* “በክፉ ጊዜ የከዱን አሉ፤ ለእነሱም ፈጣሪ ልቦና ይስጣቸው”
“የመጣሁት ከትግል እንጂ ከሽርሽር አይደለም” ይላሉ ዳንኤል ሺበሺ! የቀድሞው አንድት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊና የደቡብ ቀጠና ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ ላለፉት 22 ወራት በእስር ላይ ቆይተው ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ከእሥር ተፈትተዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ አየር ጤና አካባ በተለምዶ ቻይና ካምፕ በተሰኘው የአቶ ዳንኤል መኖሪያ ቤት ተገኝታ በእስር ቆይታቸው ስላሳለፏቸው ነገሮች፣ ስለወደፊት ሀሳባቸውና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡
እንዴትና በምን ሁኔታ ነበር የተያዙት?
የተያዝኩት ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በተለምዶ ጀርመን አደባባይ በሚባለው ቦታ ነው፡፡ ከያዙኝ በኋላ ከፍተኛ ድብደባ አደረሱብኝ፡፡ ከድብደባው በኋላ ራሳቸው እየመሩ ወደ መኖሪያ ቤቴ ይዘውኝ መጡና ቤቴ እስከ ምሽቱ 2፡30 ሰዓት ድረስ ሲበረበርና ሲፈተሽ አምሽቶ መጨረሻ ላይ ወደ ማዕከላዊ ምርመራው ተወሰድኩ፡፡ እንግዲህ እዚያ ለ120 (አራት ወራት) ቆይቻለሁ ማለት ነው፡፡
በማዕከላዊ ስለነበርዎ የእስር ቤት ቆይታና ሁኔታ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
ማዕከላዊ ከባድ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ሳይቤሪያ ተብሎ በሚጠራውና እጅግ ቀዝቃዛ ክፍል ነው ታስሬ የነበረው፡፡ ክፍሉ ቀዝቃዛ ብቻ ሳይሆን በረዷማ ነው ቢባል ይቀላል፡፡ በዚህ ቆይታዬ ግራ እጄ ከትከሻዬ እስከ ጣቶቼ ድረስ ደንዝዞ ሽባ ሆኖ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መጣ እንጂ አይሰራም ነበር፡፡ አሁንም ቅዝቃዜ ሲሆን ያመኛል፤ ሙቀት ሳገኝ ትንሽ ይሻለኛል፡፡ እና ማዕከላዊ ሁኔታዎች ከባድ ነበሩ፡፡
ከማዕከላዊ በኋላስ የት ነበር የታሰሩት?
ወደ ቅሊንጦ ነው የተወሰድኩት፡፡ በጣም የሚገርመው ለምን እንደሆነ ባላውቅም፡፡ እኔ ላይ ሁኔታዎች ጠንክረው ነበር፤ እርግጥ የጉዳት መጠኑ እኔም ሀብታሙ አያሌውም የሺዋስም ሆነ አብርሃ ደስታ ላይ እኩል ነው፤ ግን ዝም ብዬ ሳየው እኔ ከወዲያ ወዲህ ብዙ ተንገላትቻለሁ፡፡ በመጀመሪያ ቂሊንጦ ዞን አንድ አስገቡኝ፡፡ ከዞን አንድ ወደ ዞን ሶስት ወሰዱኝ። ከቂሊንጦ ዞን ሶስት እንደገና ወደ ቃሊቲ ዞን ሶስት አመጡኝ። ከቃሊቲ ዞን ሶስት ወደ ዞን ስድስት ወሰዱኝ፤ ከዞን ስድስት አወጡና ደግሞ ወደ ዞን ሁለት አመጡኝ፡፡ ከዞን ሁለት አንደኛ ቤት አውጥተው ደግሞ መስኮትም ምንም የሌለው ጨለማ ቤት 60 ቀናት አሰሩኝ፡፡ ብቻ ምን አለፋሽ.. ብዙ አንከራትተውኛል፡፡ ከዚያ ከጭለማ ቤት አውጥተው ዞን ሁለት ሁለተኛ ቤት አስገቡኝ። እንደገና ደግሞ ዞን አንድ ጭለማ ቤት ውስጥ 120 ቀናት (አራት ወር) አሰሩኝ፡፡ ያላዳረስኩት እስር ቤት የለም፡፡
ከዞን ዞን፣ ከክፍል ክፍል ሲዘዋወሩ ምክንያቱን ያውቁታል?
እኔ እስከዛሬ የማውቀው አንዱን ምክንያት ነው፤ ሌላውን አላውቀውም፡፡
እስኪ እሱን ይንገሩኝ…
አንዱ ምክንያት አንድ ጊዜ ቤተ – መፃህፍት ቁጭ ብዬ አንድ መፅሀፍ ሳነብ ታሪኩ መሰጠኝና ወደ ሶስት ገፅ የሚሆን ማስታወሻ ፃፍኩኝ፡፡ ከዚያ በፍተሻ ወቅት ወረቀቱ ተያዘ፡፡ “ቤተ መፅሐፍት ውስጥ ያለውን ማንኛውንም መፅሀፍ ማንበብ ይቻላል፤ መፃፍና ወረቀት ይዞ መውጣት አይቻልም” በሚል ምክንያት ነው ጭለማ ቤት እንድታሰር የተደረግሁት፡፡ ከዞን ዞን፣ ከቂሊንጦ ቃሊቲ ለምን ያዘዋውሩኝና ያንከራትቱኝ እንደነበር ግን አላውቅም፡፡ መጨረሻ ላይ ከዞን አንድ ጨለማ ቤት ወደ ዞን ስድስት ወደነ አብረሀ ደስታ ክፍል ተወስጄ የመጨረሻዎቹን አስር ቀናት አሳለፍኩኝ፡፡ እስር ቤት ከገባሁ አልጋ ላይ የተኛሁትም እነዚህን አስር ቀናት ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ሳይ በእኔ ላይ ፈተናዎች ጠንክረውብኝ ነበር እላለሁ፡፡ ምክንያቱም አልጋ ከልክለውኝ ሲሚንቶ ላይ ስተኛ ነው የከረምኩት፤ ህክምናም ተከልክያለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ጠይቄ ህክምና ከተወሰድኩ በኋላ ጤና ጣቢያ ህክምና እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ፤ ህክምና እንዳላገኝ ያደረጉትን ሰዎች ስምም አውቃለሁ፤ ቤተሰቤ እንዳይጠይቀኝ ተከልክያለሁ፡፡ ለምሳሌ እናት፣ አባት፣ ሚስት፣ እህት፣ ወንድም እንዲጠይቅ ይፈቀዳል ተብሎ፣ ከእኔ ጋር የአባቱ ስም ተመሳሳይ ያልሆነ ወንድም እህት መጠየቅ አይችልም፡፡ እንዴ! የእናትሽ ልጅ የሆነ ወንድምና እህት ይኖርሻል፤ ያ ሰው የግድ እከሌ ሺበሺ ካልተባለ እኔን መጠየቅ አይችልም ነበር። እናትና አባቴ ክፍለ ሀገር ናቸው፤ በየጊዜው እየተመላለሱ መጠየቅ አይችሉም። ባለቤቴ ነበረች ስትንከራተት የነበረችው፡፡ ቤተሰብ እያስተዳደረች፣ የውጭውንና የቤቱን ስራ ሰርታ በየጊዜው እኔን ለመጠየቅ መመላለስ ምን ያህል ፈተና እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የደረሰብኝን በደልና ስቃይ በቃላት ለመግለፅ ይከብደኛል፡፡ በምኖርባት አገር የገዛ ወገኔ እንዲህ አይነት በደል በእኔ ላይ ማድረሱ ጭካኔው ከምን እንደሚመነጭ አይገባኝም። በጤናም በህይወትም የወጣሁት በፈጣሪ እርዳታ ነው፡፡
በዚያ ላይ ዛቻው፣ ማስፈራሪያው፣ “እንተያያለን አስክሬንህ ነው የሚወጣው” ይሉኝ ነበር፡፡ ብቻ የማይሆንና የማይደረግ ነገር አልነበረም፡፡ “እነ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ እንኳን አስክሬናቸው ነው የወጣው እንኳን አንተ” ይላሉ፤ ምን የማይዝቱት አለ… ብቻ አለፈ፡፡ ሌላው ቀርቶ ቀጠሮ ያላቸው እስረኞች ወደ ፍ/ቤት ሊሄዱ ሲሉ የሚያርፉበት የእስረኞች መቆያ አለ፡፡ እኔን ከሌሎቹ ጋር እዚያ እንድቀላቀል እንኳን አያደርጉም፤ ከአጃቢዬ ጋር ለብቻዬ እንድቆም ነበር የሚያደርጉኝ፡፡ ይህን ሁሉ ጫና ለምን አበዙብኝ ብዬ ስጠይቅ ለራሴ መልስ አላገኝም፡፡ እዚያ ግቢ ውስጥ ምንም ጥያቄ ብትጠይቂ መልስ አታገኚም፡፡
እስር ቤት ከገባችሁ በኋላ “አንድነት” የመሰንጠቅ አደጋ ገጥሞታል…?
“አንድነት” ተሰነጣጥቋል ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ፈርሷል፡፡ ያፈረሰው ደግሞ ራሱ መንግስት ነው፡፡ በጠራራ ፀሐይ ሰራዊት ልኮ ነው ያፈረሰው፡፡
ለዚህ ማረጋገጫው ምንድን ነው?
መንግስት “አንድነት”ን አፍርሶ በ“አንድነት” ስም ፓርቲውን ለራሱ ሰው ሰጥቷል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው አንዱ የእኛ የአመራሮቹ መታሰር ነው፡፡ በመጀመሪያ ሀብታሙንና እኔን አሰረ። ከዚያም አጋዥ የሆኑ ሰዎችን አስፈራራ፡፡ ወቅቱ የምርጫ ቅስቀሳ መጀመሪያ ነበር፡፡ በተቃውሞ ጎራው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያላቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለማዳከም አመራሮችን ከየፓርቲው ማሰር ጀመረ፡፡ ከ“አንድነት” እኔና ሀብታሙን፣ ከ“ሰማያዊ” ፓርቲ የሺዋስን፣ ከ“አረና” አብረሀ ደስታን አሰረና ፓርቲያችንን ማተራመስ ጀመረ።
አሁን “አንድነት”ን እየመሩ ያሉት አቶ ትዕግስቱ አወሉ የትግል አጋራችሁ ነበሩ፡፡ በተለይ በእርስዎ የትውልድ አካባቢ ቁጫ ድረስ በመሄድ የቁጫን ህዝብ የማንነት ጥያቄ አቤቱታ ሲያዳምጡ ነበር፡፡ እንዴት የመንግስት ደጋፊ ሊሆኑ ቻሉ ብለው ያስባሉ?
በጣም ጥሩ! እኛ ከታሰርን በኋላ መንግስት ትዕግስቱንና ሰፊው የሚባለውን ልጅ ይዞ ፓርቲውን ካተራመሰ በኋላ አንድነቶች እርስ በእርስ ተተራመሱ ለማለት አድርጐት የማያውቀውን ያንን ሁሉ የሚዲያ ሽፋን (የቴሌቪዥን) ሰጠ፡፡ እኛ እስር ቤት ውስጥ ሆነን በቴሌቪዥን እንከታተል ነበር፡፡ እኔ በበኩሌ እንዲህ አይነት የቴሌቪዥን ሽፋን ያየሁት መለስ ዜናዊ ሲሞት ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ነው ፓርቲውን ያተራመሰው፡፡ “እንዴት ትዕግስቱ አወሉ የመንግስት ደጋፊ ሆነ? አብራችሁ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለ አይደለም ወይ?” ብለሻል፤ ትክክል ነሽ፤ ሀሰት አልተናገርሽም፡፡ በፊትማ አቶ ልደቱ አያሌውም ትክክለኛ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ የቅንጅቱ አየለ ጫሚሶም መጀመሪያ ላይ ለትግል ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ ሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ሰዎች በተለያየ ምክንያት አቋማቸውን ይቀይራሉ፡፡ ለምሳሌ በኢኮኖሚ ችግር ሊሆን ይችላል አሊያም ከገዢው ፓርቲ በሚደርስባቸው ጫናና ማስፈራሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በስልጣንና በጥቅም ተደልለው ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ በምንም ምክንያት ይሁን ሰዎች የቀድሞ አቋማቸውን ከቀየሩ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡
እስር ቤት እያሉ ስለሁኔታው ሲሰሙ ምን ተሰማዎት?
እኔ እታገል የነበረው ለፓርቲ አይደለም፤ ፓርቲ ሊጠፋ አሊያም ሰው ሊቀየር ይችላል። ሊሻሻልም ይችላል፡፡ እኔ እታገል የነበረው ለነፃነት፣ ለፍትህና ለዴሞክራሲ ነው፡፡ ይህም ደግሞ ትክክል መሆኑን እስር ቤት ውስጥ አረጋግጫለሁ፡፡ በደረሰብኝ መከራ ውስጥ ሆኜ የታገልነው ትግል ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ “አንድነት” ከምስረታው፣ ከስያሜው ጥቆማና ማርቀቅ ጀምሮ ሀሳብ በማሰባሰብም ጭምር ነበርኩበት፤ መስራችም ነኝ፡፡ ለዚህ ፓርቲ ብዙ መስዋዕትነት፣ ብዙ ገንዘብ፣ ብዙ ጉልበት አፍስሼበታለሁ፡፡ ይህን ሁሉም ያውቃል፡፡ በአጠቃላይ “አንድነት” ፓርቲ ለእኔ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክት ደግሞ አንዳንዴ ውጤታማ ላይሆን ይችላል። አንድ ፕሮጀክት ሲከሽፍ በቀጣይ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለውን ወደ ማሰብ ነው የምሄደው። “አንድነት” በመፍረሱ አላዘንኩም አልልም። ሀዘኔ ግን ፓርቲው በመፍረሱ ሳይሆን በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ እየተሰራ ስላለው ሴራና በአገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ነው። ኢህአዴግ፤ ተቃዋሚ የሚባል ነገር እንዲኖር፣ ድርጅት የሚባል ነገር እንዲፈጠር በተለይም በድርጅት ውስጥ የመሪነት ተፅዕኖ ያላቸው ሰዎች እንዲኖሩ አይፈልግም፡፡ በዚህ ምክንያት “አንድነት” ከምስረታው ጀምሮ ነው የማፍረስ ሙከራ ሲቃጣበት የኖረው፡፡
እንዴት ማለት?
በ2000 ፓርቲው ሲቋቋም ምስረታውን ለማድረግ የሞከርነው ገርጂ አካባቢ በሚገኝ ሆቴል ነበር፡፡ ህንፃውን መከላከያ ገዝቶት ነበር መሰለኝ ተከለከልንና ወደ ቢሮ መጣን። ከዚያም አንድ ዓመት 2001ን አረፍንና 2002 ላይ መሪያችን ብርቱካን ሚደቅሳ ታሰረች። 2003ን አልፈን 2004 ላይ ደግሞ ከፍተኛ አመራሮቻችን አንዱአለም አራጌና ናትናኤል መኮንን ታሰሩብን። አሁንም 2005ን አረፍንና 2006 ላይ እኔና ሀብታሙን አስረው የፓርቲውን ግብአተ መሬት ፈፀሙ፤ ፓርቲውን አጠፉ፡፡ አሁንም የቀድሞው ፓርቲ አባላት አሉ፤ እምነታቸውን አቋማቸውን የያዙ፤ ፓርቲው ግን ድራሹ ጠፍቷል፡፡
እስር ቤት ውስጥ ከባድ ጊዜ እንዳሳለፉ በአዎንታዊ መልኩስ? …
እኔ እስር ቤት አገኘሁ የምለው በጣም አሪፍ ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ብዙ ስራ ትሰሪ ትሰሪና ትክክለኛ ነገር ነው አይደለም የሚለውን ለማረጋገጥ ጊዜ ወስደሽ ትመረምሪያለሽ፡፡ ያመጣሽውን ውጤት በጥያቄ ውስጥ ከትተሽ የምታረጋግጪበት አሰራር በሂሳብና በፊዚክስ ትምህርት ላይ አለ፡፡ ቼክ ስታደርጊ በሁለቱም በኩል ወይ ዜሮ ዜሮ አልያም አምስት አምስት ብቻ የሆነ ቁጥር እኩል ከመጣ፣ ስራው ትክክልና ውጤታማ ነው ማለት ነው፡፡ እስር ቤት ሳልታሰር በፊት ስታገል የነበረበት መንገድ እንዴት ነበር የሚለውን በጥሞና ለማየት አስችሎኛል፡፡ ከ97 ወዲህ ስታሰር የመጀመሪያዬ ነው፤ በ97 ዓ.ም ትንሽ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ተደብድቤያለሁ ግን ደግሞ እኔ ከእስር ውጭ ሆኜ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል በማየት የሰብአዊ መብት ጥሰትን በመቃወም የታገልኩት ትግልና የታገልኩበት መንገድ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጬአለሁ፡፡
በሌላ በኩል የተሰሩ ስህተቶችንም ስገመግም ዝም ብሎ ኢህአዴግን ከማውገዝና ከመጮህ ባሻገር ምን ማድረግ ነበረብን የሚለውን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የኢህአዴግን ባህሪ ያለመረዳት ችግርም እንደነበር በጥሞና ተረድቻለሁ፡፡ ኢህአዴግ ይህን ቢያደርግ እኛ በምን መከላከል አለብን የሚለውን የመተንበይና ቀድሞ የማሰብ ችግር በመጠኑ በእኛ በተቃዋሚዎች አካባቢም እንደነበር አሰላስዬበታለሁ፡፡ እንግዲህ ይሄን ነው አገኘሁ የምለው፡፡
በተቃውሞ ትግል ውስጥ 18 ዓመታትን አሳልፌያለሁ፡፡ በነዚህ ዓመታት ውስጥ ህይወቴን … ትዳሬን … ቤተሰቤን ጎድቻለሁ። ብዙ ነገሮችን አጥቻለሁ፡፡ አሁን ሳስብ ግን ሰዎችን ለማዳን ሌሎች ሰዎች መሞት የለባቸውም፡፡ ሰዎች ሳይሞቱ እንዴት ነው ሌሎችን ማዳን የሚቻለው የሚለውን ሀሳብ ለማሰላሰል ጊዜ አግኝቻለሁ ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ እጅግ በጣም ብዙ ችግሮችና ቀውሶች ደርሰውብኛል፡፡ ለምሳሌ በግል ት/ቤት የማስተምራቸው ልጆቼ የመንግስት ት/ቤት ገብተዋል፡፡ ይሄ የሆነውም የሚከፍሉት በማጣት ነው። ይሄ በልጆቹ ላይ ምን ያህል የሞራል ችግር እንደሚፈጥርባቸው፣ ምን ያህል የትምህርት ጥራት ችግር እንደሚያጋጥማቸው ማሰብ ነው። ከስምንት በላይ የወንድም ልጅ፣ የእህት ልጅ፣ በባለቤቴም በኩል የምናሳድጋቸው ልጆች ችግር ውስጥ ወድቀው ነው የጠበቁኝ፡፡ እንዲህ አይነት ትግል ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ይህን ቤተሰብ የሚታደግ ነገር ማበጀት ግድ ነው። ያለበለዚያ እዚያ ያለውን ለማዳን ስንታገል፣ እዚህ ያሉት ከሞቱ ሁሉም ትክክል አይመጣም፡፡ በእስር የጥሞና ጊዜ በጥልቀት ካሰብኩባቸው ነገሮች አንዱ ይሄው ጉዳይ ነው።
ከፓርቲ ስራ ውጭ የራስዎ ስራ እንደነበረዎት ይታወቃል፡፡ አሁን ወደ ቀድሞ ስራ ይመለሳሉ?
ይሄ ቀልድ ይመስለኛል፡፡ ስራ ከየት ይመጣል? በቃ ስራ አጥ ነኝ፡፡ ቤተሰቤም ስንቅ በማመላለስ ተንገላቶ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ ወደፊት አገሬ ላይ ሰርቼ ለመኖር ምን ዋስትና አለኝ የሚል ጥያቄ በውስጤ አለ፡፡ በሌላ በኩል ስራ ፍለጋ ሲኬድ የፖለቲካ እስረኛ ነው ሲባል፣ እኔን ለማሰራት ብዙ ፍላጎት የሚኖር አይመስለኝም። ያም ሆኖ ስራ መፈለጌን እቀጥላለሁ፡፡ ብዙዎች ኢህአዴግ በአሸባሪነት ከስሶ ያሰረውን ሰው ለመቅጠር ይቸገራሉ። እኔ መሀንዲስ ነኝ ግን አሁን የጉልበት ስራ ለማግኘት እንኳን መቸገሬ አይቀርም፡፡
አንዳንድ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ታስረው ከተፈቱ በኋላ ወደ ውጭ ይወጣሉ፡፡ እርስዎ በፖለቲካ ትግሉ ይቀጥላሉ ወይስ?
ትግሉን ትቀጥላለህ ወይ የሚለው ትክክለኛ ጥያቄ አይደለም፤ አሁንም የመጣሁት ከሽርሽር አይደለም፤ ከትግል እንጂ፡፡ 22 ወራት ስታገልና ስሰቃይ ቆይቼ ነው የመጣሁት፡፡ ይሄ በዚህ ይታረም፡፡ ከአገር ትወጣለህ ወይ ላልሺው እኔ ባህታዊ ነኝ፤ ባህታዊ ማለት ዓለም በቃኝ ብሎ ለነፍሱ ያደረና ገዳም የገባ ሰው ነው፡፡ እኔ ገንዘብና ጥቅም ፍለጋ አይደለም ትግል ውስጥ የገባሁት፡፡ አገሬን ጥዬ የትም የምሄድበት ጉዳይ የለም፡፡ መሄድ ካስፈለገ በፊትም መሄድ እችል ነበር፡፡ የሄዱትንም አከብራለሁ፤ ምርጫቸው ስለሆነ፡፡
በግሌ ግን ሰዎች ስለሄዱ አልሄድም፤ አምኜበት የታገልኩበት ጉዳይ ነው ከአገሬ አልወጣም፡፡ ለዚህ ነው በትግል የቆረብኩ ባህታዊ ነኝ የምልሽ። ማዕከላዊም ቃሊቲም፣ ቂሊንጦም ፍርድ ቤትም ለእኔ የትግል ሜዳዎች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ምንም በማታውቂው፣ ሰርተሽ ለመለወጥ፣ ቤተሰብሽን ለመምራት ትታገይ አሸባሪ ተብሎ መታሰር ማለት እንግዲህ ይታይሽ …
የቀድሞው አንድነት ፈርሷል ብለዋል። ይህንን ፓርቲ ከአጋሮችዎ ጋር እንደገና ለመፍጠር ሀሳብ የላችሁም?
በነገራችን ላይ አሁን እረፍትና ማሰብ እንዲሁም ከመረጃ ርቄ በነበርኩበት የሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ስለተፈጠረው ነገር ማወቅና መገንዘብ ነው የምፈልገው፡፡ አይደለም ሁለት ዓመት፣ ሁለት ቀን ከመረጃ መራቅ በእውቀት ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም። ስለዚህ ይሄን እመረምራለሁ፤ በበቂ ሁኔታ እረፍት እወስዳለሁ፡፡ ከመረጃ በራቅሁበት ሁኔታ ስለ አንድነት እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ እስካሁን ያወራሁትም በነበረኝ መረጃ ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ አሁን ስለአንድነት ምንም ማለት አልችልም፡፡
በመጨረሻ የሚሉት አለ …
ጉዳያችንን ሲከታተሉ የነበሩትን የሚዲያ ሰዎች፣ ቤተሰቤን፣ በተለይ ባለቤቴን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ፣ ጠበቆቻችንን አመሀ መኮንን እና ተማም አባቡልጉን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በክፉ ጊዜ የከዱን አሉ፤ ለእነሱም ፈጣሪ ልቦና ይስጣቸው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ (ምንጭ: ናፍቆት ዮሴፍ፣ አዲስ አድማስ)
Leave a Reply