኣንዳንድ ክስተቶች ሁሉ የሚመነጩት በምርጫ ላይ ያለው እምነት ከማነሱ የተነሳ ነው። የዚህ መንግስት በምርጫ ላይ ያለው እምነት ዝቅ እንዲል የሚያደርገው ርእዮቱ ብቻ ሳይሆን ይዞት የተነሳው የኢኮኖሚ የበላይነት ጥያቄም ነው። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በገዢው በኩል በምርጫ ላይ እምነት እንደሌለ ማሳያ ይሆኑናል። ህወሃት ኢሕዓዴግ በምርጫ ላይ እምነት የለውም።
ሌላው በዚህ ክፍል የምናነሳው ደግሞ ራሱ ህዝቡ ነው :: ህዝቡም ቢሆን በኣሁኑ ምርጫ ላይ ያለው እምነት በጣም ዝቅተኛ ነው። ዝቅተኛ የሆነ እምነት ያለው ለውጥን ከምርጫ ሳጥን መዛቅ ሳይፈልግ ቀርቶ ኣይደለም። ነገር ግን ካለፈው ልምዱ እንዳየው ድምጹ ኣልተከበረም። ብዙ ዓመት ያየው ህወሃት ኢህዓዴግም በምርጫ ስልጣን ይለቃል ማለት ሞኝነት ነው የሚል ኣይነት እምነት ላይ ደርሷል። ካለፉት ምርጫዎች የህዝብ ተስፋ ከፍ ብሎ የነበረው በኣስራ ዘጠኝ ዘጠና ሰባቱ ጊዜ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ከምርጫ ለውጥን ኣገኛለሁ የሚለው እምነቱ ዝቅተኛ ይመስለኛል።
በሶስተኛ ደረጃ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ለምርጫው የተመዘገቡትን ሃቀኛ ተቃዋሚዎች ስናይ እነሱም ቢሆኑ ምርጫውን ኣምነው የተነሱ ኣይመስለኝም። ምን ማለት ነው? ኢህዓዴግን ኣያምኑትም። ጉልበት ስላለው እንደባለፈው ይዘርፋል ብለው ያምናሉ። ምርጫ ቦርድንም ኣያምኑትም:: ታዛቢዎችንም ኣያምኑም:: ያም ሆኖ ግን ምን ኣልባት ከውጤት በሁዋላ የህዝቡን ጉልበት ተመክተው ሊሆን ይችላል ወደ ምርጫ ገብተዋል። ነገር ግን መንግስት እየተጠቀመ ያለው ዘዴ ከዚህ በፊት ከምርጫው በሁዋላ ውጤቱን ማምታታት ሲሆን በዚህኛው ምርጫ ግን ፓርቲውን ማብዛት፣ ሃይል መበተን፣ የኣንድነት ሃይሎችን ማፍረስ፣ እጩዎችን መጣል ወዘተ. እየተጋ ይገኛል። ይህ እንቅስቃሴው ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እምነት መውረድ ጉልህ ሚና ኣለው።
በኣጠቃላይ በዚህ መንግስት ጊዜ የተደረጉ ምርጫዎች በተለይም ኣሁን የሚመጣው ምርጫ በሁሉም ህዝብ ዘንድ እምነት የጎደለው በመሆኑ ኣንዱን ትልቁን የምርጫ ቁም ነገር ኣፍርሷል ማለት ነው።
ሌላው የዓለም ኣቀፉ ማህበረሰብም ቢሆን ካላፉት ምርጫዎች የታዘበው ነገር ከዚያም ደግሞ የሃገሪቱን የሰብዓዊ መብት ሪከርዶች ሲያገላብጥ የሚኖረው እምነት ዝቅተኛ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።
2. ዋስትና
ሌላው የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን የሚያራምዱ ኣገራት ወደ ምርጫ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ኣንድ ወሳኝ ነገር የዋስትና መኖር ነው። ዋስትናው ምንድን ነው? ካልን እርስ በርስ ያለመጠፋፋት:: በምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ የመንግስትነትን ስልጣን ሲወስድ እነዚያን ያሸነፋቸውን ፓርቲዎች ኣያጠፋቸውም። እንደገና ሃይላቸውን ኣድሰው ለሚቀጥለው ምርጫ ሊገጥሙ የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል፣ የመቻቻል ባህል ያለበት ድባብ ያሰፍናል። ኢትዮጵያ በኣሁኑ ሰዓት ይህ ዋስትና የላትም። ፖለቲካው የቀዝቃዛውን ጦርነት ኣለቀቀም። በጣም ጽንፈኝነት ያለበት የፖለቲካ ስርዓት ነው በሃገራችን ያለው። ርቀቱ ሰፊ ነው። ሌላው ቀርቶ በዘጠና ሰባት ጊዜ እንኳን ስናይ ቅንጅት ስልጣን ቢይዝ የብሄር ድርጅቶችን እንደሚያጠፋቸው ይዝት ነበር። የብሄር ፌደራሊዝምን ያፈርሳል፣ እነ ህወሃትን ይበትናል ወዘተ ይህ ሁኔታ ኣንዱን የምርጫን ትልቁን ጉዳይ ዋስትናን ስለሚያጠፋ እውነተኛ ምርጫ በሃገሪቱ እንዲኖር ኣያደርግም። ይህንን የምለው የብሄር ድርጅቶችን ደግፌ ኣይደለም። የማንነት ፖለቲካ ለሃገራችን ኣይጠቅምም ከሚሉት ኣንዱ ነኝ። እያወራሁ ያለሁት የብሄር ፖለቲካ ባለበት ኣገር ከብሄራዊ ፓርቲዎች ጋር ለውድድር ሲቀርቡ የሚገጥመውን ደረቅ እውነት ነው። ይህ ሁኔታ ይህ ድባብ እንዲፈጠር ያደረገው ደግሞ ራሱ ወያኔ ኢህዓዴግ ነው። በሃያ ኣመቱ እንኳን ወደ ውህደት ባለማምራቱ ይህ ችግር እንዳለ እንዲቆይ በማድረጉ ተጠያቂ ነው።
መንግስት የኣንድነት ሃይሎችን ጽህፈት ቤት ከፍተው በተወሰነ ደረጃ እንዲንቀሳቀሱ ሲያደርግ ልበ ሰፊ ሆኖ ኣይደለም። ይህን የሚያደርገው በምርጫ ወቅት ስለሚያምናቸው ኣይደለም። የብዙውን ህዝብ ቀልብ ስለሚያውቀው ብዙው ህዝብ ልቡ ኣንድነትን ስለሚናፍቅ ይህ ህዝብ ወደ ሌላ የትግል ኣቅጣጫ እንዳያመራ ለመያዝም ነው። እነዚህን የኣንድነት ሃይሎች እስከተወሰነ እንዲንቀሳቀሱ ያደርግና እውነተኛ ምርጫ ሲመጣ ያጠፋቸዋል። ልክ ኣሁን በቅርቡ በUDJ ና AEUP ላይ እንደሆነው ማለት ነው። የብሄር ድርጅቶችና የኣንድነት ሃይሎች በጣም የተራራቁ ስለሆነ ይህ ልዩነታቸው እንዲህ በቀላሉ ከምርጫ ሳጥን በሚገኝ ውጤት የሚሸናነፉ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። ይሄ የሃገራችን ፖለቲካ ተፈጥሮ ያመጣው ኣሳዛኝ የጽንፈኝነት ውጤት ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስናይ ኣንድ በሬ ወዲህ ኣንድ በሬ ወዲያ ኣይነት ተጠምደው የሚታይ ነው የሚመስለው። በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ኣሰላለፍ ለውጥን ከምርጫ ሳጥን መጠበቅ በጣም በጣም ይከብዳል።ከምርጫ በፊት ዋስትናዎች፣ ውይይቶች መቅደም ኣለባቸው።መንግስት ይህን እያወቀ የምርጫ ድግስ የሚደግሰው ሁል ጊዜም ምርጫውን የመቀልበስ ኣቅም ኣለኝ በሚል ነው። ለእውነተኛ ምርጫ የሚያስገድደው ቢመጣ ደግሞ ከብሄር ፖለቲካ ኣራማጆች ጋር ይወዳደራል እንጂ ከኣንድነት ኃይሎች ጋር ኣይሞክረውም።
3. ብሄራዊ ማንነት
ብዙ ጊዜ ስለ ምርጫ ስናነሳ ቶሎ የሚታየን የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መሆን ያለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ከዚያ የዘለለ ብዙ ችግር ኣለባት። ከፍ ሲል ከጠቀስኳቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ጋር ኣንዱ ትልቁ መታየት ያለበት ጉዳይ የብሄራዊ ማንነት ጉዳይ ነው። ብሄራዊ ምርጫ ያለ ብሄራዊ ማንነት የሚታሰብ ኣይደለም። መፈክሩ፣ ካምፔኑ መዝሙሩ ሁሉ የሚደምቀው ኣንድ ጠንካራ ብሄራዊ ማንነት ለሁሉም ጥላ ሆኖ ሲታይ ነው። በየሰፈሩ ኢትዮጵያ….. ኢትዮጵያ….. ኢትዮጵያ…. እየተዘመረ የብሄራዊነት ማንነት መንፈስ መግነን ኣለበት። ብሄራዊ ማንነት ያልገነባ ኣገር ለብሄራዊ ምርጫ መነሳት የለበትም። በኢትዮጵያ ውስጥ ኣንዱ እክል ይሄ ነው። መንግስት ባለፉት ሃያ ሶስት ኣመታት ብሄራዊ ማንነትን ሲያኮስስ ኣካባቢያዊ ማንነትን ሲያራግብ ነው የከረመው። ብሄራዊ ማንነት በጣም ኮስሶ የቡድነኝነት ስሜት ማየሉን እንደ ድል ያየውም ይመስላል። የዜጎች ተስፋም ዝቅ እንዲል ያደርጋል። ወደ ከፍተኛ ስልጣን የመጣውን ሰው እያዩ ይጠረጥራሉ። ዜጎች ኣንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ብቅ ሲል ሁለት የፖለቲካ ካባ ለብሶ ስለሚመጣ የውስጠኛዋን ፖለቲካዊ ማንነት ማወቅ ይሻሉ። በዚህ ጥንድ የፖለቲካ ስብእና መካከል ተቃርኖ ኣይፈጠርም ብለው ላያምኑ ቢችሉ ኣይፈረድባቸውም። ኣንዱን ማንነት ለሌላው ማንነት ዝንባሌ (interest) እንዲገዛ ሊያደርግ ይችላል ብለው ቢያስቡ ኣይፈረድም። የሚንስትሩ ብሄራዊ ማንነቱ ሳይሆን ቡድናዊ ማንነቱ ጎልቶ ይታያቸዋልና የኔ ነው ብለው ለመውሰድ ይቸገራሉ። በምርጫ ጊዜም ቢሆን በተለይ እንደ ኣዲስ ኣበባ ኣይነት ኣካባቢዎች ለማንነት ድምጽ (identity voting) ይጋለጣሉ። ትክክለኛ ምርጫ ይካሄዳል ብለው ተስፋ እንዳያደርጉ ያደርጋል።በኣጠቃላይ የሃገራዊ ምርጫ ጨዋታን ያበላሻል።
4. ታዛቢ
ሌላው የምርጫን ሂደት ፍትሃዊ መሆኑን የሚያሳየው ደግሞ ኣገሪቱ በምርጫ ድግሷ ጊዜ የምትጠራቸው ኣለም ኣቀፍ ታዛቢዎችና፣ የሃገር ቤት ታዛቢዎች ናቸው።እውነተኛ ምርጫ ያለ ታዛቢ ኣይካሄድም። በዚህ በኩል መጪውን ምርጫ ስናይ እንደሚታወቀው ከዚህ በፊት የነበረውን ምርጫ የታዘበው የኣውሮፓ ህብረት ለዚህ ለመጪው ምርጫ ታዛቢ ቡድን ኣያሰማራም። ኣያሰማራም ብቻ ሳይሆን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሚሰጠውን እርዳታ ነጥፏል። ይሄ በራሱ የሚያሳየው ኣንዱ ትልቁ ጉዳይ ህብረቱ በምርጫው ላይ ያለውን ኣመኔታ ነው። ይሄ ኣንድ ጎዶሎነት ሲሆን የኣካባቢ ታዛቢዎች ደግሞ ገለልተኛ መሆናቸው ብዙ ጊዜ ይታማል። ከፍ ሲል እንዳልነው መንግስት በምርጫ ላይ በዴሞክራሲ ላይ ያለው እምነት ዝቅተኛ በመሆኑ የራሱን ኣባላት፣ ወይም የሚፈሩትን ወይም በቀላሉ የሚደለሉትን እየፈለገ በምርጫው ኣካባቢ ቁጭ ብለው እንዲያንቀላፉ ሊያደርግ ይችላል የሚል ጥርጣሬ በፓርቲዎችም በህዝቡም ዘንድ ኣለ። በመሆኑም ኢትዮጵያ በኣሁኑ ዘመን ምርጫዋ ይህንንም ኣጥታለች ማለት ነው። ያለ እውነተኛ ታዛቢ የሚደረግ ምርጫ……
5. የተቋማት ነጻነት
በተለይ ከምርጫው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነቱ በሳይንስ ኣልተረጋገጠም። ይህ ተቋም ሃይሉን ተግፎ ኣድርግ የሚባለውን የሚያደርግ ኣንድ የመንግስት ተቋም ነው የሚመስለው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ ክስ የሚያሰሙበት፣ ህዝቡ ከመጠን ያለፈ የሚጠረጥረው ተቋም ነው።
የዓለም የብልጽግና ጠቋሚ (World prosperity index) በ 2010 ባጠናው ጥናት መሰረት 21% ብቻ የሚሆነው ህዝብ የምርጫ ሂደት ተዓማኒነት ኣለው ብለው ያምናሉ ይላል። በሌላ ኣገላለጽ 79 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በምርጫ ሂደት ወቅት ኣድሏዊነት ኣለ ብሎ ያምናል ማለት ነው።ይህ ኣስገራሚ ውጤት እንደ ተቋም የምርጫ ቦርድ ውጤት ነው። የሚገርመው ጥናቶች የሚያሳዮት ህዝቡ ምርጫ ቦርድን የማያምነው ከራሱ ከኢህዓዴግም በላይ ነው። ከኢህዓዴግ በላይ ምርጫ ቦርድ ይጠረጠራል። ይገርማል።
“Unsurprisingly, only21% of the population believe that the electoral process is honest.” (World prosperity index)
ይህ ተቋም የምርጫን ድግስ ለመደገስ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ዜጎች ሊደገፉበት የሚገባው ነው። ሃምሳና ስልሳ በመቶ እምነት ኣግኝቶም ቢሆን እንኳን የምርጫ ኣስተናጋጅ ሊሆን ኣይገባውም።በሌላ በኩል የፍርድ ቤቱን ነገር ስናነሳም እንዲሁ በጥገኝነት የሚከሰስ በመሆኑ ዜጎች ምርጫ ተጭበረበረ ብለው ሊከሱ የሚሄዱበት ከባቢ የለም። ይሄው የብልጽግና ጠቋሚ ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ገለልተኛ የሆነ ፍርድ ቤት የላትም።ይህንን ስናይ ኢትዮጵያ ኣገር ኣቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ ኣለማመቻቸቷን ነው የሚያስተምረን።
6. ኮንስትቲየንሲ
የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ በያዝነው ኣመት ለምርጫ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ እንደተመዘገበ ይገልጻል። ስድስት ሺህ ለፓርላማ ኣባላት ውድድር እንደቀረቡ፣ ወደ ሰላሳ ኣምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ህዝብ ተመዝግቧል ይላሉ። መራጩ በቦታው ቢኖርም ነገር ግን ለእጩነት በሚቀርቡት ላይ ምን ያህል እምነት እንዳለው ኣላውቅም። ዋናው ግን ይህ መራጭ እምነቱ ስለተሸረሸረ ለምርጫ ያለው መንፈስ የወረደ ይመስላል። ሰው ለምርጫ መመዝገቡ ብቻ ሳይሆን መታየት ያለበት ለውድድር የሚቀርቡት ፓርቲዎች ኮንስትቲየንሲው ኣላቸው ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው ዋናው። መራጩን የሚያረካ ኣማራጭ ለውድድር መቅረብ ኣለበት። በኣሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ስናይ የተሻለ ኮንስትቲየንሲ ያላቸውን ለረጅም ጊዜ ሲያደራጁ የነበሩትን ኣንድንድነትንና መኢዓድን በትኗል።በኣሁኑ ሰዓት የተሻለ ኮንስትቲየንሲ ወይም መራጭ ወይም ፖለቲካዊ መሰረት ኣለው የሚባለው ሰማያዊም ብዙ ወከባ እየደረሰበት ነው። ይህ የሚያሳየው መንግስት ራሱ ሆን ብሎ ኣማራጮችን በማሳጣት ድምጽ ለራሱ ለመውሰድ ነው። በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለምርጫ የሚያበቃ ሁኔታ ላይ ኣይደለችም። ሚሊዮን ህዝብ የምርጫ ካርድ ይዞ ነገር ግን ልቡ የፈቀደው ተወዳዳሪ በዚያ ምርጫ ኣካባቢ ከሌለ ምርጫ ተካሄደ ለማለት ኣያስደፍርም።
ስለ መራጭ ስናነሳ የመራጩን የመምረጥ ኣቅም ማየትም ኣለብን። በርግጥ ኣርብቶ ኣደሩ ወገናችን፣ ገበሬው በተለይም ከቤት ብዙ የማትወጣው ሴቷ ገበሬ እናታችን በፓርቲዎች መካከል ያለውን የፖሊሲ ልዩነት ለመረዳት የትምህርት ማነስ ኣለ። ይሁን እንጂ እነዚህ ወገኖቻችን ከግብርናው ጋር ከኑሮው ጋር በተያያዘ በሚገባቸው ቋንቋ ከተገነዘቡ የመምረጥ ኣቅማቸው ከፍ ይላል። ከሁሉ በላይ እንደ ተወካይ የሚያዩት የተማረው ልጃቸው በምርጫ ላይ ተጽእኖ ኖሮት በኢትዮጵያ ውስጥ ይታያል።በኣጠቃላይ ኢትዮጵያ የሚያድግ ለምርጫ የሚያበቃ ኮስንስትቲየንሲ ቢኖራትም ሰፊ ኮንስትቲየንሲ የሌለው ፓርቲ ለምርጫ ከቀረበ በምርጫው ላይ ተፈላጊ ኮንስትቲየንሲ የለም ነው የሚባለው።
7. የፖለቲካ ለሂቁና ፓርቲዎች
ምርጫ ከሚፈልገው ኣንድ ዋና ጉዳይ ተመራጭ መኖሩ ነው። የፈለገውን ያህል ጥሩ የምርጫ ድግስ ካምፔን ቢኖር ህዝብ ልቡ የሚያርፍበት ኣማራጭ ከሌለ የምርጫን ትርጉም ያበላሻል።በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ያለባት ችግር በጣም የገዘፈ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የፖለቲካው ስሪት(political set up) ራሱ ዜጎችን ሁለት ጊዜ ፖለቲከኛ ስለሚያደርግ የፓርቲ መዓት እንድንቀፈቅፍ ኣድርጎናል። ከዚያ ባሻገር በፕሮግራም የሚለያዩበት ቦታ ሳይታወቅ እዚህም እዚያም የተኮለኮሉ ፓርቲዎች ስለበዙ ህዝቡ ስማቸውንም መሸምደድ ተቸግሮ ይታያል። ኣንዳንዶቹ ደግሞ በራሱ በመንግስት የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ዓይነቱ ችግር ህዝቡን ግራ የሚያጋባ በመሆኑ ለምርጫ ምቹ ሁኔታን ኣልፈጠረም። የምርጫ ጥራት ከሚለካበት ኣንዱ ጥራት ያላቸው ጥቂት ፓርቲዎች ሲቀርቡበት ነው። ህወሃት ኢህዓዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ ወደ መቶ የሚጠጉ ፓርቲዎችን ኢትዩጵያ ፈልፍላለች። ይህንን ጉዳይ የመንግስት ኣካላት እንደ በረከት ያዩት ይመስላሉ። በኣሳብ ብዙ የማይራራቁ ኣንዳንዶቹ ደግሞ ጨርሶ ልዩነትም ሳይኖራቸው ፓርቲ ሲኮለኩሉ ይታያል። ይህ ደግሞ ለመንግስት ደስታን ፈጣሪ ነው። ኣንዱ ደስታው ሃይል በመበተን የምርጫው ጨዋታ እንዲደበዝዝ ስለሚያደርግለት ነው።
በዚህ ረገድ መሬት ላይ ለህዝቡ የተዘረጋውን ኣማራጭ ስናይ ግራ የሚያጋባ፣ የሃገሪቱን ምስል በመራጭ ህሊና ኣድምቆ የማያሳይ ነው። ከፍ ሲል እንዳልነው የብሄራዊ ማንነት ጉዳይ የጠራ ስእል ስለሌለ ምርጫውን ያደበዝዘዋል።
በሌላ በኩል ፈንድ ፎር ፒስ ያጠናውን ስናይ የለሂቁ ክፍፍል ከ 2006 እስክ 2014 ድረስ በስምንትና በዘጠኝ ነጥብ መካከል ነው የሚዋዥቀው ። ይሄ ማለት በጣም ከፍተኛ ክፍፍል እንዳለ የሚያሳይ ነው።የመጨረሻው የክፍፍል ነጥብ ኣስር ነጥብ ሲሆን ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ የሚያስመዘግቡት ነጥብ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ኣስር በጣም የተጠጋ ነጥብ ያላት መሆኑ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በኣጠቃላይ ለሃገሪቱ መጻኢ እድል ኣስጊ ነው። የዘጠና ሰባቱን ምርጫ ያደመቀውና የብዙሃንን ቀልብ እንዲስብ ያስቻለው፣ ያንን ኣገር ኣቀፍ ንቅናቄ የፈጠረው ኣንዱና ዋናው ምክንያት የለሂቁ ክፍፍል መቀነስ ነበር። ልክ ምርጫው ኣልቆ ሁኔታዎች ከተበለሻሹ በኋላ የጀመረው ክፍፍል እስካሁን በከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ ይሄ ጉዳይ በምርጫው ላይ ጥላ ይጥልበታል።ኢትዮጵያ ሌሎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ድርጅቶች ሁሉ ባለቤት ናት። በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ወገኖችም ሁለትና ሶስት እየሆኑ ድርጅት መስርተው ቁጭ ይላሉ። ኣንዳንዶቹ ይህን የሚያደርጉት ለፕሮፋይል ለስም ሲሉ መሆኑ ያሳዝናል። ማንትሴ የተሰኘ ድርጅት ሊቀመንበር ወይ ጸሃፊ ነኝ በማለት የሚጠቀሙ ኣሉ። ሃላፊነት የጎደለው ጉዳይ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሻው የነጻነት ትግል በመሆኑ መሰባሰቡ መልካም ነው። ብዙ ፓርቲዎች ባለመዋሃዳቸው የጠቀሙት ወያኔን ነው። በተለይ በምርጫ ጊዜ ውህደት የሚያስፈልገው ምርጫውን ለመወዳደር ብቻ ሳይሆን የሚመጡ ትግሎችን ለመምራት፣ ሁኔታው ድንገት እንዳልነበር ቢሆን ኣገር ለማዳን ነው።
8. ካምፔን
በምርጫ ወቅት ለቀቅ ባለ ስሜት ካምፔን ለማድረግ ወለሉ ኣለ ወይ? ብለን ስንጠይቅ በዚህ በኩልም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ ሲያማርሩ ይታያል። በተለይም በሚዲያ ሽፋን በኩል በጣም ዝቀኛ የሆነ ሽፋን ነው ያላቸው። በሌላ በኩል ገበሬውና ኣርሶ ኣደሩ ከመረጃ መረቦች በመራቁ የነዚህን ፓርቲዎች ኣቋም ለመስማት ይቸገራል። በኣካል እየተገኙ ካምፔን ለማድረግም በጣም ይከብዳል። በተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩል ከፍተኛ የሪሶርስ ችግርም ኣለ።ይህም በምርጫው ላይ የራሱ ጥላ ይኖረዋል።
በዚያ ላይ የፖለቲካው ኣሰላለፍ የፈጠረው ጽንፈኝነት የተቻቻለና የሰለጠነ ካምፔን ለማድረግ ኣስቸጋሪ ነው። በዘጠና ሰባት ህዝቡ ለለውጥ ያለ ልክ ጓጉቶ ስለነበረ የነበረው ካምፔን መልካም ነበር። ያ ጊዜ ብዙ ልዩ ሁኔታዎች ኣሉት። በኣሁኑ ጊዜ ግን ጥሩ ካምፔን ለማድረግ በራሱ በመንግስትም በኩል ብዙ መሰናክል ተፈጥሯል።
መደምደሚያ
እንግዲህ ከፍ ሲል ባነሳናቸው ነጥቦች ኣንጻር ሲታይ በኣሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የለም ወደሚል ድምዳሜ ያደርሳል። ችግሮቹ መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን በኣጠቃላይ መሰረታዊ የሆኑ የምርጫ መጫወቻዎች ፈጽመው የሉም። የሚያሳዝን ድምዳሜ ቢሆንም ምርጫ በኢትዮጵያ የለም። ዜጎችም ከምርጫ ሳጥን ለውጥን እናመጣለን ብለው በየኣምስት ኣመቱ መድከም ዋጋ የለውም።
መንግስት የምርጫን ፕሮፓጋንዳ ኣንድ የፖለቲካ የስልጣን ማራዘሚያ መሳሪያ ኣድርጎ ነው የሚያየው። ይህ መታወቅ ኣለበት። በተለይም የዓለም ባንክን፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅትንና የዓለምን ዴሞክራቲክ ኮምዩኒቲ ለመደለል ምርጫ መሳሪያ መሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል።
በኣጠቃላይ ይህ መንግስት በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ከስልጣን የሚወርድበት እድል ወደ ዜሮ የተጠጋ ሲሆን ምን ኣልባት ጥቂት ጭላንጭል የምትታየው ኣንድ ነገር ከተፈጠረ ነው። ምን ኣልባት የታጠቁ ሃይሎች ትግላቸው በርግጥ ከንድፈ ሃሳብነት ኣልፎ ማጥቃት ከጀመሩና ጫና ከፈጠሩ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነት በየቦታው ከታየ፣ የፖለቲካ መሪዎች ትግሎችን በየፊናው የመምራት ቁርጠኝነት ካሳዩ፣ የለሂቁ ክፍፍል መጥበብ ካሳየ፣ በቅርቡ ታላቋ ብሪታኒያ እንደወሰደችው ኣቋም ሌሎች ኣገራት ከቀጠሉ፣ መንግስት ምርጫን ሰበብ ኣድርጎ ሸርተት ሊል ይችላል። እነዚህ ኣስገዳጅ ሁኔታዎች ካልገፉ መጪው ምርጫ ተስፋ የሚጣልበት ኣይሆንም።በቅርቡ ታላቋ ብሪታኒያ የወሰደችው ርምጃ በርግጥ የኢትዮጵያውያንን ትግል በጅጉ የሚያግዝ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን በውሳኔው ፈንድቀዋል። ኢሃዴግም ከብሪታኒያ የሚያገኘው 98 ቢሊዮን ብር ነጥፎበታል። ከሌሎች የምእራብ ኣገሮችና ከኣሜሪካ ግፊቱ ከጠነከረ፣ የሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በየፊናው ከከሰሱ ጫናው ስለሚጠነክር ለኢሓዴግ የሚሻለው ኣወዳደቅ በምርጫ ስም ይሻላልና ምን ኣልባት በዚህ መንገድ ምርጫ ተስፋ ሊኖረው ይችላል።
ይህ ግን ከመንግስት ተፈጥሮ ኣንጻር ሲታይ በጣም ጠባብ እድል ነው። መንግስት ባለፈው ጊዜ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ኣሸንፊያለሁ በማለቱ ብዙ በመተቸቱ በኣሁኑ ምርጫ ትንሽ ወንበር ለተቃዋሚዎች ለቀቅ ኣድርጎ ካለፈው የተሻለ ምርጫ ተካሄደ በሚል ኣለምን በመደለል ሌላ ኣምስት ኣመት መቆየት ነው በጣም የሚፈልገው።በኣሁኑ ምርጫ በሰፊው የሚጠበቀውም ይሄኛው ስትራተጂ ነው። ይህንን መዘንጋት የለብንም። ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ይህን የመንግስት ቀመር ይረዳል ብየ ኣምናለሁ።
እንግዲህ ታዲያ ምርጫ በኢትዮጵያ የለም ስል ሰላማዊ ትግል ኣዋጭ ኣይደለም ማለቴ ኣይደለም። ሰማያዊ ፓርቲ ጀምሮት የነበረው ነጻነት ለፍትሃዊ ምርጫ ትክክለኛ ካምፔን ነው። ሰላማዊ ታጋዩች በምርጫ የማያምን መንግስትን ይዘው ወደ ምርጫ የሚገቡት የህዝቡን ጉልበት ተማምነው ይመስለኛል። መንግስት እንደፈለገው ምርጫውን ኣጭበርብሮ የሰጣቸውን ጥቂት ወንበር ተቀብለው “ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል” እንደሚባለው ዝም ካሉ ይህ ሰላማዊ ትግል ኣይባልም። ሰላማዊ ትግል ማለት ወደ ምርጫ ሄዶ ምርጫው ሲዘረፍ ዝም ማለት ኣይደለም። ይሄማ የሌባ ተባባሪነት ነው። ስለዚህ መንግስት ሲያጭበረብር ህዝብን በጽናት ማታገል ከሰላማዊ ታጋዮች ይጠበቃል። ። ድምጻችን ሊሰረቅ ኣይገባውም! በሚል ህዝቡ ድምጹን እንዲያስመልስ ማታገል፣ ማሳመጽ ኣለባቸው።በምርጫ ጊዜ የቅርጫ ጨዋታም ኣስፈላጊ ኣይደለም። በዚህ መንገድ ነው ይህ የምርጫ ድግስ ለእውነተኛ ተቃዋሚ ሃይላት እድል የሚሰጠው። ከምርጫው በፊት ከውድድር ውጭ በማድረግ ሴራ ሲሰራ፣ በምርጫው ጊዜና በውጤቱ ጊዜ ሴራዎች ሲፈጸሙ እነዚህ ሴራዎች የለውጥ ማንቀሳቀሻ (Stimulants for change) ሊሆኑ ስለሚችሉ ተቃዋሚዎች ትልቅ ታሪካዊ ሃላፊነት ኣለባቸው።ይህንን ሃይል ተጠቅመው ለውጥ ማምጣት ኣለባቸው።በኣንዳንድ ሃገሮች የምርጫ መጭበርበር ለህዝቡ የለውጥ ትግል ትልቅ ኣስተዋጾ ኣድርጓል። ኢትዮጵያም ይህን ማነቃቂያ (stimulant)ለተፈላጊ ለውጥ ትግል ልትጠቀምበት ከቻለች ነው ከዚህ ምርጫ የምትጠቀመው። ከዘጠና ሰባቱ ካለፉት ምርጫዎች መማር ኣለብን። ኣለበለዚያ መንግስት ቆንጥሮ የሚሰጠውን መቀመጫ ተቀብሎ በመግባት “ፓርላማ ገብተን እንታገላለን” የሚለው ትግሉን ወደ ፊት ኣይወስደውም። ቆራጥ የሆኑ ሰላማዊ ታጋዮች የሰላማዊ ትግሎችን ኣቅም ኣሟጠው በመጠቀም የህዝቡን ድምጽ ማስከበር ትግሉን በሃላፊነት ስሜት መምራት ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ኣሁን ባለው የፖለቲካ ኣሰላለፍ ኢትዮጵያ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ ኣትችልም። በተለይ በገዢው ኣካባቢ ትንሽ የሃላፊነት ስሜት ቢኖር ቅድመ ውይይቶች፣ ሰነዶች፣ ዋስትናዎችና ሲስተም ሊዘረጋ ይቻል ነበር። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ስምምነቶች ካልተደረጉ የምርጫ ነገር በኢትዮጵያ የሚታሰብ ኣይሆንም።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
dij mj says
ትንታነዉ በጣም ጥሩ ነዉ የ2007 ምርጫ የፓርቲዎች ቅስቀሳ ለመከታተል በአብዘኛዉ ሀገራችን መብራትናETV መደበኛ የለም ራሱን የቻለ ተእፅኖ መኖሩን ያሳያል።